የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት በቅርቡ በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሩ የሚታወስ ነው። ከነዚህ መካከል – ኢትዮጵያን በቱሪስት አስጎብኚዎች ዕይታ” በሚል ርዕስ የፎቶ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሙዚየም አካሂዶ ነበር። የዝግጅት ክፍላችን የማህበር ምስረታ፣ አላማውንና በአሁኑ ወቅት በዘርፉ እየሰሩ ያሉትን ተግባራት አስመልክቶ ከ15 ዓመታት በላይ በዘርፉ በፕሮፌሽናል አስጎብኚነት ከሰሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ካሳ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበርን ከመሰረታችሁ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ? ምን አይነት አላማ ራእይ ሰንቃችኋል?
አቶ አሸናፊ፦ ምስረታውን ከአንድ ዓመት በፊት ነው የፈፀምነው። ሁላችንም በፕሮፌሽናል ደረጃ በትምህርት የታገዝን አስጎብኚዎች ነን። ማህበሩን ስንመሰርት እንደ ራዕይ ይዘን የተነሳነው በቱሪዝም ዘርፍ ዓለም አቀፍ ደረጃን የያዘ “የአስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር” እንዲሆን ነው። ይሄ ዋነኛው ሲሆን በርካታ አላማዎችን የያዘም ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በጋራ የአስጎብኚዎችን መብቶች ከማስጠበቅ ጀምሮ ግዴታዎች ለመወጣት፣ እውቀት ለመገበያየት እንዲሁም በህብረት ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ለመስራት በማሰብ ነው ያቋቋምነው። በተጨማሪ ከእኛ የሚፈለገውን ግብአት ለመንግሥትም ሆነ ለፖሊሲ አውጪዎች በተደራጀ መልኩ ለማድረስ በማሰብ ነው።
አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓላችንን ስናከብርም እንዲሁ ተሰባስቦ ከመበታተን ይልቅ “ኢትዮጵያ በአስጎብኚ ባለሙያዎች” እይታ ምን እንደምትመስል ለማሳየት ፣ በሰላምና በኮሮና ወረርሽኝ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ፍሰት ለማነቃቃት አስበን የተለያዩ የመስህብ ቦታዎችን የሚያሳዩ “የፎቶ አውደ ርዕይ” በብሄራዊ ሙዚየም አሳይተናል። በቀጣይም መሰል የቱሪዝሙ ዘርፍ የሚያነቃቁና አያሌ የተግባር ስራዎችን የመስራት እቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። የማህበራችን ምስረታ አስፈላጊነትም ከእነዚህ ቁልፍ ተግባራት የመነጨ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የቱሪዝም አስጎብኚዎች የቱሪስቱን ቆይታ ከማራዘምና ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረግ አንፃር ላቅ ያለ ሚና አላቸው። እንደ ማህበር ይህን ድርሻ ባለሙያው እንዲወጣ ምን ትሰራላችሁ?
አቶ አሸናፊ፦ እውነት ነው የአስጎብኚው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህን ድርሻውን መወጣት ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የመስህብ ስፍራዎች በሚገባ ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል። ይህን ሲያውቅ ለቱሪስቱ አማራጮችን ማሳየት ይችላል። ስለዚህ የኛ ማህበር ባለሙያው ያለውን እውቀት እንዲያዳብርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተለያዩ የስልጠና መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በዚህ በአንድ አመት ውስጥ ሲሰጥ ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪ “የካምፕ ጉብኝቶች”ን በማዘጋጀት አስጎብኚው በቀጥታ ስፍራዎችን አስቀድሞ የሚያይበትን ሁኔታ እናመቻቻለን። በዚህም በእውቀት፣ በስነ ምግባር እንዲሁም በአመለካከት ብቁ እንዲሆን የማድረግ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መሥራት ችለናል።
አዲስ ዘመን፦ ማህበራችሁ የአስጎብኚዎችን ሙያዊ ብቃትና ዘርፉ ከሚፈልገው አንፃር እንዴት ይገመግመዋል?
አቶ አሸናፊ፦ ቱሪስቶችን ለመሳብ ከሚሰራው የፕሮሞሽንና የገበያ ልማት በላይ የአገር ገፅታን የሚገነባውና በቀጥታ ከቱሪስቱ ጋር የሚገናኘው አስጎብኚው ነው። እንግዳውን ከመቀበል አንስቶ ከማህበረሰቡ ጋር አቀላቅሎ የሚፈልገውን የመስህብ ስፍራ አስጎብኝቶ መልሶ የሚሸኘው ይሄው አስጎብኚው ነው። ስለዚህ አስጎብኚው የአገር አምባሳደር ነው። ስለዚህ አስጎብኚው የአገር አምባሳደር ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም እንደ ማህበር እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በዘርፉ በትምህርትና ስልጠና ብቁ የሆነ ሙያተኛ ከህጋዊ አካል ፍቃድ ያለው ብቻ ነው የማህበራችን አባል የሚሆነው። ስለዚህ ማንኛውም አካል ቋንቋ ስለቻለ ብቻ ሳይሆን ዘርፉ በሚፈልገው የትምህርት መስክ ተፈትኖ ማለፍ ይኖርበታል። እኛም ይሄ እንዲሆን እየታገልን ነው። በሥራችን ያሉ ባለሙያዎችም አንድ አይነት ባይሆንም ተመጣጣኝ የእውቀት ደረጃ ላይ እንዲገኙ እየሠራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፦ የሙያ ግዴታቸውን እየተወጡ የሚገኙ የማህበራችሁ አባላት የመስህብ ስፍራዎችን ለማስጎብኘት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ምን አይነት ችግር ይገጥማቸዋል?
አቶ አሸናፊ፦ ሙያዊ ግዴታችንን ስንወጣ በርካታ ችግሮች ያጋጥሙናል። እዚህ ጋር ሁሉንም ዘርዝሮ ማንሳት የሚከብድ ይመስለኛል። ሆኖም ግን ዋንኛ ችግራችን ከሆኑት መካከል አንዱን መጥቀስ እፈልጋለሁ። እርሱም ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኚዎችን ይዘን በምንንቀሳቀስበት ወቅት ከክልሎች አሰራር ጋር በተያያዘ ወጥ የሆነ አሰራር አይገጥመንም። ይሄ ለስራችን እንቅፋት ይሆናል። በእርግጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያለው አቀባበልና ቢሮክራሲን የሚቃወም የአሰራር ስርዓት አለ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ግዜ ይህን መሰል ችግር ይገጥመናል። ሌላው በቀጥታ ለሙያዊ ብቃት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑና በዚህ ዘርፍ ላይ ልምዱም እውቀቱም ያላቸውን አካላት የሚደግፍ የአሰራር ስርዓትና ምቹ ሁኔታ አለመኖሩ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረትና የአደረጃጀት ለውጥ ተከትሎ ለውጦች ይመጣሉ ብለን እናምናለን። በተለይ ሙያተኛው በቀጥታ በዘርፉ ላይ እንዲገባና ለቱሪዝም እድገት የድርሻውን እንዲወጣ የመግቢያ ሜዳው ክፍት መሆን አለበት እንላለን። ለዚህም አሳሪ የሆኑ ህጎችና የአሰራር ስርዓቶች ይሻሻላሉ የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፦ አስጎብኚው አብዛኛውን ጊዜ ከውጪ የሚመጣ ቱሪስት በመጠበቅ ላይ የተመሰረተ ነው በሚል ይታማል። ይህን ችግር ለመቅረፍና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን እንዲበዙ እናንተ እንደ ማህበር ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ አሸናፊ፦ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማበረታታት አንፃር ተሳትፏችን በጣም የላላና ምንም አልተሰራም በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው። ይህን በመገንዘብም ነው እንደ ማህበር ምስረታችንን በማስመልከት የፎቶግራፍ አውደ ርእይ ያዘጋጀነው። በዚህ ዝግጅት ላይ የውጪ ጎብኚዎችን ሳይሆን የአገር ውስጥ ዜጎችን ለመሳብ በማቀድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በቅርብ እርቀቶች ላይ በሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለምሳሌ “የጀልባ ላይ ቀዘፋ” (ራፍቲንግ)፣ የተራራ ላይ ጉዞ፣ የፓርኮች ጉብኝት እንዲሁም መሰል መስህቦችን የአገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲሳተፉበት እቅድ ነድፈን እየሰራን ነው። በተለይ በ”ራፍቲንግ” መስክ ኢትዮጵያውያን ያሳተፈ ስኬታማ የጀልባ ላይ ጉዞ ጉብኝቶችን አድርገናል ወደፊትም በተመሳሳይ እንሰራለን። በተለይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲበረክቱና ዘርፉ እንዲነቃቃ የመሪነቱን ድርሻ ለመወጣት በርካታ እቅዶችና የትግበራ መርሃ ግብሮች አሉን።
በዋናነት ግን እስካሁን የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዳይስፋፋ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት የፖሊሲ ችግር እንደሆነ አምናለሁ። ምክንያቱም አንድ አስጎብኚ በአመት 25 ሺ ዶላር ካመጣ እውቅና ወይም (ሰርተፍኬት) እንደሚያገኝ ህጉ ያስቀምጣል። ይሄ ህግ ደግሞ አስጎብኚዎች ትኩረታቸውን የውጪ ዜጋ ላይ እንዲያደርጉና የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲዳከም አድርጎታል ብዬ አምናለሁ። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ አቅም ያላቸው የአገራቸውን መስህብ መመልከትና ማወቅ የሚሹ ዜጎች ስላሉ እነሱ ላይ ቢሰራ፤ በተለይ ማነቆ የሆኑ ህጎች ቢሻሻሉ ስኬታማ መሆን ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ የመስህብ ስፍራዎች በግንዛቤ እጥረትም ሆነ በተለያየ ምክንያት ከሚደርስባቸው ጉዳት እንዲጠበቁ እንደ አንድ ባለድርሻ አካላት ምን ትሰራላችሁ?
