መነሻና መነሳሻ
የሥነ ልቦና ጥናት አባት በመባል የሚታወቀውና በይበልጥ ሳይኮ አናሊሲስ በሚባል ቲወሪው ዓለም አቀፋዊ አንቱታን ያተረፈው ታላቁ ጀርመናዊ የሥነ ልቦና ሊቅ ሲግመንድ ፍሩድ “ልጁ የአባቱ አባት ነው” የሚል አባባል አለው። ይህ አባባል ላይ ላዩን ሲያዩት ወይንም ከሩቅ ሆነው ሲመለከቱት ብዙም የማይገባ ይልቁንም ግራ የሚያጋባ ተቃርኗዊ ምጸት ይምሰል፤ ቀረብ ብለው ጉዳዩን በጥልቀት መርምረው፣ መጋረጃውን ገልጠው፣ ወርቁን ከሰሙ ለይተው፣ በልቦና ብርሐን አጉልተው ሲመለከቱት ግን እጅግ የገዘፈ ሚስጥር የያዘ መሆኑ ይገለጥልዎታል።
የፍሩድ ቅኔ በአጭሩ ሲመሰጠር “ሰዎች ሁሉ በአዋቂነት ዘመናቸው የሚኖራቸው ማንነት በልጅነት ዘመናቸው የተቀረጸ ነው፤ በሕይወት ዘመናቸው የሚሆኑት ሁሉ በልጅነታቸው ጊዜ የሆኑትን ነው፤ እናም ልጅነት የአዋቂነት መፈጠሪያ ነው፤ ልጆችም የአባቶቻቸው ፈጣሪዎች(አባቶች) ናቸው” የሚል ወርቃማ እውነትን ያስተላልፋል። ይህም ሁለቱም ሳይንሶች(የተፈጥሮም የማህበራዊ ሳይንስም)፣ ፍልስፍናና ሃይማኖታዊ እሳቤዎችም ሳይቀር የሚስማሙበት፣ በአጠቃላይ የሰው ልጆችን የስብዕና አቀራረጽና ማንነት ግንባታ በተመለከተ የሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ሁሉ መነሻና ማጠንጠኛ፣ ብሎም የመጨረሻ መዳረሻ እውነት ተደርጎ ይወሰዳል።
እኔም ዛሬ ላይ ሆኜ ስለ ራሴ ሳስብና አንዳንድ መሰረታዊ የሚባሉ ኃልዮቶችን የምመለከትባቸውንና የምገነዘብባቸውን የአስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን ምንጫቸው ከወዴት እንደሆነ ቆም ብዩ ስመረምር ከልጅነቴ ጀምሮ ቤት ውስጥ እየሰማሁት ያደኩት አንድ አባባል ለአሁን ማንነቴ ዋነኛ መሰረት የሆነ ይመስለኛል። ልጅ እያለሁ ከቤተሰቦቼና ከአካባቢው ማህበረሰብ የምሰማው “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” የሚል አንድ አባባል ነበረ። ይህ አባባል አሁን ላይ ለእኔ አባባል ብቻ አይደለም። ከአባባልነት አልፎ በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ሚና ካላቸው ጥቂት ቋሚ እሳቤዎች መካከል በባህሪይው “ርኩስም፣ ቅዱስም” በመሆኑ፣ በውስብስብነቱና በአይጨበጤነቱ ስለሚታወቀው የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ያለኝ አመለካከት የተቃኘበት መሰረታዊ መርሄ ነው።
ፖለቲካዊ እሳቤዎችን የምበይንበትና የምመለከትበት ከቤተ-ሰቦቼ የወረስኩት ቤተ-ሃሳቤም ነው። ፖለቲካን በተመለከተ የምመራበት መሪ ፍልስፍናዬም ነው። እናም የሰዎች ሁለንተናዊ ማንነት የሚቀረጸው በልጅነታቸው መሆኑን ለማረጋገጥ እኔ ጥሩ ማሳያ ነኝ። ከፈጣሪዬ ጀምሮ የአስተማሪዎቼ፣ የጓደኞቼና የአደኩበት ማህበረሰብ ድርሻ እንዳለ ሆኖ አሁን ያለው የእኔ ማንነት ሙሉ በሙሉ የልጅነቴ ነጸብራቅ መሆኑን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። ለዚህ ጽሁፍ አሁናዊ መነሻ የሆነኝም በልጅነቴ እየሰማሁት ያደኩት “መንግሥት እና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” የሚለው የያኔው የቤተሰቦቼ አባባል የአሁኑ የእኔ የፖለቲካዊ ፍልስፍና መመልከቻ መነጽር ነው።
የፍሬ ነገሩ ትንታኔ
ልብ ብሎ ለመረመረው ሰው “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” የሚለው አባባል ከአባባልነት በላይ ትልቅ ሚስጥርን ያዘለ ዕፁብ ድንቅ የሚያስብል አስተሳሰብን የተሸከመ ትልቅ ፍልስፍና ነው። ለምን ቢባል በዚህ አባባል ውስጥ ሁለት ታላላቅ አካላት፡- እግዚአብሔርና መንግሥት ግብራቸውን ጠብቀው በየራሳቸው አውድ(Just the way as they are) “አንድ ናቸው” በሚል በተለዋጭ ዘይቤ ይነጻጸራሉ። የሁለቱን ታላላቅ አካላት ማንነት ለማሳየት ጥቅም ላይ የዋለው ተለዋጭ ዘይቤ ዋነኛ ዓላማው የመንግሥትንና የእግዚአብሔርን የግብር ተነጻጻሪነት መግለጽ ነው! ታዲያ እዚህ ጋር “መንግሥትና እግዚአብሔር የሚመሳሰሉበት(አንድ የሚሆኑበት) ማለትም የግብር ተመሳስሎሻቸው በምንድር ነው?” የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ ነው አባባሉ ተሸከመው ግዙፍ ፍልስፍናዊ ሚስጥር የሚገለጽልን።
በዚህ ጥያቄ ምላሽ ውስጥ የምናገኘው ጥቅል የሃሳብ ቱባ “እግዚአብሔር የዓለሙን ፍጥረት ከፈጠረ በኋላ ዝም ብሎ ውጡ-ህግ ለቅቆ አልተወውም” የሚል ነው። የሰማይና የምድሩ ጠቅላይ ገዥ ሕይወት ያለውንም ሕይወት የሌለውንም፣ የሚታየውንም የማይታየውንም፣ ሰማይንም ምድርንም፣ የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ፣ የሚያስተዳድርበት ህግና ሥርዓት አበጅቶለታል። ዳር ድንበር፣ ወሰንና መዳረሻ፣ ቅርጽና መጠን፣ ልኬት ህልቆ መሳፍርት በሌለው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ፍጥረት ሁሉንም እንደየ ፍጥርጥሩ በሥርዓቱና በአግባቡ ይመራል፣ ያስተዳድራል።
በሕጉ መሰረት የሚያለማን ይሸልማል፣ የሚያጠፋን ይቀጣል፣ የተጣመመን ያቃናል፣ ከጥፋቱ የሚመለስን ይምራል፣ እምቢ ከጥፋቴ አልመለስም የሚልን ያጠፋል። ይህም ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ለሚመራውና ለሚያስተዳድረው ፍጥረቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ አንዳችም ሳያስቀር አሟልቶ ያቀርባል። ቀንና ሌሊትን፣ ፀሐይና ጨረቃን፣ ክረምትና በጋን እያፈራረቀ ፍጡራኖቹን ይመግባል። ይህንንም የሚያደርገው ማንም ሳይጠይቀው በራሱ ተነሳሽነትና በሙሉ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም ሰማይና ምድርን መምራትና ማስተዳደር ታላቅ ስልጣን ብቻ ሳይሆን ታላቅ ኃላፊነትም መሆኑንም ያውቃልና።
መንግሥት ስንልም ደህንነታቸውን እንዲ ጠብቅላቸው፣ የጋራ ፍላጎታቸውንና ማህበራዊ ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ሰዎች፣ ህጋዊ ውክልና እና ይፋዊ ዕውቅና ሰጥተው፣ የበላይ መሪ እና አስተዳዳሪ እንዲሆን ፈቃዳቸውንና ስልጣናቸውን ሰጥተው የሚያቋቁሙት ሕዝብን በበላይነት የሚመራና የሚያስተዳድር ሉዓላዊ ተቋም ማለታችን ነው። እናም መንግሥትም ከሁሉም በላይ ከባዱንና ትልቁን ሕዝብን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣን የተሸከመ በመሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር ያመሳስለዋል።
