“ድንኳን ሰባሪነት” – የፈሊጡ ዳራ፤
ድንኳን አንጣሎ ማሕበራዊ ጉዳዮቻችንን መከወን ሥር ሰዶ ከእኛው ጋር በቤተኛነት የኖረ ባህላችን ነው። ለሠርግ፣ ለኀዘን፣ ለልደትና ለልዩ ልዩ መስተንግዷችን ድንኳን ከትናንት እስከ ዛሬ ተመስጋኝ አገልግሎቱን በመስጠት ዛሬም ድረስ አብሮን ዘልቋል። ጉዳያችን ስለ ድንኳን አገልግሎት ጠሊቅ ትንታኔ ለመስጠት ሳይሆን ከድንኳን ስም ጋር ተያያዥ የሆነን አንድ የጀብደኞች ትርዒት ለማስታወስ ነው።
“ድንኳን ሰባሪ” የሚለው ፈሊጣዊ አባባል የተሸከመው ትርጉም አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ሳይወዱ የሚያዝናና ድርጊት የሚከናወንበት ጭምር ነው። ከላይ በተዘረዘሩት ማህበራዊ ምክንያቶች ድንኳን ጥሎ ወይንም በራስ ግቢና ቤት ውስጥ ደግሶ እንግዶችን የሚያስተናግድ አንድ ባለጉዳይ ከሚገጥሙት ፈተናዎች መካከል አንዱና ተቀዳሚው ምናልባትም አሳሳቢው ፈተና “የድንኳን ሰባሪዎች ወረራ” ሊሆን ይችላል።
“ድንኳን ሰባሪዎች” – “ጠሪ አክባሪ” የሚል መልዕክት ደርሷቸው የሚታደሙ እንግዶች አይደሉም። ደጋሾቹ ራሳቸውም ላያውቋቸው ይችላሉ። እነዚህ “በድንኳን ሰባሪነት” የሚታወቁ ግለሰቦች የሚንቀሳቀሱት በየአካባቢው በተደራጀ ኔት ወርክ ነው። ጉለሌ አካባቢ ያሉ ድንኳን ሰባሪዎች ቦሌ ካሉት ጋር “እኛ ሠፈር ድግስ ሲኖር እናሳውቃችኋለን እናንተም ዘንድ እንዲሁ ግብዣ ሲኖር ቀድማችሁ አሳውቁን” በሚል መሃላ የተቆራኙ ቡድኖች የተደራጁበት የቅልውጥ ማህበር ነው። አልፎ ተርፎም ዘዴው እስከ ሌብነት ደረጃ ሊራዘም ይችላል።
በዚህ ቡድን ውስጥ የተደራጁት ጀብደኞች የሠርግ ዕልልታ በሚደመጥበት፣ የኀዘን እምባ ማድረቂያ ማዕድ በሚቆረስበት፣ የማህበራዊ ፌሽታዎች በደመቁበት ቦታ ሁሉ አይታጡም። ዐይናቸውን አፍጥጠው፣ መጎናጸፊያቸውን አሳምረው እንደ ቅርብ ዘመድ ሳይጠሩ በፊት ወንበር ላይ የሚሰየሙት ከደጋሾቹ እኩል በፈገግታ እየተፍለቀለቁ ወዳጅ በመምሰልና እንዳይጠረጠሩ ከተስተናጋጆቹ ጋር የደራ ጨዋታ በመክፈት ጭምር ነው።
በአነጋገራቸው የማይጠረጠሩ፣ በአለባበሳቸው የማይታሙ፣ በረቀቀ ዘዴያቸው በቀላሉ ሊለዩ የማይችሉት እነዚህ “ማዕድ አድራቂ ቀላዋጮች” የቤቱን ባለቤቶች ሳይቀር “የሚስት የሥራ ባልደረባ ይሆን ወይንስ የባል ወዳጅ” እያሰኙ ከፍ ያለ የማደነጋገር ተሰጥኦ የተካኑ ናቸው። በረኞችን ማነሁለል፣ ቤተሰቦችን ማታለል፣ ታዳሚውን ማጃጃል ሥራቸው አድርገው ህሊናቸውን ለመብል አሳልፈው የሚሸጡት እኒህን መሰል “የድግስ ቤት ፀሮች” ከሆዳቸው ዝክር አልፈው ተርፈው በሌብነት ዘዴያቸው የምን ያህሉን ትዳር እንዳራቆቱ “ቤቱ ይቁጠረው” ብሎ ማለፉ ይቀላል።
ሀገሬን እያቆሰላት ያለው ከሃዲው የውስጥ ጠላት፤
“ሀገር ድንኳን ትኹን፤ ጠቅልዬ የማዝላት፣
ስገፋ እንድተክላት፤ ስረጋ እንድነቅላት”
በማለት ከተቀኘው ደራሲ እኒህን ሁለት ስንኞች ተውሰንና ሀገራችንን “በዘላለማዊ ድንኳን መስለን” ያለንበትን ወቅት በጥቂቱም ቢሆን ለመዳሰስ እንሞክራለን።
“የድንኳን ሰባሪነትን” ፈሊጣዊ አነጋገር በዘመናዊ ትግበራ ሥራ ላይ አውለው ዓለም አቀፍ “ቀላዋጭ” የሆኑት ጀብደኞች “የሉዓላዊነታችንን ድንኳን” ሰብረው ለመግባት ያለ የሌለ ኃይላቸውን አስተባብረው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ሰነባብቷል። ይህ “የድንኳን ሰበራ” ከበባ ከጊዜያዊ ፍላጎት ማርኪያነት ከፍ ብሎ ሀገርን ራሷን “እስከ ማፈራረስ” የተመከረበትና የተሴረበት ስለመሆኑ ድርጊቶቹ አፍ አውጥተው እየመሰከሩ ነው። ነብየ እግዚአብሔር ዕንባቆም “የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ” (ትንቢተ ዕንባቆም 3፡7) ያለው ትንቢታዊ ቃል ምናልባትም ይህንን መሰሉን የእኩያን ተግባር ከዘመናት በፊት ለማመልከት ይሆንን ያሰኛል።
ሀገርን እያፈራረሰ ሲመራ የኖረ ግፈኛ ቡድን፤ ለማፍረስ የተሳነውን ደግሞ ሌሎች የውጭ ጠላቶች ተባብረው እንዲያፈርሱ በትጋት ሲያመቻች ኖሮ ያለፈ አሸባሪው ህወሓት ይሉት የክፋት ጥግ ተግባሩ በዓለማችን ላይ እስከ ዛሬ ተስተውሎ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በነባር ታሪኮች ብቻም ሳይሆን ወደፊትም ሊደገም ይቻላል ብሎ ማሰብም በራሱ አዳጋች ነው። የሚመራውን ሀገር እየናደ፣ በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ ቂም ይዞ እያባላ ለሦስት ዐሠርት ዓመታት የዘለቀ ወንጀለኛ ሥርዓት ከአሸባሪው ህወሓት ውጭ ምድራችን አብቅላ ነበር ብሎ የሚከራከር ተሟጋች ስለመኖሩም መገመት ይከብዳል። ምክንያቱን ደግመን አጽንኦት እንስጠውና ህወሓትን መሰል ከሃዲ ቡድን ከአሁን ቀደም ዓለማችን አላፈራችም ለወደፊቱም ይፈጠራል ተብሎ ስጋት አይገባም።
ይህ የጥፋት ኃይል ከሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓትና ከዘረፋ ድርጊቱ ከሥሩ ተነቅሎ ከተወገደ በኋላ የፈጸማቸውን ሀገራዊ ክህደቶችና ሠይጣናዊ ተግባሮች ዘርዝሮ ለመጨረስ ሰፋ ያሉ የዓመታትን ዕድሜ ይጠይቃል። በሀገር ሀብት ዘረፋ ተተኪዎቹን እኩያን ለመፈልፈል የሄደበት ርቀት፣ በጀግናውና አይደፈሬው የመከላከያ ኃይላችን ላይ የፈጸመውና በታሪክ ፊት ይቅር የማያሰኘው ክህደት፣ ሰላማዊ የሀገሪቱን ክልሎች በመድፈርና በመውረር የፈጸማቸው የንጹሐን እልቂቶች፣ የጭካኔ ተግባራትና የዘረፋ ድርጊቶቹ የአውሬነት ባህርይው መገለጫዎች ስለመሆናቸው ተነግሮና ተዘክሮ ስለማያልቅ ለታሪክና ለትውልድ ፍርድ ማቆየቱ የተሻለ ይሆናል።
ወደፊት በሚገባ ሊጠናና ሊተነተን የሚገባው ሌላው ተጓዳኝ ጉዳይ የዚህ የአሸባሪ ቡድን መሪዎች በርግጡ ይህንን ሁሉ ግፍ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሲፈጽሙ ይነዱ የነበረው በሰውኛ ምክር ነው ወይንስ መናፍስታዊ አጋንንቶችም የአሸባሪው ህወሓት አባላት ሆነው ይረዷቸው ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ ቢጠየቅ ተገቢ ይሆናል። ግልጽ ያለውን የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ግን ለጊዜ ጊዜ መስጠቱ ግድ ስለሚል ወደፊት መጋረጃው ሲገላለጥ እውነቱን እንረዳለን።
በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱ ዓለም አቀፍ “ድንኳን ሰባሪዎች”፤
አሸባሪው ህወሓት የሚሉትን የጥፋት ኃይል ለአን ዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስትንፋሱን ነጥቆ ለማስወገድ በሚደረገው ሉዓላዊነትን የማስከበር ፍልሚያ የዓለም አቀፋዊ “የድንኳን ሰባሪዎች” ሽር ጉድ በእጅጉ ለግርምት የሚዳርግ ነው። ቢሆንላቸው ቡድኑን ወደ ሥልጣን ለመመለስ ካልሆነላቸውም እድገታችንን ለማደናቀፍ መድከማቸው እያሳጣቸው መሆኑን እንኳን የተረዱት አይመስልም።
እነዚህ ሳይጠሩ አቤት ባይ ዓለምአቀፋዊ ቀላዋጮች ከፊሉ የኢኮኖሚ ጡንቻቸውን፣ ከፊሉ የሚዲያ የአየር ሞገዳቸውን፣ ከፊሉ የተራድኦ ስንዴያቸውን፣ ከፊሉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ የሚሰኝ ስማቸውን፣ ከፊሉ የሽምግልና ካባቸውን ወዘተ. ሽፋን በማድረግና በማመካኘት በራሳችን የብሔራዊ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተን ካልፈተፈትን በማለት ሉዓላዊ “ተራዳችንን” ሰብሮ ለመግባት የሚያደርጉት ያፈጠጠ ሙከራ እብደትና እብሪት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ስያሜ ሊሰጠው አይችልም።
በግልግል መሃል ዱላ ለማቀበል የማትሰንፈው አሜሪካና በአንድ የፖለቲካ ሳምባ አብረው የሚተነፍሱት ብጤዎቿና “በአርቴፊሻል ኅብረት” የተደራጁት አን ዳንድ የአውሮፓ ሀገራትም በተጠለሉበት ሰባራ የኅብረት ጃንጣላ ሥር ተሰባስበው በማያገባቸው እየገቡ መዶለታቸው እንኳንስ እኛን ባለጉዳዮቹን ቀርቶ የራሳቸው ህሊናም እንኳን ሳይታዘባቸው የሚቀር አይመስለንም።
አንዴ የህዳሴ ግድባችንን ማእከል አድርገው በታሪካዊ ጠላቶቻችን ጀርባ ላይ እየተፈናጠጡ እጃችንን ሊመጠምዘዝ ይፈልጋሉ። ይህም አልሆን ሲላቸው “ማዕቀብ” ይሉት መዝሙራቸውን እየዘመሩ ሊያስፈራሩን ይሞክራሉ። ደስታችንን ለማጠለሸት፣ በኀዘናችን ለመሳለቅ፣ ከጥረታችን ለማሰናከልና ከብልጽግናችን ጉዞ ለመግታት የማያደርጉት ጥረትና ዘመቻ እንደሌለ እያስተዋልን ነው። የእነርሱ ዋነኛ ምኞት “ድንኳናችንን ሰብሮ በመግባት” ተከፋፍለን እንድንነካከስና በደካማዋ ኢትዮጵያ ለመሳለቅ ነው። እንዴት እንፈቅድላቸዋለን ?
