በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፖች እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥም ሆነው ለችግር ተዳርገው ቆይተዋል።
እነዚህን ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን ከአገር ውስጥና ከውጭ ወገኖቻቸው የሆኑ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ሲያደርጉላቸው ቆይተዋል እያደረጉላቸውም ይገኛል።
እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከቁሳዊ ጥቅሙ ባለፈ በተደጋፊዎች ስነ ልቦና ላይ የሚፈጥረው የእኔነት ስሜት እንደሚኖር ይታመናል። እኛም በዚህ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና መምህር እንዲሁም በመሰላል የማማከር አገልግሎት የማህበራዊ ስነ-ልቦና አማካሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ የማህበራዊ ስነ-ልቦና ተማሪ የሆኑትን አቶ ጌታ ዋለልኝን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል። ባለሙያው እንደሚያብራሩት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች እያደረጉት ያለው ርብርብ ከቁስ ባለፈ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ጦርነት፤ ፖለቲካዊ ቀውስ፤ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ሲከሰቱ ከአካላዊ ጉዳት ባለፈ በስነልቦናና በማህበራዊ ግንኙነት ብሎም በመንፈሳዊ ህይወት ላይ የሚያደርሱት ጫና አለ። እነዚህን በዝርዝር ለማየት ያህልም በማህበራዊ መስክ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማሻከር በእለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚኖራቸውን መስተጋብር የላላ ያደርገዋል። በሁለተኛነት እንደ ግለሰብ በስነ ልቦናው ረገድም ድባቴ በመፍጠር፤ ስጋት እንዲኖራቸው በማድረግ፤ እንቅልፍ በማሳጣትና ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥና ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ራስን የመጥላት ስሜት ሊከሰትባቸው ይችላል። በሶስተኛ ደረጃም በሃይማኖታዊ/ መንፈሳዊ ህይወታቸው ደግሞ የፈጣሪን አዳኝነት፤ ደግነት የመፈታተን ስሜት እየፈጠረባቸው ይመጣና ይህም እያደገ ሲሄድ ሃይማኖትን ብሎም አምላክን እስከመፈታተንና እስከመካድ ሊያደርሳቸው ይችላል። እነዚህ ሁላ ቀውሶች ከተፈጠረው አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት ጋር ያሉ ተደራቢ ችግሮች ናቸው። በዚህ አይነት በተደራራቢ ችግር ውስጥ ያሉ አካላት ወገኔ ከሚሉት ከሌላ ቦታ ያለ ሰው ቁሳዊ ድጋፍ ሲያደርግላቸው በተደራቢነት ትልቅ ስነልቦናዊ ድጋፍም እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ይሆናል። የሚደረገው ድጋፍ ደግሞ እነሱን ከማበረታታት አልፎ እነሱም የሚረዳኝ ወገን አለኝ፤ ብቻ ሳይሆን እኔም ልረዳው የሚገባው ወገን አለኝ የሚል ስሜት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል። ይህም በህዝቦች መካከል ያለን የመደጋገፍ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህል የሚያዳብረው ይሆናል። በሃይማኖትና በመንፈሳዊ ጎኑም ቢሆን እነዚህ አካላት ችግር ቢደርስብኝም የሚረዳኝ አምላክ ወገኖቼን ከጎኔ አቁሞልኛል በማለት አምላካቸውን እምነታቸውን ከማማረር ወደ ማመስገን መንፈሳዊ ወደመሆን ይለወጣሉ። በተጨማሪ ሰዎች የሚያደርጉላቸውን ድጋፍ ምክርና አይዞህ ባይነት፤ አለሁ ባይነት ሲመለከቱ ተስፋ ከመቁረጥ ወጥተው ተስፋ አለኝ ህይወትም ይቀጥላል የተሻለ ቀንም ይመጣል የሚል እሳቤ እየተፈጠረባቸው ይመጣል። ይህም ከላይ የተገለጹትን ድባቴ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ለመቀነስ ብሎም እስከ መጨረሻ ለማስወገድ የሚጠቅም ይሆናል። ተጎጂዎች ከስነ ልቦናና ከማህበራዊ ቀውሶች ራሳቸውን ሊታደጉ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ባለሙያው ሲያብራሩም። በተከሰተው ነገር የስነልቦና ጫና የተፈጠረባቸው ሰዎች ራሳቸውን ከመውቀስ በቅድሚያ መቆጠብ አለባቸው። ብዙ ግዜ ይህ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ያለፈውን ነገር በማንሳት ይህን ባደርግ ኖሮ ይህን ባላደርግ ኖሮ የሚል በውስጣቸው ይፈጠርባቸዋል። ይህ ስሜት እየዳበረ ሲመጣ ደግሞ ከራሳቸውም አልፎ በአካባቢያቸው ያሉትን መንግሥትንና ሌሎችንም አካላት ራሳቸውን ጨምሮ ወደ መውቀስ ሊያሸጋግራቸው ይችላል። ይህ የጭንቀትና የድባቴ ምንጭ ይሆናል።
በመሆኑም የጉዳት ሰለባ የሆነ ሰው በቅድሚያ ችግሩ በመሰረቱ የመንግሥትም የማህበረሰቡም፤ የግለሰቡም ወይንም የተወሰኑ ተቋማት ሳይሆን ከአሸባሪው ቡድን ጀርባ ብዙ ባለ ድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን መረዳት ያሻል። ይህም ሆኖ ሁሉም ነገር ጊዜ እንደሚፈልግ መገንዘብ
ይገባል። በአንድ ቀን ነገሮች ይስተካከላሉ ብሎ ማመንም መታሰብም የለበትም። ሁኔታዎች ወደነበሩበት ከነበሩበት ወደተሻለውም እንዲመጡ ጊዜ ይፈልጋሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ ነገሮችን መቻል መቋቋምና ጥንካሬ ፤ ትእግስት ያስፈልጋል።
ሁሉም ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ «ቀላል ይሆኑ ይሆናል እንጂ ቀላል አይደሉም»። አሁን ያሉበት ሁኔታ ቀላል ነው ማለት አይደለም። በመሆኑም ይህም ያልፋል ብሎ ተነስቶ እንዴት እንደሚያልፍ።
ያለውንም ነገር ለበጎ ይሆናል ብቻ ሳይሆን እንዴት ለበጎ እንደሚሆም መፈተሽ ይገባል። በመሆኑም ትልቁን ነገር ሰላምን እየጠበቁ ነገር ግን ሰላም እስኪፈጠር ድረስ ያለምንም እንቅስቃሴ ቁጭ ካሉ የባሰ ጭንቀትና ድባቴ የሚፈጠርባቸው ይሆናል።
በመሆኑም በቻሉት አቅም የራሳቸውን ተሳትፎ በማድረግ ከቀን ውሏቸው ጀምሮ ዛሬ ጠዋት ስነሳ ምን ማድረግ አለብኝ። ማንን ልደግፍ ልረዳ እችላለሁ ወደ ሚል እሳቤና ተግባር መሻገር ይኖርባቸዋል። በተቻላቸው አቅም ችግራቸውን በመከፋፈል ለመፍታት በአንድ ቀን መፈታት የማይችሉ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ዛሬ ስራው ተጀምሮ ወደፊት እንደሚፈቱ ማመን። ከሁሉም በላይ ደግሞ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ተስፋ እንዳላቸው ሊያምኑ ይገባል።
ህይወት ከፍታ አለታ ዝቅታ አላት ጥሩ ግዜ እንዳለ ሁሉ መጥፎ ግዜ መኖሩም ተፈጥሯዊ ነው። በመሆኑም በጎ እምነት ያስፈልጋል ጨለምተኝነቱ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣብኝ የሚል እሳቤና ተስፋ መቁረጥ ድብርት በመፍጠር የሚረብሽ ይሆናል። የሰው ልጅ ነገ ምንም በጎ ነገር አይመጣም ብሎ ራሱን ከዘጋው ጥሩ ሊሆንለት የሚችለውንም ነገን ራሱ ሊያበላሸው ይችላል። በመስኩ የተከናወኑ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከጦርነት ከማህበራዊ ቀውስ ግጭት በኋላ በተፈናቀሉ በተጎዱ ሰዎች ውስጥ ድብርት ከሀያ አምስት በመቶ በላይ ይደርሳል። ጭንቀትም እንደዛው ነው።
