ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በሪሞት ኮንትሮል እየተቆጣጠሩ ያሻቸውን ለማድረግ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እየገቡ መፈትፈት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የነበረው ፈላጭ ቆራጭነት አክትሞ በህዝብ የተመረጠው አዲስ መንግሥት ሥራውን በጀመረበት ማግስት የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና እየበረታ መጥቷል።
አዲሱ መንግሥት ኢትዮጵያን በሞግዚትነት የማስተዳደር ፍላጎት የለውም። ምዕራባውያን እንዲህ አይነት እድል የሚያገኙ አለመሆኑን ሲገነዘቡ የሚፈልጉትን አሻንጉሊት መንግሥት ለማስቀመጥ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለምዕራባውያኑ የበላይነት እውቅና አለመስጠቱንና ጣልቃ አላስገባችሁም ማለቱን እንደሽንፈት የቆጠሩት የውጭ ኃይሎች ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር መወዳጀትን የመጨረሻ አማራጭ አድርገው ተቀናጅተውና ተናበው እየሠሩ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በመጣር ላይ ናቸው።
አንድ ጊዜ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ፣ ሌላ ጊዜ በሰላምና ጸጥታችን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እኛ የምንላችሁን ብቻ ተቀበሉ ማለታቸው የማንን ጥቅም ሊያስከብሩ እንደቋመጡ መረዳት አይከብድም።
ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቷ እንዳይረጋገጥ የግብጽና የሱዳንን ህገ ወጥ አቤቱታ ወደ ራሳቸው ችሎት ወስደው ፍርደ ገምድል ዳኝነት ሲሰጡ የነበረውም ለዚህ ነው።
ዛሬ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በርካታ ፈተናዎችን አልፎ በስኬት ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ በሰላማችንና በጸጥታችን ጉዳይ ገብተው ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን ሴራ በመፈጸም ላይ ናቸው።
በተለይም አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት የሀሳቧ ተገዢ ካልሆነ ፤ የባለስልጣናትን ቢዛ እንደምታግድ ፤ የብድርና እርዳታ ገንዘብን እንደምትይዝ ስታሳውቅ መሰንበቷ አይረሳም። ከሰሞኑም ኢትዮጵያ አድርጊ የተባለችውን ካላደረገች የአጎዋ ተጠቃሚነቷ እንደሚሰረዝ አሜሪካ አስጠንቅቃለች። ይህ ግን ኢትዮጵያን የሚያንበረክካት አይደለም። ክብሯ፣ ሉዓላዊነቷና ነጻነቷ ከአሜሪካ ድጎማ አይበልጡባትም።
ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለበርካታ ጊዜ ስብሰባዎችን አካሂደዋል፤ አብዛኛዎቹ ያለምንም ውሳኔ ሲቋጩ አንዳንዶቹ ላይ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። ስንትና ስንት አነጋጋሪ ዓለማቀፍ ጉዳዮችን ትተው የኢትዮጵያን ጉዳይ ዋና አጀንዳ አድርገው በየጊዜው ጫና ለማሳደር የመሞከራቸው እንቆቅልሽ ከሚገመተውም በላይ እንድናስብ ያደርገናል።
በእርዳታ ስም የገቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ሳይቀሩ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ተመሳጥረው እየሰሩ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ሲከሱ ከርመዋል። የእርዳታ እህል ጭነው ወደትግራይ ክልል የገቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች የውሃ ሽታ ሆነው ሲቀሩ ጠያቂ አለመኖሩ አስገርሞን ሳናበቃ ተሽከርካሪዎቹ የአሸባሪ ቡድኑን ታጣቂዎች ሲያጓጉዙ መመልከታችን የምዕራባውያኑ እና የአሸባሪው ቡድኑ ጋብቻ ጠንካራ መሆኑን እንረዳለን። የአሸባሪውን ወንጀል ከመደበቅ አልፈው የሳተላይት መረጃ በመስጠት እራሱን ከመንግሥት ጥቃት እንዲከላከል እየረዱት ስለመሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው ።
የተባበሩት መንግሥታትም ይሁን የአሜሪካን ልኡካን ወደ አዲስ አበባ እየተመላለሱ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ለማስቀየር ጫና ሲያደርጉ ከርመዋል። ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያደርጉት እውነታውን ባለማወቃቸው መስሎን፤ ብዙዎቻችን መረጃን የማድረስ አቅማችን እና የዲፕሎማሲ ክፍተታችን ያሳደረብን ተጽዕኖ ነው በሚል ተቆጭተናል።
ሰሞኑን በሚዲያዎች የተከፈቱትን ዘመቻዎች ስናይ ግን እውነታውን የማወቅና ኢትዮጵያን የማቅናት ፍላጎት እንደሌላቸው ፍንትው ብሎ ታይቶናል። አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንዲሉ ምዕራባውያን የሚሰሙት የሚፈልጉትን ብቻ ነው። በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ክህደት ፣ የማይካድራ፣ የጋሊኮማ ፣ የጭና ፣ የአጋምሳ፣ የቆቦ ፣ የደሴ ፣ የኮምቦልቻ ፣ የከሚሴ ጭፍጨፋዎች ለእነርሱ ምናቸውም አይደሉም።
የእነርሱን ጥቅም ለማስከበር የተቋቋሙ የሚመስሉት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ለእንዲህ አይነቱ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት የአንድ ደቂቃ ሽፋን ሲሰጡ አይታዩም። የሆነውን ትተው ያልሆነውን የሚያወሩ ናቸው። ጉዳዩን ከፖለቲካ ዓላማቸው ጋር በማያያዝ የሚጠቅማቸው መሆኑን ካመኑ ለዓለም ማህበረሰብ የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ አጋነው፤ ደጋግመው ያወራሉ። የማይጠቅማቸው ከሆነ ግን እውነታውን አፈር ያለብሱታል።
ከሰሞኑ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ዘገባ የተመለከተ ይህንኑ ይገነዘባል። የመንግሥትን ስም የሚያጠለሹና አቅሙን የሚያሳንሱ፤ የአሸባሪውን ቡድን አቅም የሚያገዝፉ ዘገባዎች ሲሰራጩ ሰንብተዋል።
በተለይም ሲ ኤን ኤን በዘገባው ‹‹ሕወሓትና ሸኔ አዲስ አበባን ከበዋል፤ የአሜሪካ መንግሥት አማጽያኑ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ አስጠነቀቀ፤ የትግራይ ተቃዋሚዎች ከአዲስ አበባ እየወጡ ናቸው።›› የሚሉ ዘገባዎችን ሁኔታውን በማይገልጹ ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች እያስደገፈ ሲያሰራጭ ታዝበናል። ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ኒዎርክ ታይምስ ፣ ፍራንስ 24 ተመሳሳይ ዘገባዎችን በማሰራጨት ዓለምን በይበልጥም በቦታው ያለነውን ኢትዮጵያውያንን አስገርመውናል።
ለነገሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀደም ሲልም በዲጂታል ወያኔ የሚሰራጩትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች ይከታተል ስለነበር የእነዚህን ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ድራማ ከተራ የፌስቡክ ወሬ ለይቶ አይመለከተውም የሚል እምነት አለኝ።
