ሕዝብ ለመሰኘት የሚበቃው የግለሰቦች ቁጥር ምን ያህል ነው? ቡድኖችን ወይንም የጥቂት ግለሰቦችን ስብስብስ ሕዝብ ማለት ይቻላል? የመንግሥት መንግሥትነት መገለጫዎችስ ምን፣ እንዴትና እነማን ናቸው? በእርግጥስ “የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ ነው?” መንግሥትና ሕዝብስ አንደበትና ጆሮ ተዋውሰው ያውቃሉ? እኒህን መሰል በርካታ ጥያቄዎች ለዘመናት ምላሽ ሳያገኙ እየተንከባለሉ እኛ ዘንድ ደርሰዋል፤ ዛሬም የሚመጥናቸው ምላሽ ሊገኝላቸው ስላልቻለ “የእንቆቅልሻቸው ፍቺ ድፍን ዕንቁላል እንደሆነ” ወደ ነገው ትውልድ እየተንሸራተቱ ከእንፉቅቅ ጉዟቸው አልገቱም።
ቁጥሩና ባህርይው ምንም ይሁን ምን ሕዝብ ሲናገር መንግሥት፣ መንግሥትም ሲናገር ሕዝብ ለመደማመጥ እኩል ኃላፊነት አለባቸው። ይህም ሲባል ግን በለሆሳስ ለሚነገሩት፣ በሹክሹክታ ለሚታሙት፣ በኡኡታ ለሚገለጹት “ሕዝባዊ ጉዳዮች” በሙሉ አንዱ አካል ጠያቂ ሌላኛው አካል ተጠያቂ ሆነው አታካራ በመግጠም ይሟገቱ ወይንም ይፋለሙ ማለትም አይደለም፤ በጭራሽ።
ለርዕሰ ጉዳዩ ገልጽነት እንዲረዳ ስለ ኮሙዩኒኬሽን ምንነት ጥቂት መሠረታዊ ጉዳዮችን እናስታውስ። ኮሙዩኒኬሽን የሚለው ቃል እንደ ብዙዎቹ የባዕድ ቃላት ለባህሎቻችንና ለቋንቋዎቻችን ቤተኛ ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል። ወደ ምዕተ ዓመት እየገሰገሰ ባለው የሀገራችን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ምክንያት “ኮሙዩኒኬሽን” የሚለው ቃል ከሕጻናት እስከ አዛውንት በዕለት ተዕለት ንግግራችን ውስጥ ሳይጠቀስ አያልፍም። መሠረቱን ከላቲን ቋንቋ (Comunis) ያደረገው ይህ ጽንሰ ሃሳብ የያዘው ትርጉም ረቂቅና ጠሊቅ ሲሆን “የጋራ የሆነን ጉዳይ በእኩልነት መጋራትና በስሜት ቁርኝት መተሳሰርን” የሚገልጽ ነው።
ኮሙዩኒኬሽን ለሚለው ቃል “ግንኙነት ወይንም ተግባቦት” የሚሰኙት ሁለት የአማርኛ ፍችዎች ተደጋግመው በተለዋጭ ፍቺነት ቢቀርቡም ኦርጂናል ጽንሰ ሃሳቡን ለመሸከም ደከም ሲለሚሉ የተለመደው ቃል “ቤተኛ” እንደሆነ እንዲቀጥል የዚህ ጸሐፊ አቋም ነው። ኮሙዩኒኬሽን ለሰብዓዊነታችን መገለጫ እንዲሆን ለሰው ልጆች ከፈጣሪ ዘንድ የተሰጠ የሕይወት ምራቂ ወይንም ድጎማ ሳይሆን ማንነታችን ራሱ የተገነባበት ምሥጢራዊ የህልውናችን ማሳያ ጭምር ነው። የሰው ልጅ ያለ ኮሙዩኒኬሽን መኖር እንደማይችል የዘርፉ ምሁራን አስረግጠው አስምረውበታል።
