በአገራችን የዲጂታል ቴክኖሎጂው እድገት በጣም ፈጣን እየሆነ መጥቷል። ክንውኑ ከዓለም ስርአትና ስልጣኔ ጋር በቀጥታ ተያያዥ ከመሆኑ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ትስስርና ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚደረጉ ጥረቶች የሉአላዊነት ህግና ስርአትን መከተል ብሎም ከእርሱ ጋር ከሚገናኙ ስልጣኔዎች እኩል መራመድን ይጠይቃል።
ለዚህም ይመስላል በአገራችን ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሊያም ከመረጃ መረብና በይነ መረብ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች በፍጥነት ሲቀያየሩና አዳዲስ ለውጦች ሲከሰቱ የምናየው። አሁን አሁን የእያንዳንዱ ማህበረሰብ የእለት ተለት እንቅስቃሴ ከበይነ መረብና ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ከተሳሳሩ ጉዳዮች ጋር የተገናኘ ነው። የህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የመንግስትና የግል ተቋማት አያሌ ክንውኖችም ከዚሁ የአራተኛው ትውልድ አብዮት ውጤት ከሆነው ቴክኖሎጂ ጋር ይያያዛል።
ይህን ተከትሎ የአገራችን መንግስት ዘርፉን የሚቆጣጠር፣ ከጥቃት የሚከላከልና ከሚፈለገው የአለማችን የዘርፉ እድገት ጋር ተቀላጥፎ ስልጣኔውን እንዲቀላቀል ለማድረግ የሚያስችል ተቋማትን እየገነባ ይገኛል። ከነዚህ መካከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ይገኙበታል።
እነዚህ ተቋማትም በሰው ሃይል ልማት ፣ በምርምርና በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሚላመዱ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታና ሌሎች የቁጥጥር ተግባራት ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይሳተፋሉ። በዛሬው የ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ›› አምዳችን ላይ የአንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተግባርና ሃላፊነት ከሆነው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባርና ሃላፊነት ውስጥ “መረጃን የመስጠትና የማንቃት” ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ በአብዛኛው ጥንቃቄ ላይ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
በተለይ ዘመኑን መዋጀትና የምንጠቀመውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ በተገቢው መንገድ መገንዘብ ግድ ስለሚል ከተቋሙ የደረሱንን መረጃዎች እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን። የዲጂታል ግብይት ሥርዓት በዚህ ሰሞን ከሰማናቸው መረጃዎች ውስጥ በዲጂታል ስርአት ዉስጥ በሚከናወኑ ግብይቶች ላይ የሚከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች እንዳሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ይህን ቴክኖሎጂ የሰዎችን አኗኗር ካቀለለባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የበይነመረብ ግብይት (የኢንተርኔት ማርኬቲንግ) ሲሆን በፊት ላይ ከነበረው ተለምዷዊ አሰራር ማለትም ሰዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ጉልበታቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን ከማባከን ይልቅ የሚፈልጉትን ነገር ወይም አገልግሎት በቀላሉ ከኦንላይን የሽያጭ ማዕከላት በመምረጥና በማዘዝ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉበት ስርዓት ቢሆንም ከተለያዩ የሳይበር ጥቃቶች ራስን ለመካላከል ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ጉዳይ ነው::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ያለው የበይነመረብ ግብይት አገልግሎት ደረጃ በመስፋፋት ላይ ነዉ። በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ ክፍያ ስርዓት በሳይበር ምህዳሩ ዉስጥ በኦን ላይን ክፍያ ስርዓት (Online Digital Payment Platform) በብዛት እንደሚተገበር ይጠበቃል። ስለሆነም የኦን ላይን ግብይት ስርዓቱን ደህንነት ማስጠበቅ ያስፈልጋል። ከላይ የተነሳውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም በዲጂታል ግብይቱ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቃቶች ምን እንደሆኑ እንደሚከተለው መረጃውን አድርሶናል።
በዚህም የአገልግሎት ማቋረጥ (denial of service)፣ ሰርጎ መግባት (Interception)፣ ሲስተሞች ላይ የተለያዩ ሊንኮች በመላክ ገንዘብ መስረቅ (financial theft)፣ የማጭበርበር አደጋ፣የግብር አከፋፈል አደጋ ስጋት፣የክፍያ ግጭቶች ስጋት፤ የአፕሎኪሽን እና የኔትወርክ መጨናነቅ፤ ለተጭበረበረ ዌብ ሳይት መጋለጥ፤ ጥራቱን ላልጠበቀ ምርት መጋለጥ፤ ለሀሰተኛ ፕሌትፎርሞች መጋለጥ፤
