
ገጣሚው የግጥም መድበሉን ሊያስመርቅ በአዳራሹ ውስጥ ተገኝቷል። ታዳምያን እንዲሁ በአዳራሹ ውስጥ ናቸው። መድረክ አስተዋዋቂው ወደ መድረክ ወጥቶ መርሃ ግብሩን አስጀመረ። ሚዲያዎች ዘገባቸውን ለማድረግ ካሜራቸውን ደግነዋል። የግጥም መድብል ምርቃት። መድብሉ ከማተሚያ ቤት ወጥቶ በእለቱ ግዢ ለሚፈልጉ እየተሸጠ ነው። ሰው እንደፍላጎቱ እየገዛ ወደ ውስጥ ገብቶ፤ አዳራሹን ሞልቶታል። ከመድረኩ ላይ የተመረጡ ግጥሞች በንባብ ተሰሙ። የተለመደው የመጽሐፍት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት፤ የተለመደው የግጥም መድብል ምርቃት። የተለመደው የሁነት አዘገጃጀት። እንግዳን ተቀብሎ መሸኘት። በአደባባይ የክት ልብስን ለብሶ የመገኘት ደስታን ተጋርቶ ወደ ራስ ዓለም መግባት።
ከምርቃቱ በኋላ ደራሲው ወደመኪናው ሲገባ አንድ እንግዳ ሰው እየተራመደ መጣ። ገጣሚው በግርታ እንግዳውን ሰው ይመለከተዋል። ከታዳምያን መካከል አንዱ ሰው ነው። አለባበሱ የተቀዳደደ ትኩረትን የሚስብ፤ ራሱን የጣለ ሰው። ለተመልካች የግለሰቡ ሁኔታ የሚሰጠው ትርጉም ራስን የጣለ ቢሆንም እርሱ ግን ራሱን የሚያየው የጥበብ አፍቃሪ እንዲሁም የጥበብ ጠበቃ የሆነ አድርጎ ነው። በአገኘው አጋጣሚ የጥበብ አፍቃሪ መሆኑን የሚገልጽ፤ በተለይም የግጥም አፍቃሪ።
ገጣሚው በመገረምና በፍርሃት ሆኖ እየተመለከተው እያለ እንግዳው ሰው ገጣሚውን “አትደንግጥ፤ በአለባበሴም ግር አትሰኝ። እኔ የጥበብ አድናቂ ነኝ፤ በተለይ የግጥሞችህ አድናቂ። መድብልህን ገዛሁት ፕሮግራሞ ተጀምሮ እስኪያልቅም አነበብኩት። እንደተለመደው ግጥምህ አስደማሚ ነው።”ገጣሚው አሁንም ከግርታው አልወጣም። ሰውዬው ንግግሩን በመቀጠል “ወደፊት መጻፍህ ስለማይቀር ስለ ሕይወት ጥቁር ገብያ ልነግርህ ነው።” አለው። “የሕይወት ጥቁር ገብያ” ገጣሚው ጠየቀ። እንግዳው ሰው በመቀጠል “አዎን የሕይወት ጥቁር ገብያ።” አለ። “ምንድን ነው የሕይወት ጥቁር ገብያ?” ሲል ደራሲው ጠየቀ። እንግዳው በመቀጠል “የሕይወት ጥቁር ገብያ የማንነት ቀውስ የፈጠረው የማስመሰል ኑሮ ነው። የሁለት ሰውነት ኑሮ። ሁሉም በራሱ በጨለማ ክፍል ውስጥ ስላለው ኑሮ ዝምታን መርጦ በገሚስ ሕይወት ላይ ብቻ የሚመሰረት ሕይወት ነው። የማንነት ቀውስ የፈጠረው ስብራት።” እንግዳውና ገጣሚው ለሴኮንዶች በዝምታ ውስጥ ተያዩ። አንዳች የመድረክ ተውኔት የሚሰሩ እንጂ ድንገት የተገናኙ አይመስሉም። እንግዳው ከአፍታ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ “አንተ ብእረኘ ነህ። አንተ በግጥምህ መልእክተኛ ነህ። አንተ የሕይወትን ጥቁር ገብያ መግለጥ የምትችል ሰው ነህ። የማንነት ቀውስ ሰለባ ስለሆኑት ሚሊዮኖች መናገር የምትችል ነህ። እናማ ግለጠው። ለምን እንደ እኛ ትቀብረዋለህ። እኛ እንደምታየን አለባበሳችን ለሁላችሁም ግልጽ ሆኖ ይታያል። እናንተ ግን ጥሩ ለብሳችሁ፤ በደንብ አጊጣችሁ ነገር ግን በማንነት ውልድ ቀውስ ውስጥ ስታልፉ እውነተኛ ትመስላላችሁ።” ገጣሚው የእንግዳው ንግግር ሥርዓት የጎደለው ሆኖ ተሰማውና ሊያስቆመው አሰበ። ግን ከግጥሙ መካከል እውነትን ፊት ለፊት ስለሚናገሩ ድምጾች ይገኝበት ነበርና ራሱን ወቅሶ ዝምአለ።
እንግዳው ቀጠለ “ስለ ምን እንደማወራ እየገባህ ነው። በይሉኝታ ሁሉን ተቀብሎ የሚያሳልፈው ማለቴ ነው። ስብሰባ ላይ ሃሳቡን ከመስጠት ተለጉሞ ውሎ ነገር ግን ከበስተጀርባ የሚያንሾካሹከው ማለቴ ነው። በልብስ ውስጥ የውስጡን ድምጽ ደብቆ እየኖረ የሚመስለውን ማለቴ ነው። በማንነት ቀውስ ስብርብሩ ወጥቶ እንዲሁ ወጥቶ የሚገባውን ማለቴ ነው። ወንድሜ የሕይወት ጥቁር ገብያ ሊጠፋ አይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ተዋጋው። ጥበብ የአደባባይ መልእክተኛ ነች። እኔን መልሰህ ዳግም አታየኝም፤ እኔ ግን በቀጣይ ሥራዎችህ ውስጥ አልፌ ጭምር አይሃለሁ። የጥበብ ሰው ስለሆንክ የአደባባይ ነህ። አንተም እኔም አንድ ከሆነን ጥቁር ገብያው እያየለ ሄዶ ሁላችንም በፍጥነት ጉዞችን ወደ መጥፊያው ገደላችን ሲሆን ተጠያቂው ማንነው?” በማለት ጠየቀ።
አሁንም ሌላ የአፍታ ዝምታ። ገጣሚው የመኪናውን ሞተር አስነስቶ መንዳት እንዳለበት እያሰበ ግን የሚመታውን ልብ ማስቆም አቅቶት ዝም ብሎ ያደምጣል። እንግዳው የለበሰውን የተበጫጨቀ ልብስ አስተካክሎ ትንፋሽ እየወሰደ እያለ ባለ 35 ቁጥር የተራድኦ መኪና ሲያልፍ ተመለከተ። ቀጠለ ንግግሩን “በእርዳታ ሰበብ ለራሱ እየኖረ ደሞዙ በመቶ ሺዎች ውስጥ በሆነበት ከተማ አንድ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ሦስት ሺ ብር እየተከፈለው ወሩን ግፋበት ሲባል። የአንድ ሚንስትር ደሞዝ በአስር ሺ ብር ውስጥ ተሰፍሮ ግን አገር የሚያክል ተራራን እንዲቀይር ሲጠበቅ። አገሪቱ ድንበር የለሽ ሆና ከውጭ ትርኪምርኪው ሁሉ ማራገፊያ ሆና የቤተሰብ አባላት በቀን ሁለቴ መመገብ ተስኗቸው አንድ ኮስታራ አባወራ ግን ለእራቁት ዳንስ ቤት ሺዎችን በየቀኑ የሚያፈስባት ከተማ። ትምህርት ቤት አጠገብ ንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ ሺሻ ቤቶች ከተማሪ መካከል ገንዘብ መሥሪያ ተማሪን በይፋ እየመለመሉ በሚታይበት መንደራችን ጥቁር ገብያው እንዴት ከብእርህ እራቀ?” ገጣሚው እንግዳውን ማስጨረስ እንዳለበት ወሰነ። ተመቻችቶ ተቀምጦ ዝም ብሎ መስማቱን መረጠ። የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብቶ በነበረ ጊዜ ያለፈበት አስቸጋሪ ወቅት ትዝ ብሎት ይህን ሰው አስጨርሶ ለመስማት ወሰነ።
