ጸሐዬ ዮሐንስ ለካስ ያለነገር አይደለም “ማን እንደ እናት ማን እንደሀገር “ ሲል ያዜመው። የሰው ሀገር ሃሳብ ከላይ ተብለጭልጮ ቢታይ ፣ የረባ ቢመስል ጠብ የሚል ነገር እንደሌለው በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ወንድሞቻችን ሕይወት ተጨባጭ ምስክር ነው። እራሳችንን ስንመለከትም ብዙ ራሳችንን መሆን የሚያስችለን ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ባለቤቶች ነን።
ለዘመናት ተቻችለን በፍቅር የኖርን ህዝቦች ነን ።በዚህም ለመላው ዓለም የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር ተምሳሌት ተደርገን የምንወሰድ ነን ። ከዚህ ወጥተን ከውጭ በተሰጠን የአንዱ በዳይ የሌላው ተበዳይ ትርክት ሂሳብ ለማወራረድ እላይ ታች ስንል ከእድገት ሩጫችን ተገትተናል።
እንኳን ሰው ራጉኤል ቤተክርስቲያን እና አንዋር መስኪድ አጥር ተጋርተው ተደጋግፈው መቆማቸው የትናንት የመቻቻልና የመፈቃቀር ታሪካችን አካል ናቸው ።ብሔር ብሔረሰቦቻችን ለዘመናት በፍቅር አብረው መኖራቸው፣ በጋብቻ ተሳስረው ቤተሰብ የመሆናቸው እውነታው የዚሁ ሀቅ ማሳያ ነው ።
አድዋ ላይ ወራሪን አዋርደን የመለስነው ከዚህ ማህበራዊ እሴቶቻችን በተገነባ አንድነት አባቶቻችን ሕይወታቸውን ስለገበሩ ነው። ዓለም ገና ሳይሰለጥን እኛ ወደ ላይ ከፍ እንበል ስንል ከአንድ ድንጋይ አክሱምን ያነጽን፤ሲያሻን ከዓለም በተቃራኒው ከላይ ወደታች የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የፈለፈልን ነን።አደግን ሰለጠንን ያሉ እንደቅርጫ እጣ ተጣጥለው ዓለምን ለመቆጣጠር በየፊናቸው ሲሰማሩ፤ በወራሪ አንገዛም፤ ባርነትን እምቢ ብለን ለነጻነት በዱር በገደሉ መታገልን ያስተማርን እኛ ነን።
ይህ ማንነታችን በየዘመኑ ጠላቶቻችን መልካቸውን እየቀያየሩ የመንገድ ላይ እሾህ እንዲሆኑ ፣በእኛና በእኛ ጉዳይ ተኝተው እንዳያድሩ አድርጓቸዋል። ዛሬም የራሳችንን እጣ ፈንታ በራሳችን እንወስናለን ብለን ስንነሳ እያጋጠመን ያለው ተግዳሮት የዚሁ ታሪካዊ እውነታ ቀጣይ ምእራፍ ነው ።
በሰብዓዊ መብት ስም የሚነሱ ጥያቄዎች ፣ በእርዳታ ስም የሚከናወኑ ሴራዎች ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን ላይ እየተደረጉ ያሉ የተቀናጁና የታቀዱ ጫናዎች መልካቸው አዲስ ቢሆንም ተልእኳቸው ግን የቆየ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ማሳነስ ነው ።
ለወትሮው የህጻናት መብት ይከበር እያሉ ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ የሚጮሁ፣ ከእኛ በላይ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ላሳር የሚሉት ምእራባውያኑ ፤ በትግራይ ያለፍላጎታቸው በሽብርተኛው ቡድን ለጥይት ሲሳይነት የሚማገዱ ህጻናትን ማየት አልፈለጉም ። በአማራ እና በአፋር ክልል የታዳጊዎች ደም በሽብርተኛው ቡድን ሲፈስ ለነሱ ምናቸውም ያልሆነው ለዚህ ነው ።
ሀገርና ህዝብን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥትና የመከላከያ ሰራዊቱ ዜጎችን ለመታደግ ከህገመንግሥት የመነጨ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ፤መንግሥትና የመከላከያ ሰራዊቱ የህዝብ ጠላት አድርጎ ለመሳል ያለመቦዘናቸው ፣ለኢትዮጵያ ህዝብ ከራሱ በላይ ሆኖ ለመታየት የሚደረገውም ጩኸት የዚሁ ታሪካዊ አካል ነው።
ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ እየሆነ ነው ።ህዝባችን ከትናንት ታሪኩ መማር ችሏል ።ከራሱ በላይ ስለራሱ የሚያስብለት እንደሌለ በተጨባጭ ተረድቷል። የዘገየ ቢመስልም በቁጥርም በአይነትም መብዛታችን ውበት መሆኑ ገብቶታል ። አንተ ተቃዋሚ እኔ ደጋፊ እያለ እርስ በርስ ከመጠላለፍ መደጋገፍ ለሀገር ልእልና እንደሚጠቅማት ተገንዝቧል። ለችግሮቹ መፍትሄው እሱ ራሱ እንደሆነ ነጋሪ በማያስፈልገው ደረጃ ላይ ደርሷል ።
ለዚህም አንዱ ማሳያ በ2013 ዓ.ም ያደረገው ምርጫና በምርጫው የታየው አዲሱ ባህል ነው። በምርጫ ቅስቀሳ ላይ እኔ ካሸነፍኩ የተፎካካሪዎቼ ሃሳብ ባክኖ አይቀርም አብረን ሀገር እናስተዳድራለን የሚል አዲስ የፖለቲካ ትርክት ተጀምሯል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተራርቀን ከመተቻቸት በጋራ ለአገር መፍትሄ እናምጣ ወደሚል ተሸጋግረዋል ።
