
አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በጤና ተቋማትና በጦር ግንባር የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ገለጸ።
በኤጀንሲው የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ክምችትና ስርጭት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አድራሮ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ ኤጀንሲው በጤና ተቋማትና በጦር ግንባር የግብዓትና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የህልውና ዘመቻ አንጻር አጠቃላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮችን ከማገዝና የሚያስፈልገውን ግብዓት ከማቅረብ አንጻር የተለያዩ ኮሚቴዎችን የማዋቀር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ኤጀንሲው በ2013 የበጀት ዓመት 27 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መሰረታዊ መድኃኒቶችና በአጋር ድርጅቶች የሚገዙ የፕሮግራም መድኃኒቶች ለጤና ተቋማት መቅረቡንም አመልክተዋል። የመሰረታዊ መድኃኒት አቅርቦት ከስድስት ወር በፊት ከ35 በመቶ የነበረውን ወደ 85 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የግዢ ሂደት መጓተት በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛልያሉት ኃላፊው ፣ አንድን መድኃኒት ገዝቶ ወደ ሀገር ለማስገባት ከ200 በላይ ቀናት ይፈጃል ሲሉ ገልጸዋል።
የህክምና ግብዓቶች ግዢ ሌሎች ቁሳቁሶች በሚመሩበት የግዢ መመሪያ መመራት የለበትም ያሉት አቶ ተስፋለም፣ ኤጀንሲው የመድኃኒትን ባህሪ፣ አንገብጋቢነትና አጭር የመጠቀሚያ ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የግዢ መመሪያ እንዲዘጋጅ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኤጀንሲው አዋጅም ይህን መፍቀድ በሚችል መንገድ እንዲሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚገጥሙት ፈተናዎች በሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት ሂደቱ በታቀደው ልክ እንዳይሆን ማድረጉን አመልክተዋል።
ኤጀንሲው 80 በመቶ የሚሆነውን የህክምና ግብዓት የሚያስመጣው ከውጭ ሀገራት መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ተጽእኖ ማድረሱን አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የዋጋ ንረት፣ የግብዓትና የኮንቴነሮች እጥረት፣ የጤና ተቋማት በዱቤ የወሰዱትን በወቅቱ ያለመክፈልና በጤና ተቋማት የሚስተዋለው የትንበያ ችግር ኤጀንሲው የሚገጥሙት ፈተናዎች ናቸው ብለዋል።
የህክምና ግብዓቶች አቅርቦት ሰንሰለት በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ነው። ከባንኮች፣ ከኢንሹራንሶች፣ ከአየር መንገድና ከሌሎችም የትራንስፖርት አካላት፣ ጉምሩክ እንዲሁም ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር የነበረው ግንኙነት የተሳለጠ እንዳልሆነ አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባለድርሻ አካላት ፎረም ተቋቁሞ ዘርፉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚረባረቡለት መሆኑን ገልጸዋል።
አብዱረዛቅ መሐመድ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም