በኢትዮጵያ ዶሮና እንቁላል አዘውትሮ መመገብ እምብዛም አልተለመደም። ከዚህ በተቃራኒ ግን የዶሮ ወጥ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ አድካሚ ከመሆኑ አንፃርም አውድ ዓመት ሲመጣ እንጂ የዘወትር ምግብ አይደለም፡፡ ማጣፈጫ ቅመማ ቅመሙም ብዙ ወጪ ያስወጣል። ከእዚህ አንፃር ኢትዮጵያውያኖች በስፋት የዶሮ ተጠቃሚ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ይሁን እንጂ ዶሮን አርዶ በመጠበስና ከሌሎች ምግቦች ጋር ቀላቅሎ መመገብ ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ መመገብም ለጤና ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፡፡ የዶሮ ዋጋ በአሁኑ ጊዜ በእጅጉ የተወደደ ቢሆንም ከበሬ፣ በግና ፍየል ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የዶሮ ሀብት ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፅጌሬዳ ፍቃዱ እንደሚናገሩት፤ የዶሮና እንቁላል አቅርቦቱን በማስፋት እጥረቱን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በአስር ዓመት ውስጥም 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን እንቁላልና 106 ሺህ ቶን የዶሮ ሥጋ ለማምረት ታስቧል። ከዚህ ውስጥ በ2013 ዓ.ም 3 ቢሊዮን እንቁላል ለማምረት ታቅዶ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን እንቁላል ማምረት ተችሏል። ይህም በአስር ዓመቱ ከታቀደው 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን አፈፃፀሙ 90 ነጥብ 9 በመቶ ነው።
ቀደም ሲል አንድ ሰው በዓመት ይመገብ የነበረው የእንቁላል መጠን 0 ነጥብ 6 በመቶ ኪሎ ግራም ነበር። ይሁንና አንድ ሰው በዓመት ውስጥ እስከ አንድ ኪሎ ግራም ወይም 25 እንቁላል እንዲመገብ በማድረግ የምርት ተጠቃሚነትን በ2 ነጥብ 7 በመቶ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ የተጠናቀቀው ዓመት ከፊተኞቹ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ህዝቡ የተሻለ የእንቁላል ተጠቃሚ ሆኖም ተመዝግቦበታል።
የዶሮ ሥጋን በሚመለከትም 51 ነጥብ 5 ሺህ ቶን የዶሮ ሥጋ ለማምረት ታቅዶ 70 ሺህ ቶን ተከናውኗል። ይህም አፈፃፀሙ ከመቶ በመቶ በላይ ነው። በተጨማሪም 26 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሰራጨት ታስቦ 24 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጫጩቶች ተሰራጭቷል፡፡ ከዚህ አኳያ የ2013 አፈፃፀም ከፊተኞቹ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የእንስሳት ሀብት ልማት ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ ሰፋፊ ዕቅዶች ታቅደው በመሰራታቸው የተሻለ ሆኗል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የመኖ ዋጋ መጨመሩ የዶሮና የእንቁላል ዋጋም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዶሮ እርባታ ከ75 በመቶ በላይ ለመኖ ግዢ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ የአንድ እንቁላል መሸጫ ዋጋ ወደ ስምንት ብር ማደጉ ከፍተኛ ዋጋ ነው ማለት አይቻልም።
ሆኖም የዶሮ ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬ ማህበረሰቡ ካለው አቅም አንፃር ዋጋው ከፍተኛ በመሆኑ ገዝቶ ሊመገብ በሚችል መልኩ መቅረብ አለበት ብሎ አምኗል፡፡ ይህም የመኖ አቅርቦት የሚጠይቅ በመሆኑ አቅርቦቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዋጋ የሚጨምረው የአቅርቦት እጥረት ሲኖር በመሆኑ እጥረቱ በዶሮ ምርት ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ከፍላጎትና ከመግዛት አቅም ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም መስሪያ ቤቱ መኖ ለማልማት እየሰራ ይገኛል። ባለሀብቶችም በመኖ ልማት ዘርፉ እንዲሰማሩ ያበረታታል። ተጨማሪ ፕሮጀክቶችም ተቀርፀው መኖ ልማቱን ለማሳደግ እንዲሁም የዶሮ ምርቱን በመጨመርና የእንቁላል አቅርቦቱን በማሳደግ ረገድ በትኩረት እየተሰራም ይገኛል፡፡ የዶሮም ሆነ የእንቁላል አቅርቦትን እያሳደጉ መምጣቱ ዋጋው እንዲረጋጋና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጥ ብሎም እጥረቱ እንዲቀንስ ያስችላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሲዳማ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ አምስት ክልሎች ላይ ‹‹የቤተሰብ ዶሮ እርባታ›› በሚል የሙከራ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል። ፕሮጀክቱም በአምስቱ ክልሎችና 27 ወረዳዎች እየተተገበረ ነው። ቢሾፍቱ ላይ ያለውን የዶሮ አርቢዎች ጫጩት አሳድገው አቅርቦቱን እንዲያሰፉ በማድረጉ ላይ ይገኛሉ። በፕሮጀክቱ በዓመት ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። በፕሮጀክቱ የመኖ አቅርቦትንም ጎን ለጎን ይካሄዳል፡፡
በዚህ መልኩ እየተከናወነ ከሚገኘው ልማት አንፃር እንደልብ ባይሆንም የዶሮ ሥጋም እንቁላልም በቂ አቅርቦት አለ። ኮቪድ- 19 ሊያሳድር የሚችለውን ተፅእኖ ተቋቁሞ ዶሮና እንቁላል ምርት ከፍተኛ አፈፃፀም ማሳየት ችሏል። በተለይ ደግሞ መኖ ልማት ላይ መሥራት ከተቻለ የዋጋ ንረቱም ሆነ የአቅርቦቱን ችግር መፍታት ይቻላል፡፡ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ስላልተመጣጠነም የዶሮና እንቁላል ምርትን ወደ ውጭ ገበያ የማቅረብ ሀሳብ የለም።
ሆኖም በቀጣይ የዶሮ ሀብት ልማቱ እየጎለበተ ሲሄድ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታስቧል። በሀገር ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማጎልበትም አምራቹ ከሚያመርተው ምርት 15 በመቶውን የአንድ ቀን ጫጩት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ የተለያዩ ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከዚህ በሻገር በመስኩ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች በፖሊሲ፣ በስትራቴጂና በተለያየ ሁኔታ የመደገፍ ሥራ ይሰራል። ድጋፉ የሚፈልጉትን እንዲያገኙ የሚያስችል የድጋፍ ደብዳቤን ከመፃፍ ጀምሮ ሙያዊ ክህሎትን ማስጨበጥንም ያካትታል። በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት መንግስት አብዛኛዎቹ የዶሮ እርባታና ምርት መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑም አድርጓል። በአሁኑ ወቅትም ጫጩት ማስፈልፈያና የተለያዩ መሣርያዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ። ያኔ አቅርቦቱ ስለሚሰፋ የእንቁላልላና ዶሮ ገበያ ይረጋጋል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014