የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት ከተፈጠሩ ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችን ያለምንም ማመንታት በዓለም ሀገራት ላይ ለመጫን የሚን ደረደሩት ለምን ይሆን? የሚለውን ምስጢር ለማወቅ በቅድሚያ የአውሮፓ ኅብረትን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማን፣ ለምን ፣ መቼ ፣ እንዴት ተፈጠሩ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እነኝህን ቁልፍ ጥያቄዎች መመለስ የሚችል ማንኛውም ሰው የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለአሜሪካ ያደሩበትን ምስጢር በቀላሉ መገንዘብ ይችላሉ፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት በማን፣ ለምን ፣ መቼ፣ እንዴት ተፈጠረ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማን፣ ለምን፣ መቼ ፣ እንዴት ተፈጠረ? የሚለውን አንድ በአንድ ከተመለከተን የመንግሥታቱ ድርጅት ለምን ለአሜሪካ የእጅ አዙር ፖሊሲ አስፈጻሚ ሆነ የሚለውን በቀላሉ እንድንገነዘብ ያስችለናል። በቀጥታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማን፣ ለምን ፣ መቼ ፣ እንዴት ተፈጠረ? የሚለውን ከማየታችን በፊት ግን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የሚመሳሰለውን የመጀመሪያውን የዓለም ማህበር /ሊግ ኦፍ ኔሽን/ (League of Nation) አፈጣጠር እና ውድቀት በወፍ በረር ማየቱ ስለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚኖረን እይታ ስለሚያሰፋ እንዴት እንደተመሰረተ እና አሰራሩ ምን ይመስል እንደነበር በትንሹ እንመልከት።
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የዓለምን ሁለንተናዊ ሰላም እና እድገትን ለማረጋገጥ በሚል ምክንያት የዓለም ማህበር (League of Nation) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተባሉ ሁለት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መመሥረታቸው ይታወቃል፡፡ በ1920 ዓ.ም የተፈጠረው የዓለም ማህበር (League of Nation) በአንደኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ በነበሩ ሀገራት ማለትም ኢንተንት ፓወርስ (Entente Powers) ሃሳብ አመንጭነት የተፈጠረ ነው። በ1945 ዓ.ም የተፈጠረውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም እንዲሁ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች ሃሳብ አመንጭነት እና የበላይነት የተፈጠረ ነው ፡፡
እ.ኤ.አ በ1920 ዓ.ም ለተፈጠረው የዓለም ማህበር (League of Nation) መመስረት በሃሳብ አመንጭነት ቁልፍ ሚና የተጫወቱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን እና የብርታኒያው ውጭ ጉዳይ ጸሐፊ ኢድዋር ግሬይ ናቸው፡፡
የዓለም ማህበር ( League of Nation) ሲመሰረት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን ከማንም በላይ ጉልህ ሚና የነበራቸው ቢሆንም አሜሪካ ግን የዓለም ማህበር ( League of Nation) አባል ሀገር አልነበረችም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ፕሬዚዳንቱ ሀገራቸው አሜሪካ የዓለም ማህበር አባል ሀገር እንድትሆን ለአሜሪካው እንደራሴ ምክር ቤት ያቀረቡትን ጥየቄ በምክር ቤቱ ውድቅ በመደረጉ ነበር።
በአሜሪካ እና ብሪታኒያ ሃሳብ አመንጭነት የተፈጠው የዓለም ማህበር (League of Nation) ለምስረታው እንደምክንያት የተጠቀሰው የዓለምን ሰላም እና እድገት እውን ማድረግ በሚል ሽፋን ነው፡፡ እውነታው ግን በአንደኛው የዓለም ጦርነት በተሸናፊዎች ጎራ የተገኙትን ጀርመንን፣ ኦስትሪያን፣ ኦቶማን ቱርክን እና ሌሎች የሴንትራል ፓወርስ (Central Powers ) አባል ሀገራትን እግር ከወርች በማሰር እና በአንደኛው የዓለም ጦርነት ድል ለቀናቸው የአላይድ ፓወርስ (Allied powers) ደግሞ በጦርነቱ ያወጡትን ወጪ እንዲከፍሉ ለማስገደድ ነው። በተለይም ጀርመን፣ ኦስትሪያ እና ኦቶማን ቱርክ ኢፓየር ግዛቶችን ደግሞ ለአሸነፊዎች በቅርጫነት ያቀረበውን የቨርሳይል ስምምነት( Treaty of Versailles) ለማስፈጸም ነበር።
የቨርሳይል ስምምነት( Treaty of Versailles) ጀርመን በአውሮፓ የነበሯትን ግዛቶችን ከመቀራመት ባለፈ 6 ቢሊዮን 6 መቶ ሚሊዮን የጦርነት ካሳ እንድትከፍል ፣ የጦር ኃይሏም ከአንድ መቶ ሺህ እንዳይበልጥ እና ከባድ መሳሪዎችን እንዳትታጠቅ የሚከለክል ነው፡፡ የዓለም ማህበርም (League of Nation) በአድሎ የተለወሰውን የቨርሳይል ስምምነት (Treaty of Versailles) የሚያስፈጽም አድሎ የተሞላበት ድርጅት እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
የኋላ ኋላ ነገሮች ተቀይረው ጀርመን ፋሽስት ጣሊያን እና ጃፓንን ከኋላ በማሰለፍ ለዓለም ስጋት ሆና ተከሰተች፡፡ ነገር ግን የዓለም ማህበር (League of Nation) መስራች ኃያላን ሀገራት ራሳቸው ስላልተነኩ ብቻ ብዛት ያላቸው የዓለም ሀገርት በፋሽስት ጣሊያን ፣ ናዚ ጀርመን እና ጃፓን የጥፋት ቡድን ለከፍተኛ ችግር ሲጋለጡ ቢመለከቱም በጀርመን እና ተከታዮቿ ላይ ምንም እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ፡፡ ይልቁንም የዓለም ማህበር (League of Nation) መስራች ኃያላን ሀገራት «የማባበል ፖሊሲ» (Appeasement policy) በመከተል ጀርመንን እና ተባባሪዎቿን ማባበል ያዙ፡፡
ለምሳሌ ብቸኛዋ በቅኝ ግዛት ያልተያዘቸው አፍሪካዊቷ የዓለም ማህበር (League of Nation) አባል ሀገር ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረች ጊዜ ኢትዮጵያ በእውነት ለዓለም ሰላም የቆመ ማህበር ያለ መስሏት ጣሊያን ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ስትል ለዓለም ማህበር አመለከተች፡፡ የአባል ሀገራቱም የኢትዮጵያን ቁስል እንደምንም ባለመቁጠር በኢትየጵያ ጥያቄ ላይ አፌዙ፡፡ ይልቁንም «በድሎ ካሱኝ እሾህ ይዞ እጄን ዳብሱኝ » እንዲሉ ጣሊያን በወልወል በኩል ኢትዮጵያን በወረርኩ ጊዜ ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ወታደሮች ተገድለውብኛል ስትል አቤቱታ አቀረበች። ጣሊያንን የፈሩት የዓለም ማህበር ኃያላን ሀገራት ኢትዮጵያ ለጣሊያን ካሳ እንድትከፍል የሚል ውሳኔ ለማስተላለፍም ዳድቷቸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡
ጃፓን ማንቹሪያ የተሰኘውን የቻይና ግዛት ስትወር እና ጀርመን በርካታ የአውሮፓ ሀገራትን በማን አለብኝነት በወረራ ስትይዝ በእነብሪታኒያ የበላይነት ይመራ የነበረው የዓለም ማህበር ለእነብሪታኒያ ደህንነት በመስጋት በወራሪ ሀገራቱ ላይ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ፡፡“ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ እንኳንስ እርምጃ መውሰድ ይቅርና ለጉዳዩ አንድም ነገር ትንፍሽ ለማለት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀሩ፡፡ እያዩ እንዳላዩ ሆነው አለፉት፡፡
በአጠቃላይ በ1920ዓ.ም የተፈጠረው የዓለም ማህበር (League of Nation) ለአንድ ወገን ያደላ እና መርጦ አልቃሽ በመሆኑ ከተወለደ ሁለት አሥርት ዓመታትን መቆየት እንኳን ሳይችል ፈራርሶ ለመ ቀበር በቅቷል፡፡
