ሰው ማለት
ሰው ማለት
ሰው የሆነ ነው
ሰው የጠፋ ‘ለት።
ገጣሚውን ባላስታውስም (የህዝብ?) ስለ ግጥሙ ግን ሳላመሰግን አላልፍም። ከማመስገንም በላይ ተገቢው ቦታ ላይ ተጠቅሜበታለሁ ብዬ አስባለሁና አርኬው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምትክ የለሽ ነው ቢባል ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም።
በሰው መሀል ሆኖ ሰው ማጣት ማንንም ያጋጥማል። ድረሱልኝ እንኳን ብለው እየተጣሩ የሚደርስልዎት ይጠፋና ሰማይና ምድር የተደፋብዎት ሁሉ ሊመስልዎት ይችላል። እውነት ነው ቢመስልዎት ብቻ አይደለም ቢሆንም እራሱ የሚገርም አይሆንም። ምክንያቱ ደግሞ “ሰው እንዴት ሰው መሀል ሆኖ ሰው ያጣል?” ያስብላልና ነው።
እንደሚታወቀው፣ ማለትም ተጨባጩ አለም እንደሚያሳየው ዘመኑ ከእውነት ይልቅ ሀሰት ሚዛኑን የሚያነሳበት ክፉ ዘመን ነው። “አደግን” የሚሉት አገራት ከ100 አመት በፊት በመርህ ደረጃ ይዘውት በነበረው “ሀብታምና ጉልበት ያላቸው አገራት በመላው አለም እንደፈለጉ የመሆን መብት አላቸው። ይህ ደግሞ የበላይነት ሳይሆን ተፈጥሯዊና መሆን ያለበት ነው።” በሚለው፤ ዛሬ ሊያፍሩበት የሚገባ አስተሳሰብ ነው።
ይህን “ሀብታምና ጉልበት ያላቸው አገራት በመላው አለም እንደፈለጉ የመሆን መብት አላቸው። ይህ ደግሞ የበላይነት ሳይሆን ተፈጥሯዊና መሆን ያለበት ነው።” የሚለውን የአውሬ ፍልስፍና ተግባራዊ ሲያደርጉ መኖራቸው እርግጥ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጀግና አገራት ጋር ሲደርሱ መከናነባቸው እንጂ በጣሊያን አማካኝነት በተደጋጋሚ ጥረዋል። አሁን በቅርቡ እንኳን በጅሉ ዚአድባሬ በኩል ሞክረዋል። ጭራሽ አሁን ደግሞ እርስ በራሳችን በማጫረስ በአደባባይ ካላፈረስናችሁ በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ላይ ሲሆኑ፤ የዚህ ሁሉ ፊታውራሪ ደግሞ፣ ድሮም ዘንድሮም፣ አሜሪካ ነች።
ለምን እንደሆነ (ባይታወቅም?) ኢትዮጵያ ተበድላም ሳትበድልም የሚያወዛግባት አካል አጥታ አታውቅም (“ለምን ትሰሪያለሽ፣ ለምንስ አባይን ትገነቢያለሽ?” እስከማለት ድረስ የዘለቀ)። የጣሊያንን ግፍ ለአለም ለማጋለጥና ፍትህን ለማግኘት ቀዳማዊ ኃ/ሥ በሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ በመገኘት አቤት ሲሉ ከአንድ አገር (ሜክሲኮ!!!) በስተቀር የደረሰላቸው ወገን አልነበረም። ሁሉም በሰውየው ከመሳቅ አልፈው እስከ ማሾፍና ማላገጥ ድረስ ሄደው ነበር። ይሂዱ እንጂ ንጉሱ ያደረጉት ንግግር ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ ምድር አንቀጥቅጥ ሆኖ ሲገኝ እነዛ፣ ሲያላግጡባቸው የነበሩት ግን አንገታቸውን ሲደፉ፤ ስለ ሰሩት ታሪካዊ ስህተት ኢትዮጰያ ይቅር እንድትላቸው ደጅ ሲጠኑ፤ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ሎቢ ሲያደርጉ ይኸው እስካሁን አሉ። የሚገርመው ይህ የአሁኑ ክፍለ ዘመንም የእነዛን አይነት ሰዎችና ተቋማት ማፍራቱ ነው።
“ለምን ስልጣኔን በህዝብ ተነጠኩ?” በሚል የድንቁርና መርሁ የተነሳ ወደ መቀሌ፤ ከዛም እንደገና ወደ ደደቢት የመሸገው አሸባሪው የህወሓት ቡድን አገሪቱን ወደ አልተፈለገና የማይገባ ጦርነት ውስጥ ማስገባቱን ተከትሎ መንግስት ሕግን በማስከበር ዘመቻው ስርአት ሊያሲዘው በሚያደርገው ትግል ውስጥ በውጪ ጣልቃ ገቦች አማካኝነት መንግስትን ወንጅለው ሽብርተኛውን የሚያነግሱ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ምክንያት ጉዳዩ ሰሞኑን (ባለፈው ሀሙስ ምሽት) በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ለውይይት ከዛም ለውሳኔ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። በውይይቱም አባል አገራት ጎራ ለይተው (“በኢትዮጵያ ላይ” እና “ለኢትዮጵያ”) ተከራክረዋል። አሜሪካንን ዞሮ መግቢያዬ ያሉ አባል አገራት በኢትዮጵያ ላይ ሲፈርዱ፤ እራሳቸውን ለእውነት፣ ለፍትህና ዘላቂ ሰላም ያስገዙቱ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ብለው ሲታገሉ አምሽተው ስብሰባው ያለ ውሳኔ ተጠናቋል።
