ዓለም የስልጣኔዋን ያህል በስይጥንና አስተሳሰብ ስር ከወደቀች ቆየች። የዚህ የስይጥንና እሳቤ ጎሬው ደግሞ ከባለፀጎቹ ሀገራት ዘንድ መሆኑ እጅግ ያስደንቃል። ስልጡን ሀገራት የስልጣኔያቸውን ያህል በደላቸውም እየከፋ የመጣበት ዘመን ላይ ነን። የሰው ልጅ ከትናንት እስከ ዛሬ ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት ውስጥ ነው። ራስ ወዳድነቱ ደግሞ በባለፀጎቹ ዘንድ እየባሰ ነው።
የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በሀገራችን በተከሰተው ጦርነት የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት ደባ ምን ያህል የከፋ መሆኑን የማይገነዘብ ኢትዮጵያዊ የለም።
ሀገራት የራሳቸው የሉዓላዊነት ድንበር አላቸው። የትኛውም አገር በየትኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌለው ዓለም አቀፉ ህግም ይደነግጋል። ይሄ ግን መሬት ላይ የለም፤ ወረቀት ላይ ቀርቷል። ኢኮኖሚያቸውንና ፈርጣማ ክንዳቸውን በመጠቀም በሌሎች አገራት ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱ አገራት ጥቂት አይደሉም። አገራቱ ዓለም አቀፍ ተቋማትንና መገናኛ ብዙሃንን እንዳሻቸው የሚዘውሩም ናቸው።
እንዳሻን ልንዘውረው አልቻልንም ብለው ያሰቡትን ሀገር መንግሥት የሚቃወም የትኛውንም አይነት ቡድንና ሀገር ይደግፋሉ። ከሞተበት ያነሳሉ፤ ለምን ሰይጣን ፣ ጭራቅ አይሆንም። የህወሓት ቡድን በስልጣን ዘመኑም ሆነ ከስልጣን ወርዶም ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረሰውና እያደረሰ ያለው ግፍና በደል ምን ያህል ዘግናኝ መሆኑን እያወቁ ለቡድኑ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው፤ ሽፋንም እየሰጡ ናቸው። አውነትን ክደው ሀሰትን ይዘው ሽንጣቸውን ገትረው እየተከራከሩለት ይገኛሉ።
በተለይ አሜሪካ ህወሓትን በመደገፍ ያልተገባ አካሄድ በመሄድ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ በማድረስ አይን ያወጣ ወዳጅነቷን እያሳየች ትገኛለች። በአሜሪካ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ሁሉንም መሪ አንድ የሚያደርግ መርህ አለ፤ እርሱም ራስ ወዳድነት ነው። የአሜሪካ ኢኮኖሚ የተገነባው በዚህ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ላይ ነው።
ልዕለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካ ከትላንት እስከዛሬ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ራሷንና ህዝቧን ስትጠቅም ኖራለች። ለዚያውም ከድሆች አፍ ላይ እየቀማች። የአሜሪካን የኋላ ታሪክ ያጠና ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች ላይ ይደርሳል።
አሜሪካ ጣልቃ ገብታበት ልክ የሆነ ሀገርና ህዝብ የለም። ዩጎዝላቢያ የፈራረሰችው፣ በአፍጋኒስታን ያ ሁሉ እልቂትና ውድመት የመጣው በእሷ ጣልቃ ገብነት ነው። ሊቢያ ቀና እንዳትል የተደረገችው በአሜሪካ ነው። ያሌላትን ኒውክሌር አላት በሚል መሪዋን ገድለው ዜጎቿን ያጨረሱባት ታሪኳን መሰረተ ልማቷን ያወደሙባት ኢራቅ ሌላዋ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሰለባ ናት።
በእኛ ሀገርም እንዲሆን እየተፈለገ ያለው ይኸው ነው። ህወሓት ስልጣን ላይ በቆየባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት እንደ አሜሪካ የተጠቀመ የለም። ህወሓት በሌላው አቅም የደርግ ዘመንን ያህል ግዙፍ ሰራዊት ሽባ አድርጋ ወደ ቤተ መንግሥት ሰተት ብሎ እንዲገባ ያረገችውም እሷው ናት።
ዛሬም ይህን ቡድን ወደ ስልጣን ለማምጣት ቋምጣለች፤ ጥቅሜ ያለችውን ለማስመለስ ነው ለቡድኑ አይን ያወጣ ድጋፍ እያደረገች ያለችው። ቡድኑ ባጠፋ ኢትዮጵያን በማዕቀብና ርዳታ መከልከል እያስፈራራች ነው።
ሁሉም ጋ እውነት አለ። የኢትዮጵያ መንግሥት እያስጠበቀ ያለው የህዝብ ይሁንታን ስለመሆኑ ዓለም ያውቃል። አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ሀገር መመዝበሩን፣ ሰብዓዊ መብት በእጅጉ መጣሱን፣ ዜጎችን በማጋጨት እድሜውን ያራዝም እንደነበር የማያውቅ የለም። ከስልጣን ተወግዶም እየፈጸመ ያለውን አረመኔያዊ ተግባር የማያውቅ ምእራባዊ ሀገር የለም።
ህወሓትን በተመለከተ የአሜሪካ ዝምታ ትርጉም ያለው እንደሆነ ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው። ኢትዮጵያንና ህዝቧን ጎድቶ ራስን የመጥቀም አላማ እንደሆነ የታወቀ ነው። የህወሓትን ማንነት እያወቀች ዝምታን የመረጠችበት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፤ የኢትዮጵያውያን ስቃይና እንግልት ምኗም ነው።
ህወሓትን ለማስቆም በቂ ምክንያቶች ነበሯት። ንጹሀን ሲገደሉ፣ ህጻናትና ሴቶች ሲደፈሩ፣ እድሜአቸው ያልደረሰ ህጻናት ለጦርነት ሲማገዱ ለምን ማለት ነበረባት፤ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፤ በቡድኑ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚወስደው ርምጃ ላይ ግን ትከሳለች፤ ታስፈራራለች።
ህወሓትና አሜሪካ እጅና ጓንት ናቸው። ሁለቱም በራስ ወዳድነት ተመርዘዋል። ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የኢትዮጵያን ጥቅም ለባዕድ ሀገራት አሳልፎ ሲሰጥ ነበር፤ የዚህ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ሀገራት ውስጥ ደግሞ አንዷ ይቺው በማንአለብኝ የምትንቀሳቀሰዋ አሜሪካ ናት።
በህወሓት የስልጣን ዘመን አሜሪካ ከኢትዮጵያ የተጠቀመችውን ያህል እኛ ዜጎቿ አልተጠቀምንም። አሁንም ያ ጥቅሟ እንዳይቀርባት ስትል ነው በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ ለአሸባሪው የተለያዩ ድጋፎችን እያረገች ያለችው። በእርዳታ ጭነት ውስጥ የመገናኛ መሳሪያዎችና መድኃኒቶች መገኘታቸውም ይህን ያመለክታል። ቡድኑ ረሀብ እንዲከሰት አላማ ያለው መሆኑን ተከትሎ እርዳታ እያስተጓጎለ ባለበት ወቅት አሜሪካ እሱን ትታ ትከስ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥትን ነበር።
የቡድኑን ጥቅም ለማስጠበቅ ነጋ ጠባ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትሰበሰባለች፤ በተመድ በአውሮፓ ህብረት በኩልም ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። ዛቻዋ፣ ማእቀቧ ከከሀዲው ጎን ምን ያህል እንደቆመች ያመለክታሉ።
ለእውነትና ለፍትህ ከቆሙ ጥቂት ወዳጅ ሀገራት በቀር አባዛኞቹ ምእራባውያን ሀገራት አሜሪካን የሚከተሉ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ህወሓት በንጹን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ማስቆም ሲችል፣ ያን ማድረግ አልፈለገም። አሜሪካ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ህወሓት ንጹሐንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመጨፍጨፍና በሌሎች ዓለም አቀፍ ህግን በተላለፈባቸው ወንጀሎች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በወንጀለኝነት ማቆም ይችሉ ነበር። በአሜሪካ የሀሰት ጩኸት ሁሉም በራቸውን ጠርቅመው ወይም ደግሞ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል።
እነዚህ ሀገሮች በሚከተሉት የተሳሳተ መንገድ ሳቢያ የሰው ልጅ ከፍትህ ይልቅ ክህደትን፣ ከእውነት ይልቅ ሀሰትን፣ ከቁም ነገር ይልቅ ቧልትን የመረጠበት ጊዜ ላይ ነን። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ህወሓት በንጹሃን ላይ ያደረሰው ግፍና በደል አፍ አውጥቶ የሚናገር ቢሆንም፣ ሰብዓዊነት በራስ ወዳድነት ተቀይሮ ከወንበዴ ጎን ቆመዋል።
በርባን ይፈታ..በርባን ንጹህ ነው የሚል የኃያላኖች ድምጽ እየተሰማ ነው። ህወሓት በርባንን ነው። በአንድ ነፍስ ሳይሆን፣ በአንድ ሺ ነፍሶች ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮን ነፍሶች ይጠየቃል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን የክብር ድንበር ያለን ኩሩ ህዝቦች ነን። ዓለምን ጥበብ አስተምረናል። ማንም ከመሬት ተነስቶ አውቅልሀለሁ የሚለን ሀዝብ አይደለንም። በፍቅር እንጂ በጠብ ለመጣብን ቁጡ ነን። ኃያላኖቹ ይሄን ቢረዱ መልካም ነው እላለሁ።
ሺ ነፍስ የበላውን በርባንን ፈተው ከነፍሰ በላ ጋር አሸሼ ገዳዎ ለማለት የሚቋምጡ ብዙ ሀገራት በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ እያደረጉ ቢገኙም፣ እኛ ግን ህልውናችንን ለነፍሰ በሎች አሳልፈን አንሰጥምና በአንድነት በመቆም ህወሓትና አሸርጋጆቹን መዋጋት ይኖርብናል።
የሀገራችን ጉዳይ የእኛ ጉዳይ ነው፤ የአሜሪካ ወይም የተባበሩት መንግሥታት ጉዳይ አይደለም። እነሱ እውነተኛ ቢሆኑ ኖሮ ብዙ ነገሮች መስተካከል በቻሉ ነበር። ሀሳባቸው ሌላ ስለሆነ ሴራቸውን እየሸረቡ ናቸው። ይህን የኃያላኖቹን ደባ ተረት ለማድረግ በጋራ መቆም ይኖርብናል፤ አማራጭም የለንም።
አሜሪካ ሁልጊዜም በአንድ ነገር ትረታለች፤ በህዝብ የጋራ ድምጽ፣ ህዝብ በጋራ ሲቆም። ህዝብ በጋራ ድምጹን ካሰማ፣ በጋራ ከቆመ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ኃያላን ሀገሮች አቅም አይኖራቸውም። እስከዛሬ ጣልቃ በመግባት ሀገራትን ያፈራረሱት ህዝብ በጋራ ሳይቆም በመቅረቱ ነው። ሀገራችንን ከኃያላኖቹ ደባ አናስጥል እያልኩ ላብቃ፤ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014