አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ፉኩያማ ታዋቂ ከሆኑ የፖለቲካ ምሁራን መካከል ይጠቀሳሉ። የአሜሪካ መንግሥትንም በተለያየ ደረጃ ለበርካታ ዓመታት በአማካሪነት አገልግለዋል። በተለይም በውጭ ጉዳይ እና ብሄራዊ ደህንነት ዙሪያ ለበርካታ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ብዙ የማማከር ሥራ ሰርተዋል። ሰውየው በ2019 እ.ኤ.አ ሰኔ ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተውም ለምሁራን ስለ ቀጣዩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመር የሚታያቸውን ነገር ዲስኩር አሰምተዋል።
ፕሮፌሰሩ በዋነኝነት የሚታወቁት በፈረንጆቹ 1992 ባፈለቁት የፖለቲካ ፍልስፍና ነው። በወቅቱ ፉኩያማ The End of History and the Last Man በሚል ርእስ የጻፉት ጽሁፍ ብዙ ውይይት እና ክርክር ቀስቅሶ ነበር። በዚህ መጽሐፋቸው የምእራቡ ዓለም ሊበራል ዲሞክራሲ አሸናፊ መሆኑን አውጀውም ነበር።
ፉኩያማ በዚህ መጽሐፋቸው የቅዝቃዛው ጦርነት መጠናቀቅ እና የሶቭየት ህብረት መፈራረስ የሊበራል ዴሞክራሲን ድል ያረጋገጠ ነው ፤ ከአሁን በኋላ ዓለም በሙሉ በዚህ የሊበራል ዴሞክራሲ ርእዮት ሥር ስለምትወድቅ የሰው ልጅ ለዘመናት ሲያካሂደው የነበረው የፖለቲካ ርእዮት ዝግመተ ለውጥ (political evolution) እዚህ ላይ ያበቃል ብለውም ነበር። ይህ የፉኩያማ ፍልስፍና በሌሎች ምሁራን ውድቅ ለመደረግ ግን ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።
ውድቅ ካደረጉት ምሁራን መካከል ደግሞ የሀርቫርዱ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሀንቲንግተን ናቸው። እንደ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ገለጻ ከሆነ ዓለም ተጠቅልላ በሊበራል ዴሞክራሲ እግር ሥር አልወደቀችም፤ ታሪክም አልተጠናቀቀም፤ እንዲያውም የምእራቡን ስልጣኔ የበላይነት የሚቃወሙ ሌሎች ስልጣኔዎች (civilizations) ይፈጠራሉ ብለው ነበር። በቀጣይ በዓለም የሚደረጉ ውጊያዎች በሁለት አገራት መካከል የሚደረግም ሳይሆን አገራት በማንነታቸው እና በሃይማኖታቸው ተቧድነው የሚያደርጉት እንደሚሆንም አመላክተው ነበር።
በፕሮፌሰር ሀንቲንግተን ገለጻ መሠረት ዓለም በቀጣይ 8 ስልጣኔዎች (civilizations) ይኖሯታል። እነሱም አንደኛ አሜሪካንን እና ሌሎች አጋሮቿን የያዘው የምእራባዊያኑ ሊበራል ዴሞክራሲያዊ ስልጣኔ፤ ሁለተኛ ደቡብ እና ማእከላዊ አሜሪካን የሚይዘው የላቲን ስልጣኔ ፤ ሶስተኛ ሩሲያን እና ምስራቃዊ አውሮፓን የሚይዘው ኦርቶዶክሳዊ ስልጣኔ፤ አራተኛ መካከለኛው ምሥራቅን ፤ ሰሜን አፍሪካን እና ሌሎች የተወሰኑ አገራትን የሚያካትተው አረባዊ ስልጣኔ ፤ አምስተኛ ከሰሀራ በታች ያሉ አገራትን የሚያካትተው አፍሪካዊ ስልጣኔ፤ ስድስተኛ ቻይናን የያዘው ሲኒክ ስልጣኔ፤ ሰባተኛ ጃፓን እና በዙሪያዋ ያሉ የምሥራቅ እስያ አገራትን የያዘው የጃፖን ስልጣኔ እንዲሁም በስምንተኛ ደረጃ ህንድን የያዘው የሂንዱ ስልጣኔ ይባላል ብለዋል።
አስገራሚው ነገር ፕሮፌሰር ሳሙኤል አብዛኛውን ዓለም አገራት በዚህ መልኩ በስምንቱ ስልጣኔዎች ውስጥ መድበው ሲያበቁ ኢትዮጵያን ግን ከየትኛውም ስልጣኔ ተለጣፊ ያልሆነች ራሷን የቻለች አገር ናት ብለዋታል።
ይህን ሁሉ ያልኩት ዛሬ ላይ ያለንበት ጦርነት እና በምእራባውያን የተከፈተብን ዘመቻ መንስኤው ምንድን ነው የሚለውን ለማስረዳት ነው። ከላይ በምሁራኑ ፍልስፍና ውስጥ ሁለት ነገሮችን እናያለን። እሱም አንደኛ ዓለም አሁን ላይ የአንድ ልእለ ሀያል ሥልጣኔ ተገዢ አለመሆኗን ነው። ሁለተኛ ኢትዮጵያ በራሳቸው በምእራባውያኑ አይን እንኳን እንደ ሌላው አገር የማትታይ መሆኗን ነው። እንደ ሌላው አገር የማትታይ ከሆነ ታዲያ እንደምንድን ነው የምታትታየው ይህን ለመረዳት አሁን የሚደረግብንን ጫና ይፋዊ ምክንያት ሳይሆን ድብቅ ምክንያቱን መረዳት ይጠቅማል።
አሁን የሚደረግብን ጫና በስም ደረጃ የሰብዓዊ መብት ለማስከበር እና ሠላም ለማስፈን የሚደረግ ጫና ነው። ይህን የምእራባውያን የሰብዓዊ መብት እና ሠላም ዘብነት ትርክት የለየለት ቅጥፈት እንደሆነ ማንም ያውቃል። ኢትዮጵያውያንም ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ይህን አረጋግጠዋል። በሌላ መልኩ አሁን በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና በፖለቲካዊ መነጽር ሲታይ ደግሞ ምእራባውያኑ በአፍሪካ ቀንድ ሁነኛ አጋራቸው የነበረ መንግሥትን እና በፖለቲካም ሆነ በሚሊተሪ እይታ ስትራቴጂካዊነቷ ወሳኝ የሆነችን አገርን ላለማጣት የሚደረግ ትንቅንቅ ነው። አሁንም በጥንቃቄ ዋነኛው የጫና ምክንያት ስንመለከት የምናገኘው መልስ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አተኩረን መጻህፍቶቻቸውን ስናገላብጥ የምንረዳው ነገር ቢኖር የዚህ ጫና አላማ አንድ ተዳፍኖ የነበረ እና አሁን ላይ መነቃቃት ያሳየ ስልጣኔን ስር ሳይዝ በፊት በቶሎ ለመድፈቅ የሚደረግ ጫና ነው።
በዘመነ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ነበረች። በተለይም በጸረ ሽብር ዘመቻ ስም ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ጦርነት ሁሉ የምትዋጋ አገር ነበረች። የነበረው ሥርዓት የአገሪቱ የፖሊሲ ነጻነት በዶላር መንዝሮ የሸቀጠበት ሲሆን እንዲያው በአጭሩ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ብቸኛ አዳኝነት አምና የተጠመቀች አገር ነበረች። ይህም ማለት ኢትዮጵያ የምእራቡ ስልጣኔ ተከታይ እና ጥቁር ምእራባዊ ሆና ለሩብ ክፍለ ዘመን ገደማ ቆይታ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡም ምእራባውያኑ በተለያየ መልኩ ድጋፍ በማድረግ በዘመነ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የነበራትን የኃይል አሰላለፍ እንድትቀጥል ጥረት አድርገዋል። እንዲያውም በድፍረት ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግን አድሰው በአዲስ መልኩ ኢትዮጵያን የምእራባዊው ስልጣኔ ጅራት እንደሚደርጉ በምእራባውያን ታምኖባቸው ነበር። ነገር ግን ይህ እቅድ አልተሳካም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው ኢትዮጵያ ወዳጅ እንጂ አለቃ አትፈልግም አሉ። እኛ ከማንም ጋር አንሰለፍም፤ የማንም መናጆ አይደለንም፤ ራሳችንን ችለን እንቆማለን፤ ከሚጠቅሙን እና ከሚመስሉን ጋር እንወዳጃለን አሉ። ይሄኔ የቀድሞው አለቆች ተቆጡ። ይህ ነገር ከዋለ ካደረ ችግር እንደሚያመጣ አሰቡ። ችግር የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያን ራሷን ችላ መቆም ነው። ስለዚህም ወደቀድሞ ተላላኪያቸው ፊታቸውን አዞሩ። አሸባሪው ሕወሓትን ሲመች በይፋ ካልሆነም በስልት መደገፍ ያዙ። ለቡድኑም የተሰጠው ተልእኮ አንድና አንድ ነው። ወደ ስልጣን ተመልሶ ኢትዮጵያን መዝረፍ ከዚያም ማፍረስ ነው። የአለቆች አላማ ደግሞ አንድ ነው፤ ሕወሓት ኢትዮጵያን ሲያፈርስ በፍርስራሽዋ ላይ አሰላለፉን ከነሱ ጋር ያደረገ ስልጣኔ መመስረት ነው።
አሁን ለኢትዮጵያውያን የቀረበው ምርጫ ሁለት ነው። አንድ እንደ ቀድሞው ከእኛ ጋር ተሰለፉ እና በሊበራል ዴሞክራሲ ተጠመቁ። ሁለት አንሰለፍም ካላችሁ ተበታተኑና ከአንድ ራሱን የቻለ ስልጣኔ ይልቅ ብዙ ጥቃቅን አገር ሁኑ የሚል ነው። ኢትዮጵያውያን ይህን አልተቀበሉም። መልስም ሰጥተዋል። አንደኛ ከእናንተም ሆነ ከማንም ጋር አንሰለፍም፤ ነገር ግን አክብሮን ወዳጅ ከሚሆን ጋር ብቻ እንሰራለን። ሁለተኛ የግድ መሰለፍ ካለብን የምንሰለፈው ከወንድሞቻችን አፍሪካውያን ስልጣኔ ሰልፍ ላይ ነው የሚል ነው።
ይህ የኢትዮጵያ መልስ ምእራባያኑን አበሳጭቷል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሁን የምታደርገው ነገር ዝም ከተባለ ነገ ላይ ራሷን የቻለች አንድ የዓለም ስልጣኔ ከመሆን ባለፈ የአፍሪካዊው ስልጣኔ እንዲነቃቃም ታደርጋለች የሚል ስጋት ይዟቸዋል። ስለዚህም ሳይቃጠል በቅጠል ብለው ኢትዮጵያን የመድፈቅ ዘመቻ ላይ ተሰማርተዋል።
ኢትዮጵያን መድፈቅ ከባድ ነው። በኩራዙ ላይ እንቅብ እንደመድፋት ነው። ነገር ግን ሙከራው ይቀጥላል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን ልብ ሊሉት የሚገባው ይህ የምእራባውያን ፍላጎት ድብቅ እንዳልሆነ ነው። አሜሪካ ከቻይና ጋር የያዘችው የኢኮኖሚ ጦርነት አይደለም ፤ የስልጣኔ ነው። ኔቶ ከሩሲያ ጋር የተፋጠጠው አንዳቸው ወደ ሌላቸው የተጽእኖ ክልል እያለፉ ሥልጣኔያቸውን እንዳያስፋፉ ነው። ህንድ በጸጥታው ምክር ቤት የምትደግፈን ራሷ ብቅ እያለች ያለች ስልጣኔ ስለሆነች ነው። በኢራን እና በሌሎች አረብ አገራት መካከል ያለው ልዩነት የሌላ የምንም አይደለም ፤ አረባዊውን ስልጣኔ ውስጥ የምእራባውያንን እጅ ካለመቀበል የመነጨ ነው።
የቱርክ ወደ አውሮፓ ህብረት መግባት እስካሁን የተጓተተው ቱርክ የሊበራል ዴሞክራሲ ርእዮትን በሙሉ ልቧ አምና አልቀበል ማለቷ የፈጠረው ነው። የኢትዮጵያና የአሜሪካውያን ፍጥጫም ስለ ሰብዓዊ መብት እና ሰላም አይደለም። አንድን ስልጣኔ ወደቀደመ ጉዞው ስለመመለስ እና ስላለመመለስ ነው። ምርጫችንም ግልጽ ነው። እንደ አገር ቀጥለን የራሳችንን ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ እንገነባለን ፤ የአፍሪካ ስልጣኔ እንዲያድግም እናግዛለን።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014