በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች የእለት ጉርስ አጥተው በችግርና በርሀብ የቀን ውሏቸውን የሚያሳልፉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። እነዚህ ዜጎች ከግለሰብ ቤት እስከ ጎዳና እንዲሁም በየሆቴሉ በር ላይ ጥቋቁር ፌስታሎችን ይዘው ሲቆሙ ማየት ለአዲስ አበባ ነዋሪ እንግዳ ትእይንት አይደለም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኑሮ ውድነቱ መባባስና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያለ ተቀባይና ያለ ስራ እድል እየጎረፉ የሚመጡት ሰዎች ቁጥር መጨመርም የችግሩ አንዱ አባባሽ ምክንያት ሆኗል። በዚህም የተነሳ የችግሩን ስፋት በመንግስት ወይንም በአንድ ድርጅትና ግለሰብ ሊቀረፍ ከማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል።
ለማንኛውም ሰው መሰረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተለዩትና በየእለቱ ተሟልተው እንዲቀርቡ የሚጠበቁት የተመጣጠኑ ምግቦችን ማሰብ ለአብዛኛው ዜጋ የቅንጦት ጥያቄ ሆኗል። ይህንን እንደ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር የገጠመንን የእለት ጉርስ የማሟላት ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፤ ግለሰቦችና መንግስት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው ተስፋ ብርሃን የምገባ ማእከል አንዱ ነው። እኛም ለዛሬ የአገርኛ አምድ ዝግጅታችን የማእከሉን ጅማሮና እንቅስቃሴ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ወይዘሮ አንቺነሽ ተስፋዬ በአዲስ አበባ ከተማ የምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ወይዘሮ አንቺነሽ የማእከሉን አመሰራረትና አሁን ያለበትን ደረጃ እንዲህ ይገልጹታል። ተስፋ ብርሃን የምገባ ማእከል የተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የሀሳብ አመንጪነትና አስተባበሪነት ነው። ከንቲባዋም ይህንን ስራ ለመጀመር ያበቃቸው ደግሞ ለስራ ሲንቀሳቀሱ የገጠማቸው ነገር ነበር። ከንቲባዋ በአንድ ወቅት ቆሼ የሚባለው አካባቢ የነበረን ፕሮጀክት ለመጎበኘት ለስራ ጉዳይ በቦታው በተገኙበት ወቅት በአካባቢው ለህሊና የሚከብድ ነገር ይመለከታሉ።
አካባቢው የከተማዋ ቆሻሻ ከየቦታው ተሰብስቦ የሚደፋበት ነው። እናም እዛ አካባቢ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አቅመ ደካሞችና ችግርተኞች የተለያዩ የምግብ መቀበያ እቃዎችን ይዘው ተሰልፈው ይጠባበቃሉ። የሚጠብቁት ደግሞ ከተለያዩ ግለሰቦችና ሆቴሎች ተሰብስቦ ከመጣው ቆሻሻ መካከል ለእነሱም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው የሚሆነውን ምግብ በመምረጥ ለመውሰድ ነበር።
በዚህ ሁኔታ የተሰባሰቡት ሰዎች የመጣው ቆሻሻ ወደማከማቸው ከመግባቱ በፊት ከመኪናው እንደተዘረገፈ ተሯሩጠው ወደሆዳቸው ሊገባ የሚችለውን፤ እግረ መንገዳቸውንም ለሚለብሱትና ለሚጫሙትም በለስ ከቀናቸውና ካገኙ ይወስዳሉ። በዚህ አይነት የየእለት ተግባር በመኖር ላይ ያሉትን ችግርተኛ ዜጎች ያዩት ከንቲባዋም አንዳች ነገር በማድረግ እንደ ከተማ ይህ መሰሉ ችግር መቀረፍ እንዳለበት በመወሰን ስራቸውን ይጀምራሉ።
ከንቲባዋ የመጀመሪያ ስራቸው ያደረጉትም ለባለ ሀብቶች፣ ለሆቴሎችና ሌሎችም ትብብር እንዲያደርጉ ለሚመለከታቸው አካላት በሚዲያ ጥሪ ማስተላለፍ ነበር። ያቀረቡትም ጥሪ «በአንድ ወገን በከፍተኛ ደረጃ ይበላው ይጠጣው ያጣ ህዝብ በከተማችን በስፋት ይታያል፤ በሌላ በኩል በየቀኑ በርካታ ምግብ እየተትረፈረፈ በብክነት እየተወገደ ይገኛል። ይህንን የተዛባ አካሄድ በማስተካከል ወገኖቻችንን መታደግ ይጠበቅብናል» የሚል ነበር። በዚህም መሰረት ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በሰጡት ፈጣን ምላሽ በአጭር ግዜ ውስጥ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ሊገባ ችሏል።
ፕሮጀክቱ በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ክትትልና በሚመለከታቸው አካላት ርብርብ በተጀመረ በሶስት ወራት ውስጥ በስድስት ክፍለ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጡ ማእከላትን ለማቋቋም ይበቃል። የተቋቋሙት ማእከላት በቦታ አቅርቦትና በማስተባበር ረገድ ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት በመውሰድ የሰራ ሲሆን ግንባታውንና የግብአት አቅርቦቱን ደግሞ ባለሀብቶች፤ መንግስታዊ የሆኑና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባደረጉት ድጋፍ ለመስራት ተችሏል።
የቅድመ ዝግጅት ስራው ተጠናቆ የመመገብ አገልግሎቱ ሲጀመርም በማእከሉ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚለዩት ሰዎች በማእከላዊ ዘርፍ የዚህ ግልጋሎት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ተብለው በየክፍለ ከተማውና ወረዳው ተለይተው የሚላኩ ናቸው። ማእከሉ እንደ ስርአት በዚህ መልኩ በየደረጃው ተለይተው የሚመጡትን ለማብላትና ለማጠጣት አሰራር ያስቀመጠ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን ማንኛውም አገልግሎቱን መጠቀም የፈለገ ሁሉ እየተመገበ ይገኛል። ይህም ሆኖ ሁሉም ተጠቃሚ ወደ ማእከሉ ሲመጣ ምዝገባ የሚደረግለት ሲሆን በምዝገባውም ለምን ወደ ምገባው ሊቀላቀል እንደቻለ ልየታ ይደረጋል።
ይህ የልየታ ስራ የሚሰራውም ለምን የእለት ምግብ አገልግሎት እንደሚጠቀም በመመርመር ታሞ መስራት አቅቶት ከሆነ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝና ራሱን ሰርቶ ችሎ እንዲበላ ለማብቃት። እንዲሁም ለመመገብ የመጣው ስራ መስራት እየቻለ የስራ እድል ባለማግኘቱ ከሆነ ምገባውን እየተመገበ በተጓዳኝ ወደ ስራ እድል ፈጠራ ተልኮ ባለው አቅም፤ ልምድና የስራ ችሎታ፤ የስራ እድል የሚፈጠርለትን ሁኔታ በማመቻቸት በአካልም በመንፈስም ከተረጂነት ለማላቀቅ በማሰብ ነው። በዚህ መልኩ ስድስት መስፈርቶች ተቀምጦ ልየታ እየተከናወነ ይገኛል።
እንዳጠቃላይ ፕሮጀክቱ እስካሁን ያለው ወደፊትም የሚቀጥለው የሚከናወነው በመንግስት በጀት ሳይሆን በግለሰብ በጎ አድራጊዎችና ፈቃደኛ ተቋማት ነው። በዚህ ሂደት የመንግስት ድርሻ የመመገቢያ ቦታዎችን በመለየት ማዘጋጀት ሲሆን መመገቢያዎቹን የሚገነቡትም ሆነ የመጠቀሚያ ቁሳቁስና የምግብ ግብአቶችን የሚያቀርቡት አገራቸውንና ህዝባቸውን ወዳድ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት ናቸው።
ከእነዚህም መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ማእከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ማእከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ማእከል አቶ ሙኒር ሴኩሪ ኸይረዲን የተባሉ ግለሰብ ባለሀብት፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ማእከል ሮሃ ሄልዝ ፋውንዴሽን የሚባል ተቋም የሚሸፈን ነው። በግንባታ ወቅትም የግንባታ እቃዎችን በማቅረብ አዋሽ ባንክ፤ ዳሸን ባንክ እና ሌሎችም ግለሰቦችና ተቋማት በርካታ አስተዋእጽኦዎችን አበርክተዋል።
የተስፋ ብርሃን የምገባ ማእከል አላማ «በአንድ ወገን ሞልቶ ተርፎ የሚደፋ ምግብ እያለ በሌላ በኩል ተርቦ የእለት ጉርስ አጥቶ ተደፍቶ የሚያድር ዜጋ መኖር የለበትም የሚል ነው።» በዚህም መሰረት ማእከሉ የሚንቀሳቀሰው በእነዚህ ሁለት የተለያዩ ተቃራኒ ነገር ግን ሊስተካከሉ በሚችሉ ክስተቶች መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ሚዛናዊ የአኗኗር ሁኔታን በአዲስ አበባ ከተማ ለመፍጠር ነው። በመሆኑም ቀዳሚ አላማው የእለት ጉርስ ያጣውን ዜጋ መመገብ ነው። ከዚህ ባለፈ እንደየችግራቸው የተገልጋዮቹን አቅም በማጎልበትና ስልጠና በመስጠት ከሁልጊዜ ተረጂነት በማላቀቅ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የሚሰራ ስራ አለ።
በአሁኑ ወቅት ማእከሉ በስድስቱም ማእከላት በየቀኑ ከአስር ሺ በላይ አቅመ ደካሞችና የእለት ጉርስ የማያገኙ ዜጎችን በመመገብ ላይ ይገኛል። በቀጣይም ማእከላቱን ማስፋፋትም ሆነ መቀነስ የሚያስፈልግ ከሆነ በየወቅቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ጥናት በማካሄድ የሚሰራ እንደሚሆንም ወይዘሮ አንቺነሽ ጠቁመዋል።
በጀሞ መስታወት ፋብሪካ ፊት ለፊት የሚገኘው የስድስተኛው ቅርንጫፍ ሙሉ የፋይናንስ ድጋፍ አቅራቢ አቶ ሴኩሪ ኸይረዲን በበኩላቸው የምገባ ስርአቱን እንዴት እንደተቀላለቀሉና አሁን ያለበትን ሀኔታ እንደሚከተለው ገልጸውታል። ከዓመት በፊት ኮሮና በተከሰተበት ወቅት በርካታ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸው ይታወሳል። በተለይም በአብዛኛው ገቢያቸውን ቋሚ ባልሆነ ስራ ያገኙና ይተዳደሩ የነበሩ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ቀኑን ጨለማ አድርጎባቸው እንደነበር የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ይህንን ችግር ለመታደግና ከወገኖቻችን ጎን ለመቆም በማሰብ አምስት መቶ ለሚደርሱ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የወር ቀለብ አስቤዛ ስናቀርብ ቆይተናል።
ወረርሽኙ ሲቀንስና በተመሳሳይ ወቅት ደግሞ እነዚህ ማእከላት እንዲከፈቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጥሪ ሲቀርብ ይህን የተቀደሰ ሀሳብ መደገፍ አለብን በሚል ተነሳሽነት ለመቀላቀል በቃን። በወቅቱ እኛ ያለንበትና ድጋፍ ስናደርግበት የቆየነው ሰፈር ለማእከሉ መመስረት ምክንያት የሆነው ቆሼ በሚባለው አካባቢ ነበር። በመሆኑም እዛው ምግብ ከከተማዋ ተሰብስቦ ከሚመጣ ቆሻሻ እያነሱ የሚመገቡት ሰዎችን ከያሉበት በመሰብሰብ ስራችንን ለመጀመር በቃን። በየቀኑ ከአምስት መቶ እስከ ሰባት መቶ ለሚደርሱ ሰዎች የምሳ ምገባ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንገኛለን። በየቀኑም ሁለትና ሶስት አይነት ምግብ የሚዘጋጅላቸው ሲሆን ሙሉ ወጨውን የሚሸፍነውም እኔው ነኝ። በተጨማሪ በማእከሉ መገኘት የማይችሉ አረጋውያንና በህመም ወስጥ ላሉ ደግሞ ማእከሉን በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ወጣቶች ያሉበት ድረስ እንዲያደርሱላቸው ይደረጋል።
እነዚህ ወገኖች ያለባቸው ችግር የእለት ጉርስ ብቻ ባለመሆኑ በየማእከላቱ የተለያዩ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበርና ከመንግስት የህክምና ተቋማትም በማስመጣት የጤና ምርመራ እየተደረገላቸው ይገኛል። አንዳንድ ግለሰቦችም በፈቃደኝነት አልባሳት የሚያመጡ የሚደግፏቸው አሉ። በአቅማችን በስራ ፈጠራው ረገድም ከጥጥ መፍተል ጀምሮ በተለያዩ ሞያዎች ራሳቸውን እንዲደግፉ እያደረግን እንገኛለን። ይህን አገልግሎትም ችግሩ እስከተቀረፈ አልያም አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ የምቀጥለው ይሆናል።
ይህም ሆኖ አሁንም ድረስ በከተማዋ ከመቶ ሺ በላይ ዜጎች የዚህ አይነት የእለት ጉርስ ድጋፍ የሚፈልጉ እንዳሉ ይገመታል። በመሆኑም ገና ብዙ መስራት የሚጠበቅብን መሆኑን እንደ ዜጋ መገንዘብ አለብን። ማእከላቱም ቢሆን አሁን ካለው በላይ መስፋፋት አለባቸው። ስለዚህ በተጀመረው መሰረት ባለሀብቱ ገንዘቡን በማውጣት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች አገልግሎት በመስጠት፤ የመንግስት ኃላፊዎች በማስተባበር፤ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ የጋራ ችግራችንን በጋራ ለመወጣት መንቀሳቀስ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 22/2014