የሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ሚኪያስ ለገሰ ይባላል። ምንም እንኳን ማህበሩ በ2008 ዓ.ም ሽንቁሩ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የተመሰረተ ቢሆንም ሚኪያስ ግን ከዛም በፊት በዚህ ችግር ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ይታደግ ነበር:: ሚኪያስ ወደዚህ ሥራ እንዲገባ ያነሳሳው የአባቱ ታሪክ ነው። አባቱ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት በሹፌርነት ይሠሩ ነበር።
እናም አንድ ቀን ከረዳታቸው ጋር በመሆን ቁርሳቸውን ይበሉና እጃቸውን ታጥበው ሻይ ለመጠጣት ሲሉ በዚያው ቅጽበት ራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ። ወደቀደመ ጤንነታቸው ሳይመለሱም በሱስ የመጠመድ ሁኔታም በዚሁ ችግር ምክንያት ይጀምራል:: እንደ ማንኛውም የእዕምሮ ህመምተኛ በቆሻሻ ቦታ ላይ የመቆየታቸውም መንስኤ ይህ ነበር::
የሚኪያስ አያቶችም በድንገት የተሰወሩ ልጃቸውን በብዙ ፍለጋ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ካገኟቸው በኋላ ለሕክምና ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ከዚያ ወደ ጸበልም ወሰዷቸው:: እድል ቀናቸውናም ከብዙ ድካም በኋላ በጸበል ተፈውሰው ወደቀደመ ጤናቸው ተመለሱም:: ይህም ሆኖ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ድንገት በተከሰተ የኤሌክትሪክ አደጋ ሕይወታቸው አልፏል። ይህ ነገር ሲፈጠር ደግሞ ሚኪያስ የሦስት ዓመት ልጅ ሲሆን፤ እያደገ ሲመጣ ግን አያቶቹ የሆነውን ነገር በሙሉ ነግረውታልና በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማንሳትን ያስብ ጀመር::
አያቶቹ የልኳንዳ ነጋዴና የተሻለ ሀብት የነበራቸው ናቸው:: በዚህም ሲያሳድጉት ምንም ሳይጎልበት ነው:: በዚያው ልክ ደግሞ ጠንካራ ሥነ ምግባር እንዲኖረውም አድርገዋል:: በሌላ በኩል አባቱም በሰፈር በወዳጅ ጥሩ ተግባቢና ተወዳጅ ስለነበሩ የአካባቢውም ነዋሪ ለሚኪያስ ያሳየው የነበረው ፍቅርና አክብሮት ለሚኪያስ በውል ለማያውቃቸው አባቱ የተለየ እይታ እንዲፈጠርበት አግዞታል። በሥራው መስክ የአባቱን ፈለግ ተከታይ በመሆኑም በሹፍርና ሙያ በተለያዩ ቦታዎች ሠርቷል:: ይህ ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች ሲንቀሳቀስና በአዲስ አበባም ሲዘዋወር የሚያያቸውን የእዕምሮ ህሙማን እንዲያይና እንዴት ሊያግዛቸው እንደሚችል እንዲያስብበት አድርጎታል::