ኮሙዩኒኬሽን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ በማስተዋልም ሆነ ባለማስተዋል፣ ይሁነኝ ብለንም ሆነ በስህተት የሚፈጸም ተፈጥሯዊና የማያቋርጥ ሂደት ነው። ስሜታችንን፣ ሃሳባችንን፣ መረጃችንን፣ ዕውቀታችንን ወዘተ. የምናስተላልፈው በንግግር (Verbal) ወይንም በቃል አልባ (Nonverbal – ልዩ ልዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችንና መሰል ዝርዝር ጉዳዮችን ያካትታል) አማካይነት ነው። በእነዚህ ተፈጥሯዊ የግንኙነት ዘዴዎች መልዕክት እንቀበላለን፣ እናስተላልፋለን፣ የተቀበልነውን መልዕክትም በውስጣችን እናብሰለስላለን፣ እናገናዝባለን፣ አስፈላጊ ሲሆንም ውሳኔ ለመስጠት እንገደዳለን።
የኮሙዩኒኬሽን ተመራማሪዎች በተለየ ሁኔታ የቃል አልባ ግንኙነት አስፈላጊነትን የገለጹት እንዲህ በማለት ነው። “የውስጥ ስሜታችንን የምንስለው በሚዳሰሰው የአካላዊ ማንነታችን ሸራ ላይ ነው። ያንን የማንነታችንን እውነታ ከምንስልበት ሸራ ላይ ሰዎች የሚያነቡት በቃል አልባ ግንኙነታችን አማካይነት በቀላሉና ሳይቸገሩ ነው።” ይህን መሰሉ የቃል አልባ እንቅስቃሴያችን በአደግንበት ባህላችን ዐውድ መሠረት በቀላሉ መልዕክት ለመቀበልና ለማስተላለፍ ብቁና ተገቢ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ብዙዎች ናቸው።
የኮሙዩኒኬሽን ማዕከላዊ አገልግሎት መልዕክት አስተላላፊውና መልዕክት ተቀባዩ በእኩል ደረጃ አንዱ አንዱን መረዳት መቻላቸው ነው። መግባባት ካልተቻለና መልዕክቱ በአግባቡ መድረሱ ካልተረጋገጠ ግቡ ምንም፤ ውጤቱም ምንም መሆኑ አይቀሬ ይሆናል። ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስዔው ደግሞ በተለያዩ አደናቃፊ ውስጣዊና ውጭአዊ ችግሮች አማካይነት መልዕክቱ በአግባቡ እንዳይደርስ መደናቀፉ ነው።
ሕዝብ ሲናገር መንግሥት ያድምጥ፤
ሕዝብ የሚሰኘው የአንድ ሀገር ታላቅ ሠራዊት ፍላጎቱና ጥያቄው የቁጥሩን ያህል የት የለሌ ነው። ለዚህ እውነታ ማሳያነት ምንም እንኳን ጉዳዩ አነስተኛ ቢመስልም ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው በየተቋማቱ ተገሽሮ የሚስተዋለው “የአስተያየት መስጫ” ሳጥን ነው። ተገልጋዮች በጽሑፍ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የሚበረታቱበት ይህን መሰሉ ሳጥን ብዙ ጊዜያት በበርካታ ቁጥር የሚከማችበት ብሶት፣ ስሞታና የእንግልት ጥቆማዎች እንጂ ምስጋናና ውዳሴ እጅግም በአስተያየት ሰጭዎች አይደፈሩም።
ሕዝብ ስንል የመላው ሀገሪቱን ዜጎች ማለት ብቻም ላይሆን ይችላል። ውሱን የማሕበረሰብ ክፍል አባላትም የሕዝቡ ክፋይ ናቸው። “ወደ ፈጣሪ በጸሎት፤ ወደ መንግሥት ለብሶት” መጮኽ ያለና ወደፊትም የማይቋረጥ የሰብዓዊ ተፈጥሯችን መገለጫ ነው። መንግሥት ከሚመሰገንበት ቁጥር ይልቅ የነቀፋው አሀዝ መብዛቱም ስለዚሁ ነው።
ሕዝብ ስሜቱን፣ ደስታውን፣ ብሶቱን፣ ሀዘኑንም ሆነ መከፋቱን የሚገልጸው በንግግሩ፣ በመደበኛው ወይንም በሶሻል ሚዲያዎች አማካይነት ብቻ አይደለም። እንደዚህ የሚታሰብ ከሆነም ስህተት ነው። በቃል አልባ ኮሙዩኒኬሽን የሚገለጸው የሕዝብ እምባና ዝምታም ከቋንቋ የበረታ ኃይል አለው። ሕዝብ በዝምታው መሪዎቹን ያከብራል፤ በዝምታውም መሪዎቹን ይረታል። ከተገለጠ ሮሮና ጩኸት ይልቅ መሪዎችን በዝምታ የተዋጠ ሕዝብ የሚያስደነግጣቸውም ስለዚሁ ነው። ከግብር ጋር ተያይዞ “ሕዝቡ ምን አለ?” የሚለው የምኒልክ አባባል እዚህ ቢጠቀስ ቦታው ነው።
ሕዝብ መሪዎቹ ልብ ተቀልብ ሆነው ጆሮዎቹን እንዲያውሱት ብቻ ሳይሆን ድምጻቸውንም ለመስማት በብርቱ ይሻል። የመሪዎች ድምጽ ሲጠፋ ሕዝብ ይደነጋገራል። ለጥያቄዎቹ ሁሉ የሚያረካ መልስ ባይሰጠውም ሕዝብ አድምጬሃለሁ መባልን አጥብቆ ይፈልጋል። የሕዝብ ድምጽ ወደ መሪዎቹ የሚፈሰው ልክ እንደማያቋርጥ ጅረት እየፈሰሰ ነው። የጅረቱ ፍሰት በአንድ አቅጣጫ ከሕዝብ የሚመነጭ ከሆነም በራሱ ችግር ነው። መሪዎች ለሕዝቡ አድማጭ ጆሮ እንደሰጡት በሚገባው ቋንቋ ሊገለጹለት ይገባል።
የሕዝበ እስራኤሉ መሪ ሙሴ ለአርባ ቀናት ያህል በተራራ ላይ የሰነበተው ለሕዝቡ የሚበጅና የሚጠቅም ትዕዛዛትን ከፈጣሪ ዘንድ ለመቀበል ነበር። ለምን ወደ ተራራ መውጣት እንዳስፈለገውና የዚያን ያህል ቀናትም በተራራው ላይ መሰንበት እንደተገደደ በእርሱም ሆነ በረዳቶቹ አንደበት ተልዕኮው በአግባቡ ኮሚዩኒኬት ባለመደረጉ መሪያቸው ጥሏቸው የጠፋ ወይንም የተሰወረ መስሏቸው ሕዝበ እስራኤል በእጅጉ እንደተጨነቁ ቅዱሳት መጻሕፍት ታሪኩን ያስነብቡናል።
መሪያችን ሳይነግረንና ምክንያቱን በዝርዝር ሳያስረዳን ከጠፋ ወይንም ከሞተ አለያም ከረሳን ምን ተስፋ ይኖረናል በማለት የራሳቸውን የጣዖት አማላክት በማበጀትና ለእርሱም በመስገድ የፈጣሪ ምትክ አድርገው ወደ ነበሩበት የባርነት ሕይወት ለመመለስ አላመነቱም። እውነት ነው አይፈረድባቸውም። ሙሴም ከተራራው ላይ ሲወርድ ስህተት እንደ ሰራ እንኳን ስላልገባው ሕዝቡ የወሰደውን እርምጃ ሲሰማ በራሱ በፈጣሪ እጆች ተቀርጾ የተሰጠውን የዐሠርቱን ቃላት የምስክር ጽላቶች በንዴትና በቁጣ ሰባብሮ በመጣል የማይገባውን ኃጢአትና ነውር ሰርቷል።
ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሊኖሩት ይችላሉ። የዕለት እንጀራውና የዓመት ቀለቡ ያሳስበዋል። ሰላሙና ጸጥታው እንዳይናጋም ይሰጋል። የሀገሩ ጉዳይ፣ እምነቱ፣ ሃይማኖቱ፣ ታሪኩ፣ ባህሉና ወጉ የሁልጊዜም “ትዝታዎቹ” ናቸው። ከመንግሥታዊም ሆነ ከመሰል ሌሎች ተቋማት አገልግሎት አሰጣጡ እንዲቀላጠፍለት ይፈልጋል። መብቱን ሲጠይቅም “እውነት ነው ይገባሃል” ተብሎ ማረጋገጫ እንዲሰጠው ይሻል። የሕዝብ ጥያቄ ዘርፉም፣ ቀለሙም፣ ዓይነቱም ብዙ ነው። ሕዝብ ለሚጠይቀው ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ይሰጠዋል ማለት ግን በፍጹም የሚቻል አይደለም።
