ቀደምት አባቶቻችን አገራችን ኢትዮጵያን በአውሮፓውያን ወራሪዎችና በቅኝገዥዎች ስር እንዳትወድቅ ለማድረግ ሰፊ መስዋዕትነት በመክፈል ነፃነቷን አስጠብቀው ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ አስረክበው አልፈዋል።
አውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች በተለያየ ጊዜያት በአገራችን ላይ በተደጋጋሚ ወረራ ቢፈጽምም በየጊዜው አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን በከፈሉት ቆራጥ መስዋዕትነት እስካሁን ነፃነቷ ተከብሮ ቆይታለች። በተለይም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነው የአድዋ ድልን ተከትሎ ሁልጊዜም ኢትዮጵያን በምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ እንድትገባ በማድረግ በግልጽም ሆነ በስውር በፖለቲካም ሆነ በምጣኔ ሀብት ጫና ስር እንድትወድቅ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ቀደምት አገር ብትሆንም፣ ህዝቦቿ በከፍተኛ ድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ ሆነው ዘመናትን አሳልፈዋል። ለዚህም ቅጥረኛ ባንዳዎች ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳሉ። በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ ሁሌም ሀገሪቱ ወደልማትየምታደርገውን ጉዞ ሲያሰናክሉ ቆይተዋል።
በሌላ በኩል የሕዝብ አንድነትን የሚያጠናክር፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድምና ኢትዮጵያ ወደ ልማት እንድትገባ የሚያደርግ መንግሥት አለ ብለው ባሰቡ ጊዜ ቅጥረኛ ባንዳዎችን በማሰማራት በአገራችን ውስጥ ሠላም እንዳይኖርና ወደጦርነት እንድንገባ በማድረግ አምራች ኃይሉን በማጥፋትና ምጣኔ ሀብትዋንም በማድቀቅ ሁሉም ነገር እንደገና ከዜሮ እንዲጀመር በማድረግ ሁሌም አገራችን በዕድገት ኋላ እንድትቀር ሲያደርጉ ኖረዋል።
እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ስር ያልተገዛችና በዓለም መድረክ የቀደመ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የነበራት አገርነች። በዚህ መሠረት ሊግ ኦፍኔሽንን፣ የተባበሩት መንግስታትንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በግንባር ቀደምትነት ከማቋቋሟ በተጨማሪ በየጊዜው በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጓ ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት የሚጠቀስላት ነው።
የሊግ ኦፍ ኔሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች መሥራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትንም እንዲቋቋም ቀዳሚ ሚና ከመጫወቷም በአሻገር በተለያየ ኃላፊነት ደረጃ ድርጅቱን ለረጅም ጊዜ የመራች ሃገርም ነች።
በዚህም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካኝነት ብዙ የአፍሪካ አገራትን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ በማድረግ ለአፍሪካውያን ነጻነት የማይተካ ሚና ተጫውታለች። በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካና በአካባቢው የሚገኙ አገራት ውስጥ የነበረውን የዘር መድሎ ሥርዓት አፓርታይድን ለማስወገድ አገራችን ኢትዮጵያ የመሪነት ኃላፊነቷን በሚገባ ተወጥታለች።
በተለያየ ጊዜ በአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሰላም አስከባሪ ጦሯን በመላክ በአገራቱ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጋለች። በተቃራኒው ምዕራባዊያን አገራትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በአገራችን ላይ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ጫና ማድረጋቸው የተለመደ ነው።
ለአብነት “አንድ የሊግ ኦፍኔሽን አባል አገር በሌላ የሊግ ኦፍኔሽን አባል አገር ላይ ወረራ መፈጸም አይችልም” የሚለውን መመሪያ በመቃረን አገራችን ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ በግፍ በተወረረች ጊዜ አቤቱታዋን ለሊግ ኦፍ ኔሽን ብታቀርብም ሰሚ አላገኘችም። በተጨማሪ ከስምንት አሥርት ዓመታት በፊት በወቅቱ የአገራችን መሪ የነበሩት ንጉሥ አፄ ኃይለስላሴን ጀኔብ ስዊዘርላንድ በአካል ተገኝተው ፋሽስት ጣሊያን በአገራችን ላይ ያደረሳቸውን በደል በተመለከተ የሚያቀርቡት ንግግር በመቃወም በጭብጨባ እንደቋረጥ በማድረግ በአገራችን ላይ ያላቸውን ንቀትና ኢፍትሐዊነት በግልፅ አሳይተዋል።
