– የወሎን መልካም እሴት ለማጠናከር የሚተጋው ግብረ ሰናይ ተቋም
‹‹ወሎ›› ሲባል ወደ ብዙ ሰው አዕምሮ ፈጥኖ የሚመጣው ደግነት፣ ውበት፣ መቻቻልና አብሮነት እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራል፤ እውነታውም ከዚህ የተለየ አይደለም። ወሎ የብዙ ባህሎችና እሴቶች መፍለቂያ፣ የመቻቻልና የመዋደድ ማሳያ፣ የውበትና የአብሮነት ሰገነት … ነው። ይህን እሴቱን የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር መሪዎች፣ ምሑራን፣ የኪነ ጥበብ ክዋክብት … የወሎን ምድር የረገጡ ሁሉ መስክረውለታል።
‹‹በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል›› እንዲሉ አሸባሪው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) በፈፀመው ወረራ ምክንያት ወሎ በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ተዳርጓል። ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች የፈፀማቸው ተግባራት ለጆሮ የሚቀፉና ከኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን ከሰው ፍጡር የማይጠበቁ አረመኔያዊ ድርጊቶች ናቸው። ታዲያ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠው ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኝና በዘላቂነትም እንዲቋቋም በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መጠነ ሰፊ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ነው። ድርጅቱ ዘርና ሃይማኖት የማይገድባቸው የበጎ አድራጎት ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ በማቅረብ ላይ በግንባር ቀደምትነት ከተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ስለማኅበሩ አመሠራረት፣ የሥራ እንቅስቃሴና የወደፊት እቅዶች ከማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ይርጋለም ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።
የማኅበሩ አመሰራረትና የመነሻ ተግባራት
የ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› አመሰራረት ባለፈው ዓመት ወሎ ውስጥ ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ካደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ጋር ይያያዛል። በወቅቱ ጉዳቱን የተመለከቱ ጥቂት በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ስለችግሩ ከማውራት ባለፈ ተግባራዊ መፍትሔ ለመፈለግ ተነጋገሩ። በጎ ፈቃደኞቹ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በ12 መስራች የኮሚቴ አባላት (ስድስት በአገር ውስጥ፤ ስድስት በውጭ አገራት) ተደራጅተው ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በሚል ጥላ ስር ተሰባስበው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ሥራቸውን ጀመሩ። የመጀመሪያ ሥራቸውም ሰብላቸው በአንበጣ መንጋ ለወደመባቸው የወረባቦ፣ የወርቄ፣ የባቲና የአርጎባ አርሶ አደሮች ድጋፍ ማድረግ ነበር።
ይህን ካከናወኑ በኋላም ሥራውን ለማጠናከር በማሰብ የማኅበራዊ ሚዲያውን (በተለይም ፌስቡክን) በመጠቀም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ ማሰባሰባቸውን ቀጠሉ። በማኅበሩ የፌስቡክ አድራሻ በኩል ሥራዎቻቸውን ሲያስተዋወቁም በጎ ምላሾችን አገኙ።
የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራትን የማስፋት እንቅ ስቃሴ
ማኅበሩ ስለሥራዎቹ እያስተዋወቀ ተቀባይነት እያገኘ ሲመጣ፣ ተግባሩን አስፍቶና አጠንክሮ መቀጠል እንዳለበት በመገንዘብ ወሎን መነሻው፣ ኢትዮጵያን መዳረሻው አድርጎ የሰብዓዊ ድጋፍና የልማት ተግባራትን የማከናወን እንቅስቃሴውን ገፋበት። በታኅሣሥ ወር 2013 ዓ.ም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በማውጣት ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቅለው በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ተጠልለው ለነበሩ ዜጎች ድጋፍ አድርጓል። ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ገንዘብ ካሰባሰበ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች ድጋፍ አድርጓል።
