
በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ክፍል የሚገኘው የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ከትግራይ ክልል በስተቀር ከተቀሩት ክልሎች ጋር የሚዋሰን ሲሆን በደቡብ ምስራቅ ከኬንያ ጋርም ይዋሰናል። ከተቀሩት ክልሎች ጋር ሲነጻጸርም በቆዳ ስፋቱ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል።
በለም መሬትና በአስደናቂ የተፈጥሮ ሀብቱ የታደለው ክልል ከጠቅላላው የቆዳ ስፋቱ 50 በመቶ የሚሆነው ለግብርና ስራ ምቹ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግልጽና ምቹ የሆኑ አዋጆችን አውጥቶ ባለሀብቶች ገብተው እንዲያለሙ እያደረገ ይገኛል። በዚህም በርካታ ባለሀብቶች እየተሳቡና ክልሉን ለማልማት እየሰሩም ይገኛሉ።
እኛም የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ከሆኑ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ጋር በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በተመለከተ ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ በኦሮሚያ ክልል በተለይም ካለው አገራዊ ሁኔታ አንጻር የኢንቨስትመንት እቅዱና አፈጻጸሙ ምን ይመስላል?
ዶክተር ተሾመ፦ አሁን ላይ እንደ ክልል ኢንቨስትመንት የመሳብ ስራችን ጥሩና ተስፋ ሰጪ ነው። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አጠቃላይ የኢንቨስትመነት እንቅስቃሴ ለመግለጽ በአሁኑ ወቅት 17 ሺ ሶሰት መቶ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች አሉ። በነገራችን ላይ በተለይም ፍቃድ አሰጣጡን በተመለከተ የሚነሱ ነገሮች ቢኖሩም አሁን ላይ ቢሮ አልሚ ነኝ ብሎ ለመጣ አካል ፍቃድ እየሰጠ ነው።
እነዚህ ፍቃድ የወሰዱ አካላትም ግማሾቹ አገልግሎት ሰጪ ላይ የሚሰማሩ ሲሆኑ ቀጥሎ ያሉት ግብርና አግሮ ፕሮሰሲንግና ማኑፋክቸሪንግ የስራ ዘርፎች ናቸው። ኢንቨስትመንቱ ከ230 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ወጪ ተደርጎባቸው ኢንቨስት የተደረጉ እንደመሆናቸው ለበርካታ የክልሉ ወጣቶችም ቀላል የማይባል የስራ እድልን ያመቻቹ ናቸው።
የሩብ አመቱን እቅድ አፈጻጸም ስናይ በተለይም ኢንቨስትመንትን በመሳብ የመጣውን በአግባቡ ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል ያሉትን ነገሮች ካየን አብዛኛው ነገር ከእቅድ በላይ ነው አፈጻጸሙ።
በሌላ በኩል ግን በተለይም የኢንቨስትመንት ስራው ላይ በቀበሌና በዞን ደረጃ ማዘጋጀት አለመቻላችን እንደ ክፍተት ሊታይ የሚችል ነገር ነው። ከዚህ ውጪ ባለው ሂደት ግን በተለይም ኢንቨስትመንቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረጉ ስራዎች ላይ በሚፈለገው ልክ አልሄድንም። ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ ብዙ አልሚዎች ቢኖሩም ስንቶቹ ግን ውጤታማ ሆነዋል ብለን ስናይ አንዳንዶቹ በሚፈለገው ልክ ውጤት ያላመጡ በመሆናቸው እነሱን ቶሎ ብለን ወደመስመሩ በማስገባት በኩል በርካታ ስራዎች ይቀሩናል ማለት ይቻላል።
ነገር ግን ተቋሙን ጠንካራ አደርጎ የሚፈለግበትን እንዲወጣ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው፤ ከዚህም መካከል ቀድሞ ቢሮው ብቻውን የነበረ ሲሆን አሁን ከኢንዱስትሪ ጋር ተጣምሮ እንዲሄድ በማድረግ አቅም የማስገኘት፤መዋቅሩ ተጠናክሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ማለትም አሰራሩ እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲወርድ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።
በሌላ በኩልም አራት ምክትሎች እንዲሾሙ ተደርጎ ስራውን አመርቂና ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ኦሮሚያ ክልል ሰፊ እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብትና በሰው ሃይል ከፍ ያለ እንደመሆኑ ይህንን ሀብትና ጉልበት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ውሏል ማለት ይቻላል? የኦሮሚያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴስ የት ላይ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ተሾመ ፦ ኦሮሚያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት፡፡ ምንም እንኳን ይህ ሀብቷ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ውሏል ባይባልም ለኢንቨስትመንት ስራ ምቹ እንድትሆን ጥረት እየተደረገ ነው። በሌላ በኩልም አገሪቱ ላይ የሚከናወኑ ዋና ዋና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በሁሉም አቅጣጫ ኦሮሚያን ነክተው የሚያልፉ መሆናቸው በራሱ ትልቅ እድል በማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ውጤትም እየመጣ ይገኛል።
ከዚህ አንጻር የኦሮሚያን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ብንመለከት በጣም ቆንጆና መሰረታዊ ለውጥ እየታየበት ያለም ነው። ለምሳሌ በክልሉ ላይ ከሶስት ዓመት በፊት የነበረው የኢንቨስትመንት ቁጥር ከአስር ሺ የማይበልጥ ነበር፤ አሁን ግን ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች ወደ 17 ሺ 3 መቶ የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማግኘት ችለናል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ የክልሉ የኢንቨስትመንት አቅም ሰፊ መሆኑን ነው። የኢንቨስትመንት መዳረሻነቱም ትልቅ መሆናቸውን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከሶስት አመት ወዲህ ክልሉ በኢንቨስትመንት መስኩ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለውኛልና እንደው ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ድጋፎችስ ተገኝተው ነው?
አቶ ተሾመ ፦ አዎ፤ ሁላችንም እንደምንረዳው ከለውጡ ወዲህ እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ በርካታ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፤ እንደ ኦሮሚያ ስንገልጸው ደግሞ በተለይም ከለውጡ በፊት የክልል አመራር ራሱን ችሎ የማይወስን የማይንቀሳቀስ ነበር፤ የክልል መንግሥት ይባል እንጂ ለስሙ የሚመጥን ስራ ለመስራት ግን የሚያስችል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነጻነት አልነበረውም።
ይህንን ሁኔታ ደግሞ ወደኋላም ሄደት ብለን ማየት እንችላለን፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የኦሮሚያ መንግሥት እንደ መንግሥት ቢመሰረትም ከላይ ያነሳኋቸው ነጻነቶች ስላልተሰጡት ኢንቨስትመንቱንም በሚፈልገውና በሚያስበው ልክ መስራት ሳይችል ኖሯል። ይህ ደግሞ የክልሉ ኢንቨስትመንት በጣም እንዲቀጭጭ በተፈለገው መልኩ ያልሄደ ነበር። ከለውጡ በኋላ ግን የኢንቨስትመንት ሂደቱ በጣም እንዲለወጥ ሆኗል።
በዚህም አሁን እያየን ያለነው ለውጦች መጥተዋል፡፡ በቀጣይም ቢሮው በሚሰራቸው ጠንካራ ስራዎች አማካይነት ነገሮች በፍጥነት ይለወጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ የአሸባሪው ሕወሓት አመራ ሮች በነበሩበት ወቅት ሆን ተብሎ በክልሉ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ ተደርጓል ማለት ነው?
አቶ ተሾመ፦ እዚህ ላይ ኢንቨስትመንት በባህርይው የፖለቲካ ነጻነት ይፈልጋል፤ ይህም ሲባል መንግሥት እንደ መንግሥት የህዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ ችግሮቹን ቀረብ ብሎ በመረዳት ምን ዓይነት ኢንቨስትመንት ቢመጣ ነው ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆነው የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል።
ያኔ ግን ይህ ነገር አይታሰብም ነበር። የክልል መንግሥት ወደእሱ እየመጡ ስላሉ ኢንቨስትመንቶች የመወሰን መብት አልነበረውም ። ይህ ደግሞ ወደክልል የመጡ ጥቂት ኢንቨስትመንቶች እንኳን የክልሉን ህዝብ ታሳቢ ያላደረጉ በመሆናቸው ተጠቃሚነት ላይም ከፍተኛ ችግር ነበር። ለምሳሌ ክልሉ ላይ በተለያዩ ባለሀብቶች አማካይነት ሲካሄዱ የነበሩ ኢንቨስትመንቶች አሉ፤ እነዚህ ኢንቨስትመንቶች የቆሙትና ስራ እየሰሩ ያሉት ኦሮሚያ ውስጥ ነው ፤ ነገር ግን የክልል አስተዳደር ይሁኑ ብሎ ስለወሰነ አይደለም፡፡
ክልል ላይ የነበሩት ከዚህ አንጻር ደግሞ የክልልን ህዝብ የማይጠቅሙ የሌሎች አካላት ኪስ መሙያ ብቻ ሆነው የቀሩም ነበሩ። ጥሩ ማሳያ የሚሆን አንድ ነገር ልናገር፡፡ ወደ ምስራቅ ሸዋ አካባቢ አዋሽ ወንዝን ተንተርሰው የሚኖሩ ግን ደግሞ የተራቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን የሚገፉት በእርዳታ እህል ነበር፤ ነገር ግን የክልል መንግሥት እነዚህ ሰዎች ህይወታቸውን በእርዳታ እህል ከሚገፉ እንደ መንግሥት ወንዙ ላይ ኢንቨስት አድርገን ቋሚ ተጠቃሚ በማድረግ ከእርዳታ እናውጣቸው በማለቱ በመዋቅሩ ውስጥ በነበሩ ጁንታዎች ከፍተኛ የሆነ ችግር ነበር የደረሰው፤ ይህ አንዱ ማሳያ ነው እንጂ መሰል ክስተቶች በርካታ ናቸው።
ኦሮሚያ የኢንቨስትመንት የስህበት ሀይል ያላት ነች። ለምሳሌ ኢስት ኢንደስትሪያል ዞን በሚቋቋምበት ጊዜ እንዴት ነው ወደእናንተ ሊመጡ የቻሉት የሚል ጥያቄ ነበር።
እዚህ ላይ ግን ማወቅ የሚያስፈልገው ነገር ኢንቨስትመንት ፖለቲከኛው ስለፈለገ ወይም ስላልፈለገ የሚመጣ ሳይሆን ኢንቨስት አድራጊው ያዋጣኛል፣ ለስራዬ ምቹ ነው አተርፍበታለሁ በሚለው መንገድ ይመጣል። በመሆኑም በዛን ወቅት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ነገር የክልሉ መንግሥት ለስሙ መንግሥት ይሁን እንጂ ለህዝቡ የሚስማማውን ወይም ከስራ አጥነት ሊያወጣለት የሚችለውን ስራ ማሰብም ሆነ መፈጸም አይችልም እንደማለት ነበር።
ይህንን ማሰብ የማይቻል የነበረው ደግሞ የፖለቲካል ውሳኔ ሰጪው የሚፈልገውን ብቻ የሚያደርግና አድርጉ የሚል ስለነበረ በፍጹም እራስን ችሎ ማሰብ አይቻልም ነበር። አሁን ከለውጡ በኋላ በርካታ የመጡ ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፦ እርሶም እንዳሉት፤ እንደሚ ታወቀውም ከዚህ ቀደም ወደክልሉ ይመጡ የነበሩ ኢንቨስትመንቶች አንድም ለስርዓቱ ታማኝ የሆኑና አልያም ጥቅም የሚያካፍሉ ነበሩ ፤ አሁን ላይ እነዚህን ኢንቨስትመንቶች ህዝብን እንዲጠቅሙ ማድረግ ተችሏል?