እንግዳውም ሰሚ ጆሮ በማግኘቱ ውስጡን ዘርግፎ ሊጨርሰው አስቦ የንግግሩን ድምጸት ቀንሶ፤ አይኑ ላይ እየመጣ የታገለውን እምባ አሁንም እየታገለ “ለማንኛውም ወንድሜ አስብበት ብእርህን አንሳ። የንግድ ግጥም አትግጠም። የእውነት ግጥም ግጠም፤ ፈጣሪ የሰጠህን መክሊትህን እየጠፋ ያለውን ለመመለስ ተጠቀምበት። የሕይወት ጥቁር ገብያን በብእርህ የገለጥክ ቀን ያኔ ከመድረክ ሆነህ ጥራኝ እኔም የሕይወቴን ጥቁሩን ገብያ በአደባባይ ተናግሬ ብእርህ እውነት መናገሯን እመሰክርልሃለሁ። ከእዚህ ማህበረሰብ ተገፍቼ ጎዳና የወጣሁ መሆኔን እነግርሃለሁ። ያለፍኩበት የማንነት ቀውስ ሁሉን አስጥሎ ብቻዬን ያስቀረኝ እንዴት እንደሆነ ተናግሬ አንድን ተረኛ ጠፊን ከጥፋት እንድታደጋለን። እዚያው ድረስ ግን ጥቁሩን ገብያ እያየሁ እቆዝማለሁ። ከአንዱ ቦታ ወደሌላው በእግሬ እየኮተንኩ ገብያውን እመለከታለሁ። በጥበብ እየተከዝኩ፤ በጥበብ እየተመከርኩ ወደ ፈውሴም እደርሳለሁ። ከውድቀቴ ተመልሼ እንድቆም የሚያደርግ ብእርን አጥቼ አንድ ሃያል ብእረኛ እስከነሳ ጠብቂያለሁ፤ አሁንም እጠብቃለሁ። ተራ ሰው መሆኔን አውቄ ተራ ኑሮን እየኖርኩ እጠብቃለሁ። ከስማችን ፊት ስላለው ማእረግ ብዙ ዘመን የተገረምኩ ዛሬ ግን ስለ እውነተኛ ግብር ብቻ የማስብ ተራ ሰው። ከስማችን ፊት ቄስ ይባል መጋቢ እንዲሁም ሼክ ሁላችን በጥቁር ገብያው ውስጥ የሕይወት መልካችን አብሮ የተደመረ መሆኑን በራሴ በሕይወቴ አይቼ ሰው የደረበው ስምና የአደባባይ ኮተቱ ውጭ ራሱን ሰውዬውን ፈልጌ ላየው የምሻ ተራ ሰው። በትምህርቱ ገፍቶ አንቱታ የተሞላው ባለ ሦስት ዲግሪው ሆነ ፕሮፌሰሩ መርካቶ ገብተው በሕይወት ጥቁር ገብያ ውስጥ ሲመላለሱ ውለው ማታ ቤታቸው ደርሰው ቀዝቃዛ ሻወር ወስደው ሪሞት ከእጃቸው አድርገው ጆሮቸውን አይናቸውን መግበው ‘በሰላም ያዋልከኝ’ ብለው ‘በሰላም አሳድረኝ’ ብለው መጨረስ ሳይችሉ ቀርተው የእንቅልፍ ኬላ ላይ የሚደርሱ ሰዎችን እያየሁ በሽታን አትርፌ ለራሴ መሆን ያልቻልኩ ተራ ሰው።”
ገጣሚው በዝምታ እያደመጠው መሆኑ ደስታን የፈጠረለት እንግዳ ሰው ሌሎች ላይ መፍረዱን ራሱ አልወደደውም። ሁሌም አይወደውም። ፍርዱንም ሆነ ንግግሩን ማቆም እንዳለበት ዋናው መልእክቱን ማድረስ ላይ ማተኩር እንዳለበት አስቦ “ወንድሜ እኔ ማንነኛና ነው ስለሌላው የምነግርህ። አንተ ግን ብእርህን ጠይቃት። ትነግርሃለች። ወደ አደባባይ ውጣ። ታክሲ ጥበቃ የተሰለፈውን ተመልከት። ሰው አለኝ የሚለውን ለብሶ፤ አለኝ የሚለውን ተቀብቶ፤ በንግግር ቃላቱ በጨዋነቱ ተደምመህ ወደ መጣህበት አትመለስ። በምናብህ ተሻግረህ ሂድ። ያ ሰው ቢሮው ሲደርስ ተመልክተው። በእጅ መንሻ ኑሮውን የመሰረተበት ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ ተመልከት። አንዱ ቀሚ ሌላው ተቀሚ አብረው መሰለፋቸውን አስተውል። አንዱ ከዳተኛ ሌላው ተከጂ ሆነው እንዲሁ ተሰልፈዋል። ሕይወት እሴት አልባ ሆኖ ከሞራል ጎድሎ፤ ሌባውን ጥበቃ በኮሚቴ ላይ ኮሚቴ ተደራርቶ ጊዜና ገንዘብ ሲባክን ስታይ ለምን ብለህ ጠይቅ። ምላሹ የሕይወት ጥቁር ገብያ ውጤት ነው። ማንነት ቀውስ የፈጠረው ጥቁር ገብያ። ገንዘብም፣ ስልጣንም፣ አንሶላም ሁሉንም ቢያግበሰብሱት የማይረካ ማንነት። ሰላም ሂድ።”