ይህ ስብሰባ፣ ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ካጋጠማቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። እውነትን በሀሰት ለመሻርና ሀሰትን እውነት አድርጎ ወንጀለኛን ነፃ በማውጣት ተጎጂን ለመወንጀል የተደገሰ ድግስ እንደመሆኑ መጠን አንድ ናቸውም ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ እውነቱ እራሳቸውን ለርትእና ፍትህ ባስገዙ አገራት አማካኝነት ሊጋለጥ ችሏል።
በእነዚህ የፍትህን ርትእ ተከታይ አገራት አማካኝነት የኢትዮጵያን ነጻነት ለማዳን ንጉሠ ነገሥቱ በዤኔቭ የመንግሥታት ማህበር ሸንጎ ላይ ያደረጉት ሙግትና በመጨረሻም ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደረገው አይነት አሳዛኝ ውሳኔ አሁንም እዚህ እንዳይደገምና ኢትዮጵያን እንዳይጎዳ ብቻ ሳይሆን ከመስራቾቹ አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ የተመሰረተው፣ እራሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቱ ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፅምና አመኔታን አጥቶ ትዝብት ላይ እንዳይወድቅ አድርጎታልና እነዚህ አገራት ከልብ ሊመሰገኑ ይገባል።
እየተነጋገርን ያለነው በዚህ በከፋ ወቅት፣ በዚህ በቁርጥ ቀን፣ በዚህ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአደባባይ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት፣ በዚህ የውክልና ጦርነት በላያችን ላይ እየተካሄደ ባለበት ወቅት፣ በዚህ ሀያላን የተባሉት አንዳቸውም ሳይቀሩ ከ27 አመታት መንግስትነት በኋላ ወደ ደደቢት ከተመለሰው ቡድን ጋር ተሰልፈው ኢትዮጵያን እንዳልነበረች ለማድረግ እየጣሩ ባሉበት በዚህ ክፉ ጊዜ ከጎናችን ተሰልፈው እውነቱን ለአለም እየነገሩልንና ከአፎቱ የወጣብንን ሾተል ወደ አፎቱ እየመለሱልን ስላሉት ወዳጅና አጋር አገራት ነው – ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ እንዲሁም ኬንያ!
ለርእሰ ጉዳያችን ማጎልበቻ በማሰብ፤
ሰው ማለት
ሰው ማለት
ሰው የሆነ ነው
ሰው የጠፋ ‘ለት።
የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ የግጥም አንጓ ስንጠቀም የሚያውቀንም የማያውቀንም፣ የገባውም ያልገባውም፤ በስኳር የተታለለውም ወዘተ ከኃያላኑ ጎን በመሆን ኢትዮጵያ ላይ ጣቱን ሲቀስር ከዛ ሁሉ ጣት ቀሳሪና ወንጀለኛን አወዳሽ አገራት መካከል እነዚህ የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ አገራት ከጎናችን መቆማቸው ሊያስመሰግናቸው፣ ታሪካቸውም ሊፃፍ ሊነገርላቸው ይገባልና ይሄንኑ ለማፅናት ነው።
የሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ እንዲሁም ኬንያን (ልክ ዛሬ ላይ ሆነን የሜክሲኮን እንዳነሳነው ሁሉ) የዛሬ ተግባርና ውሳኔ፤ ለፍትህ እና ርትእ የመቆማቸውን ጉዳይ ወደ ፊት በታሪክ ፊት ተደጋግሞ እንደሚነሳ ይታወቃል። ለወደፊቱ ታሪክ ጉዝጓዙ ደግሞ ይህ የዛሬ የጋዜጣችን ምስክርነት ነውና አገራቱንና የያዙትን ፀረ ሽብርትኝነት አቋም ለትውልድ ልናስተላልፍ፤ ትውልድም እውነቱን ሊያውቀውና ለእውነተኛው ወገን ተገቢውን ክብር እንዲሰጥ ልናደርግ የግድ በመሆኑ ሲሆን፤ በተለይ የሩሲያ ተወካይ በፀጥታው ምክር ቤት ላደረጉት ኢትዮጵያን ከጅብ አፍ የማውጣት፤ ጅቦቹ እያካሄዱብን ያለውን የውክልና ጦርነት የማጋለጥ (በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት የሩሲያን (ያኔ ሶቪየት ህብረት)ና ኩባን ውለታ ያስቷውሷል) ተግባር ከህልውና፣ ህሊናና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አኳያ እዚህ ጋ ማስፈሩ የግድ ነውና አሁንም ምስጋና ለእነሱ ይድረስ እንላለን። እናመሰግናለን!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013