ሌላው ቀርቶ በመርህ ደረጃ ፋሽስት ጣሊያን በኢትዮጵያ አገራችን ላይ ያደረገችውን ወረራ ለማውገዝ እንኳ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ባለፉት ስድሳ ዓመታት በአገራችን ውስጥ የተደረጉት ግጭቶችና ጦርነቶች መነሻቸውን ብንመለከት በዋናነት በእነዚሁ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አጋፋሪነት ሲደረግ የነበረ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው።
በዚህም በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ወጣቶች እንዲሞቱና እንዲሰደዱ በማድረግ አንድ ትውልድ እንደ ትውልድ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲታጣና አገራችንን እንደ አገር አንገቷን እንድትደፋ ለማድረግ ተሞክሯል።
ይህም አልበቃ ብሏቸው ትናንት አባቶቻቸው ለጠላት አድረው አገራቸውን ሲበድሉ የነበሩ የትግራይ የባንዳ ልጆችን ትሕነግ በሚል ድርጅት ስም በማሰባሰብ ቁስና በገንዘብ በመደገፍና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል አገራችን በጦርነት ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል። በመጨረሻም የመንግሥት ስልጣን እንዲይዙ በማድረግ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በዘር ፖለቲካን በመከፋፈል የሕዝቡን አንድነት እንዲላላ በማድረግ የአገራችንን የመልማት ጥረት ለማዳከምና በአንፃሩም የአንድን አካባቢ ማህበረሰብ ብቻ እንዲለማ ሌላው አካባቢ ደግሞ በጭሰኝነት እንዲኖር በማድረግ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ውስጥ በባርነት እንዲገዙ ለማድረግ በተለይም የአማራ ማህበረሰብን በጠላትነት በመፈረጅ በብሔረሰቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ዜጎች በእስር በግድያና በስደት በማሰቃየት ከዚህ የተረፈውን የህብረተሰብ ክፍል በድህነት እንዲማቅቁ ሲደረግ ቆይቷል።
ይሁንና ይህንን የባርነትሥርዓት ለመቀየር ሕዝቡ በውስጥም ሆነ በውጭ በተደረገ ከፍተኛ ትግል ቅጥረኛውን የትግራይ ዘራፊ ቡድን ከመንግሥትነት እንዲወገድ ቢደረግም እንደገና ወደ ስልጣን ለማምጣትና በአገራችን የባርነት ሥርዓት ለማስቀጠል በተከፈተ የውክልና ጦርነት የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራና በአፋር ላይ ወረራ በመፈጸም የተላላኪነት ተልዕኮውን በመፈፀም ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እንዲደርስ ተደርጓል። ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪና ደካማ መንግሥት እንዲፈጠር በማድረግ ቀደምት የአገራችን ጠላቶች በሆኑት ምዕራባዊያን አገሮችና በግብፅ መንግስት በግንባር ቀደምትነት የሚደገፍ ነው።
በተያያዘም በቅርቡ አገራችን የተፈጥሮ ሀብቷን በተለይም የውሃ ሀብቷን ለመጠቀም እንዳትችል ለማድረግ በተለይም የህዳሴ ግድብን በመገደብ በምጣኔ ሀብት አገራችን ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ የታቀደ ተግባር ነው።
በሌላ በኩል አገራችን ካለችበት መልክዓምድራዊ አቀማመጥ አኳያ ምዕራባውያን በቀይ ባህር አካባቢ የነበራቸውን የበላይነት በቻይና እንዲያጡ ሊያደርግ ይችላል በሚል በአካባቢው አሜሪካ የበላይ ለመሆን ካላት ምኞት በመነጨ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያደረገች ያለውን ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ትስስር እንድታቆም ለማድረግ በእብሪት የተከፈተብን የውክልና ጦርነት ነው።
በዚህም የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት በሕዝብ የተመረጠውን የአገራችን መንግሥት ላይ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ለትግራይ ወራሪ ኃይል መጠነ ሰፊ የሆነ ሁለገብ ድጋፍ በማድረግ አገራችንን ለማዳከም በግልጽ የተደረገ ጣልቃ ገብነት ነው።
ይህንን ሁሉ ደባና ሴራ በግልጽ የተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይህንን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለመመከትና ኢትዮጵያዊነትን በዓለም መድረክ ከፍ አድርጎ ለማሳየት ሰፊ ተጋድሎ እያደረገ ይገኛል።