መንግሥት ለሚጠየቃቸው ጥያቄዎች ሁሉ “እሺ! ምን ችግር አለ!” ብሎ ቅጽበታዊ መልስ እንዲሰጥም አይጠበቅም። የሚቻለው ከሆነ ለአንዳንዱ ጥያቄ ምላሹን ሰጥቶ ለማይቻለው ደግሞ “ጊዜው አሁን አይደለም፣ ትንሽ ይዘገያል” ማለት ብልህነት ነው። ጫን ካልም ከበቂ ማብራሪያ ጋር “አይቻልም!” ብሎ እውነቱን ፍርጥ አድርጎ ለጠያቂው ሕዝብ ማሳወቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
ለዚህም ነው “ሕዝብን በሽንገላ ከመደለል ይልቅ እውነቱን አብራርቶ ማስረዳት” ይበልጥ ውጤታማ የአመራር ስልት ነው የሚባለው። እውነት የሆነ ነገር ሁሉ ላይነገር እንደሚችልም ሊዘነጋ አይገባም። ባዕዳን “All truths are not to be told” የሚል ዝነኛ አባባል አላቸው። ወደ እኛ ቋንቋ ሃሳቡን ስንመልሰው ከላይ እንደገለጽነው ሁሉ “እውነት የሆነ ነገር ሁሉ አይነገርም” የሚል አቻ ፍቺ ይሰጠናል።
በየደረጃው ያሉ መሪዎች በራሳቸው መዋቅርና አሠራር የሕዝብን ቃል ለመስማት ጆሯቸውን መክፈት ብቻም ሳይሆን ቃል አልባ የኮሙዩኒኬሽን መልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴዎችንም ዓይናቸውን ገልጠው ሊያስተውሉ ይገባል። ብዙ ጊዜ ሕዝብ የሚያኮርፈውና የሚቀየመው፤ ከፍ ሲልም ለአመጽ የሚተባበረው መሪዎቹ አልሰሙኝም በሚል ምክንያት መሆኑ የታወቀ ነው።
ሕዝብም መንግሥትን ያድምጥ፤
ታላቁ የሥነ ጽሑፍ አርአያ ሰብ ከበደ ሚካኤል “አዝማሪና የውሃ ሙላት” የሚል አንድ ተጠቃሽ የዕድሜ አረጋዊ ግጥም አላቸው። ታሪኩ በአጭሩ ወንዙ ሞልቶ አላሻግር ስላለው አንድ አዝማሪ የሚተርክ ነው። አዝማሪው መሰንቆውን እየከረከረ በወንዙ ዳር ቆሞ እንደ ብሩቱ ፈረሰኛ የሚጋልበው ወንዝ እንዲጎድልና እንዲያሻግረው በዘፈን ማባበሉንና ማሞጋገሱን የተመለከተ ሌላ መንገደኛ “የዋሁን አዝማሪ” እንዲህ ሲል ይመክረዋል።
”እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ፣
ያልሰማው ሲመጣ፣ የሰማው ሲሄድ፣
ድምጹን እያውካካ መገስገሱን ትቶ፣
ማን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ።‘
የሕዝብን ጥያቄ በዚህን መሰሉ የወንዝ አወራረድ ብንመስለው ጉዳዩን አያሳንሰውም። ጀማው የሚያነሳቸውን እንደ ጅረት የሚፈሱና የማያቋርጡ ጥያቄዎች፣ ብሶቶች፣ ሮሮዎች፣ ስሞታዎች፣ ወዘተ. መቶ በመቶ መልሰው የተጨበጨበላቸው መሪዎች በዓለማችን ላይ ስለመፈጠራቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ወደፊትም መሰል መሪዎች ይፈጠራሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። የሕዝብ ጥያቄ ፍሰቱ ተቋርጦ በማያውቀው በእኛው ዐባይ ወንዝ ቢመሰል ተገቢ ይሆናል።