ድንገተኛው ሰው በድንገት እንደመጣ በድንገት ተሰወረ። ገጣሚው ከድንገተኛው ሰው ጋር ያሳለፈው ጊዜ ሙሉ ትኩረቱን ስለወሰደው ለአፍታ ከራሱ ጋር በዝምታ ውስጥ ቆየ። ሕይወት በጥቁር ገብያን ማሰብ ጀመረ። ምን አይነት አገላለጽ ነው ሲል በድንገተኛው ሰው ተገረመ። እያንዳንዱን ግጥም በጻፈ ጊዜ ምን ትርጉም ይሰጥ ይሆን እያለ ቃላትን እየመረጠ፤ የጠነከረውን እያለዘበ ለመጻፍ ያደረገውን ጥረት አስታውሶ ራሱን የጥቁር ገብያው አካል አድርጎም ቆጠረ። እንደ ማህበረሰብ እውነትን ተነጋግሮ ሰውን ከማዳን እየተሞጋገስን ወደ ጨለማው በጋራ እየሄድን መሆናችንን አሰበ። ሞተሩን አስነስቶ ስለ ሕይወት ሀሁ የጻፈውን ግጥም እያብሰለሰለ ጉዞውን ጀመረ። ጉዞውን ቀጠለ!
የሕይወት ሀሁ
የሕይወት ሀሁ በውሳኔያችን ውስጥ አለ። ውሳኔ በእያንዳንዱ ቅጽበት ውስጥ በሕይወታችን ውስጥ ይከናወናል። በቀን ውስጥ የምናደርገው አጠቃላይ ድርጊት በአማካይ ከ35ሺ በላይ ውሳኔዎችን እየወሰንን እንድውል ያደርጋል። በቀን ውስጥ የሚያልፈው እያንዳንዱ ውሳኔ በድምር ውጤት እንዴት መዳረሻችንን ይወስናል? የሚለው ጥያቄ ከግራም ከቀኝም ሙግት እየቀረበባቸው በመጓዝ ላይ ይገኛል።
በዚህ ጽሁፍ የሕይወት ሀሁን መነሻ በማድረግ ለሕይወታችን ፍሬን ማፍራት በምንችልበት መንገድ ውስጥ እንድንገኝ በማሰብ ይገለጻል። የሕይወት ሀሁ ሳንማር በምንኖረው ኑሮ ውስጥ አለ። ክፉንና ደግን በመማር አወቅነው ወይንስ ሆነን ተገኘን? ሰው በሕሊናው ውስጥ ባለው ውቅር ውስጥ መልካምነትን በመዝራት ፍሬን ያፈራ ዘንድ ይሻል። በሌላው ላይ ጡጫን ተጠቅሞ በኃይል የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ መመላለስ ለማንም ሰው ቢሆን የማይሰራ መሆኑን ሁሉም የሚረዳው ነው። እውነታው በሕይወት ሀሁ ውስጥ አለ። ከህጻን እስከ አዋቂ የሚያውቀው። የኑሮ ጉራማይሌ ግን በድርጊት ውስጥ አራባና ቆቦ እንድንሰለፍ የሚያደርግ።
የሕይወት ሀሁ ስለ መልካምና ክፉ ይነግረናል። የሕይወት ሀሁ የዘራነውን ከማጨድ አንጻር ኃላፊነት ያለብን መሆኑን ይነግረናል። ያልዘሩትን ማጨድ እንደማይቻል የገብረጉንዳን መንጋ ያስተምረናል። እንደሰው ነፍሳዊ አቅማቸው ጠንክሮ በሳይንስና ምርምር ውስጥ ያዳበሩት እውቀት ኖሮ ሳይሆን እውነታው ያ ስለሆነ ይነግሩናል። የንቦች የሕይወት ሥርዓት ውስጥ እንዲሁ የተቀመረው ትምህርት የሰውን ልጅ ከዘራኸው ውስጥ ማጨድህን አስተውል ይላል። በእንስሳት ዓለም ሆነ ከእጽዋቱ የተፈጥሮ ቀመር ውስጥ ለሰው ልጅ ሊሆን የተገባው የበዛው እውነት አለ። የሰው ልጅ በሕይወት ሀሁ ውስጥ ሊረዳው የሚገባውና ሊተገብረው የግድ የሆነ።
በሕይወት ሀሁ ውስጥ ከእኛ ዘንድ የሚገኙትን ሦስት ነጥቦችን በጨረፍታ ተመልከተን የማንነት ቀውስን በማረቅ ከጥቁር ገብያው ለመራቅ ስለመሞከር እናንሳ። ውሳኔ፤ ድርጊት፤ ውጤት!
• ውሳኔ – በሕይወት ሀሁ ውስጥ ውሳኔያችን ያለው ስፍራ ትልቅ ነው። ውሳኔን ደጋግመህ በመፈተሽ ዛሬ ያለህበትን ቦታ ታገኛለህ። በውሳኔሽ መቀነት ውስጥ ያልተቆጠረው ምንድን ነው? እናቶች ከመቀነታቸው ፈተው የቋጠሯትን ወደ መሸመት ይገባሉ። ዛሬ የሆነው እንዲሁም ነገ ልንሆን ያለነው በውሳኔያችን መቀነት ውስጥ ከቋጠርነው ሆኖ ይገኛል። ስለ ውሳኔ እውነታውን ሙሉ እናድርግ ካልን የውሳኔ መቀነቱን ከራሳችን አሳልፈን በሌሎች ላይም እናገኘዋለን። የአንድ ወጣት ሕይወት የራሱ ውሳኔ ውጤት ብቻ አድርገን ብናስብ ልንሳሳት እንችላለን። ምክንያቱም የቤተሰቡም ሆነ የማህበረሰቡ የውሳኔ ተጽእኖ በወጣቱ ላይ የተቀመጠ ስለሆነ። ውሳኔ በሕይወት ሀሁ ውስጥ ቀዳሚው ስፍራ የሚሰጠው፤ ጥራት ያለውን ውሳኔ መወሰን በመቻል ውስጥ ማደግን የሚያስተምረን ነው። ውሳኔ ብቻውን ግን ወደ የትም ሊያደርስ አይችልም፤ በድርጊት ካልታገዘ።
• ድርጊት – የጥቁር ገብያው ተዋንያኖች ግብራቸውን የለየነው በድርጊት ነው። በተቃራኒ ድርጊት ደግሞ ሊሆን የተገባው ከሚደረግበት ገብያ መድረስ እንችላለን። የለውጥ መንገድን ስናስብ ውሳኔ ቀዳሚው ሲሆን ድርጊት ተከታይ ነው። ያለ ተግባራዊ ድርጊት ሊቀየር የሚችል ነገር ነው። ደራሲው ስለ ማህበረሰብ ለውጥ ቀናዊ ቢሆን በድርጊት በብእሩ ካልገለጠው ውጤት የለውም። አገር እንድትቀየር ሌት ተቀን መሻት ቢኖር አስተዋጽኦ ከማድረግ የጎደሉ ከሆኑ እንዲሁ ጥቅም የለውም። ድርጊት ትልቁ ተናጋሪ ነው፤ ውሳኔን ተከትሎ የሚመጣ።
• ውጤት፡- የማንነት ቀውስ መነሻ ከሚሆኑ ነገሮች መካከል የውጤት ልኬት ነው። በ40ኛው የእድሜ ክፍል ላይ የሚፈጠረው ቀውስ ራስን ገምግሞ ለራስ የሚገባው ቦታ ላይ አይደለሁም ብሎ በማሰብ የሚመጣ መሆኑ ይነገራል። ዛሬ ከእጃችን ያለው ውጤት በብዙ አቅጣጫ የሚናገረው መልእክት አለው። ውጤትን መለካት አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ወደፊት ከመራመድ የሚያቆመን ከሆነ ግን አላስፈላጊ ነው። ትላንትን ልንቀይር አንችልም። በትላንት ግምገማቸውን ተስፋ ቆጥረን ወደ ጥቁር ገብያው ከመሄድ እሴታችንን ጠብቀን ሞትን መጠበቅ እርሱ ማትረፍ ነው። የማንነት ቀውስ ሰለባ የሆኑ ከውሳኔ፤ ድርጊትና ውጤት ውህደት ውስጥ ራሳቸውን ቢፈልጉ መፍትሄው ይገኛል።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014