ኡጋንዳዊ ጋዜጠኛ ዳንኤል ሉቲያ በፌስ ቡክ ገጹ የጻፈውን አንድ ጉዳይ ላስታውሳችሁ። ‹‹ወደ ኢትዮጵያ በረራ ለማድረግ እየተዘጋጀሁ ሳለሁ ሲ ኤን ኤን እና ሌሎች አለማቀፍ ሚዲያዎች የሚስተላልፉትን ዘገባ ሰምቼ ወደ ጦር ቀጣና እየሄድኩ ነው የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር። ነገር ግን ሁኔታው እንደሰማሁት አይደለም። ትናንት አዲስ አበባ ነበርኩ ዛሬ ደግሞ አዳማ ነኝ ። ምንም የጥይት ድምጽ አልሰማሁም።
ሆቴሎች ክፍት ናቸው። መንገዶችም አልተዘጉም። ካምፓላ ያየሁትን የሚኒቴሪ እንቅስቃሴ ያህል አዲስ አበባ አላየሁም ›› በሚል ጽፏል። ጋዜጠኛው ዓለማቀፍ ሚዲያዎች አዲስ አበባ በታጣቂዎች ተከባለች ብለው በዘገቡ ማግስት ያየውን ነው የተናገረው። ሚዲያዎቹ በአዕምሮው የሳሉትና እርሱ በተጨባጭ ያየው እውነታ ፍጹም የማይገናኝ መሆኑን በትዝብት አስፍሯል።
ከሰሞኑ ደግሞ ታላላቅ የማህበራዊ ሚዲያ ካምፓኒዎች ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ ርምጃዎችን ሲወስዱ ተመልክተናል። ፌስ ቡክ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት እስከ ማንሳት ደርሷል። ኢትዮጵያዊያን ድምጻቸውን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማሰማት በቲውተር ዘመቻ እያደረጉ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የቲውተር ካምፓኒ ኢትዮጵያ የቲውተር አገልግሎት እንዳታገኝ አድርጓል። እንግዲህ ቅንጅቱ ምን ያህል መናበብ እንዳለው ከዚህ መረዳት ይቻላል።
ሰልጥነዋል፣ የተሻለ የዲሞክራሲ ሥርዓት ገንብተዋል፣ ስለሚዲያ ነጻነት ተአማኒነትና ገለልተኝነት የተሻለ ግንዛቤ አላቸው የምንላቸው ምዕራባውያን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ሚዲያን በዚህ ደረጃ ማዋረዳቸው አግራሞትን የሚፈጥር ነው። ኢሰብዓዊ ግፎችን ከሚፈጽም አሸባሪ ቡድን ጋር በማበር እንዲህ አይነት ወራዳ ተግባር መፈጸማቸው ሲታሰብ ስልጣኔያቸው አጠያያቂ ይሆንብናል።
በቀዳሚ የመረጃ ምንጭነታቸውና በተከታዮቻቸው ብዛት ግንባር ቀደም የሆኑ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች በምን ምክንያት በዚህ ደረጃ ወርደው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሊያሰራጩ ቻሉ ከተባለ አዲሱን የመንግሥት አስተዳደር አስወግደው የሚፈልጉትን አሻንጉሊት መንግሥት በማስቀመጥ በኢትዮጵያም ይሁን በቀጣናው የሚፈልጉትን ጥቅም ማስጠበቅ ስለፈለጉ ነው የሚለው መደምደሚያ ያስማማናል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቹ በሚያሰራጩት ሀሰተኛ ወሬ የምታሸበርክ ቢሆን ኖሮ በዚህ አንድ ዓመት የተከፈተባት ዘመቻ ይበቃ ነበር። ዓላማቸው በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም በሚገኘው ኢትዮጵያዊ ላይ የስነ ልቦና ጦርነት በመክፈት ተስፋ ማስቆረጥ ነው። ከአንድ ሚዲያ የሚጠበቀው የተዓማኒነትና የገለልተኝነት ጉዳይ አያሳስባቸውም። ዋና ትኩረታቸው የምዕራባውያኑን አጀንዳ ማስፈጸም ነው። ለዚህ ነው ግዴለሽ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚያሰራጩት በሬ ወለደ አይነት ኢተአማኒ ዜና የሚያቀርቡት።
እኛ ኢትዮጵያውን እንኳንስ በወሬ በጦርነትም የማንንበረከክ መሆናችንን በተግባር ያሳየን ነን። ዛሬ በሀገር ውስጥ ዲጂታል ወያኔ በውጭ አለማቀፍ ሚዲያዎች የስነ ልቦና ጦርነት ከፍተውብናል። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚለውን የአበው አባባል እያስታወስን ለሚሰራጨው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ሳንሰጥ ሀገራችንን ከውጭ ኃይሎችና ከባንዳዎች ልንታደጋት ይገባል።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/2014