ሁሌም ቢሆን ለልጆች ሁለንተናዊ እድገት በእናትና አባት እቅፍ በቤተሰብ ውስጥ ማደግ የመጀመሪያው ተመራጭ ቦታ ነው። ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ህጻናት ካለ እድሜያቸው ከቤተሰባቸው የሚነጠሉበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
አንዳንዶች በሞትና በሌሎች ምክንያቶች ከሁለቱም አልያም ከወላጆቻቸው አንዱ ይነጠላሉ። በዚህ አጋጣሚ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ እናቶች ከልጆቻቸው ባይለዩም ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ አቅም ስለማይኖራቸው የልጆቹ ህይወት የችግርና የሰቀቀን ከመሆን አያልፍም። በዚህ ሁኔታ የሚያድጉ ልጆች ደግሞ ለተለያዩ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ የሚዳረጉ በመሆናቸው በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎና ያላቸው ተቀባይነት መልካም ገጽታ አይኖረውም።
በአንጻሩ የቤተሰብ ፍቅር የማህበረሰበ እንክብካቤ ሳያገኙ የሚያድጉ ልጆች በተለያዩ ደረጃዎች በሚፈጠርባቸው ተጽእኖዎች የተነሳ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች የታገለጡም ናቸው። ከእነዚህም መካከል የደባል ሱስ ተጠቂ መሆን፤ በጎዳናም ሆነ በዘመድ አዝማድ ቤት ተጠግተው የሚያድጉ ከሆነ ለጉልበት ብዝበዛና ለአስገድዶ መድፈር የመጋለጥ፤ እንዲሁም ሴተኛ አዳሪነት የአብዛኛዎቹ ወላጅ አልባ ህጻናት መጨረሻዎች ናቸው።
በዚህ ሁኔታ ህይወታቸውን ለማሳለፍ የሚገደዱ ልጆች ደግሞ ለራሳቸውም ሆነ ለህዝብና ለሀገር የሚኖራቸው ፍቅርና ክብር የተዛባ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በዚህም በግለሰብ ደረጃ የጀመረው ችግር የማህበረሰብ ብሎም ለአገር የሚተርፍ እየሆነ ይመጣል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊ የተቸገረን አይቶ የማያልፍ የሰው ህመም የሚያመው የሰው ስቃይ የሚያሰቃየው ህዝብ መሆኑን ታሪክ የመሰከረለት ነው።
በቀደሙት ዘመናትም እነዚህ አይነት ችግሮች ሲገጥሙ እንደ ጉድፈቻና ማደጎ ያሉ ጠንካራ ባህል የነበሩ ቢሆንም፤ ባለፉት ሶስት አሰርት አመታት ግን ከወላጆቻቸው ተነጥለው ለችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያዊ ልጆችን በራስ አቅም ለመታደግ ከመሞከር በጉድፈቻ ወደ ውጭ መላክ ተስፋፍቶ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ መንግሥት ለአገር ውስጥ ጉድፈቻና ለአገር በቀል በጎ አድርጎት ማህበራት እየሰጠ ባለው ትኩረት የእርስ በእርስ መረዳዳት ባህሉ እያገገመ በመምጣት ላይ ይገኛል። የዛሬው የአገርኛ አምድ እንግዶቻችንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ቤተሰባቸውን ያጡና ከቤተሰባቸው የተነጠሉ የህጻናት ድርጅት በማቋቋም እየታደጉ ያሉ የበጎ አድራጊዎችን እንቅስቃሴ ነው።
ድርጅቱ «ማህበረ ተስፋ ህጻናት እንክብካቤና ማሳደጊያ በጎ አድራጎት ድርጅት» ይባላል። በቅድሚያ የድርጅቱ መስራችና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑትን አባ ተስፋ ስላሴ ወልደ መስቀልን ስለማህበሩ አመሰራረት አንስተን ለጠይቅናቸው ጥያቄ የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። አባ ተስፋስላሴ ወልደ መስቀል በእናትና አባት እጅ ብቻ ሳይሆን በአያት እጅ በእንክብካቤ ያደጉ ናቸው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምናኔ ህይወት ከመጀመራቸው በፊት እንደማንኛውም የገጠር ልጅ በአካባቢያቸው ፊደል ቆጥረው ከሃይማኖታዊውም ከዘመናዊውም ትምህርትም ቀስመዋል። ወላጆቻቸውና ያደጉበት ሰፊ ቤተሰብ በአካባቢያቸው ላሉ የተቸገሩ ሰዎች ደራሽ ነበር።