ሌላው በአሸናፊዎች የተመሰረተው ድርጅት ደግሞ የተበባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው ፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የተበባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዴት ፣ በማን ፣ ለምን እንደተፈጠረ የሚገነዘብ ማንም ሰው ስለምን ድርጅቱ ለአሜሪካ እና ጭፍራዎቿ የእጅ አዙር የሥራ አስፈጻሚነት አሽከር እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡
የተበባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዴት፣ በማን፣ ለምን ተፈጠረ ? ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት አሜሪካ ራሷን ከዓለማቀፋዊ ጉዳዮች የመነጠል ፖሊሲ ( Isolation policy ) ትከተል ነበር። ነገር ግን ይህ ፖሊሲዋ ሌሎች ሀገራት በአሜሪካ ላይ ከሚያደርሱት ጥቃቶች ሊያተርፏት አልቻለም። ይህን የተረዳችው አሜሪካ ራሷን በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከመነጠል ይልቅ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ማድረግን መርጣለች፡፡ ይህንን ውሳኔዋን እውን ለማድረግም ሁለት ነገሮች እድል ፈጥረውላታል፡፡
አንደኛው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ እና በጦርነቱ ወቅት የዓለም ሀገራት በሁለት ጎራ ተከፍለው ወደ ለየለት ጦርነት በገቡበት ወቅት አሜሪካ የእርሻ እና የኢንዱስትሪ ውጤቷን ለተፋላሚ ወገኖች በመሸጥ በሀብት ላይ ሀብት መገንባት መቻሏ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1928 እስከ 1945 ባለው ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ ጠቅላላ ብሄራዊ ምርት (Gross National Product) ከ91 ቢሊዮን ዶላር ወደ 213 ቢሊዮን ዶላር ማደግ ችሏል፡፡
ይህም ጠቅላላ ብሔራዊ ምርቷ የብሪታኒያ ዜጎች ከሚያገኙት በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ፤የሩሲያ ዜጎች ከሚያገኙት ደግሞ በሰባት እጥፍ የሚልቅ ነበር፡፡ ይህ የአሜሪካ የኢኮኖሚ እድገት አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት በምትፈልገው መንገድ ለመጠምዘዝ እንድትችል የተሻለ እድል ፈጥሮላታል፡፡
አሜሪካ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንድትችል በር የከፈተው ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፈጠር ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከአንድ ጎራ የተሰለፉት አሜሪካ እና ብሪታኒያ ከእነሱ በተቃራኒ የቆሙትን የበርሊን ፣ ሮም ፣ቶኪዮ ጥምረት እየተሸነፉ መምጣታቻውን ተከትሎ የማታ ማታ ድሉ የአላይድ (Allied Powers) ፓወርስ መሆኑን ሲረዱ በ1941 እኤአ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሮስቬልት ጋር በካናዳ አትላንቲክ ኮስት ላይ በምስጢር ስብሰባ በማድረግ አንድ ዓለማቀፋዊ ድርጅት መመስረት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም ስለጉዳዩ ቀደም ብለው እንዳሰቡበት፤ ወደፊት ግን እንደሚያስቡበት ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ነግረዋቸው ቢለያዩም ከሁለት ዓመት በኋላ በ1943 በኢራኗ መዲና ቴህራን ከብሪታኒያ እና አሜሪካ በተጨማሪ ራሽያ ተገኝታ ሊመሰረቱት ስላሰቡት የዓለም አቀፍ ድርጅት ጉዳይ መከሩ፡፡ ቀጥለውም ”የልታ ኮንፈረስ” በተሰኘው ኮንፈረንስ ሦስቱ ሀገራት ስለ ድምጽን በድምጽ መሻር (Veto power ) እንዲኖራቸው በሚያስችል ጉዳይ ላይ መከሩ፡፡ የመከሩትንም ለመፈጸም የዓለም አቀፍ ድርጅት መሰረቱ፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህም እንዴት አሜሪካ እና ብሪታኒያ ጠላታቸውን ሩሲያን ድምጽን በድምጽ መሻር (Veto power ) እንዲኖራት ፈለጉ? የሚል ነው፡፡ ለዚህም መልሱ ቀላል ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርት የዓለም ሀገራት በሁለት ጎራዎች ተከፋፍለው ሲቧቀሱ እነኝህ ሦስት ሀገራት አፋችንን አጋጥመን በአንድ አፍንጫ እንተንፍስ የሚሉ ወዳጆች ነበሩ፡፡ የአሁኑ ጸባቸው ግን የተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመስረት በኋላ አሜሪካ እና ሩሲያ በፈጠሯቸው “እኔ እበልጥ፤ እኔ እበልጥ” በሚል የኢኮኖሚ ርእዮተ ዓለም እሽቅድምድም መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የተባባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ መጀመሪያው የዓለም ማህበር(League of Nation) በብሪታኒያ እና በአሜሪካ ተረግዞ በብሪታኒያ እና በአሜሪካ የፖለቲካ ዶክተሮች ቀዶ ጥገና የተወለደ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ማለት የድርጅቱ ፈጣሪዎች ከዓለም ሕግጋት ጋር የተጣረሰ የትኛውንም አይነት እርምጃ ቢወስዱ የመንግሥታቱ ድርጅት የፈጣሪዎቹን ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚቃረን አንድም ነገር ትንፍሽ አይልም፡፡ ለምን? የመንግሥታቱ ድርጅት ፈጣሪዎቹን ብሪታኒያ እና አሜሪካ ላለማስከፋት ሲል ለዚህ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሕግ ተገን አድርጋ አያሌ ሀገራትን እንዳልሆኑ አድርጋ በማበጣበጥ ሊወጡት ወደማይችሉት የችግር አረንቋ ከታለች፡፡ ለምሳሌ ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ ለምን ተለያዩ? በማንስ ተለያዩ? በቬትናም ጦርነትስ ቬትናምን ሰሜን እና ደቡብ ብሎ በመከፋፈል እርስ በርስ ማን አባላቸው? ፓትሪስ ሉምባን በመግደል የበፊቷን ዛየር የአሁኗን ኮንጎ ማን ከፋፍሎ እርስ በርስ እያጨረሳቸው ነው ? በተባበሩት ስም በኢትዮጵያ፣ በሊቢያ ፣ በሶሪያ እና በሌሎችም ሀገራት የውስጥ ጉዳይ በመግባት ዜጎችን እያባላች ያለች ሀገር ማን ናት? የሚለው አሜሪካ እና ጭራዎቿ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢያውቅም አሜሪካ እና ጭራዎቿን ከእኩይ ተግባራቸው ለማስቀም አንድም ቀን ምንም ነገር ሲል አልታየም ፡፡ ይልቁንም የአሜሪካ እና ጭራዎቿን የጥፋት ሴራ ለመሸፋፈን መጋጋጥን ሁነኛ የቤት ሥራው እንዳደረገው በአደባባይ እየታየ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በስድስት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ ከእነኝህም መካከል አንደኛው የጸጥታው ምክር ቤት እየተባለ የሚጠራው ነው። ይህ ክፍል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካሉት ክፍሎች ከፍተኛውን ሥልጣን የያዘው ነው። አዲስ የጠቅላላ ጉባኤ (General Assembly ) አባል መሆን የሚፈልጉ ሀገራትን በመገምገም ወደ ድርጅቱ እንዲገቡ ከመፍቀድ ጀምሮ ድምጽን በድምጽ መሻር (Veto power) ስልጣን ያላቸው ሀገራት የያዘ ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በእጩነት የሚያቀርብ ፣ የዓለም ባንክ ፣ አይ ኤም ኤፍ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) የመሳሰሉ አካላትን ለምርጫ በእጩነት የሚያቀርብ ፤ በሀገራት ማእቀብ የሚጣለውም በዚህ ክፍል ነው፡፡
እዚህ ላይ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ዋና ጸሐፊውን ጨምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚገኝ እያንዳንዱ መዋቅር የአሜሪካ ሥራ አስፈጻሚ አሽከር መሆናቸውን ነው ፡፡
