
አዲስ አበባ፡- ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የሀገርን አንድነት ጠብቆ ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ በማስቀጠል እየታየ ያለው የህብረተሰቡ መነሳሳት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በገንዘብና በአይነት 31 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትናንት ለጀግናው ሀገር መከላከያ ሰራዊት የስንቅና የገንዘብ ርክክብ ባደረገበት ወቅት አቶ አህመድ እንደገለጹት፤ እየታየ ያለው የህብረተሰቡ መነሳሳትና ድጋፍ አሸባሪ ቡድኑ እስከሚጠፋ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየተካሄደ ላለው ትግል የከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችና ህብረተሰቡ በጋራ የሀገር ጥሪን በመቀበል 31 ሚሊዮን ብር ለጀግናው ሀገር መከላከያ ሰራዊት ማበርከታቸው የሀገር ህልውናን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡን ተነሳሽነት ማሳያ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ድጋፉን ለመከላከያ ሰራዊት ለማስረከብ ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተወክለው በመከላከያ ሰራዊት ጊቢ ውስጥ የተገኙ የእምነት አባቶች፣ ኡጋዞች፣ አባገደዎችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ካቢኔዎች ሀገራዊ ጥሪን ተቀብሎ ላደረጉት ጥረትም አመስግነዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና በአስተዳደሩ የሀገር መከላከያ ድጋፍ ማሰባሰብያ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከድር ጀዋር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የድሬዳዋ ከተማ ህዝብ የሀገር አንድነትን ለማስከበር አሸባሪውን ህወሓት ለመስወገድ እየተካሄደ ለሚገኘው ዘመቻ ስኬታማነት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ከድር ገለፃ፤ ከድሬዳዋ ህዝብ፤ በተለይ ከሴቶች አደረጃጀት፣ ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች፤ ከባለሀብቶችና ከንግዱ ማህበረሰብ የተሰበሰበ ድጋፍ በገንዘብ 28 ሚሊዮን ብር፤ በዓይነት 85 ፍየሎች፣ 20 በሬዎችና ለስንቅ የሚሆኑ ግብአቶችን በድምሩ 31 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርገዋል፡፡
በድሬዳዋ የሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ክፍለ ጦር ሶስተኛ ደረጃ ሆስፒታል አሻባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ በወሰደው አፀያፊ ድርጊት በቂ ህክምና አገልግሎትና የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዲያገኙ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስ የህክምና ባለሙያዎች በግንባር ተገኝተው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የህክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ የሀገር ማዳን ጥሪውን ተከትሎ የድሬዳዋ ወጣቶችና የተለያዩ ተሸከርካሪዎች ወደ ግንባር ተልከዋል ሲሉም አመልክተዋል፡፡
አሸባሪውን ቀብረን ሀገራዊ ህልውና እስከሚረጋገጥ ድረስ የድሬዳዋ መስተዳድር ህዝብ ድጋፍ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን አይለይም ሲሉም አቶ ከድር ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጅ እንደገለጹትም፤ የድሬዳዋ ህዝብ የአብሮነትና የአንድነት ተምሳሌት ነው፡፡ የሀገር ህልውናን ለማስከበር እየተደረገ ላለው ዘመቻ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መሆኑን ለመግለፅ መስተዳድሩ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና ይገባዋል፡፡
የሀገር አንድነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ህብረተሰቡ ለማስወገድ የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ የተጀመረው ዘመቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ልማት በመመለስ ልማትን ማስቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም