
አዲስ አበባ፡- ዘ ኒው ሚሊኒየም ወርልድ ሜዲካል ዲቫይስ ማኑፋክቸሪንግ የተሰኘ ሀገር በቀል ኩባንያ ከ509 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የህክምና መሳሪያ ማምረቻ ፋበሪካ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚገነባ አስታወቀ፡፡
ኩባንያው የህክምና ምርቶቹን ለማምረት የሚረዳውን የህንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ባለፈው ቅዳሜ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባስቀመጠበት ወቅት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ በየነ እንደገለፁት ፣ ኩባንያው ቀደም ሲል የባዮቴክ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በተለይም ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያ በማስመጣት ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም ኩባንያው ፈጣን የመመርመሪያ ግብአቶችን በማምረት ስራ ላይ ያተኮረ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ተሾመ ፣ 60 በመቶ የሚሆነውን የፋብሪካውን የጥሬ እቃዎች አቅርቦት በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኩባንያው በያዘው የአምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግበአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎች ለማዘጋጀት ማቀዱን ያስታወቁት አቶ ተሾመ ፣ ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኩባንያው ሃምሳ ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ እንደሚገኝ ፣ በዚሁ የሰው ሃይል በዓመት 137 ሚሊዮን 800 ሺ የመመርመሪያ ኪት የማምረት አቅም እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ኩባንያው አዲሱን ግንባታ ሲጀምር ለ495 ያህል ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ፣ በዚሁ የሰው ሃይል በዓመት ከ500 ሚሊዮን በላይ የመመርመሪያ ኪት የማምረት አቅም እንደሚኖረው አቶ ተሾመ ገልፀዋል፡፡
ለፋብሪካው ግንባታ ኩባንያው በመጀመሪያው ዙር 181 ሚሊዮን 394 ሺ ብር እንዲሁም በሁለተኛው ዙር 327 ሚሊዮን 627 ሺ ብር በድምሩ ከ509 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል፡፡
በዚሁ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ረጋሳ በበኩላቸው፣ እስካሁን ድረስ ሶስት ባለሀብቶች በፓርኩ ገብተው እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ሰባቱ መሬት ወስደው በግንባታ ሂደት ላይ እንዳሉና የአረንጓዴ ልማትም በፓርኩ ውስጥ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰንዱቃን ደበበ ካለው አስቸኳይ ሀገራዊ ፍላጎት አንፃር ኩባንያው የጣለው የመሠረተ ድንጋይ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በፈርማሲዪቲካል ዘርፍ ገብተው ለሚሰሩ ሌሎች ኩባንያዎችም ጥሩ ምሳሌ መሆኑንም ገልፀዋል።
በፈርማሲዪቲካል ዘርፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰንዱቃን ፣ 80 ከመቶ ከውጭ ሀገር የሚገባውን የህክምና መሳሪያ በሀገር ውስጥ እንዲተካ በማድረግ ረገድ በቀጣይ ኩባንያው የሚጫወተው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ያለውን የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ችግር በመቅረፍና ከዚህ ጫና ለመላቀቅ ይህ ጥሩ ማሳያ መሆኑንም አስታውቀው፤ በቀጣይ በፈርማሲዪቲካል ዘርፍ በመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም