የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከስግብግቡ የትህነግ ጁንታ ጋር ተገደን ዳግም የገባንበት ጦርነት በአውደ ግንባር ብቻ የተወሰነ አይደለም። በእፉኝቱ ትህነግ ስፓንሰር ከሚደረገው ተልዕኮና ስምሪት ከሚሰጠው ዲጂታል ወያኔ ህልቁ መሳፍረት ከሌለው የሀሰት መረጃና ሆን ተብሎ ከተዛባ መረጃ ጭምር እና የሴራ ኀልዮት ጋር እንጂ። ይህ የከሀዲና የሌባ ስብስብ ከ27 አመታት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኋላ በሕዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሉ ከመንበሩ ከተፈነገለ በኋላ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጎ 24 ሰዓት የውሸት፣ ሆን ተብሎ የተዛባና የሴራ ኀልዮትን ፍላጻ ሲያንበለብል ባጅቷል።
በዚህም በአገሪቱ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። ንጹሐን ተገድለዋል። ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ በስግብግቡ የትህነግ ከሀዲ ቡድን ግፍ መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲንቀሳቀስ እና ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባ የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ወናፍ በተናበበና በተቀናጀ አግባብ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በማህበራዊና መደበኛ ሚዲያ የሀሰትና የተዛባ መረጃውን እያራገበ ይገኛል።
ጦርነቱን እራሱ ለኩሶ እያለ የተወረርሁ ድቤውን ይደልቃል። ያልታጠቀውን መሣሪያ ታጥቄያለሁ፤ ወታደራዊ ኢላማውን መትቶ የተመለሰን ተዋጊ ጀት ንጹሐንን ገደለ፤ ያልያዘውን ከተማ ይዣለሁ፤ ደሴን ኮምቦልቻን ያዝሁ፤ በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እገባለሁ፤ ያልማረከውን ታንክ ማረክሁ፤ ጥቃት ከፍቶ በዐቢይ ሠራዊትና በአማራ ልዩ ኃይል ተከበብሁ ተወረርሁ፤ የትግራይን ሕዝብ በግዳጅ በማዕበል እየማገደ ሊያጠፉት ነው እያለ፤ ወዘተረፈ ዓይነት ነጭ ውሸቶችን በፎቶ ሾፕና በቪዲዮ እያቀናበረ በመላው ዓለም በተበኑ ጭፍራዎቹ አማካኝነት እየነዛና እያራገበ ይገኛል።
በማህበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያው ሀሰተኛው፣ የተዛባው ሆነ አሳሳቹ መረጃ የትየለሌ በመሆኑ ሕዝብ በአሰስ ገሰስ የመረጃ አረንቋ መዋጡን ለማረጋገጥ የትህነግ ምንደኛ የፕሮፓጋንዳ ጭፍራ ማህበራዊ ሚዲያውንና ዘርፎ ያቋቋመቸውን መደበኛ ሚዲያዎችን እንዴት በውሸት እንዳጥለቀለቀው መመልከትና መረዳት ይቻላል። ከጦርነቱ ይልቅ የመረጃ አውደ ውጊያው አየሩን ፣ ምድሩንና መልካው ብቻ ሳይሆን ቨርቹዋል የሆነውን ዲጂታል ዓለምንም አዳርሶታል። ይህ አልበቃው ብሎ በሴራ ኀልዮት እያወናበደ ይገኛል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሴረኛውን የትህነግ ወታደራዊ ቡደን ውሸትና ቅጥፈት ጠንቅቆ የሚያውቀው ቢሆንም ጥቂት የዋሆችን ማሸበሩ ማቄሉና ማሞኘቱ አልቀረም ።
የውሸት፣ የተበረዘና የተዛባ መረጃ እና የሴራ ፖለቲካ አይደለም ፖለቲካዊ ግንዛቤያችን ዝቅተኛ ለሆነው እና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላላቆምነው ይቅርና ለአሜሪካና ለምዕራባውያንም ፈተና ሆኗል። የ2016ቱን የአሜሪካ ምርጫ፣ የእንግሊዝ ከኅብረቱ የመነጠል ሕዝበ ውሳኔን፤ የአሜሪካ 2020 ምርጫ፤ የፈረንሳይ ምርጫ ፤ ወዘተረፈ ያስታውሷል። በዚህ ምርጫ ጮህ ብለው ከተሰሙ የሴራ ኀልዮት /conspiracy theory /” ዲሞክራቶች ግራ አክራሪ ሶሻሊስት እና የባዕድ አምልኮ ተከታይ ናቸው። “ የሚሉት ይገኙበታል።
የኩባን ሶሻሊዝም ሸሽተው በፍሎሪዳ በብዛት ነዋሪ የሆኑ ኩባ አሜሪካውያን ትራምፕን የመረጡት ከፍ ብዬ የገለጽሁትን የሴራ ወሬ አምነው እንደሆነ ሲኤንኤን በምርጫው ሰሞን አውርቶናል። ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ሽንፈቴን አልቀበልም የሚሉት ራሳቸው አበክረው ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል ሲሉ ያሟረቱትን ሟርት ሴራ ሰበብ አድርገው ነው። እንደ ዋሽንግተን ፓስት ዘገባ ትራምፕ ከ20ሺህ በላይ ውሸቶችን በመዋሸት የነጩን ቤተ መንግሥት ጥላሸት ቀብተውታል።
እሳቸው መች በዚህ ያበቁና ዕለት በዕለት በቲዊተር ገጻቸው በሚያዥጎደጉዱት የሴራ ኀልዮት የተነሳ በአሜሪካውያን መካከል መከፋፈልን ፈጥረዋል። የምርጫው ሒደትና ውጤት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። በአሜሪካ የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ ከአንድ ጊዜ በላይ ምርጫ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፤ በገደምዳሜ የሚቀጥለውን የ2024 ምርጫም ዲሞክራቶች ማሸነፍ አለባቸው ማለታቸው ነው።
ባራክ ሁሴን ኦባማ “ዘ ፕሮሚስ ላንድ “ የተሰኘውን አዲሱን መጽሐፋቸውን ባስተዋውቁበት በዚያ ሰሞን በቢቢሲ አርት የታሪክ ሊቅ ከሆነው ዴቪድ ኡሉሶጋ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በአንድ የምርጫ ጊዜ” የእውነትን መበስበስ “ ማስቀረት አይቻልም። እንግዲህ የዴሞክራሲ ዋስና ጠበቃ በሆነችው እና የዴሞክራሲ ተቋማት በአስተማማኝ መሠረት የገነባችው አሜሪካ “እውነት” እንዲህ ፈተና ውስጥ ከገባች ዲጂታል ወያኔ 24 ሰዓት የሚረባረብባት የእኛ “ እውነት “ በምን አቅሟና ጎኗ ትችለዋለች።
አሜሪካ በዜጎቿ መካከል ልዩነትን በመጎንቆል ላይ የሚገኘውን የሴራ ኀልዮት የመቀልበስ ትልቅ ኃላፊነት ከፊት እንደሚጠብቃትም ፕሬዚዳንት ኦባማ ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቷል። በእንቅርት ላይ እንዲሉ በማንነት ላይ ለምትንጠራወዘው ሀገራችን የሴራ ኀልዮት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በተግባር እያየነው ነው። በተለያዩ ምክንያቶች በዜጎች መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚደረገው ጥረት ለአንድ ወገን ብቻ ማለትም ለፖለቲከኞች ወይም ለመንግሥት የሚተው ሳይሆን የመላ ዜጋውን ተሳትፎ፤ መዋቅራዊ ለውጥ እና በዜጎች መካከል የመደማመጥ ባህልን ማጎልበት እንደሚጠይቅ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይመክራሉ።
የሴራ ኀልዮት፣ ሚስ ኢንፎርሜሽን እና ዲስኢንፎርሜሽን እርስ በእርስ የሚመጋገቡና የሚናበቡ ሁነቶች ናቸው። ሚስ_እና_ዲስ ኢንፎርሜሽን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ስለሚመስል እየተተካኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል። ብያኔአቸው ግን ለየቅል ነው። ሚስኢንፎርሜሽን የተሳሳተ ወይም አሳሳች መረጃ ሲሆን ዲስኢንፎርሜሽን ደግሞ እውነትን ለመሸፋፈን ወይም የሕዝብ አስተያየት ላይ ተዕጽኖ ለማሳደር ሆን ተብሎ የሚነዛ የሀሰት መረጃ ነው። እፉኝቱ ትህነግ በፕሮፓጋንዳ ጭፍራው አማካኝነት ሥልጣን ላይ እያለም ሆነ ከተፈነገለ በኋላ አሳሳች፣ እውነት የሚያጠየም እና የሴራ ኀልዮትን እያዛነቀ ሌት ተቀን እየባዘነ ይገኛል።
በተለይ በሰሜን ዕዝ አረመኔያዊ ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከወሰነበት ደቂቃ አንስቶ ምን አልባት በየዕለቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀሰተኛ፣ እውነትን የሚበርዙ የሚከልሱና የደባ መረጃዎችን በተቀናጀ መንገድ በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያ እያንበለበለ ይገኛል። በጀግናው የመከላከያና የሚሊሻ ኃይሎች በቀናት አውደ ውጊያ ድባቅ ሲመታ ያለ
የሌለ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና የዘረፈውን ሀብት ለፕሮፓጋንዳ ማሽነሪው አውሎት ነበር።
ለመሆኑ የሴራ ኀልዮትስ ምን ድን ነው !? ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ባለሥልጣናት አልያም የተወሰኑ የፖለቲካ፣ የአይዶሎጂና የኢኮኖሚ ቡድኖች ምስጢራዊ ዕቅድ ውጤት የሆነ ሁነት ወይም ክስተት የሴራ ኀልዮት Conspiracy Theory ሲል ይበይነዋል የእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት ሜሪያም ዌቢስተር ። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሰናዳው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ፤ አድማን፦ ሴራ ዱለታ ፤ ሲል በአጭሩ ይተረጉመዋል ።
ሆኖም በባለሥልጣናት፣ በመንግሥት ሆን ብሎ ጉዳት ለማድረስ በምስጢር የሚፈፀም ደባም የሴራ ኀልዮት ነው ሲሉ ድርሳናት ትርጉሙን ሰፋ ያደርጉታል። ታዋቂው የፖለቲካ ሊቅ ማይክል ባርኩን በበኩሉ ኀልዮቱ አፅናፈ ዓለም universe በአፈተት በአቦሰጥ ሳይሆን በንድፍ design ትመራለች በሚለው ተረክ ላይ የተዋቀረ ነው ሲል ይሞግታል። እንደ ባርኩን ትንተና የሴራ ኀልዮት 3 መገለጫዎች አሉት። የመጀመሪያው ምንም ነገር በአጋጣሚ አይሆንም። ሁለተኛው ደግሞ ምንም ነገር ላይ ለዩን እንደምናየው ፣ እንደመስለን አይደልም። ሦስተኛው ደግሞ ሁሉም ነገር እርስ በርሱ የተያያዘ ነው ብሎ ያምናል።
ሌላው የኀልዮቱ ባህሪ ይላል ባርኩን ውሸት መሆኑን በመረጃ ለማስተባበል ፈታኝ መሆኑ ነው። የኀልዮቱ መነሻ የመሪዎች ግድያ ሲሆን ዘመኑም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ መሆኑ ድርሳናት ያትታሉ። ከእያንዳንዱ ክስተት ጀርባ ሴራ ደባ አለ በማለት በዜጎች በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን የሚቀፈቅፍ ኀልዮት ነው። በታላቁ መፅሐፍ፦
“ በእግዚአብሔር እናምናለን ። “ እና
“ አይኖቹ በምድር ሁሉ ያያሉ ። “ ከሚለው ቅዱስ ቃል ላይ ተመስርቶ በአሜሪካ የአንድ ዶላር ላይ ፈጣሪ ሁሉን እንደሚያይ፤ አሜሪካ በቅጥሩ በጥበቃው ስር እንደሆነች የሚወክለውን ምስል ( the all seeing eye ) ሳይቀር በአሜሪካ መስራች አባቶች የተሸረበ ሴራ ተደርጎ መቆጠሩ ኀልዮቱ ምን ያህል ጥርጣሬን ለመዝራት ምን ያህል ምቹ እንደሆነ ያሳያል።
አንዳንድ የስነ ልቦና ሊቃውንት ኀልዮቱ በማኪያቬሊያዊ ፅንሰ ሀሳብ በዜጋውና በሕዝብ መካከል ፍርሀትን በመንዛት ላይ ያተኮረ መሆኑን ይተነትናሉ። በዓለማችን በሴራ ኀልዮት አብነትነት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል የአሜሪካዊ 35ኛ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ላይ የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) እጁ አለበት ። እ.አ.አ በ1971 አፓሎ የተሰኘች የአሜሪካ መንኮራኮር ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ማረፏን የሚክደው እንዲሁም በተለምዶ በ9/11 አልቃይዳ በዓለም የንግድ ድርጅት ሕንፃዎች ፣ በፔንታጎንና በመንገደኞች አውሮፕላን ከ3ሺህ በላይ አሜሪካውያንና የውጭ ዜጎች ባለቁበት የሽብር ጥቃት አሁንም ሲ አይ ኤ ተሳትፎበታል።
ኤች አይ ቪ / ኤድስን አሜሪካ ነች ጥቁሮችንና ሌሎች ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የፈጠረችው እና የእንግሊዟን ልዕልት ዲያና ፈረንሳይ ፓሪስ በመኪና አደጋ የሞተችው በአገሪቱ የስለላ ድርጅት ኤም አይ 5 እና 6 እንዲሁም በንጉሣዊ ቤተሰቡ ሴራ ነው የሚሉ ይገኙበታል ።
እንደ መቋጫ
