
ከዓለማችን ትልቁ ሕንጻ እስከ ደሳሳ ጎጆ ድረስ ያረፈባቸውን የግንባታ ቁሳቁስ ተሸክመው የቆሙት ምን ላይ እንደሆነ ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ “መሠረት” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ስለ መሠረት በተነሳ ቁጥር የታነጹ ሕንጻዎችን ምሳሌ ማድረግ የተለመደ ነው፤ በቀላሉ ማስረዳት ስለሚያስችል። ተጣሞ ያደገ ዛፍን ለማስተካከል ከመሞከር አዲስ ዛፍ ተክሎ ማብቀል ይቀላል ሲባልም እንሰማለን፤ ጉዳዩ የመሠረት ነውና። መሠረትን ስለመመሥረት በምናነሳበት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለመዝለቅ ከሴቶቹ እድር ቤት ጎራ እንበል።
የአካባቢው ሴቶች ዕድር አላቸው። እድራቸው ለእነርሱ ብዙ ነገራቸው ነው። በልባቸው ያለውን አውጥተው የሚጨዋወቱበት፤ ከመደበኛ የዕድር ስብሰባው ጎን ለጎን ቡና እየጠጡ የሚነጋገሩት ትምህርት ቤታቸው። የሴቶች ዕድር አባል የሆኑ አንዲት እናት ከልጃቸው ጥያቄ ቀረበላቸው። ጥያቄው የሴቶቹ ዕድር ላይ ጥናት ማድረግ ነበር። እናትም ለሚመለከታቸው የዕድሩ ዳኛ ነግረው ለልጃቸው ፍቃድ አሰጥተው፤ ልጃቸው ለጥናት ብላ አብራ ከእድርተኞች ጋር መክረም ጀመረች።
በዙር በእያንዳንዱ ቤት በሚደርሰው የዕድር ስብሰባ ላይ እርሷም እየተገኘች የሚሆነውን ትመለከታለች፤ ጥናቷንም ታደርጋለች። ሴቶቹ ወርሐዊ የእድር ክፍያቸውን ሲከፍሉ፣ አጀንዳ ይዘው ሲመክሩ፣ የሚቀመስ ነገር ቀርቦ ቤት ያፈራውን ዳቦ እየቆረሱ ቡና እየጠጡ የሚያወሩትን ወዘተ እየተመለከተች ትከትባለች። እናቷ አክብረው የሚይዙት ለአጥኚዋ ልጅ ግን የከበደ ሆኖ ይታይ ያልነበረው የሴቶች ዕድር እውነታ ልጃቸውን እየገባትም መጥቷል። “አጃኢብ” አለች አንድ ቀን፤ ዘወትር ስትገረም የምትናገረውን ቃል በማውጣት።
አጥኚዋ ያገኘቸው አንድ ወሳኝ ነጥብ የሴቶች ዕድር ስለ ባሎችና ልጆች መሆኑ ነው። ሴቶቹ ግድ ብሏቸው የሚያነሱት ቁልፍ ነጥብ የሴት ዕድርን አስበው የመሠረቱት ብዙ ሰው እንደሚያስበው እንደ ሴት ከወንድ የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ሳይሆን ለቤተሰባቸው የበለጠ አስተዋጽዖ ማድረግ እንዲችሉ ለማድረግ ነው።
አጥኚዋ ትኩረቷን የሳበውን ጉዳይ አንድ ምዕራፍ ወደፊት ወስዳው ለምን ለሴቶች ላይ ከባልም ሆነ ከልጆች የሚመጣ ተጽዕኖ ኖረ ስትል ጠየቀች። ባል ወንድ ስለሆነ ብዙ የቤት ሥራ የማይሠራበት ሴት ግን ብዙ ነገር የምትሆንበት፣ ባል ትንሽ ብር ወርውሮ “አብቃቂው” ብሎ ጭንቀቱ የእርሷ ብቻ ሆኖ እርሱ ግን በነጻነት የሚኖርበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው ስትል አሰበች።
ለሴቷ የትኛውም ማኅበራዊ መስተጋብር መዝናኛ ወይንም አየር መቀየሪያ አይደለም፤ የበለጠ ኃላፊነት መወጫ እንጂ። ተገቢ ያልሆነ ኃላፊነቱን የበለጠ ማስፊያ እንጂ። አጥኚዋ ሴት በመሆኗ ብቻ ለሴት ተቆርቆሪ የሆነች ላለመምሰል በጥናቷ ሚዛናዊ ለመሆን እየሞከረች ዘለቀች። የመዳረሻው አንድ ነጥብ ስለ መሠረት ማሰብን የሚጠይቅ ነበር። ከመሠረቱ ተስተካክሎ ማደግ ያለበት ግለሰባዊ እሳቤ ሊኖር እንደሚገባ ይህም ወደ ቤተሰብ እንደሚመጣ በሂደትም ወደ ማኅበረሰባዊ እሳቤነት እንደሚያድግ እያሰበች።
ባሎች እንዲሁም ልጆች ስለ እናቶች ብዙ ድካም በተጠየቁ ጊዜ የያዙት መረዳት ከእውነታው የራቀ መሆን መሠረት መመሥረትን አንገብጋቢ ጉዳይ አድርጋ አጥኚዋ እንድትይዘው አደረጋት። መሠረትን መመሥረት ከዚህ እስከ እዚያ ድረስ።
መሠረት ለማንኛውም ነገር
በሕይወታችን እንዲሆንልን የምንፈልገው ምን ጉዳይ አለ?አንድ፣ ሁለት ብለን ለመዘርዘር ጥቂት ደቂቃዎችን ወስደን ንባባችንን ብንቀጥል ይመከራል። የዘረዘርነውን ነገር በሙሉ ደጋግመን እናንብበው። በእርግጥም ደስ ይላል፤ ምክንያቱም እንዲሆንልን የምንፈልገው ነገር ቢሆንልን ደስ ስለሚለን። ሁሉም እንዲሆኑልን የምንፈልጋቸው ነገሮች እንዲሆኑ ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች እንዲሁ መዘርዘር እንላቸዋለን፤ መሠረት የሚሆኑትን።
ለጥሩ ሥራ ትምህርት መሠረት ነው። ለጥሩ ትምህርት ጥሩ ተማሪነትና አቅርቦት አስፈላጊ ነው። ለጥሩ ትምህርት ደግሞ እንዲህና እንዲያ እያልን መቀጠል እንችላለን። ሁሉንም ወደ ኋላ እያጠነጠንን ወደ መሠረቱ እንደርሳለን። ጉዳዩ መጨረሻ ላይ ምን ላይ እንደርሳለን ነው፤ መልሱ “ራሳችን” ላይ የሚለው ይሆናል። ለእዚያ ነው ከመሠረት አራት ማዕዘኖች መካከል ቀዳሚውን “እኔ” ያልነው።
መሆን ወደ ምንፈልገው ለመድረስ መሠረት እንደሆኑ የምንቆጥራቸው ብዙ ነገሮች ቢሆኑም ቁልፉ መሠረቶች ግን ራሳችንና ፈጣሪያችን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ግላዊ መነሳሳት፣ ቁርጠኝነት፣ ትጋት፣ በእውቀት ማመን፣ ከሰዎች ጋር ተስማምቶ መሥራት፣ ለጊዜ ቦታ መስጠት፣ ወዘተ እያልን ብንሄድ ሁሉም ወደ እኛው ያመለክታሉ። የቅርብ ሰዎች እገዛም ሆነ እርዳታም የሚጠቀስ ቢሆንም እርሱም የሚሠራው በራሳችን ነው ከፈጣሪ ጋር።
ለሰዓት ግድየለሽ ሆኖ ፈተና አምልጦት ውጤቱ የተበላሸ ተማሪ፤ በመትጊያው ሰዓት ጨዋታን መርጦ ውጤቱም የተበላሸው፤ በእርሻ ወቅት ከቤቱ የከረመ ገበሬ ዕጣ ፈንታ ግራ ቢያጋባን ምላሹ ወደ ግለሰቡ ነው። ግለሰቡ ብለን ዘልቀን ስንሄድ ወደ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ እንደርሳለን፤ አስተዳደግ!
በግለሰቦች ሕይወት ውስጥ አስተዳደግ የሚኖረው አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተጨባጭ አስተዳደግ ትርጉም በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም አለው። አስተዳደጋችን ወደ ፍሬ የሚያደርሰንም ከፍሬ የሚመልሰንም ሊሆን ይችላል። ከቤተሰብ የምንወስደው አስተዳደግ ተጽዕኖው በዛሬ ሕይወታችን ውስጥ በቀላሉ የሚታይ ሊሆን አይችልም።
ለማንኛውም ነገር መሠረት አስፈላጊ ነገር መሆኑን ተረድተን እንቀጥል። ጆን ማእክስዌል ሲናገሩ “የሰው ልጅ ስህተቱን ለማረም ዝግጁነት ያለው መሆን አለበት፤ ያተርፍበታልና”ብለዋል። ይህም ግን መሠረትን ይጠይቃል። የሰው ልጅ አይደለም ከሌሎች ነገሮች ስህተትን ወደ መልካም የመቀየር እድል ያለው ሆኖ ሊያድግ ይችላል። ትላንት ለነገር መሠረት ሆኖ በበጎነት እንዲያገለግል በአግባቡ ልንመረምረውና ልንጠቀምበት ይገባል።
ትምህርት መሠረትን ይሻል፣ ንግድ መሠረትን ይሻል፣ ትዳር መስርቶ መምራት መሠረትን ይሻል፤ ሁሉም ነገር። ጥራት ያለው መሠረትን የመመሥረቻው ከሁሉም ጊዜዎች የተሻለው ጊዜ መቼ ነው የሚለው ጥያቄ ምላሹ ዛሬ የሚል ነው። ዛሬ መሠረትን መሥራት ነገ የምትገነባበት እንዲሆን። መሠረት ለሕንጻ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ነገር ስለሆነ። በጉድለት ዝርዝር ውስጥ ሳንከርም ወደ መፍትሔ መድረስ የምንሻ ከሆነ።
የጉድለት ዝርዝር
እንደ አገር የጎደለን ነገርን እንዘርዝር ብንል መዳረሻችን ቀላል አይመስልም። የተወሰኑትን እንጥቀስ ብንል ድህነት፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ ጎጂ ባህሎች፣ የሴት ልጅ መደፈር፣ የሥራአጥ ቁጥር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ወዘተ ብለን ልንዘረዝር እንችላለን። ለእያንዳንዱ የጉድለት ዝርዝር ተገቢውን መፍትሔ የመፈለጉ ሂደት ስንገባ የመሠረት ጉዳይ አግጦ ይወጣል።
የጎደለው ሰላም ከሆነ የውስጥ ሰላም ያላቸው ሰዎች መብዛት የመፍትሔው መንገድ እንደሆነ ማህተመ ጋንዲ ይናገራሉ። “በአገራት መካከል ሊኖር የሚገባ ሰላም በግለሰቦች መካከል ባለ መሠረት ያለው ፍቅር ይመሠረታል” ይላሉ ማህተማ ጋንዲ። አገራት የግለሰቦች ስብስብ ናቸው። ግለሰቦች በውስጣቸው የሚሆን ሰላምና ፍቅር መሠረት ሆኖ ወደ ሰላም ያደርሳል። እያንዳንዱን ግለሰብ የሰላም ሰው አድርጎ የማሳደግ በድምር ውጤቱ የአገርን እንዲሁም የአገራትን ሰላም መጠበቅ ነው።
በሳሙኤል አዳምስ አገላለጽ ደግሞ “ለሕዝብ ነጻነትና ደስተኝነት ሃይማኖትና የሞራል ሰው መሆን ጥብቅ መሠረት ነው። ” አሁንም ጉዳዩ ወደ ግለሰቡ የሚያሳይ ነው። ግለሰቡ ባለው የሃይማኖትና የሞራል አቅም ሰፊ የሆነው ሕዝብ ላይ ነጻነትንና ደስተኝነትን የሚያመጣ የሚሆንበት።
የጉድለት ዝርዝርን መናገር ለሁላችንም የቀለለ ይመስላል። የመፍትሔ መንገዱን ግን መፈለግ አለብን፤ እርሱም መሠረትን መመሥረት ነው። መሠረቱ ጠንካራ በሆነ ቁጥር የሚታነጽበት ከፍታው ይጨምራል። ከሕንጻው ውጫዊ ውበት በላይ ሸክምን በመሸከሙ የምንደነቅበት መሠረቱ ላይ ነው።
የምርመራ ጋዜጠኞች የጎደለውን ፈልፍለው አውጥተው ለሕዝብ በማቅረብ የጎደለውን በስፋት ያጋልጣሉ። በአገራችን መሰል ጅምሮች ብዙ ፈተና እየገጠማቸው የመጡ ቢሆንም እንደ ማኅበረሰብ ያለንበትን ደረጃ የሚያሳዩን ነበሩ። በውስን ተቋማት ላይ ከእዚህ ቀደም በኢቲቪ ታይተው በነበሩ “ዓይናችን” በተሰኘ ፕሮግራም ላይ እንዲህም አለ እንዴ እስክንል ድረስ የደረስንበት ሁኔታ ነበር።
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች አለቆቻችንን ከሕግ በላይ አድርገው በማየት ትላልቅ ወንጀሎች በዝምታ ውስጥ ሲፈጸሙ ይውላሉ። መውጫው መንገድ መሠረት ያለው ሰውን መፍጠር ላይ መሆኑን ግድ የሚል ተጨባጭ ሁኔታችን። መሠረተ ጠንካራ የሆነ ግለሰብ መብቱን ያውቃል፣ ኃላፊነቱን ይረዳል፣ የግለሰብና የሕዝብ የሚባሉ ጉዳዮችን ይለያል፣ ለመፍትሔ እየኖረ እንደሆነ ራሱን ቆጥሮ ይሰማራል።
የጉድለት ዝርዝር ከግለሰብ እስከ አገር እንደ ዕድል ቆጥሮ ወደ መፍትሔ ለመሄድ ዛሬ ስለ መሠረት ልናስብ ይገባናል። መሠረት የእያንዳንዱ ግለሰብ ውስጣዊ አቅም ነው። ከልጅነት እስከ አዋቂነት በየፌርማታው የሚገነባ የሕይወት መልህቅ። በአግባቡ ለመመስረት አራቱንም ማዕዘናት ትኩረት ማድረግ የሚገባ።
የመሠረት አራት ማዕዘናት
በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው የእድገትን ጉዞ ለማድረግ መሠረት ያለውን ወሳኝነት በሚገባ ግምት ውስጥ ያስገባ ሰው መሠረቱን ከአራት ማዕዘናት አንጻር ለማጠንከር መሥራት አለበት።
እኔ – ቀዳሚው መሠረት ነኝ። እያንዳንዱ ሰው ለራሱ እኔ ብሎ የሚጠራው ራሱን ነው። ራሳችን ለራሳችን ቀዳሚው የመሠረት ማዕዘን መሆናችንን መረዳት አለብን። ለራሳችን ቦታ ሰጥተን በሕይወታችን ማሳካት የምንፈልገውን ማሳካት እንደምንችል ማመን አለብን። ማሳካት የምንፈልገውን ማሳካት እንደምንችል ስናምን በምን ላይ ማተኮር እንዳለብን፣ በምንስ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን፣ እንዴት ባለ አካሄድ ወደ ውጤት ለመድረስ መሥራት እንዳለብን ወዘተ እናስባለን።
ራስን ተራ ሰው አድርጎ ቆጥሮ የሚኖር አተያይ የመሠረት ወሳኙ ማዕዘን የሆነው በአግባቡ እንዳይመሠረት ያደርጋል። ለራስ ተገቢውን ቦታ መስጠት፣ ራስን ማወቅ፣ ራስን ማሳደግ ወዘተ ጤናማ መሠረት መሥርቶ ወደ ውጤት መድረስ ከሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ነው። ቀዳሚው መሠረት እኔ ብሎ መነሳትን ከራስ ወዳድነት ጋር በፍጹም ማገናኘት አይገባም። ራስ ወዳድነት በሌሎች ዋጋ መክፈል የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ መሄድ ስለሆነ። ራስ ወዳድነት በሕይወታችን ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም። በፍጹም! ምክንያቱም እኛ ሕይወት እንዳለን ሌሎችም እንደ እኛው ሕይወት አላቸውና። እድገታችን ከራሳችን በሚመነጭ ጥረት እንጂ የሌሎችን በመቀማት ወይንም በማደናቀፍ ሊሆን አይገባውም።
እርሱ/እርሷ – ሁለተኛው ማዕዘን ነው። ከሰዎች ተነጥሎ ልንኖር የምንችለው ሕይወት የለም። መሠረት በመመሥረት ረገድ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ተጽዕኗቸው ብዙ ነው። እያንዳንዱ ንግግርና ቆይታ የአስተሳሰብ መጋራትን ፈጥሮ አንዱ ሰው ሌላው ሰው ላይ ተጽዕኖን እያሳደረ ይሄዳል። እርስበርሳችን በተለይም በተመሳሳይ ዕድሜ ክልል ላይ የምንገኝ የምንፈጥረው ተጽዕኖ አዎንታዊነቱ የበዛ ነው። ወጣቶች ወደ አጉል ሱስ የሚሄዱበት አንዱ ምክንያት የቅርብ ጓደኞች አጉል ተጽዕኖ እንደሆነ ይቀርባል። በተቃራኒው በመልካም ለሚሆን እድገትም እንዲሁ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ውሎዬ ወደ መዳረሻዬ ለማድረገው ጉዞ የሚያግዝ ወይንስ ከጉዞ የሚያሰናክል ብለን ውሎችንን መወሰን ብንችል መልካም ነው።
በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ጥቅምም ሆነ ጉዳት መሆን ስለሚችሉ ጥቅማቸው እየጎላ ጉዳታቸው እያነሰ እንድሄድ ማድረግ አለብን። መሠረት በተቃራኒ ሃሳቦች መካከል እንደሚገነባ ማሰብም እንዲሁ አለብን። ከሰዎች ጋር አብረን ሥንሰራ ሁሉም ነገር ለእኛ እንደሚስማማን ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የተለዩ ሃሳቦች ተፋጭተው የሚበጅ ሃሳብ ይወጣዋል። መሠረትን መመሥረት ሲታሰብ የሌሎች ሰዎች የተለየ ሃሳብም ተጽዕኖ ይኖረዋል። ሁሉም እኛን ሊመስል ስለማይችል። እውነታው ግን እርሱ/እርሷ ከአራቱ የመሠረት ማዕዘናት መካከል መሆናቸውን ተረድቶ በአግባቡ መያዝ መቻል ነው።
እርሳቸው – ሦስተኛው ማዕዘን ናቸው። በሦስተኛው ምድብ የምንመድባቸው በአብዛኛው በርቀት የምናያቸው በእድሜ የገፉ፣ በልምድ የዳበሩ፣ በሥራቸው አንቱታን ያተረፉ በአጭሩ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሰዎች ናቸው። የእኒህ ሰዎች አስተሳሰብ መሠረትን ከመመሥረት አንጻር የሚኖረው አስተዋጽዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሁሉም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከእኛ የሕይወት ጉዞ አንጻር የሚጠቅሙ ላይሆኑ ይችላሉ። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከጉዟችን አንጻር የሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አንቱታን ያተረፉ ሰዎች ከሰፈራችን እስከ ዓለም አደባባይ አሉ። ጉዳዩ እንዴት እንጠቀምባቸው ነው። በአገራችንም ታሪክ ውስጥ ጀግኖችን መሳል ያለብን ለትውልድ አዎንታዊ መሠረትን ከመስጠት አንጻር መሆን አለበት።