አቶ ተሾመ ፦ በመጀመሪያ ደረጃ መታሰብ ያለበት ከዚህ ቀደም ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭና ስራ ጥቂት ግለሰቦችን ብቻ ታሳቢና ተጠቃሚ ያደረገ ነበር፤ ይህ የተፈጠረው ኢኮኖሚ እንዳለ ሆኖ እኛ እንደ መንግሥት የምናምነው ኦሮሚያ ቀድሞ ከተፈጠረው ኢኮኖሚ በላይ መፍጠር ትችላለች የሚለውን ነው። ምክንያቱም ወደፊት ልንፈጥረው የምንችለው ኢኮኖሚ በጣም ጠንካራ ይሆናል የሚል እምነት አለን።
ከዚህ በኋላ ህዝባችን ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ወደፊት ኦሮሚያ በምትፈጥረው የኢኮኖሚ አቅም እንጂ ከዚህ ቀደም የነበሩት ቀድሞም አልጠቀሙም፤ ከዚህ በኋላም ይጠቅማሉ የሚል ግምት የለንም።
እኛ አሁን እነሱን ሳይሆን የምናስበው ወደፊት ምን ዓይነት ኢንቨስትመንት ፈጥረን ህዝባችንን ራሱን እናስችላለን የሚለውን ነው። በነገራችን ላይ ኢኮኖሚ ውጤታማ የሚሆነው ከአንዱ ቀምተህ ለሌላው ስለሰጠህ ሳይሆን ሌሎች ኢኮኖሚዎችን መፍጠር ሲቻል ነው። 27 ዓመት ህዝብን ተጠቃሚ ያላደረጉ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ስለዚህ አሁን እያሰብንበት ያለው ነገር ወደፊት ልንሰራባቸው የሚያስችሉ እድሎች ስላሉ እንደ ክልል መንግሥት በደንብ ትኩረት ሰጥተን በመስራት ነው፡፡ ለምሳሌ አርሶ አደሩ የግብርና ስራውን የሚያዘምንበትን መንገድ መፍጠር የብድር ሁኔታዎችን ማመቻቸት የቅድሚያ የትኩረት አቅጣጫዎች ሲሆኑ ቀድመው ክልል ላይ አልሚ ባለሀብት ሆነው ሲሰሩ የነበሩም አሁን ያለውን ፖለቲካዊ አስተዳደር አክብረው ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚንቀሳቀሱከሆነም ያለ ምንም ችግር ስራቸውን የሚሰሩበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ነገር ግን ቀድሞ ሲሄዱበት በነበረበት ሁኔታ እንደማይቀጥሉ እርግጠኞች ነን። ለእነዚህ ሰዎች ተብሎ ገበሬው ከእርሻ ቦታው እንደማይፈናቀል እርግጠኞች ነን። እኔ በግሌ የማምነው ወደፊት የምንፈጥራቸው የኢኮኖሚ አማራጮች አሁን ካለንበት ትልቅ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤ በመሆኑም አሁን ትኩረታችን አዳዲስ ሃሳቦችን መቅረጽ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ለኢኮኖሚው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ስለሆነ አሁን ትኩረት አድርገን እንሰራለን።
አዲስ ዘመን ፦ ከሶስት ከአራት አመት በፊት በክልሉ በነበሩ ችግሮች ብዙ ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል ይህ ሁኔታ ምናልባትም አሁን ላለው የኢንቨስትመንት መሳብ ስራ ተጽዕኖ አልፈጠረም? አሁን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ተሾመ ፦ በመጀመሪያ ደረጃ የለውጥ ባህርይ የተለያየ አይነት የፖለቲካ ኪሳራን ያመጣል። በተለይም በአገራችን ለውጡ የመጣው ከረጅም ዓመት በኋላ በመሆኑ የሚለወጠውን አካል የሚፈልጉ አካላት ደግሞ የሚፈጥሯቸው ችግሮች አሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በኦሮሚያ ደረጃ በለውጡ ወቅት የተለያዩ ፋብሪካዎች መጎዳት ያለመረጋጋቶች ተፈጥረዋል። አሁን ላይ ሆነን እነዚህን ሁኔታዎች ስናይ ግን ችግሮቹ ከመፈታታቸውም በላይ አሁን ላይ ምንም ዓይነት የጸጥታ ስጋት የለም። ቀድሞ የነበሩ የግዛት ጥያቄዎችና እነሱን ተከትሎ የሚመጣ ችግር ነበር፤ አሁን ላይ ግን እንደሱ አይነት ችግር የለም።
በፊት ለምን ተፈጠረ ቢባል ኦሮሚያ በሚፈነዳ ቦንብ የታጠረች እንድትሆን ተደርጋ በመዘጋጀቷ ነው። ኦሮሚያ ክልል ነህ ብለውት ግን ደግሞ ወሰን ያልሰጡት ክልል ነበር፤ በዚህ የተነሳ ደግሞ ከአጎራባች ጋር ያለመስማማት ቄሮዎችም እንደ አማራጭ በፈጸሟቸው አንዳንድ ነገሮች ክልሉ መረጋጋት ርቆት ነበር፡፡
አሁን ግን በተሰሩ በርካታ ስራዎች ለውጦች መጥተዋል። ከለውጥ በኋላ በተለይም እንደ ክልል ነጻነቱን ካወጀ በኋላ ምንም ዓይነት አለመረጋጋት መፈጠር የለበትም፤ ምክንያቱም ለአራትና አምስት ዓመት ተበድያለሁ ብሎ እንቅስቃሴ ከተደረገና ለብጥብጡ መንስኤ የነበረው ገዢ ፓርቲ ከሄደ በኋላ የሚነሱ ብጥብጦችና አለመረጋጋቶች ፍትሀዊ አይደሉም።
ከፖለቲካል አፈናው ነጻ ከተወጣ በኋላ ሊመጣ የሚገባው ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ነው። ይህ በስራ የሚመጣ መሆኑንም የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት መተማመን ላይ ደርሰናል፤ አሁን ላይም በክልሉ ሰላም ሰፍኗል።
በሌላ በኩል ከለውጡ በፊት ኦሮሚያ ውስጥ የኢንቨስትመንት አስፈላጊነት የገባው አልነበረም፤ ይህም ብቻ አይደለም ሲካሄዱ የነበሩ ኢንቨስትመንቶችም ሰዋዊ አልነበሩም። ባለሀብት መጥቶ አንድን መሬት እስከፈለገ ድረስ በቦታው ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች መፈናቀል ምን ችግር ያስከትላል ተብሎም አይታሰብም ነበር።አሁን ግን እነዚህ ነገሮች እንዲለወጡ ሆኗል።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ጋር ላቋርጦትና እንደው በኢንቨስትመንት ስም ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች በአሀዝ ምን ያህል ናቸው?
አቶ ተሾመ ፦ አሁን ቁጥሩን መግለጽ ባልችልም በቁጥር መገለጽ የሚችሉ ግን አሉ። ይህንን በሚመለከትም መልሶ ማቋቋም ቢሮ ተቋቁሟል። ይህ ቢሮ ደግሞ ከየአካባቢው በልማት ምክንያት የተፈናቀሉትን ሰዎች መረጃም አጠናቅረው ይይዛሉ። በመረጃው መሰረትም እቅድ አውጥተው እየሰሩ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ያማል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዙሪያ ላይ ብትመለከት በልማት ስም የተፈናቀለው ማህበረሰብ በጣም ብዙ ነው። ኦሮሚያ አብዛኛው ክፍሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኑ በጣም ጥሩ ነገር ቢሆንም ደሃውን ከኖረበት ቦታ በማፈናቀል መሆኑ ግን እጅግ ያማል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን ከዚህ በፊት ለሆኑት ነገሮች ቢሮው የተጠናከረ መረጃን እያሰባሰበ ሰዎቹ የሚካሱበትን ሁኔታ እያመቻቸ ይገኛል። ከዚህ ውጪ ግን መሰል ጥፋቶች እንዳይደገሙ ሁሉም የበኩሉን ይወጣል።
አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ እርስዎም እንደ ጠቀሱት ህብረተሰቡ በክልሉ ላይ እየተካሄደ ባለው የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ምንም ዓይነት የኔነት ስሜት እንዲያድርበት ስላልሆነ አይጠብቀውም ነበር፤ እንደውም ጉዳት አድርሷል፤ ይህ ሁኔታ አሁንስ ምን ይመስላል?
