ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ አዲስ አብዮት ለመፍጠርና እድገቷን በዚያ ላይ ለመገንባት ቆርጣ ወደ ትግበራ ከገባች ሰነባብታለች። ሁሉም ቁልፍ ዘርፎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲከተሉም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል።
በእርግጥ ዓለም በዘርፉ ከደረሰበት የላቀ ደረጃ አንፃር የአገሪቱን ስንገመግም እጅግ ወደኋላ ከቀሩት የዓለም ክፍላት ጋር የምትመደብ መሆኗ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን እየተመለከትን ነው። በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ በጎ ውጤት የሚያሳይ የሳተላይት ቴክኖሎጂና መሰል እንቅስቃሴዎችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ አግኝተው መንግሥታቸውን የመሰረቱት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ “ለሳይንስና ቴክኖሎጂ” ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ በርካታ ማረጋገጫዎችን ማግኘት ይቻላል። ከዚህ ውስጥ የሚከተለውን ንግግራቸውን እና የወሰዱትን ተግባራዊ እርምጃ መመልከት ይበቃል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ዓለም ባልተጠበቀ ፍጥነት አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት እያካሄደች ትገኛለች። ማኅበረሰባችን ከዚህ ክስተት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማረጋገጥ እና ወጣቶቻችን በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ በንቃት መሥራት ይጠበቅባታል። በአሁኑ ወቅት እንደ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence)፣ የበይነ መረብ ቁሶች (Internet of things)፣ ናኖ ቴክኖሎጂ፣ እና ውሒብ አስተኔ (Big Data) ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚደገፉ የማምረት፣ የመገናኛ እና የአኗኗር ዘዬ ሽግግርን እየተመለከትን ነው። ታዳጊዎች አዳዲስ ክሂሎት እና ዕውቀቶችን ይፈልጋሉ ፤ የወደፊቱን ጊዜ በተሻለ ለመጠቀም እንዲችሉ የማድረግ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ኅብረተሰብን ለመገንባት የሚያስችላትን አቅም ገና አልፈጠረችም። ዐቅምን በማጠናከር ስኬታማ ለመሆን ደግሞ ፈጣን ፣ እና ልበ-ሙሉ የተቀናጀ ርምጃ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን ። በ2011 ዓ.ም. ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አጀንዳ እና የአሥር ዓመት ብሔራዊ የልማት ዕቅድ (2011-2021) አጽድቀናል። አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ዕድገትን ዘላቂ ለማድረግ እና እያንዳንዱ ዜጋ ከሀገር አቀፍ ብልጽግና ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ዕድል ይሰጣሉ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ከላይ የገለፅነውን ራእይ ወደ መሬት ለማውረድና ኢትዮጵያውያን የትሩፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ስልጣን፣ ተግባርና፣ ኃላፊነት በህግ ተወስኖ ተሰጥቷቸው ከሚሰሩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚመደብ ነው። በዚህም አዲሱ መንግሥት ከተመሰረተበት መስከረም 30 አንስቶ አጠቃላይ የዘርፉት አቢዮት መምራት የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎችን እና ልማት እያከናወነ መሆኑን ማየት ይቻላል። ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችንም ይህንኑ በተመለከተ የተለያዩ የመስሪያ ቤቱን እንቅስቃሴዎችና ፕሮጀክቶች ከዚህ እንደሚከተለው ለማየት ሞክሯል።
የአፍሪካ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መዳረሻ
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን እና ይሄም አዳዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ዕድገትን ዘላቂ ለማድረግ ከሚሰሩ ተግባራቶች መካከል አንዱ መሆኑን በቅርቡ ሰምተናል። በተለይ የ2021 የአፍሪካ ቴክ ፌስቲቫል በበይነ መረብ በተካሄደበት ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ “በቴክኖሎጂ ሃያል ለመሆን የኢትዮጵያ ጉዞ” የሚለውን የመንግሥትን እቅድ ይፋ ባደረጉበት ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ ፊት ለመራመድ እንድትችል እየሠራቻቸው ያሉ ሥራዎችን ተናግረዋል። በዋናነትም የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ፣ የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አዋጅ፣ የግል ዴታ ጥበቃ አዋጅ፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የሥራ ቅልጥፍናና የኢ-ክፍያ ስትራቴጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በትኩረት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች መሆናቸውን ገልፀው ነበር።
“ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዳረሻ ለማድረግ እየሰራን ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለዚህ ስኬትም ምቹ የቴክኖሎጂ ከባቢ ሁኔታን መፍጠር ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር መሆኑን ነው ያመላከቱት።
ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ መንግሥትና የጉዳዩ ቀጥተኛ የትግበራ መሪ የሆኑ ተጠሪ ተቋማትና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ ፓርኮችን መሠረተ ልማት ማሟላት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ማስፋፋት፣ የዲጂታል እውቀትን ማስፋት፣ የበይነ መረብ ደህንነትን ማስጠበቅ እና የሰው ኃይል ግንባታ ላይ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
በቅርቡ ይፋ እንደተደረገው የበይነ መረብ አውደ ርዕይው ላይ ከ300 በላይ ባለ ራዕዮች ንግግር አድርገው ነበር። በዚህ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለው ሚኒስትር ደኤታዋ ራእያቸውን አጋርተዋል። ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች አመራሮች፣ የቴክኖሎጂ የፋይናንስ ተቋማትና የባንክ ኃላፊዎችም ተሳትፈውበታል። ይህ ሁነት በመግቢያችን ላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያ ለዘርፉ እድገት የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነ ይታመናል።
ሁዋዌና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አመራር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ተግባርና ኃላፊነቶች በጥሩ ንቃተ ሕሊና ተፈፃሚ እንዲሆኑ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከመንግሥትም ሆነ ከግሉ ዘርፍ ከመጡ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተፈጠረ ያለው ትስስር ነው። ለዚህ እንደ ማሳያነት መጥቀስ ከቻልን በቅርቡ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ.ኤች.ዲ) የሁዋዌ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂስ ግሩፕ ልዑካንን ተቀብለው ማነጋገራቸውን በቀጣይ በስፋት ስለሚሰሩ ሥራዎች መተማመን ላይ መድረሳቸውን ነው።
እንደ ዶክተር በለጠ ሁዋዌ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አበረታች ስኬቶችን እያስመዘገቡ ካሉ ድርጅቶች በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ አበረታች እንቅስቃሴ እያደረጉ ካሉት ድርጅቶች አንዱ መሆኑን በመጥቀስም የነበሩትን ሂደቶች በማድነቅ በቀጣይ በጋራ ተባብረን እንሰራለን ብለዋል። በአይ.ሲቲ፣ በዲጂታላይዘሽን እና ሌሎች ተዛማጅ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የነበሩ ስምምነቶችን በማደስ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ የትብብር ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቀጣይ ከአገራዊ የትኩረት መስኮችና የትብብር ዘርፎች መነሻነት የጋራ ስምምነቶችን በማድረግ ከድርጅቱ ጋር በትብብር መሥራት የሚቻልበት የትግበራ ሂደት እንዲቀመጥ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ይህ አይነት ውሳኔ ከሌሎች መሰል ተግባራት ጋር ተደምሮ በጥቅሉ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገቱና ለዲጂታል አብዮቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ምርምር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትንና ትስስሮች የሚያጠናክሩ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን እያካሄደች እንደምትገኝ ይናገራሉ። ይህን ለመደገፍም እያንዳንዱን ዘርፍ በኢኖቬሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ የማገዝ ሥራዎች ቀዳሚ ተግባራት መሆናቸውን ነው የሚያነሱት።
ባለፉት ሦስት ዓመታት አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የነጻ ገበያ ሥርዓት መከተል በመጀመሩ ኢኮኖሚያችን በሚያስደንቅ ፍጥነት እየተለወጠ ነው። ይህን ለውጥ በተጠናከረ መንገድ ለመተግበር እና አገራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ የመንግሥት ጽኑ እምነት መሆኑን ከበርካታ ብሔራዊ ስትራቴጂካዊ ሰነዶችና ጥብቅ ክትትሎች መመልከት ይቻላል።
የአይሲቲ ዘርፉ የሚመራበት የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ፣ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ስትራቴጂውንና የአስር ዓመት እቅዱን ለማሳካት በቁልፍነት እንደተካተተበትም ሚኒስቴር ዴኤታው አረጋግጠዋል። በተለይም ያልተገደበ ራዕይ ባለቤት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን ለመለወጥ ካላቸው ቁርጠኝነት በመነጨ የሚያደርጉት ድጋፍና ክትትል ሁሉም ለውጡን በወኔ እንዲቀላቀል ከፍተኛ አቅምም የፈጠረ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥ ፈጠራ አካል የስራ እድል የሚፈጠርበት ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ ለማንበር የኢኖቬሽን አፍሪካን የመሳሰሉ ጉባኤዎች መካሄዳቸው ለእውቀት ሽግግር፣ ኢንዱስትሪ ትስስር፣ የገበያ አማራጮችን ለመክፈት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ነው የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች የሚጠቁሙት።
ለምሳሌ ያህል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ኤክስቴንሺያ በመተባበር በየዓመቱ የሚያካሂዱት 18ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጅታል ጉባኤ የተቀመጡለትን ግቦች አሳክቶ በስኬት መጠናቀቁን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን በቂ ዝግጅት ተደረጎባቸው የቀረቡት የመወያያ ሃሳቦች፣ ቁልፍ መልዕክቶችና የተከናወኑ ፍሬያማ ውይይቶች የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ለመሳብና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በሚያስችል መልኩ ትስስር እንደሚፈጠር ነው ተስፋ የተጣለባቸው።
ዶክተር ባይሳ “የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎችና የዘመኑ ዲጅታል ፋይናንስ፣ ዲጅታላይዜሽንና ዲጂታል ለውጦችን በመተግበር ለእድገት መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ የተመከረበትም የሁለተኛ ቀን ፕሮግራም በርካታ ቁም ነገሮች ተገኝተውበታል ብለዋል” በማለት መሰል ጉባኤዎች ምን ያክል ወሳኝነት እንዳላቸው ለማሳየት ሞክረዋል። የዘንድሮው ጉባኤ ዋና ጭብጥ በኢኖቬሽንና ዲጂታል ከባቢያዊ ሁኔታው ያሉ እድሎችንና ተግዳሮቶችን በመለየት ማሳየት በመሆኑ በዚህ ረገድም የተሳካ ነበር ብለውታል።
የብሔራዊ አጀንዳዎችን ላይ የመመካከር ግብ አስቀምጦ የተከናወነው 18ኛው የአፍሪካ ኢኖቬሽን ዲጅታል ጉባኤ እነዚህንና መሰል ክዋኔዎችን አስተናግዶ በተቀመጠለት ጊዜ መጠናቀቁ ስኬታማ እንዳደረገው ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ አመርቂ እድገት ለማስመዝገብ ከምታደርገው ጥረት ባሻገር ቀጠናዊ ትስስር ለመፍጠር የሚደረገው ሙከራ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህን መሰል ትብብር ለዘመናት ወደኋላ ቀርተንበት የነበረውን ዘርፍ በፍጥነት አሻሽሎ ዓለም የደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይ ለማሰለፍ ግዙፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሆነ፣ በማደግ ላይ ላሉ ኢኮኖሚዎች የሳይበር ደኅንነት፣ ጎጂ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት፣ በሀብታሞች እና በድኻዎች መካከል እያደገ የመጣው ክፍተት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በብቃት ለመጠቀም ያለመቻል ተጠቃሽ ስጋቶች ናቸው። ለምሳሌ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን ግለሰቦችን ለመከታተል እና ለማግኘት፣ የክትባት ምርምር ለማመቻቸት ፣ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ውድቀትን ለመታደግ ሰዎች በርቀት እንዲሠሩ በመርዳት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጠቀሜታ ላይ ጠንካራ ትምህርቶችን ለመውሰድ አስችሏል።
ዞሮ ዞሮ ትልቁ ፈተና የዲጂታል መገለጫን ወይም ምንነት ሙሉ በሙሉ ለመረዳትና ለማሰስ የሚታየው ቸልተኝነት ነው። እንዲሁም ከሥርዓተ ጾታ፣ ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና በዋዛ እንዳይታለፉ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስጋት ተጋፋጭነትና የባለቤትነት ስሜት አስፈላጊ ነው።
በመሆኑም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን በማላቅና አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት በፍጥነት ለመቀላቀል ከላይ ያነሳናቸውን ተግባራት በቁርጠኝነት ማከናወንና እራሳችንን ለዘርፉ እድገትና ይዞት ለሚመጣው ፈጣን ለውጥ ክፍት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ ደግሞ በጥቅሉ የአገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ እንችላለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014