እያንዳንዱ የመንግሥታቱ ድርጅት ክፍሎች በአሜሪካ ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ በተመሰረተው የተባበሩት መንግሥታት እጩነት የሚቀርቡ ከሆነ ምን ያህል ከእነ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ተጽዕኖ ስር ናቸው የሚለውን ለማየት የሩቁን ትተን የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ በኢትዮጰያ ላይ እየፈጸሙት ያለውን ተግባር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
በተለይ በጸጥታው ምክር ቤት (Security Council) ስም በአሜሪካ የሚሽከረከሩ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፣ የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) የመሳሰሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት በትግራይ ብቻ ርሃብ እና መፈናቀል ያለ ይመስል ትግራይን ብቻ እየረዱ በአማራ እና በአፋር ክልል ያለውን መፈናቀል እና ርሃብ እንዳላዩ ማየትን መርጠው ያለቅሳሉ፡፡
የአፋር እና የአማራ ህዝብ በትግሬ ወራሪ ኃይል ሲጨፈጨፍ እና ከመኖሪያ ቀየው ሲሰደድ እያዩ አሜሪካ እና አሽከሮቿ ማውገዝ ሲገባቸው የዓለም ሕግጋትን አክብሮ በመንቀሳቀስ ዜጎቹን ከትግራይ ወራሪ ኃይል ጥፋት ለማታደግ ደፋ ቀና የሚለውን የኢትዮጵያ መንግሥትን በሀሰት በመወንጀል ሀገሪቱን ለትግራይ ወራሪ ኃይል ለማስረከብ እና ለማፈራረስ ሲጥሩ እያየን ነው፡፡ ይህም የዓለም ማህበር ( League of Nation) መስራች ሀገራት ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ጣሊያንን ማውገዝ ሲገባቸው በኢትዮጵያ ላይ ያሳደሩትን ያልተገባ ተጽዕኖ ያስታወሰ ነው፡፡
የአውሮፓ ኅብረት እንዴት የአሜሪካ የእጅ አዙር ሥራ አስፈጻሚ ሊሆን ቻለ?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የአውሮፓ ኅብረት እንዴት ፣ በማን ፣ ለምን እና መቼ ተመሠረተ የሚለውን ስንመለከት ደግሞ የአውሮፓ ኅብረት እንዴት ተፈጠረ? የአውሮፓ ኅብረት የመጀመሪያው ስሙ እ.ኤአ 1957ዓ.ም የአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (Eropean Economic Comission) የሚባል ነበር፡፡ ይህ ድርጅት የተፈጠረውም በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ነው፡፡ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ደግሞ በቀዝቃዘው ጦርነት ወቅት የአሜሪካ ወይም የካፒታሊስቶች ደጋፊ ሀገራት የነበሩ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ይገባል፡፡ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት የኢኮኖሚ የልብ ትርታ መሠረቱ አሜሪካ መሆኗን ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር መገንዘብ ያስፈለገው ከሰሞኑ የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተሰብስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ያለስምምነት ተበትኗል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በምስራቅ አውሮፓ የሚገኙ ሀገራት የአውሮፓ ኅብረትን እንደፈጠሩት የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ለአሜሪካ የንዋይ ፍርፋሪ ያላጎበደዱ እና ለእውነት ያደሩ ስለሆኑ ነው ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአባል ሀገራቱን እኩል የማያይ እና መርጦ አልቃሽ ከሆነ እንደ መጀመሪያው የዓለም ማህበር (League of Nation) የሚፈርስበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014