ገዢው ፓርቲ ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ማግስት ሁሌ ከሰለቸን ምርጫው ተጭበርብሯል ክስ ፣ግርግርና ሁከት ወጥተው አብሮ ለመስራት መወሰናቸው ለሀገራችን ፖለቲካ አዲስ ምእራፍ ከፍቷል።
በቀጣይም ለአገራችን እና ለህዝቦቿ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ የሚያስችል ቁመና ላይ ስለመድረሳቸው እምነት አለኝ። በምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ ኢትዮጵያውያን ገዢ እና ተቃዋሚ ከሚል ፍረጃ ተላቀን በጋራ ለሀገራችን መፍትሄ የምንፈልግበትን አዲስ ምእራፍ ስለከፈታችሁልን ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
የተጀመረው አዲስ ምእራፍ እንዳይዘጋ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የአብረን እንስራ ጥሪ ያቀረበው የብልጽግና ፓርቲ ጥሪው ለይስሙላ ሳይሆን፤ አብሮ ለመስራት ሊሆን ይገባል። የችግሩን መክፈቻ ቁልፍ አርቆ ወርውሮ፤ በመፈለግ ጊዜ ሲያባክኑ በእድሉ አልተጠቀሙም ብሎ ለመውቀስ እንደማይሆን ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። አብሮ ለመስራት የተስማማችሁም የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከልባችሁ ህዝባችሁን አስባችሁ በቀና መንፈስ እንደምትሰሩ እምነቴ ነው ።
አዲስ ተሿሚዎች ያለፉትን አመራሮች እና ትተው የሄዱትን ተቋም በመተቸት መጠመድ እና የነበረውን በሙሉ ትቶ ከዜሮ ለመነሳት መፍጨርጨር የአዲሱን ምእራፍ እንደማይመጥን ሊያውቁት ይገባል። ይልቁንስ በመደመር እሳቤ የነበረውን መልካም ነገር በማስቀጠል እና የጎደለውን በመሙላት ወደፊት መቀጠል ፣ ለሀገር እና ለህዝብ የማይጠቅመውን በመቀነስ ያለውን አዳብሮ መሄድ ያስፈልጋል ። አመራር በአዲስ በተተካ ቁጥር የተጀመረው መሰረት እየፈረሰ፤ የተጀመረው ቤታችን እልፍ ሳይል ለዘመናት ቆይቷል።
እየተጠናወተን ያለውን አፍርሶ ከዜሮ የመነሳት እና መፍትሄን ከምእራባውያን የመፈለግ ልክፍት ሊለቀን ይገባል። ሀገር በቅብብሎሽ እንጂ በአንድ ጀንበር እንደማታድግ ከሌሎች ሳይሆን ከራሳችን በበቂ ተምረናል። ከቀደሙት ጋር ከመወነጃጀል ወጥተን አብረን በጋራ በመመካከር ለሀገራችን ልንቆም ያስፈልጋል ።በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ሳይገቡ፤ ሊያግዙን የፈቀዱትን እና በሰጥቶ መቀበል መርህ አብረው ለመስራት የፈቀዱትን እንደ ባህላችን እጅ ነስቶ ማስተናገድ ያስፈልጋል።
የውጪውን ዓለም ለማስደሰት የምንከፍለው ዋጋ የለም።ከዚህ ስነምግባር እና ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ወገናችንን ከመጣበት የችግርና የጉስቁልና ህይወት ለመታደግ ቀበቷችንን ማጥበቅ አለብን። በሕይወት እያለን አቀባበራችን እንዲያምር አስበን እድር የምንገባ አርቆ አሳቢ ነን። ስለአሟሟታችን የተጨነቅነውን ያህል ለእኛ ሲሉ በዱር በገደሉ ለሚዋደቁት ጀግኖች እና ቤተሰቦቻቸው ምን እናድርግ ብለን መጨነቅ በአዲሱ ምእራፍ የሁላችንም ግዴታ ሊሆን ይገባል።
ዛሬ በነጻነት የተሰማኝን ለመጻፍ እና እናንተም እንድታነቡ በርካታ ጀግኖች የሕይወት መስዋእትነት ከፍለዋል። በዚህም በርካታ ህጻናት ወላጅ አልባ ሆነዋል፤ በርካታ አረጋውያን በእርጅና ዘመኔ ይጦሩኛል ያሏቸውን ልጆቻቸውን አጥተዋል ስለነዚህ ሁሉ ኃላፊነት አለብን ።
ከዓለም አስቀድመን በጉዲፈቻ የተቸገረን ወገን ከቤተሰብ ቀላቅለን በስጋ ከተወለዱ ልጆች ምንም ሳንለይ፤ አሳድገን ድረን ኩለን ለቁም ነገር የምናበቃ ህዝቦች ነን። ዛሬም የውጭዎችን እርዳታ ከመጠበቅ ወጥተን፤ እኛ ተርፎን ስንበላ የእኛ ዜጋ ሲቸገር ዝም የሚል ህሊና ሊኖረን አይገባም።
በዚህም ለወገን ከመድረስም በተጨማሪ ከሀገራችን ትከሻ መውረድ ለማይፈልጉት ምእራባውያን እና ረጂ ድርጅቶች የነገ ክስ መነሻ እናሳጣቸው። ለህዝባችን አሳቢ መሆናችንን በተግባር እናሳይ።
ወደ አዲስ ምእራፍ በመሻገራችን ለሀገር እና ለህዝብ የሚያስቡ ነገር ግን አስተሳሰባቸው የሚለያይ ሰዎች መደማመጥ ጀምረው አይተናል። እኛ ልጆቿ በጋራ ካሰብንላት ሀገራችን እውነትም በአዲስ የታሪክ ምእራፍ ላይ ናት።
ትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014