ራስን ለማጥፋት ማሰብና መሞከርም አምስት በመቶ ይደርሳል። ለዚህ ችግር የተጋለጡ ሰዎች ደግሞ የሚያሳዩአቸው ምልክቶች ከፍተኛ ጸጸትና ሀፍረት፤ ከመጠን በላይ ለቅሶ ፤ ከመጠን በላይ እንቅልፍ መተኛት አልያም ማጣት፤ ከመጠን በላይ የሰው ጥገኛ መሆን «ለእያንዳንዱ ድጋፍ ረዳት መፈለግ» በአሰቃቂ ትውስታዎች መረበሽ ትኩረት ማጣትና ራስን ለማጥፋት ማሰብ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ምልክቶች የሚታዩባቸውን ሰዎች በማቅረብ ተስፋ እንዲሰንቁ ይህ ቀን እንደሚያልፍ ማሳወቅ በቅርባቸው ካለ ሰው የሚጠበቅ ይሆናል። በሌላ በኩል የተፈጠረውንም ነገር ለህብረት ለትብብርና ለመደገፍ በመጠቀም ለበጎ ማዋል መለመድ አለበት።
ችግሮች ሲከሰቱ ብዙ ግዜ ጎልተው የሚወጡት ችግሮች ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ናቸው። በዚህ ውስጥ ግን የሚፈጠሩ በጎ ነገሮች እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል። በዚህ ረገድ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ አድርገን ብንመለከት።
በአንድ ወገን ለችግር የተጋለጠው ህዝብ እየተጎዳ ቢሆንም አጋጣሚው በሌላ በኩል ላልቶ የነበረ መተሳሰብ የመረዳዳት ባህል እንደአዲስ እንዲነሳሳ በር የሚከፍት ሆኗል። መረዳዳትና መተባበር ምን ያህል ይጠቅም እንደነበር ግንዛቤ እንዲፈጠርም አድርጓል። በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየጠነከረ የመጣው የብቸኝነት ባህል ወደ ነበረበት እየተመለሰ እንዲመጣ አድርጎታል።
በተለይም የተከሰተው ጦርነት አንድ ግለሰብ ብቻውን ወይንም ጥቂቶች ብቻቸውን ምንም ሊያደርጉ እንደማይችሉ ለውጥ እንደማያመጡ ያስተማረም ነው። በዚህም ከብቸኝነት ወደመተሳሰብ ድሮ ወደነበረው የመረዳዳት ባህል ለመመለስም በር ከፍቷል። በዚህም እነዚህን ባህሎቻችንን መለስ ብለን አይተን አንስተን እንደአዲስ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ እንድንጠቀምባቸው እያስቻሉን ነው። አንድ ስንሆን መተባበር መደጋገፍ ሲኖር እንዲህ አይነት ችግሮቻችንን ለመሻገር እንችላለን የሚል ማህበራዊ ስነልቦና ለመፍጠር ያስችላል።
የየትኛውም ማህበረሰብ ስነ ልቦና በአንድ ፖሊሲ ወይንም በአንድ ተግባር ሊቀረፍና ሊበላሽ የሚችል አይደለም። የማህበረሰብ ስነ ልቦና እሴት በአኗኗር ሁኔታው ውስጥ ጠልቆ የገባ ነው። የማህበረሰብ ስነ ልቦና በአንድ ማህበረሰብ አንድ ትውልድ ውስጥ ብቻ የሚኖር ሳይሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገርና በደንብ ሰርጾ የገባም ነው። ይህ ሊሸረሸር ሊዳፈን ይችላል እንጂ ፈጽሞ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ አይችልም።
በእኛም አገር የነበረው ከላይ ከላይ የመለያያት የመራረቅ ነገሮች የሚታዩበት ቢሆንም የኖረው አመለካካት አስተሳሰብ ክብር ግን የህብረተሰቡ ስነ ልቦና ውስጥ እንደቀድሞው ነበር።
አሁን የተከሰተው ችግርና የህዝቡ ምላሽም የሚያሳየው ከጥቂቶች በቀር ዛሬም በየትኛውም ቦታ ያለ ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው መተሳሰቡን መፈቃቀሩን እንደሆነ ነው።
ይህ አጋጣሚ ከዚህም አልፎ አንድነቱ ህብረቱ መተሳሰቡ ጠፍቷል ለሚሉም ምላሽ የሚሰጥ ነው። ቀድሞውንም ቢሆን በተደጋጋሚ ጠፍቷል በተበርዟል ተሸርሽሯል የሚሉ አካላት እውነት እዛ ደረጃ ደርሶ ሳይሆን እነሱ እንዲጠፋ የሚፈልጉ ብቻ የሚያራግቡት ወሬ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሁሉም ሃይማኖቶች የማህበረሰቡን ስነ ልቦና በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