በመሆኑ ምምዕራባዊያን በአገራችን ላይ በምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማድረግ የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ላይ ቢገኙም እኛ የአድዋ ልጆች ዛሬም እንደትናንቱ ‘ነፃነት ወይም በሞት’ በሚል መንፈስ ተነስተን ሁሉንም ጫና በመቋቋም የአገራችንን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት ከጠላት ተላላኪዎች ጋር እየታገልን እንገኛለን። የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እጅ ላለመስጠት ጠላትን ድባቅ በመምታት ዳግም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ የጥቁር ሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በራሳቸው እንዲወስኑ ለማድረግ የሚያደርጉትን ትግል በፊታውራሪነት እየመራች የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ዳግም ለመለኮስ በጽናት እየታገለች ትገኛለች።
ይህን እውነት በተግባር ለማረጋጋጥ የአፍሪካ ድምፅ ይሰማ የሚለው ጥሪ ሰሚ አግኝቶ የአፍሪካን እድል በአፍሪካዊያን እንዲወሰን ለማድረግ # NO MORE /# በቃ/ የሚለውን ማነቃቂያ በሁሉም የዓለማችን ክፍል በተለይም በአፍሪካ አገራት በከፍተኛ ድምፀት በማስተጋባት ሁሉንም የአፍሪካ አገራት ከአገራችን ኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገራት ጋር የምታደርገው የአፍሪካን ጦርነት ነው” በማለት ከፍተኛ የሆነ ድጋፍና መነቃቃትን ፈጥሯል።
አሁን የተጀመረውን # NO MORE ንቅናቄ ይበልጥ በማጠናከር ዛሬም እንደ ትናንቱ የምዕራባዊያን አገራት የአፍሪካን ሀብት ከመዝረፍ እንዲታቀቡና አፍሪካ ለአፍሪካውያን ብቻ እንድትሆን ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መጠን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ምዕራባዊያን እጃቸውን ከአፍሪካ እንዲያነሱ ለማድረግ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም የአፍሪካ አገራት በጋራ ሊቆሙ ይገባል።
ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካ በሕዝብ ቁጥራቸው ከአፍሪካ አህጉር እጅግ ያነሱ የአውሮፓ አገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የቋሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ድምፅን በድምጽ የመሻር መብት እንዲኖራቸው /Vetto power/ ሲደረግ የአፍሪካ አህጉር የዚህ መብት ተጠቃሚ እንድትሆን አለመደረጉን የቀድሞ የኢትዮጵያ ንጉሥ አፄ ኃይሌ ሥላሴ አቅርበውት የነበረውን ጥያቄ አሁን የቻይና÷ የሩሲያና የሌሎች አገር መንግስታት ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ ነው።
በያዝነው ዓመት የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የቻይና ፕሬዚዳንትና የኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህንን ጥያቄ በይፋ አቅርበዋል። እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በአግባቡ በመጠቀም ቀደም ሲል በአድዋ ድል የተጀመረውን የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እውን ለማድረግ አፍሪካ ራሷን በራሷ ለማስተዳደር ወይም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ድምጽን በድምጽ መሻር መብት ባለቤት እንድትሆን ሁሉም አፍሪካውያን በአንድነትና በቁርጠኝነት መነሳት አለባቸው።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ አገራችንም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ችቦ የለኮሰችበትን የአድዋ ድል ዛሬም በቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት በጠላቶቻችን ላይ ዳግማዊ የአድዋ ድልን በመቀዳጀት የተለመደውን መሪነቷን በመጠቀም የአፍሪካ አህጉርን ከምዕራባዊያን የእጅ አዙር አገዛዝ ነፃ እንዲወጣና ባለው ሃብትና ፀጋ ልክ የሚገባውን ዕድገትና ብልጽግና ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ አፍሪካን የዓለም የዳቦ ቅርጫት በማድረግ በፖለቲካው ላይ ወሳኝ የሆነውን እንድትጫወት ኢትዮጵያዊነትን ብሎም አፍሪካዊነትን በማስቀደም የፓን አፍሪካኒዝም ህልምን እውን ለማድረግ ሁላችንም በጋራ እንነሳ ለማለት እወዳለሁ። ኢትዮጵያዊነት የፓን አፍሪካኒዝም መሠረትነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ያማል ነገሩ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2014