አቶ ተሾመ፦ አሁን ላይ ይህ ነገር የለም፡፡ እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት ፖለቲካዊ ለውጡን ነው፡፡ ለውጡ ላይ ከተሰሩ ስራዎች መካከልም በፊት ያለው የጨቋኝነት አስተዳደር እንዳይኖርና በተቻለ መጠን ህዝቡን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች መሰራት አለባቸው በሚል ነው የተሰራው።
በሌላ በኩል መታየት ያለበት ኢንቨስትመንት አስፈለጊ ነው። ነገር ግን የህዝቡን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ አለበት። በመሆኑም ህዝቡን ማዕከል ያደረገ ኢንቨስትመንት አስፋፍተን ኢኮኖሚውን ፈጥሮ ራሱ ተወዳዳሪ መሆን እንዲቻል የሚያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አከናውነናል።
ድህነት ውስጥ ማንም አልተፈጠረም፡፡ ነገር ግን አጋጣሚ ሆኖ ደሃና ሀብታም ተብለናል፡፡ ሆኖም ሁሉም የራሱን አቅም ካጠናከረ ወደብልጽግና መሄድ ይቻላል ብለን እየሰራን ነው። በመጀመሪያ ያደረግነው ከለውጡ በኋላ ለህዝቡ የሚሆን መንግሥት መቋቋሙን ነው ያስተማርነው፤ መንግሥት ደግሞ የአንድ ማህበረሰብ መነሻ መሆኑን እንዲያውቁም አድርገናል፤ ከዛ ውጪ የሰላም መዋቅራችንን በማጠናከር የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎችን መስራት ጀምረናል።
ይህ በመሆኑም በፊት የነበረው ጥላቻ በክልሉ ላይ ያለው ኢንቨስትመንት የኔ አይደለም ብሎ በማሰብ ጉዳት ለማድረስ የሚደረገው ሙከራ ሁሉ ቀርቷል፤ ህዝቡም ተገንዝቧል፡፡ አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል ምንም ዓይነት ኮሽ የሚል ነገር የለም።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንዲሁም በመሀል ኦሮሚያ ኢንቪስትመንት ስም የመሬት ወረራዎች አሉ የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ? ቀደም ሲሊም ማን ነበር ወራሪው፤ አሁንስ?
አቶ ተሾመ፦ አሁን ይህ ነው ብዬ መናገር አልችልም፤ አለመረጃ የሚነገር ነገር በጣም ከባድ ነው። በመሆኑም እዚህም እዚያም የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ ግን በመረጃ የተደገፈ መሆን አለበት። ከዛ ውጪም አሉ የሉም የሚለውን ለመመለስ ሳይንሳዊ ጥናት ይፈልጋሉ።
ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች ብቻ የሆነውን እያነሳን የምናወራ ከሆነ ችግር ውስጥ መግባት ይመጣል። የመሬት አስተዳደር አቅማችን ዘመናዊ ባለመሆኑ መሬት አሸናሸናችንም በተመሳሳይ ተናበን የማንሰራ በመሆኑ ከዚህም በላይ እያንዳንዱ የሚሰሩ ወይም የተሰሩ ስራዎችን ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ በማይመዘንበት ጊዜ እነዚህ የተነሱት ነገሮች ይፈጠራሉ።
አሁን ለምሳሌ መንግሥት መሬት በጨረታ ወይም በሌሎች አማራጮች ይሰጥ የሚለውን ነገር ዘግቶ ይተላለፍ የሚለው በቦርድ ነው። ይህንን ያደረገውም ህገወጥነቱን ለመከላከል ነው። በኦሮሚያ ደረጃም የመሬት ባንክ አቋቁመን በተለይም በህገ ወጥ ሁኔታ የተያዙ መሬቶች ወደባንኩ ገቢ እንዲሆኑም እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በክልሉ 17 ሺ በላይ ኢንቨስ ትመንቶች በክልሉ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ነግረውኛል፤ እንደ አገር በተለይም ኢንደስትሪው ኢኮኖሚውን እንዲመራ ተደርጎ ነውና አቅጣጫው የተቀመጠው በእናንተ በኩልስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ተሾመ፦ ልክ ነው፤ በክልሉ ካሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት ዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። ነገር ግን አንድ ኢኮኖሚን በሚገነባ አገር በተለይም ደግሞ እንደ ኦሮሚያ አይነት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባሉበት ሁኔታ ይህ መሆን የሌለበት ነው።
ኢንደስትሪው ሊመራ ነበር የሚገባው፤ ኢንደስትሪው ላይ እስኪደረስ ድረስ ደግሞ ግብርና ነበር ሊመራው የሚያስፈልገው፤ በመሆኑም ሂደቱ ጤናማ እንዳልሆነ እናውቃለን ለዚህ ጤናማ ያልሆነ እንቅስቃሴ ደግሞ ዋናው ምክንያት ላለፉት ብዙ ዓመታት በክልሉ ላይ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት አለመኖሩ ነው።
በመሆኑም ከለውጡ በኋላ ይህንን ክፍተት ለመሙላትና የኢንዱሰትሪ ክፍሉ እንዲጠናከር ሰፋፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ተሾመ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27/2014