ከለውጡ በኋላ ባሉት ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዲስ አበባ ነዋሪዎችን ህይወት በመሰረታዊነት የሚቀይሩ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። በነዚህ ስራዎችም የከተማዋ ገጽታ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተቀየረ ይገኛል። ከተማዋ የአፍሪካ መዲና እና የበርካታ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት መቀመጫ እንደመሆኗ በከተማዋ ሊሰራ ከሚገባው ስራ አንጻር በቂ ነው ብሎ መናገር ግን አይቻልም።
በተለይም የከተማዋን ነዋሪዎች እያማረረ ያለው የኑሮ ውድነት እና የቤት ችግር ማቃለል ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው። በመሆኑም የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት፣ የቤት እና የመጠጥ ውሃ ችግሮችን ለመቅረፍ በ2014 ዓ.ም በርካታ ስራዎች ለመስራት እቅዶች መያዛቸውን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።
የነዋሪውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች መታቀዳቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች፤ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ምርትን በብዛት ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት እንዲሁም በሸማቹና በአምራቹ መካከል ያለውን ሰንሰለት ለማሳጠር የእህል፣ የከብት እናየአትክልት ገበያ ማዕከላት እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
ከአትክልት ገበያ አንጻር ላፍቶ የተገነበው አይነት ሌላ አንድ ትልቅ የገበያ ማዕከል እንደሚገነባ የተናገሩት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ሌሎች ትናንሽ ማዕከላትም በየቦታው እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማዋን በማይመጥን እና ንጽህናዋን በሚያጎድፍ መልኩ በየቦታው እንስሳት መሸጫዎች አሉ። እነዚህ የከተማዋን ንጽህና በጣም የሚፈትኑ ናቸው። እንደ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚታዩ የከብት መሸጫ ገበያ ግንባታም እንደሚካሄድ አንስተዋል። ይሄ ወደ ገበያ ቦታ እንዲሄድ የቁም ከብት ገበያ ማዕከል እንደሚገነባም ጠቁመዋል። እነዚህ የገበያ ማዕከላት የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና በማቃለል ረገድ በጎ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
እንደ ወይዘሮ አዳነች ማብራሪያ ከስልሳ ዓመት በኋላ የመጀመሪያው የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ ይጀመራል። ገርቢ ፕሮጀክት ባለፈው ዓመት የጥናትና ቦታውን የማጽዳት ስራ ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር አልቀዋል። ቦታው ጸድቶ ለገንቢው ኮንትራት ተሰጥቷል። ሰሞኑን ግንባታው ይጀመራል። የበጀት ምንጭም የተገኘ ሲሆን ከገበሬውም ጋር ስምምነት መደረሱን አንስተዋል። ከቦታው የሚነሱ አርሶ አደሮችን ህይወት በቋሚነት ለመለወጥ የሚያስችል ስራዎች ይሰራሉ። በዚህ ግድብ
ምክንያት የሚፈናቀሉ ገበሬዎች ኑሯቸው እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑን ነው የተናገሩት። የካሳ ክፍያ ግማሹ ተከፍሏል። ይሄ ከለገዳዲ ግድብ በኋላ ሁለተኛው ይሆናል። የከርሰ ምድር ውሃ አላቂ ስለሆነ ግድብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
የከተማዋ አንዱ ትልቁ ችግር የመጠጥ ውሃ ችግር ነው። የመጠጥ ውሃ ችግርን በመሰረታዊነት በመፍታት ረገድ ግድቡ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የጠቆሙት።
በተያዘው በጀት ዓመት ከሚደርሱ ፕሮጀክቶች አንዱ ለገዳዲ ቁጥር ሁለት መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች፤ ከሚቀጥለው ጥቅምት ጀምሮ የውሃ ማምረት ስራውን እንደሚጀምር ገልጸዋል።
የሁለተኛው ግድብ ግንባታ ደግሞ ጥናት እየተካሄደ ነው። ሱሉልታ፣ ጫንጮ እና አሌልቱ አካባቢ እየተጠና ነው። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የአዲስ አበባ የውሃ ችግር ከመሰረቱ ይፈታል ብለዋል።
በ2014 ዓ.ም 120 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ለማምረት ታቅዷል። አምና በአዲስ አበባ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መቶ ሜትርክ ኪዩብ ውሃ ማምረት መቻሉን ገልጸው፤ የዘንድሮው በከተማው ታሪክ ከፍተኛው እንደሚሆንም ነው ያብራሩት።
እንደ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጻ፤ የከተማውን ነዋሪ እያሰቃዩ ካሉ ችግሮች አንዱ የቤት ችግር ነው። የቤት ጉዳይ በመሰረታዊነት መፈታት ያለበት ነው። ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ ብዙ ለመስራት ጥረት የተደረገ ቢሆንም የነዋሪዎችን የቤት ችግር በመሰረታዊነት መፍታት አልተቻለም።
በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለባለእድሎች ያልተላለፉ ቤቶችን ለባለእድሎች ለማስተላለፍ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች፤ ይህም በቅርቡ ይተላለፋል ብለዋል። በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ አንድ ሚሊየን ቤቶችን ለመስራት ታቅዷል። ዘንድሮ መጀመር ያለባቸውን የማስጀመር ስራዎች እንደሚሰራም አብራርተዋል።
5 ሺህ የሚሆኑ የ2005 ተመዝጋቢዎች በማህበር ተደራጅተው ለመገንባት ዝግጁ ሆነዋል። ቦታውም ተዘጋጅቶላቸዋል። አሁን ሂደቶችን ጨርሶ ግንባታ የማስጀመር ስራ ብቻ እንደቀረ ነው ያብራሩት።
ከዚህ በተጨማሪም ገንዘብ እና መሬት ያለው ሰው በማገናኘት አንድ ላይ ሆነው የሚሰሩበትን ወደ ስራ የማስገባት ስራ ይሰራል ብለዋል። እነዚህም በዚህ ዓመት ወደ ስራ እንደሚገቡ ነው የተናገሩት። በሌላ በኩል በከተማው በጀት ወደ ዘጠኝ ሺ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት ተደርጓል። እነዚህን ወደ ተግባር ለማውረድ በጥንቃቄ እንደሚሰሩም አብራርተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014