አባታቸው ከጎረቤቶቻቸው የተቸገረ የታመመ ካለ የራሳቸውን መሬት ከማሳረሳቸው አስቀድመው የእነሱን ለማሳረስ በሬ የሚያስጠምዱ፤ የሚያሳርሙና ወቅቱ ሲደርስም እህሉን አሰባስበው ጎተራ እስኪገባ የሚከታተሉ ነበሩ። አባ ተስፋስላሴም በልጅነታቸው እሳቸውም ልክ እንደ ወላጆቻቸው ለትልቅ ለትንሹ መታዘዝ የለመዱ፤ አቅማቸውም በፈቀደ በአካባቢያቸው የተቸገረ ሰው ካገኙ መርዳት ደስ የሚያሰኛቸው ነበሩ።
በዚህ ሁኔታ የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት አባ ተስፋስላሴ ሃያ ሁለት አመት ሲሆናቸው ግን እንደ ህይወት የመረጡት አቅጣጫ ምናኔን ነበር። በምናኔ ህይወታቸውም ቀዳሚ ያደረጉት በምድር ያላቸውን ህይወት በሙሉ የተቸገሩን በመርዳት የወደቁትን በማንሳት ለማሳለፍ ነበር። በዚህም ረጀሙን ጊዜ በተለይ በጎንደር ክፍለ ሀገር አርማጭሆ በሚባለው አካባቢ ቤተ ክርስቲያን በማሰራትና የተቸገሩትን በመርዳት አሳልፈዋል። ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም በልባቸው ይዘውት የመጡት ሀሳብ አንድ ቦታ ፈልገው የተቸገሩ ህጻናትንና አረጋውያንን እንዲሁም በደዌ የተያዙትንም ለመታደግ ነበር።
አዲስ አበባ መጥተው ስራቸውን የጀመሩትም ባረፉበት አለም ባንክ በሚባለው አካባቢ ጀሞ ቅድስት ማርያምና ስላሴ ቤተክርስቲያን ጸበል በማጥመቅ ለህሙማን በመጸለይ ነበር። በዚህ ስራ ውስጥም ሆነው ግን እንዳቅማቸው የተቸገሩትን በሙሉ በስጋዊም በመንፈሳዊም መንገድ ይንከባከቡ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም ጸበል ይጠመቁ ከነበሩት መካከል በኤች አይ ቪ ህመምና በሌሎችም በሽታዎች ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ይመለከቱ ስለነበር አንዳች ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ለራሳቸው ቃል ይገባሉ። በዚህ ጉዞ ውስጥ እያሉም የእርሳቸውን ፈለግ ተከትለው የበጎ አድራጎት ስራዎችን አብረዋቸው ሲሰሩ ለነበሩ ምእመናን እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን ያጋሯቸዋል።
«እኔ አቅመ ደካማ ለነፍሴ የምኖር ነኝ፤ የገንዘብም ሆነ የእውቀት ሀብት የለኝም፤ ነገር ግን የተቸገሩትን ስረዳ የመኖር ሀሳብ አለኝ፤ በአቅማችሁ ብትደግፉኝ» የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። እነዚህ ቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ብቻ ሳይሆን በየቤቱ የተቸገሩትን እየተዘዋወሩ ይደግፉ የነበሩ ሰላሳ ስምንት የሚደርሱ ወጣቶችም እኒህ አባት ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል አብረው ለመስራት ተስማምተው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።
የመጀመሪያ ስራቸው ያደረጉትም የሚሰሩትን በመለየት እንደተቋም በህጋዊ መንገድ እውቅና ማግኘት ስለሚያስፈልግ ሁኔታዎችን አመቻችቶ በህጋዊ መንገድ ለመመዝገብ መንቀሳቀስ ነበር። በዚህ ሂደትም በመንግሥት ህግና ደንብ መሰረት ቦርድ አቋቁመው ህጋዊ እውቅናና ፈቃድ አግኝተው ስራቸውን መስራት ይቀጥላሉ።
ማህበሩ እውቅና ካገኘና በህጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ ያለውን ሂደት ደግሞ የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ፋንቱ እንደሚከተለው አብራርተውልናል። መስራቾቹን የምናውቃቸው እኔም ሆንኩ ሌሎቹ አባሎቻችን በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው ነው።