እዚህ ጋር ከፊት ለመሆን መመረጥ፣ ለመምራት ከህዝብ ፈቃድ ማግኘት ከሁሉም የበለጠ ትልቅ ኃይል ለመንግሥት ያስገኝለታል። ሌሎች የማያገኙት “ስልጣን” የሚባል ልዩ ተጠቃሚነት(Special privilege) ይፈጥርለታል። ስልጣኑ የተለየ መብትን ያጎናጽፈዋል። በዚህ መንገድ የተገኘው መብት ለራስ(ለመንግሥት) ከሚያስገኘው የተለየ ጥቅም ባሻገር መንግሥትን መንግሥት ያስባለውን በሰዎች ላይ ለማዘዝና ለመወሰን የሚያስችለውን ልዩ ኃይልም ያስጨብጠዋል። ይህም ልክ እንደ እግዚአብሔር በበላይነትና በታላቅነት ፍጡራንን፤ ከፍጡርም ታላቁን ፍጡር ሰውን ለመምራትና ለማስተዳደር የሚያስችለውን “ስልጣን” የሚባለውን ታላቅ እግዚአብሔራዊ ባህሪይ መንግሥትም እንዲኖረው ያደርጋል።
በሌላ በኩል መንግሥትን እንደ እግዚአብሔር ታላቅ ያደረገው ይህ ስልጣን የሚባለው ልዩ መብት ለባለ መብቱ (መንግሥት ተብሎ ለሚጠራው አካል) የሚፈጥርለትን ታላቅ ኃይል ያህል በዚያው ልክ ከባድና ታላቅ ተጠያቂነትን(ኃላፊነትንም) ያሸክማል። እናም መንግሥት ሁሉንም ከፊት ሆኖ በበላይነትና በአዛዥነት ለመምራትና ለማስተዳደር የሚያስችል ታላቅ ስልጣን ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም ጎትጓችነትና ጠያቂነት የሚመሩትን አካል ደህንነትና ጥቅም በአግባቡ አስጠብቆ የመገኘት ታላቅ ግዴታም አለበት።
መንግሥትነት ከታላቁ ስልጣን ጀርባ ታላቅና ከባድ ተጠያቂነት መኖሩንም አውቆ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣትን ይጠይቃል። ታዲያ ህዝብን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንና ኃላፊነት ወይም የመንግሥት ተግባር ምን ያህል ከባድ መሆኑን ለመግለጽ “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” ከሚለው የእኛው ኢትዮጵያዊ አባባል በላይ የተሻለ የለም ቢባል ማጋነን ሊሆን ይችላልን? ዓረፍተ ነገሩ ከአባባልነትም በላይ ግሩም ድንቅ የሆነ ሚስጥር በውስጡ አምቆ የያዘ ጥልቅ ፍልስፍና ነው ቢባልስ ያንስበታልን? የተባለበት ምክንያትም ይኸው ነው።
ጥንት
እስኪ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን የአገር ማስተዳደርና የመንግሥትነት እሳቤዎች ጥቂት ከዘመኑ እውቅ አሳቢዎች አዕምሮ ጨልፈን እንመልከት። ከግሪክ ምድር በቅለው ዛሬም ድረስ ለመላው የሰው ልጆች ሚሆኑ ትልልቅ ሃሳቦችን ካበረከቱልን ታላላቅ አሳቢዎች መካከል ፕላቶና አርስቶትል የመንግሥት ዋነኛው ሥራ የዜጎቹን ህልውና መጠበቅና መልካ ህይወት እንዲኖሩም ማስቻል መሆኑን አበክረው አስተምረዋል። መንግሥታት ዜጎቻቸውን በነፍስ ወከፍና ሕዝባቸውንና አገራቸውን በጥቅሉ ወደ ከፍተኛው የሰውነት ደረጃ እንዲደርሱ የመሪነት ሚናውን ከፊት ሆነው መወጣት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል። መንግሥት የሚባለው ፖለቲካዊ ማህበር ዋነኛ ዓላማም በሚያስተዳድረው ግዛት ሁሉ (ዓለም አሁን በደረሰችበት ማህበረ ፖለቲካዊ የዕድገት ደረጃ አሰያየም) በመላ አገሩ ሁለንተናዊ መልካም ዕሴቶች(Universal Vertues) እንዲያብቡ፣ በሥነ ምግባር የታነፁ መልካም ዜጎች እንዲፈጠሩ፣ በአጠቃላይ በሕዝቡ መካከል የጋራ ማህበራዊ ደህንነት(Common Good) እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑንም በሰፊው አስተምረዋል።
መካከለኛው ዘመን
ብዙ ሺሕ ዓመታትን አልፈን ወደ መካከለኛው ዘመን ስንመጣም የመንግሥትነት አውራ ብያኔና የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ከጥንቱ ብዙም ያልተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህ ዘመን ከተነሱ ታላላቅ አሰላሳዮችና የፖለቲካ ፍልስፍናውን ዘርፍ በትኩረት ከዳሰሱ ጉምቱ የነገረ ፍልስፍና ልሂቃን መካከል እንግሊዛዊው ቶማስ ሆብስና ፈረንሳዊው ዣን ዣክ ሩሶ ከፊት ይሰለፋሉ። ቶማስ ሆብስ “ሌቭሃታን” በተባለ ቱባ የፍልስፍና ድርሳኑ፤ “መንግሥት እንዲኖር የሚፈለግበት መሰረታዊ ምክንያት ለሚመራቸው ዜጎች የህይወታቸው ጠበቃና ዘብ እንዲሆን ነው።
ዋነኛ ሥራውም የሚመራውንና የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ህልውና ማስጠበቅና ደህንነቱን ማስጠበቅ ነው” ይላል። መንግሥት ሕዝቡን ከማንና እንዴት እንደሚጠብቀው ሲያብራራም፤ “ዜጎቹን ከእርስ በእርስ መጠፋፋትና ከውጭ ጠላት ከሚሰነዘር ጥቃት ሊጠብቃቸው ይገባል፤ ይህንን የሚያደርግበት ብቸኛ መሳሪያውም ህግና ሥርዓትን ማስከበር ነው” የመንግሥት ሚና ከእነ መፈጸሚያ መንገዱ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። ይህ ካልሆነ ግን ይላል ሆብስ፤ “ምድር የህገ ወጦች መፈንጫ ትሆናለች፤ ሰዎች የልፋታቸውን ፍሬ አይበሉም፣ ሥራ፣ ዕውቀትና ጥበብ አይኖሩም፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ጥፋትና ሞት ይነግሳሉ”።
የአሁኑ ዘመን
ዘመናዊ በሚባለው በአሁኑ ዘመን፤ ዛሬም ቢሆን የዘመናችን ቁንጮ የነገረ መንግሥትና ፖለቲካ ሊቃውንት ደግመው ደጋግመው የሚያስረግጡትም የመንግሥት ዋነኛ ተግባር የግለሰቦችን ተቃራኒ ፍላጎት የሚያስታርቅበትና ቅጥ ያጡ የግል ፍላጎቶችንና የሚያስከትሉትን መዘዝ የሚያርቅበት ህግ ማበጀትና የዜጎችን ሥርዓትን ማስከበር ብሎም የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ነው። በዚህ ረገድ ከፊት ከሚቀመጡ የዘመናችን አሳቢያን መካከል የአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመኑን ኤድመንድ በርክና አሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዊሊያም ሄግል እናገኛለን።
በርክ “ሰዎች ስሜታዊም ምክንታዊም ፍጡር በመሆናቸው፤ መንግሥት የሚያስፈልገው ስሜት በምክንያት ላይ አዛዥ ሆኖ ጥፋትን እንዳያመጣ ለመቆጣጠር ነው። ስለሆነም የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ነጻነትን በአግባቡ የማይጠቀሙበትን ዜጎችን ሥርዓት ማስያዝ ነው” ይላል። ነጻነታቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ ግለሰቦችን ሥርዓት ማስያዝ የሚቻለው በሕግና በሕግ ብቻ መሆኑን የሚነግረን ደግሞ ሌላኛው ጉምቱ የዘመናዊው ዘመን ፈላስፋ ጆን ስቱዋርት ሚል ነው።
መልዕክት
ከዚህ ሁሉ የምንማረው በየትኛውም ጊዜ በየትኛውም ቦታ መቼም የማያረጅና የማያፈጅ የመንግሥትነት እሳቤ አልፋና ኦሜጋ፣ በማንኛውም ዘመን በምንም የማይካካስ፣ መንግሥት የሚባል ተቋም በምድር ላይ እስካለ ድረስ ሁሌም የሚኖረው የመጀመሪያውና የመጨረሻው የመንግሥት ተግባርም ህግና ስርዓትን ማስከበርና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ነው።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ታላቋን አገር ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የለውጡ መንግሥትም ከለውጡ ውስብስብ ባህሪ አንጻር ፤ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ የፀጥታና የደህንነት ችግሮችን በሚጠበቀው ደረጃ ማስቆም አልቻለም ። ችግሮቹ አሁነኛ አለመሆናቸውና ቀደም ሲል በግልጽም በስውርም ከፍያለ ዝግጅት ሲደረግባቸው የቆዩ መሆናቸው ከዛም በላይ ከፍ ባለ የውጪ ጣልቃ ገብነት የተደገፈ መሆኑ ችግሮቹን ውስብስብ አድርጎታል ።
ይህንን የሀገርን ህልውና ጭምር አደጋ ውስጥ የከተተ የፀጥታና የደህንነት ችግር የመቀልበስ ኃላፊነት በዋነኛነት የመንግሥት እንደሆነ ቢታመንም ፤የለውጡ መንግሥት ከተቀበለው በብዙ መልክ የተከፋፈለች ሀገርና በፓርቲ ፖለቲካ የላሸቁ ተቋማት አንጻር ኃላፊነቱ የሁሉም ዜጋ የመሆኑ እውነታ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ።
ለውጡ በራሱ በጥቂት ግለሰቦች ሳይሆን በመላው ህዝባችን መራራ ትግል የመጣ ከመሆኑም አንጻር፤ለውጡ አቅም ገዝቶና ጎልብቶ የተነሳበትን ዓላማ እንዲያሳካ የሕዝባችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ።
በተለይም አሁን ለውጡን ለመቀልበስ ከዛም በላይ ሀገርን ለማፍረስ ከውስጥም ከውጪም ጠላቶቻችን እየተናበቡ ባላቸው አቅም ሁሉ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ ሕዝባችን እንደ ሕዝብ መንግሥትም እንደ መንግሥት ለውጡን ለማሻገር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል!
በተለይም መንግሥት ከዘመን ተሻጋሪ የመንግሥትነት እሳቤዎች ከፍ ባለ መልኩ በአንድ በኩል ለዜጎች ደህንነት በሌላ መልኩ የተጀመረውን ለውጥ በስኬት ለማሻገር ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል። ዓላማችንና ፍላጎታችን ሁሉ ኢትዮጵያ ናት፤ ሁሉንም አሸንፋ እርሷ ለዘላለም ትኑር!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014