ምናልባት የይዘት መጠኑ ይቀንስ ካልሆነ በስተቀር የወንዙ ፍሰት እንደማያቋርጥ ሁሉ የሕዝብ ጥያቄም እንዲሁ ነው። ጥያቄዎች ሊዥጎደጎዱ ይችላሉ፣ መንግሥትም ይተቻል፣ ይታማል፣ ይገሰጻል፣ ጠርጥረነዋል ሊባልም ይችላል። ብቻም አይደለም በሌላም መልኩ መንግሥት ይመሰገናል፣ ይወደሳል፣ ይሰደባል፣ ይነቀፋል … የተዥጎረጎረውና የማያቋርጠው የሕዝብ ስሜት ከወንዝ ፍሰት ጋር ካነጻጸርነው ምሳሌም ሊበረታ ይችላል።
የሚሻለው ሕዝባዊውን የጥያቄና የአስተያየት ጎርፍ፣ የብሶትና የሮሮውን ዶፍ ለጊዜው ገታ አድርጎ የመንግሥትን ምክንያትና ምላሽ ማድመጥ “ከብልህ ሕዝብ” የሚጠበቅ ኃለፊነት ነው። ጥያቄን በጥያቄ እያነባበሩ መንግሥትን መሞገትና ማደነጋገር ምንም እንኳን “ዴሞክራሲያዊ መብት” የሚሰኝ ላይሰንስ ቢሰጠውም ወቅትና ሁኔታውን በማገናዘብ “ትንፋሽን ዋጥ አድርጎ” ሰበበ ምክንያቱን ከራሱ ከመንግሥት ወኪሎች አንደበት ማዳመጥ ከብዙ አደጋ ይታደጋል።
በተለይም እንደ ዛሬው እንደ እኛ የሀገር ምጥና ጭንቀት በከፋበትና እኩይ ዓለም አቀፍ ሴራዎች በረቀቀ ስልት እየተጎነጎኑ በምንፈተንበት ወቅት ሕዝብ ሰከን ብሎና ጉዳዩን በሚገባ አጢኖ ለችግሩ ስብራቶች ሳይሸነፍ፣ ለመከራው ሸክምም ወገቡ ሳይጎብጥ እየተረዳዳ መረጋጋቱ አማራጭ የለውም። የሕዝብ ጠበቃዎች ነን፣ አንቂዎች ነን ወዘተ. የሚሉ ፊት-ቀደም ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሕዝብ የስሜት ቁጣ እንዲገነፍል እሳቱን ከማግለብለብ ይልቅ ረጋ ብሎ ሕዝቡ ራሱ ነገሮችን በጥሞና እንዲመለከት ሊያግዙት ይገባል።
ሕዝብና መንግሥት መደማመጥ ከተሳናቸው ክፍተት ተፈጥሮ በሮች የሚከፋፈቱት ለጠላቶች መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በተለይም ዛሬ ሀገራችንን የውጥር ሰንገው የያዟት ኃይላት የምናውቃቸውና እየተፋለምናቸው ያሉት የውስጥ ጠላቶቻችን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ባላጋራዎቻችን ቁጥርና ዓይነትም ከ እስከ ከ የሚባል አይደለም። በዚህ ወቅት ሕዝብና መንግሥት አንደበትና ጆሮ እየተዋዋሱ ለክብርና ለነፃነት መቆም ካልተቻለ የተጠመዱልን ፈንጂዎችና የተዘረጉልን አሸክላዎች የሚያደርሱብንን ታሪካዊ መከራ ለመገመት አይከብደም። ስለዚህም ነው ሕዝብ ሲናገር መንግሥት፤ መንግሥትም ሲናገር ሕዝብ ያድምጥ፣ በመካከላቸውም መተማመን ይኑር የምንለው። ሕዝብ በድምጹ መንግስት በልሳኖቹ በመጯጯኽ ብቻ አተርፋለሁ የሚባል ከሆነ “በጥፋት ንግዱ የሚከብሩት” ያሰፈሰፉት የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን መሆናቸው በሚገባ ሊጤን ይገባል። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2014