ሕይወት የዋዛ አይደለምና ላይ ታች ያሯሯጣል። እያወጣ እንደሚያወርደው ሁሉ ከፍና ዝቅም ያደርጋል። ዛሬ እዚህ ነኝ ሲሉት ነገ እዛ ላይ፤ ወይም፣ እዛ ታች አውጥቶ ወይም ጥሎ ይገኛል። ባህር አቋርጠው፣ አየር ሰንጥቀው፣ የብስን ተጉዘው ይሄዱ ዘንድም ሕይወት ግድ የሚልበት ጊዜ ቀላል አይደለም። “ምነው?” ቢሉ መልሱ “እንጀራ ፍለጋ” ወይም “የእንጀራ ጉዳይ” ከመሆን አይዘልም። የዛሬው እንግዳችንም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ የ”እንጀራ ፍለጋ” ጉዳይ ምን ያህል እንዳንገላታው ስንደርስበት ያወጋናል።
እንግዳችንን እናንሳ እንጂ ሕይወት ለማንም ቢሆን አልጋ ባልጋ አይደለችም፤ አትሆንምም። ደረጃው፣ አይነቱ፣ ይዘቱና ይዞታው ይለያይ እንጂ ሕይወት ሁሉንም ትፈትናለች። የበረታ ፈተናውን ያልፍባታል፤ ያልበረታም ይረታና መሀል መንገድ ላይ ይቀርባታል። የሚበጀው ደግሞ መታገሉ ነውና ለሁሉም የሚሻለው በርትቶ መገኘት ነው። የዛሬው እንግዳችን ወጣት ሻምበል ተሾመም ይህንኑ ነው ያደረገው፡፡
ሻምበል የትውልድ አካባቢው ወሎ ክፍለ ሀገር፣ አማራ ሳይንት ሲሆን፤ በመግቢያችን ላይ እንዳልነው ሕይወት ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ከምዕራብ ወደ ማዕከል አሽከርክራዋለች። ይሁን እንጂ ብታዞረውም መልሶ ሊያሽከረክራት አልፈቀደም፡፡ በጥረቱ በሚሽከረከረው እንዝርት እየሾረ ሳይሆን እያሸነፈ እንዲሄድ እየተጋ ነው፡፡ ምክንያቱም ነገ ለእሱ ብሩህ እንደሚሆን ያምናል።
ወጣት ሻምበል ተሾመ ከትውልድ አካባቢው ወደ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ ያቀናው አስቦበት፣ ቦታውን አውቆት አይደለም። ወደ እዛ እንዲሄድ ያደረገው የተሻለ እንጀራ ፍለጋ ነው። በዚህ የተሻለ እንጀራ ፍለጋ ህልሙ ውስጥ ግን ለብዝበዛ ተጋልጧል። ጉዳዩ እንዲህ ነው።
በ1991 ዓ.ም ወሎ ደሴ ውስጥ ሲዘዋወር ወለጋ ማለትም ሆሮ ጉዱሩ የሚባል ቦታ ላይ በአንድ የሰሊጥ ፋብሪካ ውስጥ የሥራ እድል እንዳለ በአንድ አሰሪ ድርጅት ሲነገር ይሰማል። ድርጅቱ ሰራተኛ በብዛት እንደሚፈልግ፣ ሁሉ ነገር የተመቻቸ (መጠለያ፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ፣ ምግብ …) እንደሚያሟላና ደሞዙ በቀን 90 ብር መሆኑ …፤ በአጠቃላይ የሚሄዱበት አካባቢ ገነት ተደርጎ በቀጣሪ ድርጅቱ አማካኝነት ለእሱና መሰሎቹ ይነገራቸዋል።
ያለ ምንም ማመንታት ጉዞ ይጀመራል፡፡ አካሂዳቸው ግን በተሸፈነና ወዴት እንኳን እንደሚሄዱ በማያሳይ መኪና ነበር፡፡ የሚያውቁት እንደተነገራቸው ወደ ፊት ሲደርሱ ወለጋ የአቶ በዳሳ ተረፈ ሰሊጥ ማምረቻ ፋብሪካ መሆኑን ብቻም ነው፡፡ እዛ ሲደርሱ ግን እውነታውና የሆነው ከተነገራቸው ጋር ሊገናኝ አይደለም ለማነፃፀር እንኳን የማይችል ሆኖ ያገኙታል። ደሞዝ በቀን 13 ብር፣ መጠለያ የለም፤ ሌላውም ሌላውም የለም። የተባሉት ሁሉ የለም። በዚህም ሳር አጭደው መጠለያቸውን በመስራት እራሳቸውን “የቤት ባለቤት” አደረጉ። ቀለብም እንደዛው ከራሳቸው የሚያገኙበትን መንገድ ፈጠሩ።
በአጠቃላይ በአሁኑ ዘመን አገላለፅ ቀጣሪው ድርጅት “ሿሿ” እንደ ሰራቸው የተረዱትም ከቆዩ በኋላ ነው። ይግባቸው እንጂ ፀጥ ለጥ ብሎ ከመሥራት ውጪ አማራጭ አልነበረምና ሥራቸው ላይ በማተኮር ሕይወትን መግፋት ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ነበርም ወጣት ሻምበል ተሾመ በዚሁ ሥራ ለስምንት ዓመታት አገልግሎ ወደ አዲስ አበባ ፈትለክ ያለው። ወለጋን በዚሁ ሁኔታም ተሰናብቷታል።
አዲስ አበባ እንደ ደረሰም የከተማዋ እምብርት ወደ ሆነው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አቀና፤ እዛም ውሎ ማደር ጀመረ። ግን ነገሩ እዚህም ሕይወት አልጋ ባልጋ አልሆነችለትም። ሕይወት “ሻምበልዬ …” ብላ አልተቀበለችውም። በዚህም ያለ ሥራ ውሎ ማደር መጣ። ሆኖም አዲስ አበባ የተለያዩ አማራጮችን ይዛለት ቀርባለችና እሱ መሥራት በሚችላቸው ዘርፎች ሁሉ ገበታዋ ሙሉ ሆነለት። ችግሩ ተፎካካሪ ሆኖ፣ በልጦና አሸንፎ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ነበርና ወጣት ሻምበል ተሾመ ምድር ባቡር (የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ሥራ) ተወዳድሮ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ተቀጠረ።
ፕሮጀክቱ እየተገባደደ ሲሄድ ግን እሱና የተወሰኑ ጓደኞቹ ተቀነሱ። የዚህን ጊዜ ጉድ ፈላ። ያው ሕይወት ከላይ እንዳልነው ነውና ፈተነችው። ይሁን እንጂ አሁንም እጅ አልሰጠም። እዛው ከወለጋ እንደ መጣ እጁን ዘርግቶየተቀበለው የባቡር መስመር ዝርጋታ ሥራውን ሲሠራበት የነበረው የለመደውና የተላመደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ዙሪያ ገባውን ማማተር ጀመረ። ማማተሩም መልሱን አመላከተው፡፡
በእሳት አደጋ በኩል ወደ ራስ መኮንን ድልድይ የሚወርደው ቁልቁለት አስፋልት መንገድ ዓይኑ ገባ። ዝም ብሎ ሊያየውም አልፈለገም፡፡ ስለዚህም ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሲያቀኑ በስተቀኝ በኩል ባለው የእግረኛ መንገድ ላይ (መሀል አካባቢ) ማዳበሪያ ወጥሮ የመሥሪያ ቦታውን አመቻቸ፡፡ ይህም የሊስትሮ እቃውን ሸክፎ ቁጭ ብሎ የሚሰራበት ሲሆን፤ እዚህ ቦታ ላይ የሚያገኙት ሰው ይህ የዛሬው የአዲስ ዘመን እንግዳችን ነው። ይህንን ወግ ያወጋነው እንግዲህ እዚህች ቦታ ላይ አብረን ተቀምጠን ነውና ታሪኩን እንከታተል።
ወጣት ሻምበል ተሾመ ወለጋ በነበረበት ወቅት ብዙ መከራ አይቷል፡፡ በ”ሆድ ይፍጀው” አይነት ብልሀቱ ሊነግረን ባይፈልግም፤ ዳር ዳሩን እንደተረዳነው የሆነ ትንሽ መንገላታት ብጤ ሳያጋጥመው አልቀረም። “እስኪ ስለ ጉዳዩ ትንሽ ብትነግረን?” ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ፤ “አሁን እሱን ማንሳቱ ምንም ስለማይጠቅም፣ ምንም ስለማይሰራ ….” በሚል ቢያልፈውም፣ ካጋጠመው መሰናክልም ሆነ መደነቃቀፍ አምልጦ፤ እዚህ፣ “እሚፈልገው” ቦታ ላይ ደርሶ፣ ዛሬ ላይ ሆኖ ያንን ማውራቱ እራሱ ጥንካሬው ነውና ሊያስመሰግነው ይገባል።
ወጣት ሻምበል በአሁኑ ሰዓት በዚህች በጠቀስናት የሥራ ቦታው ላይ ሆኖ ከዋና ሥራው – ሊስትሮነት ጎን ለጎን ሌሎች ሥራዎችንም ይሠራል። ከእነዚህ መካከልም ሞባይል ካርድ፣ ካልሲ፣ የታሸጉ ውሀዎች ወዘተ መሸጡ አንዱ ነው። የትራፊክ ጽሕፈት ቤት እዚህ ጋር ማቆም ክልክል ነው ምልክትን በማቆሙ ምክንያት ሥራው ተቀዛቀዘ እንጂ ፓርኪንግ ይሠራ የነበረው ሌላው ሲሆን፤ ፈረንጆች (“ሹ ዶክተር” እንዲሉ) የተጎዱ፣ የተጎሳቆሉ፣ የታመሙ … ጫማዎችን ማከምም ሥራው ነው፡፡
“ሊስትሮነት እንዴት ነው፣ ከእለት ገቢ አኳያ ብትነግረን?” ብለነው ነበር። ወጣት ሻምበልም “ምንም አይልም። ይሁን እንጂ እንደ በፊቱ አይደለም። ድሮ በቀን እስከ 300 ብር ይገኝ ነበር። አሁን እንደዛ የለም። እኔ ከተለያዩ ሥራዎች በማገኘው ነው የሊስትሮነት ገቢዬን የምደጉመው። ዋና ሥራዬና መተዳደሪያዬ ግን ሊስትሮነት ነው” በማለት መልሶልናል። አጠቃላይ ካፒታሉን ጠይቀነው “ትንሽ ነው?” ብሎ ቢያልፈውም “አንድ ጫማ ስንት ነው የምታሳምረው?” ለሚለው ተከታይ ጥያቄያችን “15 ብር” መሆኑን ነግሮናል።
መኖሪያ ቤትን በተመለከተም ጠይቀነው ነበር። እርሱም ‹‹የምኖረውም እዚሁ ነው፤ ወደ ላይ ከግንቡ በላይ›› በማለት በጣቶቹ እየጠቆመ አሳየን፡፡ እዚያው እንደሚያድርም ነግሮናል፡፡ ለእርሱ የሠራው “ቤት” ነበር፡፡ “ቦታው ለጊዜው ባዶ ይሁን እንጂ በኋላ ለመሰረተ ልማት ግንባታ መዋሉ አይቀርም። ይህንን አስበህበታል፣ ያን ጊዜ ወደ የት ትሄዳለህ?” ላልነውም “አዎ አውቃለሁ። ያኔ ወደ ወረዳ ሄጄ አንድ ነገር ቢያደርጉልኝ እጠይቃለሁ።” በማለት መልሶልናል።
በወጣቱ ሥራና መኖሪያ ቦታ ላይ አንድ ለየት ያለ ሁኔታ ለዓይን የሚገባ ነገር አለ። አዎ፣ ወጣት ሻምበል ተሾመ የጓሮ አትክልት ያለማል። እሸት ከጓሮው አይጠፋም። ከራሱ አልፎ ለአካባቢ ሰዎች ሁሉ ይተርፋል። አጠቃላይ ሁኔታውን እንዲያስረዳን ጠየቅነው። ፈገግታን በተላበሰና በደስታ ስሜት እንዲህ ነበር ያለን፤ይህ እንደምታየው ባዶ ቦታ ነው [እንዳለ አካባቢው እስከ ውቤ በረሃ ድረስ ነዋሪዎች በልማት ምክንያት ተነስተው አብዛኛው ስፍራ ገና ግንባታ አልተካሄደበትም]። ጫካ እየሆነ ነው።
ነገር ግን አካባቢው ንፅህናው የተጠበቀ እንዲሆን በማሰብ፤ ለአንዳንድ ሕገወጥ ተግባራት ምቹ እንዳይሆን ከመፈለግ የተነሳ ነው ቦታውን ወደ ማልማቱ ሥራ የገባሁት። ደግሞም የጓሮ አትክልትም ሆነ እንደዚህ አይነት ሥራ የመከወን ልምድ አለኝ። በዚህም ሁሉንም አይነት የጓሮ አትክልቶች እተክላለሁ። ጎመን አለ፤ ሽንኩርት አለ፤ በቆሎውም ይኸው እንደምታየው ነው፤ ቃሪያም አለ። [በዛ አካባቢ ሲያልፉ፤ ወደ ጊዮርጊስ ቢቴክርስቲያን ሲያቀኑ ወደ ቀኝ ዞር ብለው ሲመለከቱ በቆሎው አዝርዕት ካዩ እሱ ሻምበል የዘራው፤ የተከለው የጓሮ አትክልት ነው]። እሸት ሁሌም እንበላለን።
እኔ ሁሌም ቢሆን የጓሮ አትክልቱ ሲደርስ ብቻዬን በልቼ አላውቅም። ሼጬም አላውቅም። ወደ ፊትም አልሸጥም። ሁሌም ለሰው ነው የምሰጠው። ለአካባቢው ሰው፣ ለሾፌሮችም፣ ለሚያልፍ ሰውም ሆነ ላገኘሁት ሁሉ እሰጣለሁ። እኔም እበላለሁ። በቃ፤ ይህ በጣም ነው የሚያስደስተኝ [በቆሎው ውስጥ እየተዟዟረና እያስጎበኘን ነው ይህንን ሁሉ ታሪክም የሚነግረን]። መኖሪያ ቤቴም ይሄ ነው [ወደ ዳር በኩል እያሳየን]።
እርግጥ ነው፤ ወጣት ሻምበል አካባቢውን በማልማቱ ለራሱና ለአካባቢው እሸት (የጓሮ አትክልት) ይቸራል፤ ነዋሪዎችንም ጠቅሟል። ራሱንም መግቧል፡፡ ከሁሉም በላይ አንዳንድ በልማት ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ተነሺ በሆኑባቸው ቦታዎች ስፍራው ጫካ ሆኖ ለፀጥታና ለጤና ችግሮች ሲጋለጡ ይታያሉ፡፡ ከዛ አኳያ ወጣት ሻምበል ከጓሮ አትክልትነቱም በላይ ለጤናና ለፀጥታ ችግሮች ተገቢውን መፍትሄ ሰጥቷል፡፡ ሌሎችም አርአያነቱን ሊከተሉ እንዲሚገባ የሚነገርለት ወጣት ሆኗል፡፡
ሌላው ወጣት ሻምበል ተሾመን የጠየቅነው የወደፊት እቅዱን ሲሆን፤ የወደፊት ሱቅ መክፈት ነው ብሎናል። ኮንቴነር ገዝቼ በማምጣት እዚሁ ቦታ በዲዛይን በማሰራት ቆንጆ ሱቅ መክፈትና ከዛ ማደግ እፈልጋለሁ። ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ እየተዘጋጀሁ ነው። ከእግዚአብሄር ጋር ይህ የማይቀር ነው። ለወረዳዎችም እያስረዳሁ፣ አስፈላጊነቱን እያብራራሁ እገኛለሁ፡፡ እየመጡም እያዩልኝ በመሆኑ ጥሩ መልስ እንደሚሰጡኝ አምናለሁ፡፡ ሁሉንም ነገር እያደረኩ ነው ብሏልም።
ቅድም እንዳልኩህ ይህ አካባቢ ለግንባታ እንደሚፈለግ አውቃለሁ። በመሆኑም ከመኖሪያ ቤት አኳያ ወረዳ (አራዳ፣ 5) አንድ የሆነች ቦታ ይፈልግልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ደሞም ጥሩ ግንኙነት ስላለን እስካሁን ምንም ስላላስቸገርኩ ያደርጉልኛል ብዬ አስባለሁ። እዚህ አካባቢ የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር ቢፈጠርም እንዳይስፋፋና የባሰ ሁኔታ እንዳይፈጠር ሠርቻለሁ።
ሁኔታውንም ለፀጥታ ኃይሎች ከማሳወቅ አኳያ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ስለሆነም በአካባቢው ላይ ምንም ችግር የለም። እዚህ አካባቢ ያለሁት እኔ ስለሆንኩ ምንም አይነት ችግር እንዲፈጠር አልፈልግም። ችግር ሲፈጠርም አሳውቃለሁ። እኔ ሁሌም፣ ምን ግዜም ሰላም እንዲሆን እፈልጋለሁ። ሰላም እንዲሆንም እሰራለሁ። በዚህ ደግሞ ከአካባቢው ጀምሮ ሁሉም ይወዱኛል፤ ምን እንርዳህም ይሉኛል። ቀበሌውም ይህንን ተንተርሶ የተሻለ ነገር ያደርግልኝ ይሆናልም የሚል ተስፋ አለው፡፡
“ለወጣቱ የምታስተላልፈው መልእክት ካለ?” ብለነውም “ወጣቱ መሥራት ነው ያለበት። ሥራ መምረጥ ምንም አያደርግም። አልባሌ ቦታ መዋል ምንም አይጠቅምም። የሚጠቅመው መሥራት ብቻ ነው፤ የተገኘውን ሥራ ከመተግበር ማንም ሊቆጠብ አይገባም፡፡ የሆነ ነገር ዘርግቶ መሸጥ እኮ ይቻላል። ጥቅም አለው።
አጉል ቦታ መዋል ግን ምንም አይነት ጥቅም የለውም። ሰው ካልሰራ ምን ያገኛል? ስለዚህም ለማግኘትና ለመለወጥ መሥራትን የውዴታ ግዴታ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደኔ አስተያየት ወጣቱ በቀጥታ ወደ ሥራ ነው መግባት ያለበት። ሁሌም ዳይ ወደ ሥራ እላቸዋለሁ” በማለት ነው ከራሱ ልምድና ገጠመኝ ጋር በማያያዝ የመለሰልን። እኛም ወጣት ሻምበል ተሾመ ታታሪነቱን፣ አርአያነቱን ሌሎች እንዲከተሉት፤ ያሰበውም እንዲሳካለት እየተመኘን በዚሁ ተሰናበትን። ሰላም !
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014