በኢትዮጵያ ያለው ማህበረሰባዊ ስነ ልቦና የተቀረጸውም ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ነው። አብዛኛዎቹ ባህሎች የመጡትም ከሃይማኖታዊ እሴት ጋር ተያይዘው ነው። በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራ በሆኑ ቁጥር በማህበረሰቡ መካከል ያለው ሰላማዊ ተጋብሮት እንዲጠናከር ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል።
ለሰው መኖር ፤ ለአገር ያለን ፍቅር ወዘት ከሃይማኖት ጋር የተያያዙና ዛሬም ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ልናበለጽጋቸው የምንችል መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህም ሆኖ በጣም ጥቂቶች የምንላቸውና ዛሬ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበሩ ባህሎችን የሚበርዙ አንዳንድ ነገሮችን ሲያደርጉና ሲናገሩ ይስተዋላል።
እነዚህ በአስተሳሰብም ሆነ በአሀዝ በምንም አይነት መልኩ ሰፊውን ማህበረሰብ የሚወክሉ አይደሉም። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዛሬም ድረስ ሰላም አንድነት ፍቅር ያለውና አገሩ አንድ ሆና እንድትቀጥል ፈላጊ ነው።
ለዚህ ማሳያው በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት ችግሮችና ግጭቶች እንኳን የብዙሃኑ ፍላጎት ሊኖርባቸው የብዙሃኑ ትብብር ቢታከልባቸው እንኳ በመንግሥት ሀይልም ሊቆሙ የሚችል አልነበሩም። አሁንም ችግሩን ለመቅረፍና ያለውን መልካም ነገር እያስከተሉ ለመቀጠል በቅድሚያ ማየት ያለብን ልዩነቱን ስጋቱን ሳይሆን በተቃራኒው ያለውን እውነታ ነው። በተቃራኒው ያለው እውነታ ደግሞ ህዝቡ ሰላም ፈላጊ በግለሰብ ደረጃ በአገሩ ሰርቶ መለወጥ ወገኑን መርዳት መደገፍ የሚፈልግ መሆኑን ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው የመረዳዳት የመደጋገፍ የአለሁ ባይነት ባህላችንን አጠናክሮ ለማስቀጠል መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ።
በቅድሚያም የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችን በማብቃት ረገድ ቤተሰብ በልጆቹ ላይ ስነ ምግባራቸውን በተመለከተ ተከታታይነት ያለው ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል።
ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎችን የእውቀት ብቻ ሳይሆን የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ስለ ወገን ስለ አገር መኖር እንዲለምዱ ማስቻል ይጠበቅባቸዋል። በሌላ በኩል ዛሬ በበጎውም በክፉውም የምናነሳው የማህበራዊ ሚድያ አንዱ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው።
በመሰረቱ ማህበራዊ ሚድያ በአግባቡ ከተጠቀምነበት በርካታ ፋይዳ ያለው ነው። በእኛ አገር ማህበራዊ ሚድያ የሚናፈሰው በሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብና እውነታ የሚገልጽ ነው ብለን ማመን የለብንም።
ዛሬ ዛሬ የማህበራዊ ሚድያ ጥቅም የገባቸው ነገር ግን ለክፉ የሚጠቀሙበት በዝተዋል። በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት እንዲሁም አገርና ሰላም ወዳድ ግለሰቦች ማህበራዊ ሚድያን እየተከታተሉ በመስራት እንደ አንድ የትክክለኛ መረጃ ምንጭ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይሆናል።
በዚህም ለበጎ ስራ ለአገር ለወገን የሚጠቅም ሲሆን ማበረታታት ህዝብን የሚለያይ የሚያቃቅር ሲሆን ደግሞ ስህተቱን እያወጡ ማሳየት የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 29/2014