ፈጣሪ – አራተኛው ማዕዘን ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ፈጣሪ ብዙ ነጋሪ የማያሻን በሕይወታችን ውስጥ የበላይ መሆኑን እንደ እምነታችን የምንናገር መሆናችን ግልጽ ነው። እምነት ያላቸው ሰዎች ለእምነት ግድየለሽ ከሆኑ ሰዎች ሕይወትን በደስታ የመምራት ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ በተደረጉ ጥናቶች ማረጋገጥ ተችሏል። ፈጣሪ በሕይወታችን ውስጥ የሚኖረው ድርሻ በመሠረት ምሥረታው ላይ ሰፊ ዕድል አለው። ለፈጣሪ ቃል ልቡን የሰጠ ሰው ባልንጀራውን እንደ ራሱ ይወዳል። ለፈጣሪ ቃል የሚያድር ሰው ለሌሎች ሰላምን መፍጠርን የሕይወቱ አካል አድርጎ ይወስዳል።
በቅርቡ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ከወርቁ ወልደማርያም ‹‹የከፋ ተረት›› ጽሁፍ “ምክር በምሳሌ”በሚል አምድ ስር የቀረበን ታሪክ እናንሳ። የቀረበው ታሪክ ቆንጆ ወፍ በመዳፉ ይዞ ጨምቆ ሊገድላት የሚያስብ ግለሰብና ወፏ መካከል የተደረገ ውይይትን ነው። ወፏ ከመሞቷ በፊት የምትናገረውን እንዲሰማት ትፈልጋለች። ግለሰቡም እድል ሲሰጣት “ሶስት ጠቃሚ ነገሮች እነግርሃለሁና አትግደለኝ”አለችው። የመጀመሪያው ምክር “በእጅህ ያለውን አትልቀቅ ነው” አለችው። በመቀጠል ደግሞ ሁለተኛውን ነገረችው። ሁለተኛው ምክር “ስለሆነው ነገር ሁሉ አትቆጭ” የሚል ነበር።
ከእዚህ በኋላ ወፏ ዝም አለች። ሰውዬውም ሦስተኛውን ምክር መናገሯን እንድትቀጥል ሲጠይቃት። የወፏ ምላሽ “ሦስተኛው ምክር ለልጆችህና ልጅ ልጆችህ በጣም ወሳኝ ስለሆነ ካልለቀከኝ አልነግርህም” አለችው። ሰውዬውም ለመስማት ስለ ጓጓ ለቀቃት። በዚህ ጊዜ በርራ አንድ ዛፍ ላይ ወጣች። ዛፍ ላይ ሆና የተናገረችው አስቀድማ የተናገረችውን ምክር አለመስማቱንና በመሆኑም በሆዷ ውስጥ ያለውን ለልጅ ልጆቹ የሚሆነውን ወርቅ እንዳጣ የሚናገር ነበር። ምክሩን ባለመቀበሉ በድህነት እንደሚኖር አረዳችው።
የወፏን ምክር ባለመቀበሉ ኪሳራን ከሰረ። በሕይወት ውስጥ በቅርባችን ያሉ ሰዎች ምክር ለሚኖረን መሠረት ወሳኝነት አለው፤ አንቱ የምንላቸው ሰዎች ምክር እንዲሁም ሃሳቦች ተጽዕኖቸው ከፍተኛ ነው፤ የፈጣሪ ደግሞ ከሁሉም በላይ። መሠረትን መመሥረትን ባህላችን እናድርግ። በልጆች ላይ እንሥራ። በራሳችን ላይ እንሥራ። በዙሪያችን ላይ እንሥራ። በተሰማራንበት ዘርፍ ሁሉ የፍሬ ሰዎች እንሁን። መሠረትን እንመሥርት። መሠረትን!!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014