አንድ ቀን የልቤን መሻት ልፈጽም በሚል እሳቤ የተነሳው ሚኪያስ፤ ተወልዶ ባደገበት ቀጨኔ መድኃኒዓለም አካባቢ የነበረን አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ ጸጉሩን እየቆረጠ፣ ገላውንና ልብሱን እያጠበ ወደህክምና እየወሰደ መንከባከቡን ጀመረ። ህመምተኛውን አማኑኤል ወስዶ ሲያሳክመው በልቡ ያስብ የነበረው ወዲያው ነገሮች እንደሚጠናቀቁ ነበር። ለካስ የተሰጠውን መድኃኒት ተከታትሎ ማዋጥ፣ መድኃኒቱን የሚቃረኑ አልኮልና ሲጋራ የመሳሰሉትን እንዳይወስድ ማድረግም ይጠበቅበታል። በመሆኑም የግድ ልጁን ወደጤናው ለመመለስ ቤት ተከራይቶ ማስቀመጥ እንዳለበት ይወስናል። ውሳኔውንም ሽንቁሩ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በአምስት መቶ ብር ቤት በመከራየትና አጥማቂ በመቅጠር ጸበልም እንዲከታተል በማድረግ ተገበረው::
በዚህ አይነት በጀመረው ሥራ የልጁ ጤና እየተስተካከል መምጣቱን ሲመለከት ሌላ አንድ ታማሚ ጨመረ:: በራሱ መኪና ወደአማኑኤል እያመላለሰም የቀደመ ተግባሩን አጠነከረ:: ቤተሰቦቹ ውጭ ሊወስዱት አልያም በንግዱ ተሰማርቶ አንቱ የተባለ ነጋዴ እንዲሆን ይፈልጉ ስለነበር በጀመረው ነገር ደስተኛ አልነበሩም። ከጊዜ በኋላም ቢሆን ሰለሞን ለገሰ የሚባለው አጎቱ ብቻ ነበር በተወሰነ ደረጃ ሀሳቡን ተቀብሎ ከጎኑ የቆመው። የሠራው ተግባር ፍሬ እያመጣ ሲሄድና በአካባቢው ያሉ ሰዎችም በያገኙት አጋጣሚ ምስጋናቸውን ሲቸሩት ግን አያቱ፤ መንታ እህቱና በካናዳ የሚኖሩት ስምንት ቤተሰቦቹ ሁሉም ሥራውን መደገፍና አብረውት ህሙማኑን መንከባከብ ጀመሩ::
ሚኪያስ በዚህ ሁኔታ በተነቃቃ ሞራል ችግሩን የራሱ አድርጎ ስለያዘው በየመንገዱ የሚያያቸው የአዕምሮ ህሙማን በሙሉ መነሳት እንዳለባቸው ቢያስብም በእርሱ አቅም ብቻ የማይደፈር መሆኑን ይገነዘባል። በመሆኑም የሚያውቃቸውን ጓደኞቹንና በቤተክርስቲያን ማህበር ስር የተሰባሰቡ ወጣቶችን አብረውት እንዲሠሩ ያማክራቸዋል። አብዛኛዎቹ ነገሩ የሚዘልቅ ስላልመሰላቸው መልካም ምላሽ አልሰጡትም:: በዚህም ጥቂት በሀሳቡ ከተስማሙት ጋር ሥራውን ቀጠለ። በወቅቱ የገንዘብ እጥረት ስለነበረባቸው እንደ ገቢ ምንጭ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ጫማ ይጠርጉ፣ መኪና ያጥቡም ነበር።
በዚህ ሁኔታ ቆይተው ህክምና የሚደረግላቸው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣም እዛው አካባቢ በአራት ሺህ ብር አንድ ሙሉ ግቢ በመከራየት በርካቶችን መታደጉን አጧጧፉት:: በዚህ ሁኔታ አራት ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ለህክምናውም በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ለሚያደርጉና ለሌላውም ወደ ከተማ መጠጋት እንዳለባቸው ይወስናሉ። እናም እንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በመምጣት ከቤተክርስቲያኒቷ ቦታ በመከራየት ተግባራቸውን ይቀጥላሉ።
በማዕከሉ ያሉት ታካሚዎች ያለባቸው ችግር የአዕምሮ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እንደ ኤች አይ ቪ፣ ኤድስ ስኳርና ሌሎች በሽታዎችም ናቸው። በተለይ ሴቶቹ ካላቀዱትና ካልፈለጉት እርግዝና ጀምሮ ብዙ ተደራራቢ ችግሮች ነበሩባቸው። በዚህም ረገድ ሚኪያስ በአንድ ወቅት የገጠመውን ነገር እንዲህ ያስታወሰዋል። በማቆያው ከጎዳና ስትነሳ የስድስት ወር አካባቢ ነብሰጡር የሆነች አንድ ወጣት ነበረች። በማእከሉ ከገባች በኋላ በጴጥሮስ ሆስፒታል ህክምናዋን ትከታተልላለች። እናም አንድ ቀን እንደተለመደው ምርመራ ስታደርግ ‹ገና ስለሆንሽ ከአስር ቀን በኋላ ተመልሰሽ ነይ› የሚል ምላሽ ይሰጧታል:: በዚህም ሚኪያስ ከአስር ቀን በኋላ ይዟት እንደሚሄድ ቀጠሮ ይይዝላታል:: ነገር ግን በነጋታው ደመ ነፍሱ ነግሮት ወደእርሷ ይሄዳል። የጠበቀውንም አልነበረም ያገኘው::
ልጅቱ ነብሰጡር በመሆኗ ምንም አይነት መድኃኒት ስለማትወስድ በጣም አስቸጋሪ ነች:: ያን ቀን እሱ በግቢው ሲደርስም ቤት ዘግታ እየጮኸች ነው። እንደ ምንም የተዘጋውን በር ከፍቶ ሲገባ ልጅቱ መሬት ላይ ወድቃ ውሃ ሽንት ፈሷት ምጥ እንደጀመራት ያያል። ከዚህ ቀደም የዚህ አይነት ነገር የገጠመው ባይሆንም ሊያስተካክላት ሲሞክር መውለድ መጀመሯን ይገነዘባል።
የአካባቢው መንገድ ምቹ ባለመሆኑና በቅርበት መኪናም ስላልነበር አብረውት ያሉትን ከሰፈረተኛው እናቶች እንዲጠሩለት በመጠየቅ እሱ የሚችለውን ወደ ማድረጉ ይገባል:: ልጅቱ ጩኸቷን ባይቆምም እንዲህ አድርግ እያለችው የሚፈለጉት አዋላጆች ከመድረሳቸው በፊት በፈጣሪ ፈቃድ ለመገላገል ትበቃለች። ከዚህ በኋላ የነበረውን ግን አንዲት እናት በመድረሳቸው በእሳቸው ምሪት ሁሉንም ነገር ለመጨረስ ቻሉ።
ዛሬ ሁለቱም እናትና ልጅ በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ይህ ለሚኪያስ ከትዝታዎቹ መካከል ቢያስቀድመውም ሳይታሰብ ከመደብደብ ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል። በአንድ ወቅት ሆስፒታል ለማሳከም የወሰደው ልጅ ስም ሲጠራ ሚኪያስ አቤት በማለቱ ‹‹እንዴት የእኔ ስም ሲጠራ አንተ አቤት ትላለህ›› በሚል ራሱን እስኪስት ኩላሊቱ ላይ የተመታበትም ጊዜ ነበር።
የሰሊሆም አገልግሎት በኢትዮጵያውያን ብቻ የተወሰነም አልነበረም። ከዓመት በፊት አንዲት እነሱ በኋላ ሚያ እያሉ የሚጠሯት የውጭ ዜጋ አሜሪካ ኤምባሲ አካባቢ መንገድ ላይ ወድቃ ትገኛለች። በአካባቢው ያሉት የፖሊስ አካላትም ሁኔታዋን ካዩ በኋላ ለእነ ሚኪያስ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲያነሷት ትብብር ይጠይቋቸዋል። ሴትዮዋ ሙሉ ለሙሉ ራሷን የሳተችና ሰውነቷም በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳ ነው::
ያበጠና ልዩ መልክ የያዘም ነበር። በዛ ላይም ሯሷን ችላ ምንም ማድረግ የማትችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰች የምትጸዳዳው እላዩዋ ላይ ነበር። በማዕከሉ ከገባች በኋላ ግን በተደረገላት ሁለንተናዊ እንክብካቤ ራሷን እያወቀች መጣች:: ይሁን እንጂ ከማዕከሉ ወጥታ መኖር የሚያስችላት ሁኔታ ላይ አልነበረችም። በመሆኑም ማዕከሉ ለሌሎች እንደሚያደርገው ሁሉ ቤተሰቦቿን ለማግኘት የማፈላለጉን ሥራ በተጓዳኝ ይሠራ ነበር።