ባለፉት ሦስት አመታት ጎልቶ ይስተዋል የነበረ የተግባቦት ዳተኝነትና ክፍተት ለፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ሽንፈትና ሕዝብን ግራ ለመጋባት በመዳረግ በምንም ሊተመን የማይችል ውድ ዋጋ አስከፍሎናል። በወቅቱ ከስር ከስር ማስረዳት ማብራራትና መግለጽ ባለመቻላችን እውነትን ታቅፈን ቀርተናል። አሁን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሚኒስቴር ደረጃ መዋቀሩ ይሄን ክፍተት ለመሙላት ያግዛል።
ተቋሙ እውነተኛ መረጃን ወዲያው ወዲያው ተደራሽ በማድረግ የተጋነኑና በማህበረሰቡ ዘንድ ሽብር የሚለቁ መረጃዎችን መከላከል ይችላል። መንግሥትም ሆና ባለድርሻ አካላት ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎችን ማዕከላዊነትንና ወጥነትን በጠበቀ አግባብ እግር በእግር እየተከታተለ የማድረስ ኃላፊነትም ግዴታም አለባቸው። እግረ መንገድ ሕዝብን ካልተገባ ፍርሀትና ውዥንብር መከላከል ይቻላል። ዳሩ ግን ትክክለኛ መረጃን የማድረስ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑ ሊጤን ይገባል።
አንድ መረጃ ከማጋራት ወይም ከመለጠፍ በፊት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ፤ በምንጭነት ከመጠቀም በፊት ከሌሎች ምንጮች ጋር ማመሳከር የተቀናጀ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል። የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀም ሰዎች ስለምናጋራው ጽሑፍ፣ ምስልና ድምፅ ቆም ብለን ማሰብ፣ ለዋቢነት ፣ ለአጋዥነት ስለምንከፍተው ድረ ገፅ ፣ ጦማር ታማኝ ምንጭ መሆን አለመሆን ማጣራት በማስከተል አስተያየት (ኮሜንት) ከመስጠታችን በፊት ማውጣት ፣ ማውረድና ማመዛዘን ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን ሀሰተኛ ፣ የተዛባና የጥላቻ መረጃ ዘርጋፊዎችን ፣ ነዥዎችንና ለፋፊዎችን በሒደት ማስቆም እንችላለን።
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከወሰነ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት ከጎኑ ከመቆም ባሻገር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እና ግምቱ ቀላል ያልሆነ የዓይነት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን እንዳረጋገጠው ሁሉ በውጭም በአገር ቤት ያሉ ዜጎች በተቀናጀና በኢትዮጵያዊ አርበኝነት የዲጂታል ወያኔን ፕሮፓጋንዳ እየመከቱ ነው።
እውነትን ይዞና ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ አገርና ሕዝብ ለዛውም ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ለሚደረግ የጸረ ፕሮፓጋንዳ ትግል ሁሉም ዜጋ ይበልጥ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ሊንቀሳቀስና ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻ በጦር ግንባር ያስመዘግቡትን አንጸባራቂ ድል እኛ በእነሱ መስዋዕትነት በሰላም እየኖርን በእጅ ስልካችንና በኮምፒዩተር ቁልፎች የምንደኛውንና የቅጥረኛውን የዲጂታል ወያኔ ጭፍራ ፕሮፓጋንዳ መክተን የፕሮፓጋንዳ አውደ ውጊያውን ማሸነፍና የጀግናው ሠራዊታችንን አኩሪ ድል መደገምና ማህበራዊም ሆነ መደበኛ ሚዲያውን በአገር ፍቅር ሱናሚና በአርበኝነት ማጥለቅለቅ ይጠበቅብናል።
ለአገራችን ሁላችንም አምባሳደር፣ ጋዜጠኛና ሕዝብ ግንኙነት ነንና። ይህ ዘርፈ ብዙ ጦርነት በድል እስኪደመደም ሁላችንም የእውነት፣ የፍትህና የሉዓላዊነት ሠራዊት መሆን አለብን ። ለዚህ ክቡር አላማ የሕይወት መስዋዕትነት ብንጠየቅ እንኳ ወደ ኋላ የማንል ጊዜያችንን፣ እውቀታችንንና ገንዘባችን ሰውተን የድሉ ተቋዳሽ መሆን ይጠበቅብናል።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና እውነተኛ ዜጎች ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2014