ድርጅቱ ከሰብዓዊ ድጋፍና የልማት ተግባራት በተጨማሪ ለአገራቸው አስተዋፅዖ ያበረከቱ ባለውለታዎች እንዲዘከሩና ትውልዱ በታሪክ እውቀትና በመልካም ሥነ ምግባር እንዲታነፅ የማድረግ ዓላማ ስላለው፣ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር፣ ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም የንጉሥ ሚካኤል አሊ (የወሎ ንጉሥ፣ የአልጋ ወራሽ ልጅ ኢያሱ አባት) የልደት መታሰቢያ ቀን በተንታ፣ በደሴና በአዲስ አበባ ከተሞች እንዲከበርና ለተንታ ቤተ መጽሐፍትም የመጽሐፍት ድጋፍ አድርጓል።
ወቅታዊው ሁኔታና የማኅበሩ እንቅስቃሴ
በእርግጥ የማኅበሩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በልማት በተለይም፤ በትምህርት፣ በጤናና በቱሪዝም፤ ተግባራት ላይ የነበረ ቢሆንም አሸባሪው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) የከፈተው ጦርነት ድርጅቱ በሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት ላይ አተኩሮ እንዲቀጥል አድርጎታል። እስካሁን ድረስ ስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችና ለፀጥታ ኃይሎች የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል። ከእነዚህም መካከል፡-
- ለድሬ ሮቃ አካባቢ ወላድ እናቶችና ሕፃናት ምግብና አልባሳት
- ተሁለደሬ ወረዳ፣ ሰግለን አካባቢ ለሚገኙ 250 አባወራዎች የምግብ ድጋፍ
- ራያ ቆቦ፣ ዞብል አካባቢ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች የምግብ ድጋፍ (በዚህ አካባቢ ድጋፍ ያደረገት በአፋር፣ ጭፍራ በኩል ተጉዘው ነው)
- ውርጌሳ አካባቢ ለሚኖሩ 900 አባወራዎች የምግብ ድጋፍ
- ከሰሜን ወሎና ፀሐይ መውጫ አካባቢዎች ተፈናቅለው ወገልጤና ለነበሩ 600 አባወራዎች የተደረገ ድጋፍ
- ከሰሜን ወሎና ዋግ ኸምራ ዞኖች ተፈናቅለው ባህር ዳር፣ ዘንዘልማ ለነበሩ አንድ ሺ 200 ተፈናቃዮች የተደረገ 200 ኩንታል የምግብ ድጋፍ
- አግሪት እና ፍላቂት አካባቢዎች ለነበሩ 600 አባወራዎች የምግብ ድጋፍ
- አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ ከደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ለነበሩ ተፈናቃዮች የተደረገ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመኝታ ፍራሽና የንፅህና መጠበቂያ መሳሪያዎች ድጋፍ
- መካነ ሰላም ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የተደረገ የ700ሺ ብር የምግብ ድጋፍ (ሩዝ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ የሕፃናት ወተት)
- ደብረ ታቦር ሆስፒታል ለሚገኙ ቁስለኞች የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ (ከአሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ጋር ሲፋለሙ ጉዳት ደርሶባቸው ደብረ ታቦር ሆስፒታል የሕክምና ክትትል ላይ ለነበሩ ቁስለኞች የቁስል ማጠቢያና የቀዶ ጥገና ጓንት ድጋፍ አድርጓል)
- ለጋሸናና ላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች የተደረገ የ200 ኩንታል የምግብ ዱቄት ድጋፍ
- ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የፍራሽና ብርድ ልብስ ድጋፍ
- ደላንታ አካባቢ ለነበሩ የአማራ ልዩ ኃይል ቁስለኞች የተደረገ የአልባሳት ድጋፍ
- ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የተደረጉ የምግብና የአልባሳት ድጋፎች
- በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ሕዝባዊ የፀጥታ አካላት የተደረጉ የምግብና የአልባሳት ድጋፎች … ይጠቀሳሉ።
በመስከረም 2013 ዓ.ም እንቅስቃሴውን የጀመረው ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሕጋዊ እውቅና አግኝቷል። ዋና መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን ደሴ እና ወልድያ ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት።
ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራቱ የሚያስፈ ልገውን ገንዘብ እያገኘ ያለው በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከሚኖሩ በጎ ፈቃደኞችና ለጋሾች ነው። በተለይም በአረብ አገራት፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለድርጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋሉ። ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ብዙ ኤርትራውያን ለጋሾችም ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
ድርጅቱ አብዛኛውን ገንዘብ የሚሰበስበውም ማኅበራዊ ሚዲያውን፣ በተለይም ፌስቡክንና ቴሌግራ ምን፣ በመጠቀም ነው። ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እውቅናና ፈቃድ ያገኘ በመሆኑ እያንዳንዱን ግዥ በሕጋዊ መንገድ በመፈፀም አሰራሩን ግልፅ የማድረግ ሥርዓትን ይከተላል። ገንዘብ ወጭ ሲደረግም በሁሉም የኮሚቴው አባላት ስምምነት ብቻ እንዲሆን ተደርጓል።
ተግዳሮቶች
‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ሥራውን ሲያከናውን ካጋጠሙት ችግሮች መካከል አንዱ የትራንስፖርት ችግር ነው። ድርጅቱ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ ለማቅረብ የተንቀሳቀሰባቸው አንዳንዶቹ ቦታዎች በአቅራቢያቸው ጦርነት ይደረግባቸው ስለነበር እንደልብ ተንቀሳቅሶ እርዳታ ማቅረብ አስቸጋሪ ነበር።
በጦርነቱ ሰበብ የግንኙነት መስመሮች ተቋርጠው ስለነበር የጉዳት መጠንን የሚያሳይ የተደራጀ መረጃ ማግኘትም ለድርጅቱ ፈታኝ ሆኖበት ነበር። የችግሮች ስፋትና የማኅበሩ አቅም ተመጣጣኝ ያለመሆንም ሌላው የድርጅቱ ፈተና ነው።
ቀጣይ እቅዶች
የ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› መሪ ቃል ‹‹የወሎን መልካም እሴት እናስቀጥላለን›› የሚል ነው። ዘር ሳይቆጥሩና ሃይማኖትን ሳይለኩ ሰውን በሰውነቱ መቀበልና ማክበር፣ መቻቻልና መደጋገፍ ወሎ ከሚታወቅባቸው መልካም እሴቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ድርጅቱም ሥራውን ሲጀምር ይህን መልካም እሴት የማጎልበትና የማስቀጠል ዓላማን ይዞ ነው። ትውልዱ በስነ ምግባር ታንፆ ይህን እሴት ይዞ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን እቅዶች አሉት።
ወቅቱ ጦርነቱ ብዙ ምስቅልቅሎችን ያስከተለበት በመሆኑ ድርጅቱ በጦርነቱ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከችግሮቻቸው እንዲያገግሙ በተጠናከረ ሁኔታ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎችን ይሠራል። የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢዎቻቸው እንዲመለሱና ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውም ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲሁም ከቁሳዊ ውድመት ባሻገር ስነ ልቦናዊ ጉዳት ያጋጠማቸው ወገኖች እንዲፅናኑ ጥረት ያደርጋል። የወደሙ የትምህርትና የጤና እንዲሁም ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ላይም የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ ይሆናል።
ጦርነቱ በአገር ላይ የተቃጣ አደጋ በመሆኑ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን የማቋቋም ሥራው በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለእነዚህ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርግም ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ጥሪውን አቅርቧል።
ሁልጊዜም እርዳታ በመስጠት የሰውን ሕይወት በዘላቂነት መቀየር እንደማይቻል የሚያምነው ድርጅቱ፤ ከእርዳታ የተሻገሩና ዘላቂ እድገትና ጥቅም የሚያስገኙ የልማት ተግባራትን የማከናወን እቅድም አለው። አሁን የሚስተዋሉት ወቅታዊ ችግሮች እልባት ሲያገኙ በልማት ተግባራት ላይ በማተኮር በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታና ልማት ላይ የሚሳተፍ ይሆናል። ታሪክና ባሕልን ለማስተዋወቅና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትንም ያከናውናል።
ወሎ የሃይማኖት መቻቻል ተምሳሌት እንደሆነ በተደጋጋሚ ተመስክሮለታል፤ የበርካታ ባህሎችና እሴቶች መፍለቂያ እንደሆነም ይታወቃል። ስለሆነም ኅብረተሰቡ ከዚህ ባህሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ድርጅቱ አበክሮ ለመሥራት እቅድ ይዟል።
ሌላው ማኅበሩ በቀጣይ ለማከናወን በእቅድ የያዘው ተግባር ሱሰኝነትን ማስወገድ ነው። በብዙ የወሎ አካባቢዎች የበርካታ አርሶ አደሮች ማሳ በጫት የተሸፈነ ነው። ይህ ሁኔታ ሱሰኝነትን ከማስፋፋት አንፃር ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ብሎ የሚያምነው ‹‹ወሎ ቤተ አምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› አርሶ አደሮቹ ጫት ከማምረት በመውጣት አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎችን እንዲያመርቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ጨምሮ ተጓዳኝ ተግባራትን ያከናውናል።
ከወሎ አካባቢ ወደ አረብ አገራት የሚሰደዱ በርካታ ወጣቶች ስደትን እንደአማራጭ ማየትን አቁመው በአገራቸው ሰርተው ሕይወታቸውን መለወጥ እንደሚችሉ ማሳየትና ማስገንዘብ እንዲሁም እድሎችን ማመቻቸት ላይ አተኩሮ የሚሰራም ይሆናል። በአጠቃላይ የወሎን መልካም እሴቶች የሚያስቀጥሉ ተግባራትን ለማከናወን እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 15/2014