ሀገሬ በአፍሪካ ቀንድ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናና በመላው የአፍሪካ አህጉር እንደ መብራት ማማ (Lighthouse) ከፍ ብላ እንድታበራ አይፈልጉም። የድህነታችንን ቱሻ በጣጥሰን ራሳችንን እንድንችልም አይፈቅዱም። ምኞታቸው አጥንት የሌላት ኢትዮጵያን ማየት ነው። ቢቻልም መንግሥትና ፖለቲካዊ ሥርዓታችን ልምሻ ቢጣባውና የእንፉቅቅ እየሄድን እጃችንን ለእርጥባን በመዘርጋት ብንማጸናቸው ደስታቸው ነው። የኢትዮጵያ ከፍታ እንኳንስ በተግባር ተገልጦ ማየት ቀርቶ በአፍ እንኳን ሲወራ የተቆራኛቸው ቆሌ እየተደናገጠ ያስበረግጋቸዋል።
የእነርሱ አፈቀላጤ የሆኑና ታላላቅ ስም ኖሯቸው በታናናሽ “ብዕረ ዱልዱም” ጋዜጠኞቻቸው የሚመሩት የሚዲያ ተቋማትም ሳይቀሩ “በድንኳን ሰባሪነት” ተልዕኮ ላይ መሠማራታቸው በእጅጉ የሚያሳፍር ነው። የሚያሳፍረው በተግባራቸው ለምንኮንናቸው ለእኛ እንጂ እነርሱማ “ነውራቸው ክብራቸው” ስለሆነ ድርጊታቸውን የሚቆጥሩት እንደ መልካም ጀብድ ነው።
በሰብዓዊ መብት ተከራካሪነትና በተራድኦ ተግባር ግብራቸውን ሳይሆን ስማቸውን ሲገነቡ የኖሩ አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማትም እንዲሁ “በድንኳን ሰባሪነቱ” ሰልፍ ውስጥ ተሰይመው ማስተዋል በእጅጉ የሚያሳፍር ነው። በተለይም የተራድኦ በጎ ሥራ እንሰራለን በማለት ባጃቸውን የሚያሳዩን የእነዚህ ተቋማት ሠራተኞች የመሃላ ኪዳን ገብተው እንመራበታለን ካሉት መርህ በማፈንገጥ ለአሸባሪው ህወሓት ቡድን የሎጂስቲክ አቅራቢ ደጀን ሆነው መንቀሳቀሳቸውን የተረዳው መንግሥት በቅርቡ የወሰደውን እርምጃ እናስታውሳለን።
እንግሊዛዊው ደራሲና የCNN ጋዜጠኛ የነበረው ግራሃም ሐንኩክ ከዓመታት በፊት ያሳተማቸው ሁለት መጻሕፍት (Lords of Poverty እና Ethiopia: The Challenges of Hunger) በተራድኦ ስም ሲሰሩ የነበሩ ድብቅ ዓለም አቀፋዊ ሴራዎችን ያጋለጠው በድፍረትና በግልጽነት በማስረጃ አስደግፎ ነበር። ያኔ በመሽኮርመምና ከመጋረጃ ጀርባ እየተደበቁ ይፈጽሙ የነበረውን ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊታቸውን ዛሬ በግላጭ ሲከውኑት ማስተዋል የተለመደ ክስተት ሆኗል።
ከዓለም ማሕበረሰብና መንግሥታት ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ መጓዝ የነበረ፣ ያለና የሚኖር የፀና የሁሉም የጋራ መርህ ነው። አገራችንም ከዚህ እውነታ አፈንግጣ አትቅረቡኝ የምትል ደሴት ልትሆን እንደማትችል አልጠፋንም። ሰጥቶ የመቀበል መርህንም (Win-Win Strategy) ተቀበይ ተብላ የምትመከር አይደለችም። ታሪኳና ተሞክሮዋ ለሌሎች ምሳሌ ይሆን ካልሆነ በስተቀር አንዳችም የሚያሸማቅቅ የተደበቀ ገመና የላትም።
ይሄ ማለት ግን በራሷ ሉዓላዊ ክብርና ጉዳይ ላይ “ለድንኳን ሰባሪ” መንግሥታትና ተቋማት ትንበርከክ ማለት አይደለም። በፍጹም። እጆቿን ለባርነት ሰንሰለት ዘርግታ ለመዋረድም አትፈቅድም። እርዳታ፣ ድጋፍና ብድር በምንም ተዓምር በነፃነታችን ላይ ጥላቸውን አጥልተው ለትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ ሊያኖሩብን አይገባም። የእኩይ ሴራቸው “ጢስ” እያፈነንም ማስነጠስ አንሻም።
“ድንኳን ሰባሪዎቹ” ጀብደኞች ኢትዮጵያን እንኳን ሊያፈራርሷት ቀርቶ በጣታቸው እንኳን እንዲጠነቁሉ ልንፈቅድላቸው አይገባም። የታሪካችን ዐምድ የቆመው በደምና በአጥንት ተለውሶ ነው። መሠረቱም የተገነባው ጠልቆ እንጂ በድቡሽት ላይ አይደለም። ዜጎች በሉዓላዊነታቸው ክብር እንዳይደራደሩ መሃላው በኪዳን ማኅተም ታትሞ የደረሰን በክብር ነው። እንዴት ክብራችንን ለውስጥ ጠላቶቻችንና ለውጭ “ድንኳን ሰባሪዎች” እንዲያዋርዱት አሳልፈን እንሰጣለን? “ኢትዮጵያ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!” ያለው ማን ነበረ? ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014