የተጠናቀቀው ዓመት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የደስታ ዘመን አልነበረም። በተባባረ የጀግንነት ክንዳችን ባንደቁሳቸው ኖሮ ሁለቱ ቫይረሶች (ኮሮናና ትህነግ) ዘመን የማይሽረው ጠባሳ ሊያስቀምጡልን ሞክረው ነበር። የኮሮናው ዓለም አቀፍ ስለነበር እሱን ለጊዜው ልተወውና ወደኛ ቫይረሶች ልመለስ።
ለአቅመ ንባብ በደርስኩ ጊዜ በቀዳሚነት ካነበብኳቸው መጻህፍት መካከል ቀሪን ገረመው የሚለው መጽሀፍ አንዱ ነው። መጽሀፉ በሁለተኛው የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ህዝባቸውን ከቅኝ ግዛትና ከባርነት ለመታደግ የተዋደቁትን ጀግኖች የሚዘክር ነው።
ጸሀፊው አርበኛው ታደሰ ዘወልዴ በመጽሀፋቸው መግቢያ በብዙ ድካም ከሸዋ ብቻ ያገኟቸውን ለዚያውም ጥቂት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግኖች ታሪክ ማስቀመጣቸውን አስታውቀዋል። በተለያየ ምክንያት ላላካተቷቸው ደግሞ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ልብ በሉ በዚህ አይነት ታሪካቸውን ብንከትብላቸው ከሁሉም ጠቅላይ ግዛት የሚሰበሰቡት ጀግኖች ቁጥር ስንት ሺ ጥራዝ መጽሀፍ ይወጣው እንደነበር መገመት አያዳግትም። እንግዲህ የመጽሀፉን የውስጥ ታሪክ ለእናንተ ትቼ እኔ ወደ ዋናው መነሻ ጉዳዩ ልመለስ።
እንደየሰው ግላዊ ምልከታ ቢለያይም እኛ ኢትዮጵያውያን ተንኳሽና ወራሪ አጥቶን አያውቅም። እኛም የትኛውንም ሀገር ለመዳፈርና ለመውረር እንዳልሞከርን ሁሉ የትኛውንም ወራሪ ለመመከት ሰንፈን አናውቅም። እንዲያውም በቀደመው ዘመን በአንዲት የክተት አዋጅ ጥሪ ነጋሪት ተጎስሞ ሳይጨርስ ማቄም ጨርቄን ሳይል እየፎከረ በመትመም ነፍሱን ለሀገሩና ለህዝቡ ለመገበር የሚዘምተው ለቁጥር የሚታክት ወጣት ነበር። እንዲህ አይነት የማይናጋ ዘመን የማይሽረው ጀግንነት ስለነበረን በየትኛውም ዘመን ቢሆን ድልን ነጥቆን የሚያውቅ አልነበረም ፤ አሁንም የለም። ወደፊትም አይኖርም።
ይህ እውነታ ደግሞ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ሲያስቡ የቅድሚያ መዳረሻቸው የሚያደርጉት እንደእሳት የሚፋጀውን መሬቷን ሳይሆን የሆዳም ባንዳዎችን ልብ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። በእውነትም የሚፈልጉትን ያህል ውጤት ባያገኙበትም በተወሰነ ደረጃ አላማቸውን ሲያሳኩላቸው የኖሩት እነዚሁ የእናት ጡት ነካሻች ብቻ ናቸው። እኛም ለውጪ ጠላት ክንዳችን ሳይበገር ሁሌም እንቅፋት ሆኖ ሲያስቸግረን የኖረውና አሁንም እየረበሸን ያለው የእነዚሁ የቅኝ ግዛት መርዝ በጭንቅላታቸው የያዙ አልጠግብ ባይ ስመ ኢትዮጵያውያን ተግባር ብቻ ነው።
“ላም እሳት ወለደች “ እንዲሉ ለኛም ጀግኖች እንደ ባእድ ወራሪ አፈር ከድሜ ለማስገባት የሚይዛቸው የወኔ ማጣት አልያም አነጣጥሮ መተኮስ አለመቻል ሳይሆን ነገሩ እጄን በእጄ ሆኖባቸው ነው። የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ደግሞ በጊዜ በቦታና በሁኔታዎች የሚገደብ አይደለም። ሲያስማቸው የኖረውና አሁንም የሚያስማማቸው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች የአሸናፊነት ምስጢሩ ደግሞ ህብረታቸው ነው። ማንም ጀግና ብቻውን ታሪክም ተአምርም ሊሰራ አይችልም። ከእያንዳንዱ የጦር አውድማ ጀርባ በርካታ ደጀን የሚሆኑ ጀግኖች አሉ። የኢትዮጵያ እናቶች እሳትን የሚያውቁት ከምድጃ ስር ብቻ ሳይሆን ከጥይት አሩርም ነው። የደጀን ህዝብ ጀግንነትን ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን የሚያይ ሁሉ የአይን እማኝ ነው። የህክምና ባለሙያው፤ መሀንዲሱ የጥበብ ባለሙያው አራሹ ፤ ተኳሹ….. ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል።
ይህንን ስመለከት አሁን የተነሱብን ኢትዮጵያን ጠል ኢትዮጵያውያን የኖሩባትን ያሳደገቻቸውን ሀገር በውል አያውቋትም ለማለት ያስደፍረኛል። በእነሱ ጠባብ እይታ ራሳቸውን ሊጠብቅ የተቀመጠውን ሰራዊት መተው ሲበትኑ በህጻን ልጅ እፍኝ ውስጥ እንዳለ ገለባ ኢትዮጵያም አብራ የምትበተን መስሏቸው ነበር። ያንን መላ ህይወቱን ዋሻ ውስጥ አድርጎ ሲጠብቃቸው የነበረውን ሰራዊት እሱን ተማምነው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ እንዳልነበር «በመብረቃዊ ጥቃት ለህልውናችን የሚያሰጋንን አስወገድነው» ብለው ፉከራና ቀረርቷቸውን ደርድረዋል።
በእነሱ እይታ ለኢትዮጵያ ያላት መከታ የሰሜን እዝ ብቻ ነበር። ይህንን በድፍረት ሊያስብላቸው የቻለው ደግሞ ሌላ ጀግና እንደሌለ አጥተውት ሳይሆን ለሃያ ሰባት ዓመታት በአዋጅ ያፋታነው ህዝብ ዳግም በሰማኒያ አይጋባም የሚል የቀዘቀዘ እሳቤ ነበር። የቀዘቀዘ ያልኩበት ምክንያት በአንድ ወገን ለሺ ዓመት የኖረ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በሃያ ሰባት ዓመት ስብከት ጠራርጎ ለማስወገድ መሞከራቸው ሲሆን። በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊ ማንነት እነሱ እንደሚሉት በግድና በግፍ የተጫነ ማንነት ሳይሆን እያንዳንዱ ከአያት ቅድም አያቱ በክብር የተቀበለውና በክብር የሚያቆየው፤ የሚሞትለት ማንነቱ መሆኑን ነው።
ከፋፍለነዋል ከእንግዲህ ዋጋም የለውም ያሉት ህዝብ ከታሰበውና ከተሰራበት በተጻረረ መልኩ የአካል ብቻ ሳይሆን የመንፈስና የአመለካከት አንድነት ፈትሮ መግቢያ መውጫ እያሳጣቸው ይገኛል። እርስ በእርሱ ይፋጃል ያሉት ህዝብም የአባትና የእናቶቹን ጀግንነት በማስታወስ የሚወቃቀስበት ጊዜ እንኳን ሳይኖረው ሀገሩን ለመታደግ ወደስራ ገብቷል።
የቻለ ትጥቁን አንስቶ ለመዋደቅ ሲዘምት ቀሪው ጀግና ደግሞ የእሱን እርሻ ያርሳል፣ የእሱን ልጆች ይንከባከባል። የዘንድሮው ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ደግሞ ከዛሬ ነገ ኢትዮጵያን የደም አባላ ይበላታል ብለው በቴሊቪዥንና በፌስቡክ አፍጠው ሲጠብቁ የነበሩ ባንዳዎችንም አንገት አስደፍቷል። ይህም ዛሬ ለተነሱብን ብቻ ሳይሆን ነገ ላሱብትም ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ለእኛ አንዱ የደም አይነት መሆኑን የሚያመላክት ነው።
ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን በውስጣቸው ያሰረጹት ከኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ሲጠራ የሚመጣ ሲላክ የሚሄድ የመንደር ልጅ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ጥቅምን መሰረት አድርጎ አልተመሰረተም። ኢትዮጵያዊነትን ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማንም አልሰጠውም ማንም አይነጥቀውም። ኢትዮጰያዊነትም ጀግንነትም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የተቀመጠ ከፍ ያለ አቅም ነው። ኢትዮጵያን አልያም ህዝቦቿን የሚነካ ሲመጣ አደባባይ የሚሞላ ፍንዳታ ነው።
ሰሞኑንማ የጀግኖች ዜና እየተሰማ ያለው ከጦር ግንባር ብቻ አይደለም። አሸባሪው ትህነግ በመደበኛ ጦርነት አልገኝ ያለውን ድል ንጹሀንን በመግደልና ማፈናቀል ለመቀዳጀት ሲሞክር ኢትዮጵያ ደግሞ እኛ እያለን አትራቡም የሚሉ የችግር ደራሽ ጀግኖችን አፍርታ ጠብቃዋለች። ከየተቋማቱ የሚሰበሰበው ድጋፋም ለቡድኑ አመራሮችና ሰራዊት ትልቅ ራስ ምታት ነው።
ከሁሉም በላይ ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት ያቆበቆቡትን እሳት ለበስ ወጣቶች ብቻ መመልከቱ በራሱ ለጠላት የሚያስተላልፈው ጥብቅ መልእክት አለ። ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች አሸናፊነት ጎረቤቶቻችን ሱዳንና ሶማሊያ፤ ባላንጣችን ግብጽ እንዲሁም ባህር አቋርጣ የመጣችው አውሮፓዊቷ ጣሊያንም ሳትቀር ቋሚ ምስክሮች ናቸው። ለነገሩ አስራ ዘጠኝ ስልሳ ስድስት ላይ ዝጎ የቆመ ጭንቅላት ሆኖባቸው እንጂ፤ እነሱም እኮ በኢትዮ- ኤርትራ ግጭት ጉሮሯቸው ጫፍ የደረሰች ነፍሳቸውን የታደጉት ኢትዮጵያን በማወደስና ኢትዮጵያዊ ጀግኖችን በመሰብሰብ ነበር።
ከሀዲዎቹ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አውጥተው የጣሉት የመሰላቸው ኢትዮጵያዊነትም እንደ አዲስ እያበበ መምጣት ጀምሯል። ብቻችንን ለምስራቅ አፍሪካ እንበቃለን ባሉ ማግስት በጥቂት ጀግኖች ለራሳቸውም ሳይሆኑ ቀርተዋል። አሸባሪዎቹ ትህነጎች ዛሬም እብሪት አይናቸውን ጋርዷቸው እንጂ ኢትዮጵያ ብዙ አብዲሳ አጋ፤ ብዙ ዘርአይ ደርስ ብዙ ሸዋ ረገድ ገድሌ አሏት። ገና ብዙም ታፈራለች።
ዛሬ ሁሉም ነገር ተቀይሯል ሁለቴ የሚታለል አይኖርም፤ በወሬ የሚፈታ ጦር የለም። ዛሬ የትግራይ ሚዲያ ሀውስን የሀሰት አሉባልታ የሚያምን አልያም በነስታሊንና አሉላ ማስፈራሪያ ልቡ የሚርድ ወጣት የለም። ጫና የፈጠሩ መስሏቸው ከሸኔ ጋር ያደረጉትም ጋብቻ ቢሆን ያለእድሜ የተፈጸመ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም።
አሸባሪው ትህነግ በየጦር አውድማው የሚያስጨ ርሳቸውን የትግራይ ወጣቶች የሚታደግበት ልብ ፤ ከቅዡቱና ከዚህ ከሚመነጨው ስራው እንዲመለስ ወደ ቀልቡ የሚመልሰው እድል ፈጣሪ ይስጠው የሚለው የዘወትር ጸሎቴ ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በእውነትም ጠቅላዩ እንዳሉት “ፀሀይ በምስራቅ ከመውጣት ኢትዮጵያም ጀግና ከመውለድ ቦዝነው እንደማያውቁ “ አስረግጬ ልናገር፤ ጽሁፌንም በዚሁ ላበቃ እወዳለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013