አንድ ቀን እኝሁ አባት ከሌሎችም ጋር በመሆን ሁለት ስራዎችን ለመስራት እንሻለን አንደኛው ወላጅ አልባና ለችግር የተዳረጉ ህጻናትን እየተንከባከቡ ማሳደግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጧሪ ደጋፊ አለሁ ባይ የሌላቸውን አረጋውያን መንከባከብ ነው።
ነገር ግን እኛ ለአገሩም እንግዳ ነን፤ የት እንደምንፈጽመው አናውቅም የሚል ጥያቄ አቀረቡልን። እኛም በየግላችን የዚህ አይነት ምግባረ ሰናይ ለመፈጸም እናስብ ስለነበር በሀሳባቸው ተስማምተን ሰኔ ሶስት ቀን በሁለት ሺ አራት ዓ.ም ከተወያያን በኋላ አስፈላጊውን ሁሉ አድርገን ህጻናትን የሚንከባከብ ማእከል ለማቋቋም ከስምምነት ደረስን። ማህበሩን ለመመስረት ስንስማማ በቅድሚያ ተደራሽ ለማድረግ የወሰነው ለጸበል መጥተው በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በመያዝ ነበር።
ከዛ በኋላ ግን ሌሎች ህጻናትን ከየት እንደምናመጣና ያሉትንም ቢሆን የት እንዴት እንደምናኖራቸው የወሰነው ነገር አልነበረም። በዚህም ላይ ተሰብስበን ከመከርን በኋላ በፍጥነት ወደሥራ መግባት ስለነበረብን በአራት ህጻናት ስራችንን ጀመርን። ከዚያም በኋላም ፈቃድ ስላወጣን ከወረዳውና ከክፍለ ከተማው ሴቶችና ህጻናት ጋር በመሆን እየተቀበልን መስራታችንን ቀጠልን።
ይህም ሆኖ ምንም እንኳን ማእከሉ የተመሰረተው በቤተክርስቲያን ስር በጸበል ቦታ ቢሆንም ለፈውስ መጥተው እዛው ከቀሩትም ሆነ በመንግሥት ከሚመጡት ህጻናት መካከል የሌሎች ሀይማኖት እምነት ተከታዮችም ይገኙ ነበር። ስራውን ከጀመርን በኋላ ግን በቋሚነት ልጆቹን የምናኖርበት ቦታ ማግኘት እንዳለብን ስለተገነዘብን ቦታ ወደማፈላለጉ ገባን። ነገር ግን ይህንን ችግር በቀላሉ መሻገር ስላልተቻለ ከየራሳችን ከየአባላቱ ግቢ ለመጠቀም ከወሰንን በኋላ አንድ አባላችን በጣም በትንሽ ክፍያ ቦታ ሊሰጠን በመስማማቱ ለጊዜውም ቢሆን ስራችንን ተረጋግተን መስራት ለመጀመር በቃን።
እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ለህዝብ መታወቅና በመንግሥትም አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግ ስለወሰንን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ፈቃድ አውጥተናል። ፈቃድ ለማውጣት በነበረን እንቅስቃሴም ክፍለ ከተማው በጎ አድራጎት ኤጀንሲውም ሆነ ሌሎች ህጻናትና ሴቶች በሙሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉልን ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ድርጅቱን ለመቆጣጠር የሚመጡ የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ የተለያዩ ድጋፎችን ከማድረግ አልፈው የአመት በአላትን በተቋሙ የሚያሳልፉበት ጊዜም አለ። እኛም ሁላችንም የቦርድ አባላትና የማህበሩ አባላት ያለፉትን ሰባት አመታት አመታዊ በአላትን የምናሳልፈው በድርጅቱ በመገኘት ከልጆቹ ጋር ነው። በእነዚህ ቀናት አባላቱ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በመገኘት በተቋሙ ድንኳን በመጣልና ከምግብና ከመጠጥ ጀምሮ አስፈላጊውን የበአል ዝግጅት በማሟላት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ሀይማኖታዊና ሌሎች ጉዞዎችን በማድረግ ልጆቹ ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር ይደረጋል። ዛሬ በማእከሉ ሀያ የሚደርሱ ህጻናትና ልጆች ሁለንተናዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። ነገር ግን ያሉበት ቦታ በቂ ባለመሆኑ ወንዶቹም ሴቶቹም ልጆች የሚኖሩት አንድ ክፍል ውስጥ ነበር። ከመጀመሪያዎቹ ገቢዎች ህጻናት መካከል ደግሞ አሁን ላይ እድሜያቸው አስራ ስድስትና አስራ ሰባት አመት ሞልቷቸው ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን እየደረሱ ስለሆነ እነዚህን በአንድ ቤት ውስጥ ማኖሩ ለማህበሩ አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ሆነ።
በመሆኑም እንደ ተፈጥሯዊ ሂደት ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ከግምት በማስገባት ያሉበትን ክፍል ለሁለት የመክፈል ሥራ ተሰርቷል። ነገር ግን ይህ በዘላቂነት ልጆቹን በእንክብካቤ ለማሳደግ በቂ አይሆንም። ይህም ሆኖ ድርጅቱ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችና ሌሎችም በተለያዩ አጋጣሚዎች ልጆቹ ያሉበትን ሁኔታ ሲሰሙ ከሚያደርጉት ድጋፍ በቀር ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የለውም።
ዛሬም ድረስ የድርጅቱ ዋና የገቢ ምንጭ እነዚህ ድጋፍ አድራጊዎች በተለያየ መጠን በአይነትና በጥሬ ገንዘብ የአቅማቸውን የሚቸሩት ነው። ከእነዚህም መካከል አንዲት በጎ አድራጊ ግን ላለፉት ሰባት አመታት በየወሩ ከሀያ አንድ ሺ ብር በላይ በማውጣት የልጆቹን የትምህርት ቤት ክፍያ እየደገፈች ትገኛለች። ምን አልባትም ይህቺ ፈቃደኛ በጎ አድራጊ ባትኖር ኖሮ ልጆቹን በመንግሥት ትምህርት ቤት ለማስተማር የምንገደድበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። ከዚህ ባለፈ ለድርጅቱ ገቢ የማሰባሰብ ሥራ የሚሰራው በአዘቦቱና በአመታዊ በአላት ጀሞ ቅድስት ማርያምና ስላሴ ቤተክርስቲያን ከሚመጡ ምእመናን ነው።
ዛሬ በማእከሉ የሚኖሩት ልጆች ቁጥር ሀያ የደረሱ ሲሆን አስራ ሁለት ልጆች ደግሞ ባሉበት ሆነው ሙሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። ልጆቹን የሚያሳድጉትም ሆነ የሚንከባከቧቸውና በጥበቃ ሥራ የተሰማሩትም በመንፈሳዊ ህይወት የሚኖሩ አምስት የገዳም መናኝ መነኮሳት ናቸው። ዛሬም የማህበሩ አባላት ተደጋፊዎቹን ቁጥር ለማሳደግ እቅድ የተያዘ ሲሆን ለድርጅቱ ገቢ ማስገኛ የስራ ፈጠራ የሙያ ስልጠና መስጫ ለማቋቋም ሀሳብ አላቸው። እነዚህ ተቋማትም በአንድ ወገን ልጆቻቸውን ማሳደግ እጅ ላጠራቸው ወላጆች የሥራ እድል ለመፍጠር ሲሆን፤ ልጆቹ ትምህርታቸውን ጨርሰው ምን አልባት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እድሉን ካላገኙ የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ የታለመ ነው።
የማህበሩ መስራች አባ ተስፋስላሴም በአሁኑ ወቅት ቦሌ አካባቢ በሚገኘው በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ጸበል ማጥመቅ እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህ ስራቸውም በርካታ ወጣቶች በአእምሮ ህመምና በሱስ ተጠምደው እየተጎዱ መሆናቸውን በማየታቸው ለመታደግ የረጅም ጊዜ እቅድ መያዛቸውን ይናገራሉ። አባ ተስፋስላሴ እንደሚሉት እነዚህ በተለያየ ሱሶች የተያዙ ወጣቶች አብዛኛዎቹ ከቤተሰባቸው የተለያዩ ሲሆን በከፍተኛ ጭንቀትና ችግር ውስጥ ያሉ ናቸው። ከዚህ ነገር ቢላቀቁ ደግሞ ለራሳቸው፣ ለአገራቸውና ለቤተሰባቸው ብዙ ማድረግ የሚችሉ ናቸው።
በመሆኑም እነዚህን መታደግ ህብረተሰቡንም አገርንም እረፍት መስጠት ነው። በተጨማሪ በመጦሪያ ዘመናቸው ያለ አይዞህ ባይ ብቻቸውን የቀሩትን አረጋውያን ለመታደግም እቅድ አለኝ የሚሉት አባ ተስፋ ስላሴ፤ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ዜጋ ትኩረቱን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ችግር ላይ ማድረግ እንደሚገባው በማሳሰብ፤ በያለንበት በአቅማችን መረዳዳት ከቻልን እኛ ኢትዮጵያውያን የማንንም ድጋፍ ሳንሻ ለራሳችን ችግር ራሳችን መፍትሄ መፍጠር እንችላለን ሲሉም አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሳሣሥ 1/2014