በኅዳር ወር 2014 መጨረሻ ግን አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። እሷን ሲፈልጉ የነበሩ ሰዎች እሷም ካለች ለማየት፤ ካልሆነም እንደዚህ አይነቱን በጎ አድራጎት ድርጅት ለመጎብኘት ብለው ወደ ሰሊሆም ሲመጡ ያገኟታል። ለካስ ሴትዮዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ትሠራ የነበረች ናት። በፍጥነትም ከመጡት ሰዎች ጋር በመሆን ውጭ ካለችው እናቷ ጋር በእስካይ ፒ እንድትገናኝ ያድርጓታል። ከዚህ በኋላ ያለችበትን የሰሙ የሥራ ባልደረቦቿ ልጅዋን ጨምሮ በመምጣት የማዕከሉን ግቢ ያጣብቡታል።
በሰሊሆም በተመሳሳይ ሌላም የኬንያ ዜግነት ያለው የዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና የራሱ ትምህርት ቤት የነበረው አንድ ሰውም እስካሁን በማዕከሉ ይገኛል። ሰውየው ማዕከሉን ከተቀላቀለ ሰባት ወር ሆኖታል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌስ ቡክ የተለቀቀውን ፎቶውን እያዩ ለመጠየቅ የሚመጡ በርካታ ሰዎች አሉ። እናም ሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር በማእከሉ ያሉትን ከማሳከም ባለፈ እንደ ዋና ተግባሩ ያደረገው ቤተሰብ በማፈላለግ ፈቃደኛ ከሆኑ የማቀላቀልን ሥራ ነው። በዚህም ከቤተሰባቸው ጋር ብዙዎችን አገናኝቷል:: እንዲገናኙ ከተደረጉት መካከል ሚኪያስ ሁሌም ከአዕምሮው የማይጠፋውን አጋጣሚ እንደሚከተለው ያስታውሳል።
በአንድ ወቅት አንዲት ልጅ ጎዳና ላይ ወድቃ ትገኝና ማዕከሉን እንድትቀላቀል ይደረጋል። በወቅቱ ልጅቷ አትናገርም ራሷን ችላ መጸዳዳትም ሆነ ምንም ማድረግ አትችልም። በዚህ ሁኔታም ነው ማዕከሉን ተቀላቅላ አንድ ዓመት ከስድስት ወር የቆየችው:: በኋላ ግን በአንዲት የተባረከች ቀን ሳይታሰብ በአካባቢዋ ሲያልፍ ልጅቷ ሚኪ ብላ ትጠሯዋለች። ሚኪያስም የተፈጠረውን ነገር ማመን እየተሳነው ቀረብ ይልና ያናግራታል:: እሷም ቀስ እያለች ታዋራዋለች:: ለካስ ልጅቷ ጎበዝ ተማሪ የነበረችና አስከ አስረኛ ክፍል የተማረች ስትሆን በአንዲት ያልታሰበች ቀን ወደ አረብ አገር ለመሄድ ከጓደኛዋ ጋር ከወሎ ክፍለ አገር ወደ አዲስ አበባ መጥታ ችግር የደረሰባት ሴት ነበረች።
አዲስ አበባ ስትገባ ያመጣት ደላላ ነበር:: እሷንም ጓደኛዋንም ትቷቸው ተሰውሯል። የነበራትን ብቸኛ አጋጣሚ በመጠቀም ከአንድም ሁለት ቤት በመግባት ተቀጥሮ መሥራት ብትሞክርም አልሳካ ይላትና ሯሷን ስታና ታማ ለጎዳና ሕይወት ተዳርጋለች። በዚህ ሁኔታ ማዕከሉን ከተቀላቀለችና ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ከሞላት በኋላ ቀስ እያለች ወደራሷ መመለስ ጀመረች:: ብዙ ነገሮችን እያስታወሰች መጣችም:: እናም የቤተሰቧንም አድራሻ ለሚኪያስ የነገረችው የዚህን ጊዜ ነው::
ሚኪያስም ጊዜ ሳይሰጥ በተሰጠው አድራሻ ሲደውል አንዲት እናት ስልኩን ያነሱታል። ሰላምታ ከተለዋወጡም በኋላ ‹‹ሰአዳ የምትባ ልጅ ያውቃሉ›› ሲል ይጠይቃቸዋል።ሴትየዋም ‹‹ሰአዳ ልጄ ነበረች። ነገር ግን ከዓመታት በፊት ሕይወቷ አልፏል፤ እኛም እርማችንን አውጥተናል›› የሚል ምላሽ ይሰጡታል። በተፈጠረው ነገር ራሱም ይደናገጥና አጠገባቸው ሌላ ሰው ካለ እንዲያገናኙት ይጠይቃቸዋል።
እሳቸውም ወንድሜ አለ ብለው ያገናኙታል። የቀረበውም ሰው በተመሳሳይ የእሷን መሞት መረዳታቸውንና እርማቸውን ማውጣታቸውን ይነግረዋል። በዚህ ንግግር መካከል ለሰውየው ሚኪያስ ሰአዳ በሕይወት መኖሯን ሲነገው እናትየው ስለሰሙ ራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ። እንደምንም አረጋግተው በስልክ አገናኝተዋቸው በነጋታው መጥተው ልጃቸውን ይዘው ይሄዳሉ:: ከዚያ በኋላም የሰአዳ ቤተሰቦች ዛሬም ድረስ እየደወሉ ሚኪያስንም ማዕከሉንም ይጠይቃሉ፤ ቤተኛም ሆነዋል::
ዛሬ ላይ ሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር ፈቃድ በማውጣትና ሕጋዊ ሰውነት በማግኘት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ሁሉም የማዕከሉ ተደጋፊዎች ህክምና እንዲከታተሉ ይደረጋል:: የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ቢኖርበትም ታካሚዎቹ ከጤና ሚኒስቴር፤ ከአማኑኤልና ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ጋር በትብብር የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙት ህዳሴና ጥበብ በቀጨኔ ጤና ጣቢያዎች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማዕከሉ ድረስ በመምጣት ሁሌም የህክምና አገልግሎት በመስጠት ትብብር ያደርጉላቸዋል። በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ከአንድ መቶ ሀያ በላይ የአዕምሮ ህሙማንን በመያዝ እየተንከባከበ ይገኛል።
ሚኪያስና ጓደኞቹ ግን ዛሬም በርካቶችንም ለማንሳት የልብ እቅድ አላቸው። ይህም ሆኖ የታካሚዎችን ቁጥር ለመጨመርና በተሻለ ማቆያ ለማኖር ሕንጻ ለመገንባት የቦታ አለማግኘት ችግር ገጥሟቸዋል። በተጨማሪ እስካሁኑ ማዕከሉ የቅርብ ሰዎች በጊዚያዊነት ከሚያደርጉት ትብብር ውጭ አንድም ተሽከርካሪ የሌለው በመሆኑ ህሙማኑን ወደህክምና ጣቢያ ለማድረስ ትልቅ ፈተና ውስጥ ናቸው። እነሚኪያስ እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ ያላንኳኩት በር፣ ያልሞከሩት ነገር ባይኖርም እስካሁን አልተሳካላቸውም።ሠእናም ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ የጋራ ችግርን በጋራ ለመፍታት ሊተባበር የሚፈቅድ ቢያየን ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2014