አቶ አሸናፊ፦ የመስህብ ስፍራዎች በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ለዘላቂው ጉዳት እንዳይደርስባቸው መስራት ተገቢ ነው። በዋናነት ከቱሪዝም ሙያ መርሆዎች አንዱ “ግንዛቤ” ነው። ለጎብኚውም ሆነ በመዳረሻ ስፍራው አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎች መስህብ ስፍራው በቸልተኝነት ጉዳት እንዳይደርስበት ማስተማር፣ ማሳወቅና ጠቀሜታውን ማሳየት ያስፈልጋል። በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ አኳያ እየተሰራ ያለው ሥራ ደካማ ነው። የእኛ ማህበርም ከዚህ አንፃር በሰው ኃይል ልማት ላይ በመስራት የአመለካከትና ችሎታው እንዲዳብር በማድረግ እታች ድረስ ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው። ከዚህ ቀደም በአፋር ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር “እናፅዳ” የሚል ንቅናቄ በማድረግ የፓርኮችን አካባቢ ፅዳት ለመጠበቅ ስራዎችን ሰርተናል። በቅርቡ ደግሞ ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ በሁሉም በሮች ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት አቅደናል። ይሄ በቀጣይ በስፋት የመስህብ ቦታዎችን ለመጠበቅና ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሰራውን ሥራ የሚደግፍና እንደ መነሻ መሰረት የሚሆነን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻ ላይ ማንሳት የሚፈልጉት አሊያም ቢታሰብበት የሚሉት መልእክት ማንሳት ይችላሉ።
አቶ አሸናፊ፦ እንደሚታወቀው አሁን ላይ በኮሮና ወረርሽኝ እና በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት አስጎብኚው (ቱር ጋይዱ) ገቢው በእጅጉ ተቀዛቅዟል። በዚህ ምክንያት ከኢኮኖሚው ችግር ባለፈ ወደ ማህበራዊ ቀውስ ደረጃ እየደረሰ ነው። መንግሥት ይሄን አስከትሎ የጀመረው ድጋፍ ነበር። በተፈጠረው እድልም ጥቂት የማህበራችን አባላት ብቻ ተጠቃሚ ቢሆኑም አብዛኛው ግን ይህን እድል አላገኘም። ይህን መሰል ድጋፍ ችግሩ እስኪቃለል ቀጣይነት ቢኖረው በዘላቂነት መፍታት ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም በቀጣይ የቱሪዝም ፍሰቱ ሲረጋጋ ይሄው አሁን የታገዘው ባለሙያን ነው የሚያገለግለው። ካላገዝነው ግን በቀጣይ ሙያዊ ግልጋሎቱን ስንፈልግ በቦታው ላናገኘው እንችላለን። ስለዚህ ይሄን መንግሥት በትኩረት ሊያስብበት ይገባል።
በሁለተኛ ደረጃ ቱሪዝም ዘርፉ ላይ በጣም ተስፋ ጥለንበታል። በአዲሱ አወቃቀር መሰረት ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲካተት ተደርጓል። ይሄ አስደሳች ነው። ምክንያቱም ትኩረቱ ከፍ እንዲል ያደርገዋል። ሆኖም ግን በትግበራው ወቅት በተለመደው አካሄድ መሄድ አስፈላጊ አይደለም ለማለት እወዳለሁ። በተለይ የአመራር ምደባና የሰው ሃይል ልማት ላይ ጥንቃቄ ተደርጎ መሰራት አለበት። እውቀቱና ቀጥተኛ ብቃት ያላቸው ሰዎች የረጅም ዓመት የስራ ልምድ ባይኖራቸው እንኳን በቀናነት አስጠግቶ አብሮ መስራት ይገባል። ይህ ከተደረገ የቱሪዝም ዘርፉን ተስፋ እንዳደረግንበት በፍጥነት ለውጥ እናይበታለን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ጊዜዎትን ሰጥተው ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን።
አቶ አሸናፊ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም