ክፉ ሰዎች ለክፋት አላማቸው የሌሎችን የአዕምሮ ከንቱነት ይጠቀማሉ። ምክንያቱም ባለ ከንቱ አዕምሮ የተባለውን ሳያመዛዝን የሚያምን፤ የመጣለትን ሳይመዝን የሚቀበል፤ አድርግ ያሉትን ለምን ብሎ ሳይጠይቅ ለማድረግ የሚንደረደር ሰብዕናን የተላበሱ ናቸው እና ነው። ክፉ ሰዎችን ይሄን በወጉ ስለሚረዱ ለእኩይ ዓላማቸው፣ ለሽብር ተግባራቸው በዚሁ ላይ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ፤ አበው “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉም በብዙ ቦታዎችን በዚህ ተግባራቸው ውጤታማ ሲሆኑ ይታያሉ።
ዛሬም አሸባሪው ህወሓት ይሄን የቀደመ ብሂል ተቀብሎ፤ የቀደመ የተንኮል መስመሩን ተከትሎ፣ በከንቱ ሽንገላ እና የበሬ ወለደ የወሬ ፕሮፓጋንዳ ታግዞ ህዝብን በማደናገርና በማሸበር አገር የመበተን ህልሙን እውን ለማድረግ ዘርፈ ብዙ መረቡን ጥሎ እየተጋ ይገኛል። ከዘመኑ ጋር መሻገር፣ ከህዝቡ አሁናዊ ስነልቡና ጋር መታረቅ ያቃተው ይህ የሽብር ቡድን አሮጌውን አቁማዳ ከአሮጌው ወይን ሳይነጥል ተሸክሞ ከእርሱው ጋር ቆመው የቀሩ ከንቱ አዕምሮዎች ካሉ ለማደናገርና ትንሽ የተደናገሩ አካላትን ይዞ ብዙሃንን ለመረበሽ የሚያደርገው ሰሞንኛ ጉዞ የቡድኑን ከቆመበት አሻግሮ መመልከት ያለመቻል ያረጋገጠ ተግባር ሆኗል።
በእርግጥ ነው አሸባሪው ህወሓት በሀሰት ትርክት ተፈጥሮ በዚሁ መስመር ያደገ፤ በውስጡ ያሉት አዛውንቶችም በማደናገር ተረክ የብዙ ንጹሃንን ደም የጠጡ፤ የትግራይ እናቶችም በልጆቻቸው መስዋዕትነት ያገኙትን የተስፋ ብርሃን ያጨለሙ፤ በውሸት ዋሻ ውስጥ ዘለዓለም ተሸሽጎ መኖር የሚቻል የሚመስላቸው፤ በውሸት ኖረው ትውልዱን በሀሰት ወሬ በመንዳት የውሸት ተራራን የገነቡ፤ መቐሌ ላይ ከተቀመጡበት መነሳት ተስኗቸው ሳሉ አዲስ አበባ ለመግባት የሚያግዳቸው አንዳች ኃይል እንደሌለ የሚተርኩ፤ በስተርጅናቸው የህጻናትን ህይወት ቁማር አስይዘው የሚጫወቱ ከሰው ተራ የወረዱ ናቸው።
ዛሬም ዙሪያው እሳት በሆነባቸው ወቅት አዲስ አበባ እንገባለን ባለ አንደበታቸው፣ መቐሌ አናስገባም የሚል ትርክትን የፈጠሩ፤ በአማራ እና አፋር ክልሎች ወርረው በያዟቸው አካባቢዎች በሚፈጽሟቸው የግፍ ተግባራት ታግዘው ህዝብን የማደናገሪያ የሀሰት ፕሮፖጋንዳን በመልቀቅ ህዝብን ለማሸበር እየሰሩ ያሉ ናቸው።
ለዚህ ተግባራቸው ደግሞ የሽብር ቡድኑ አሸባሪ አፈ ቀላጤዎችና አመራሮች በሚጠቀሙባቸው የመገናኛ አውታሮች የሚያሰራጩት የሀሰት ድንፋታና ፉከራ የታጀበ የበሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ አንዱ ሲሆን፤ በግብጽ ሚዲያዎች እንዲሁም ሲኤንኤንን በመሳሰሉ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ሳይቀር የማደናገሪያና የማሸበሪያ ስራቸውን እያስተጋቡ ይገኛሉ።
ሌላኛው የሀሰት መረጃ ማሰራጫ መሳሪያቸው የማህበራዊ ሚዲያው ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚገኙ ቅልብተኛ አክቲቪስቶቻቸው የተራባ ገጽ የሚታገዙበት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ነው። ይህ የፕሮፓጋንዳ መስክ ደግሞ የሽብር ቡድኑ በወረራቸውን የአማራ እና አፋር አካባቢዎች እንደ ማሳመኛ በመውሰድ፤ በቀጣይ እዚህ ከተማ እንደርሳለን የሚል ማሳመኛ ይጠቀማል። ካልሆነም ለገንዘብ ባደሩ የየአካባቢው ጥቂት ግለሰቦች በመታገዝ ጥቂት ሰርጎ ገቦችን በማስገባት ይሄን አካባቢ ይዘናል የሚል የሀሰት መረጃን በመልቀቅ ህብረተሰቡ እንዲረበሽ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።
ይህ የማደናገር ስራው ምንም እንኳን የተሳካለት ባይሆንም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች እና ከተሞች በህብረተሰቡ ዘንድ መደናገጦችንና ግርታን መፍጠሩ አልቀረም። ሆኖም ህብረተሰቡ በጊዜ ሂደት ተገቢውን መረጃ ሲያገኝ፤ እውነቱን ሲገነዘብ የሽብር ቡድኑን የሀሰት ወሬዎች ጆሮ ነስቶ ለጋራ ሰላምና አንድነቱ በጋራ ቆሞ መፋለምን ይዟል።
በዚህ መልኩ የህዝብ ማደናገር ስልቱ የከሸፈበት ይህ የሽብር ቡድን ግን፤ የበሬ ወለደ ወሬውን የሚያዳምጡት እና በየሚዲያዎቻቸው ሳይቀር ተቀብለው የሚያራግቡለት ምዕራባውያኑ (አሜሪካ እና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት) ግልጽ ወደሆነ የአንድ ወገን ወገንተኝነታቸውን እያንጸባረቁ ይገኛል። እነዚህ አገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ በአውሮፓ ህብረት አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር የሽብር ቡድኑን ህልውና ለማቆየት እና ጥቅማቸውን በሽብር ቡድኑ አማካኝነት ለማስጠበቅ እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ይገኛል።
ከሰሞኑም የሽብር ቡድኑ በሁሉም የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ባለበት ወቅት እንኳን “የፌዴራል መንግስት መጠነ ሰፊ ጥቃት እየፈጸመብኝ ነው” ሲል የሽብር ቡድኑ ያወጣውን የሀሰት መረጃ ከማራገብ በተጓዳኝ እውነቱን ለማጣራት የፈለገ አካል አልነበረም። ይባስ ብሎ የሽብር ቡድኑ አጥቅቶ መያዝ ያልቻላቸውን አካባቢዎች በከባድ መሳሪያ ሲደበድብ እና ንጹሃንን እየገደለ፣ ንብረት እያወደመና እየዘረፈ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ምንም እንኳን ያለስምምነት የተቋጨ ቢሆንም የአውሮፓ ህብረት የሽብር ቡድኑን ተግባር ከማውገዝ ይልቅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተሰብስቦ ነበር።
በዚህ ሁሉ ሂደት ግን ኢትዮጵያውያን ለሀሰት ወሬው ጆሮ ነስተው ቅድሚያ ለሰላማቸው እና ለነጻነታቸው ስለ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በአንድ ቆመዋል። በአንጻሩ አሸባሪው ቡድን ለእኩይ ዓላማው የሚጠቀምባቸው … ባለአዕምሮዎች (በአገር ውስጥም ሆኑ በውጭ ያሉ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች እንዲሁም ምዕራባውያን ጭምር) የሽብር ቡድኑን የሀሰት ትርክትና ፕሮፓጋንዳ እንደገደል ማሚቶ ደጋግመው ሲያስተጋቡ ይውላሉ።
በዚህ መልኩ ያለው የሽብር ቡድኑ እና የገደል ማሚቶዎቹ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ቅብብሎሽና ጫና ዋና ዓላማው ኢትዮጵያውያንን በማደናገር ሽብር በመንዛት “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚለውን ብሂል እውን ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ በህዝብና መንግስት፤ በህዝብና የጸጥታ ሃይሉ፤ በጸጥታ ሃይሉና በመንግስት መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬን በመፍጠር ለእነርሱ የሚመች ክፍተትን ለማግኘት ነው።
ይሁን እንጂ በዚህ የሀሰት ሴራም ሆነ የሽብር ቡድኑ የሀሰት ወሬዎች ምክንያት በተፈጠሩ ጫናዎች ያልተንበረከከው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ “ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እርስ በእርሳችን ብልሆች ሁሉ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” እንዲል፤ የሽብር ቡድኑን የሀሰት ተረክ ጆሮ ነስተው ስለህልውናቸው በአንድ ቆመዋል።
ይልቁንም “ለውሸት ሳሱን የሰጠ ከውሸት ተግባሩ ይቆጠብ፤ ለስርቆት የተሰማራ እና የሰረቀም ከእንግዲህ አይስረቅ” እያሉ ለሽብር ቡድኑ አባላት ትምህርት እየሰጡ፤ ከውሸት፣ ከስርቆት እና የሰው ህይወት ከመንጠቅ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካም ሊሰሩ እንደሚገባቸው ለማስተማር ለወገኖቻቸው በመድረስ ከክፋት ይልቅ መልካምነት ዋጋ እንዳለው በማሳየት ላይም ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያን በአንድ በኩል የሰው በሰውነት ውሃ ልክ ላይ ሊቆም፣ የመልካም ሀሳብ እና የበጎ ምግባር ባለቤትነትን መላበስ እንደሚገባው እያስተማሩ፤ በሌላ በኩል ይሄን ማድረግ አልሻም ብሎ በወገናቸው ላይ ሞትና መከራን ለሚጋብዝ የሽብር ቡድን የሚያስተምረውን ቅጣት እየሰጡት ይገኛል።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በወሬ የሚፈታ ጦርም ሆነ የሚፈርስ አገር እንደሌላቸው በተግባር እያሳዩ ያሉበትን ገድል ለወዳጅ ያሳዩበት፤ ለጠላትም ትምህርት የሰጡበት ነው። ምክንያቱም ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን በወሬ የሚፈታ ጦር አልገነቡም፤ ፕሮፓጋንዳ የሚፈርስ ሀገርም አልመሰረቱምና ነው።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2014