ዕምነትን በቀላሉ ለመመስረት መቸገር፤ የክሬዲት ካርድ መጭበርበር ወይም ስርቆት መሆናቸውን ነግሮናል።
ከዚህ የተነሳ ከላይ የተዘረዘሩ በበይነ መረብ ግብይት አማካይነት የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶችን በግለሰብ እንዲሁም በተቋማት ደረጃ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል:: የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት በዚህ ሰሞን ተቋሙ ልዩ ትኩረት እንድናደርግበት ካስገነዘበን መረጃ መካከል የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት እና የአደጋ ስጋት መኖሩን ከተረዳን እንደ ተቋም ሊወሰዱ የሚገቡ ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።
በዚህም የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጓል። የሳይበር ምህዳሩ የሰው ልጆችን የእለት ተእለት የኑሮ ዘይቤ ቢያዘምነውም በዚያው ልክ ተጋላጭ በማድረጉ ሚስጥራዊ ብለን ያስቀመጥናቸው ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ እንዲሁም ሃገራዊ መረጃዎችን በቅጽበት ሲያሳጡን መስማት እና ማየት የተለመደ ሆኗል።
ብዙውን ጊዜም የሳይበር ጥቃቶች ከአጠቃቀም ግድፍት ወይም ሆን ተብሎ በመረጃ መንታፊዎች በሚፈጸም ጥቃቶች ሊከሰቱ ይችላሉ።
በመሆኑም ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መኖሩን ካወቁ ምን እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል የሚለውን ከዚህ በታች ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን። የተቋሙን ማስረጃዎችን መጠበቅ፦ በሳይበር ጥቃት ተጠቅተው ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚያምኗቸውን ፋይሎች ከሌሎች መረጃዎች ለይቶ ማስቀመጥ። ሰርቨሮችን መቆጣጠር፦ የትኞቹ ሰርቨሮች ጥቃቱ እንደተሰነዘረባቸው መለየት እና ጥቃቱ እንዳይሰራጭ ከሌሎች ሰርቨሮች እና መሳሪያዎች መለየት እና የደህንነት መቆጣጠሪያ መተግበሪያዎችን መጫን።
ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ እርምጃዎችን መዉሰድ፦ ከተቋሙ ሰርቨሮች ጋር የተያያዙ ባለድርሻ ኣካላት ካሉ ስለተከሰተዉ ጉዳይ ማሳወቅና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ ፤ የተቋሙን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ስርዓቶችንና ሲስተሞች እንዲሁም የተቋሙን ፖሊሲዎች እና ስታንዳርዶች ተጣጣሚነታቸውን ያሉትን ክፍተቶች መገምገም መከለስና እርምጃ መውሰድ፤ የኢ -ሜይል አቅራቢዎች እና ፀረ ቫይረስ ፕሮግራሞችን መፈተሽ የጥቃቱን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የጥቃቱ መንገዶች እንዲሁም ለጥቃቱ ሰለባና እንደ መግቢያ በር ሆነው ሙሉ ስርዓቱን እንዲጠቃ የሚያደርጉትን የሲስተሙ ክፍሎች መለየት ተገቢውን እርምጃ ወይም እርማት እነሱ ላይ በቀላሉ ለመስጠት ያስችላል ።
የዘርፉን ባለሙያዎች ማማከር፦ ለጥቃቱ ተገቢውን እርማት ለመስጠትና ዳታውን ከጥፋት ለመታደግ ለጥቃቱ በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ልምድ ያለው እና አቅጣጫዎችን መስጠት የሚችል ባለሙያም ማግኘት መፍትሄ ነው።
ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችንና ከሕግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም ሪፖርት ማድረግ፤ የኢመደኤ ባለሙያዎችን በነጻ የስልክ መስመር 933 ደውሎ የሳይበር ደህንነት እርዳታ መጠየቅ ይገኙበታል።
ማህበራዊ ሚዲያና ሃሰተኛ መረጃዎች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከሰሞኑ የማህበራዊ ሚዲያዎችን የተመለከተ አዲስ ተጨማሪ መረጃ ሰጪ ጉዳይ ይዞልን ብቅ ብሏል። ዋናው የዚህ መረጃ ማጠንጠኛም “የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ለሀሰተኛ መረጃዎች እና ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫነት ለምን ተመራጭ ሆኑ?” የሚል ሲሆን ለዚያ ቁልፍ ምላሽ የሚሆኑ ምክንያቶችንም እንደሚከተለው አስቀምጦልናል።
ዋነኛ መነሻ ምክንያቱም አንደኛ በቀላሉ ተደራሽ (Accessible) እና ለመጠቀም ቀላል መሆኑ፤ ለሁሉም ሰው እኩል የመረጃ አቅራቢነት መብት/የጋዜጠኝነት ሚና (citizen journalism) የሚሰጥ መሆኑ፤ ሁሉም መረጃ አፍላቂነት/ምንጭነት ያለ ምንም ገደብ ሁሉም የኢንተርኔት ግንኙነት ያለውና መጠቀሚያ መሳሪያ ያለው ግለሰብ የፈለገውን መልዕክት እንደ ፈለገ ያለማንም ተቆጣጣሪነት፣ አጣሪነትና ከልካይነት መፃፍ/መለጠፍ የሚያስችል መሆኑ፤ መጠነኛ ድብቅ ማንነትን የሚፈቅድ መሆኑ ፣ የፅሁፍ ፀሃፊዎች/የመረጃ ምንጮች ማንነታቸዉን መደበቅ የሚያስችላቸውና ማንነታቸው ሳይታወቅ የፈለጉትን ፅሁፍ መለጠፍ የሚችሉበት ምህዳር መሆኑ ነው ::
ነገር ግን ተጠቃሚዎች እንደዛ ያስቡ እንጂ አሁንም ቢሆን ውስብስብ ቢሆንም በማህበራዊ ሚድያ ማንነትን ሙሉ ለሙሉ መደበቅ አይቻልም :: ፈጣን የመረጃ ልውውጥ የሚካሄድበት ፕላትፎርም መሆኑ አምስት ሴኮንድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ፈጣን የመረጃ ልውውጥን ማድረግ ያስችላል፤መረጃዎችን በቀላሉ ማጋራት ማስቻሉ ፤ ይህም በጥቂት ሰዓታት አንድ መረጃ አለማቀፍ ሽፋን እንዲያገኝ ያስችለዋል:: ድምበር የለሽ / አለማቀፋዊነቱ የሚለቀቁ መረጃዎች ተደራሽነት የተገደቡ ወይም ሃገራዊ ብቻ ሳይሆኑ እስካሁን የህግ ክልከላ እስካልተደረገ ድረስ አለማቀፋዊ ነው ::
እንደመዝናኛ ሆኖ ማገልገሉ፤ ብዙ ሰዎች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኖሩት ማድረጉ፤ ሁሉንም ሚድያዎች በአንድ ላይ የያዘ (Multimedia) ባህሪ ስላለው ፤ እንደ ሁለተኛ ማንነት መፍጠሪያ መንገድ መሆኑ ፤ ምናባዊ ዓለም (Virtual world) እንዲሁም ከሌሎች ሜንስትሪም ሚዲያዎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ተጠያቂነት ያለበት መሆኑ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከላይ ያነሳናቸውን መረጃዎች ለጥንቃቄና ቅድመ መከላከል ይረዳ ዘንድ መረጃ በቀጥታ ከማድረስ በዘለለ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብርና የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ይሰራል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ኤጀንሲዉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በመረጃ ደህንነት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ሰምተናል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር የዘመናዊ ግብይት ስርአትን ለማሳለጥ በሚያግዙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በመረጃ ደህንነት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ነው የተፈራረመት።
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ኢመደኤ በአዋጅ ከተሰጡት ሃላፊነቶች ዋናው የሃገሪቱን የኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማት ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑን አውስተው እንደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ አይነት ወሳኝ ሃገራዊ ተቋማትን ደህንነት ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ነው ብለዋል።
ኢመደኤ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመረጃ ፍስት እንዳይስተጓጎል ከመነሻው ጀምሮ እስከ መዳረሻው ሚስጢራዊነቱን እና ደህንነቱን ጠብቆ እንዲዘዋወር ማድረግ ይገባል ያሉት ዶክተር ሹመቴ ኢመደኤም የመረጃን ወሳኝ ሃብትነት በመረዳት የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎናቸው እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በበኩላቸዉ ከኢመደኤ ጋር የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ተቋማቸው ለያዘው የአፍሪካ የልህቀት ማዕከልነት ግስጋሴ እንደሚያቀላጥፍ እና ምርት ገበያው ወደፊት ለሚጀምራቸው ወሳኝ ስራዎች የቴክኖሎጂ አቅምን እና ብቃትን ለማጎልበት የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ25 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚደረጉ የግብይት ስርአት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ በየአመቱ 40 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸዉን መርቶች ተቋማቸዉ እንደሚያገበያይ ነው የገለጹት።
ኢመደኤ ከዚህ ቀደም ከተቋማቸዉ ጋር በጋራ እየሰራ መቆየቱን ያወሱት አቶ ወንድማገኝ በቅርቡም ኤጀንሲው በክልሎች ለሰባት የግብይት ማዕከላት የደህንነት ፍተሻ ካደረገላቸው በኋላ ወደስራ መግባታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
በዚህ የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ኢመደኤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስራ ክፍሎችን አገልግሎት አውቶሜትድ የማድረግ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፖሊሲ የማዘጋጀት፣ የሳይበር ኢዲት እና ምዘና ማከናወንን ጨምሮ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ድጋፍ ያደርጋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014