
ድንበሯን በአጥንታቸው ሊያጥሩ፣ ሰንደቋን በደማቸው ሊያቆም፣ ለራሱ መኖርን በመናቅ ፣በተፈጥሮው ለመፈተን፣ በቀን ሀሩር፣ በምሽቱ ቁር ኢትዮጵያን ለማገልገል የተዘጋጁ ፣ጥርሳቸውን ነክሰው ለማሸነፍ የቆረጡ፣ በአገሩ ብርሃን ላይ ያጠላውን ጨለማ ለመግፈፍ ስለ ክብራ ለመሞት የወሰኑ፣ የማይተካ ህይወታቸውን ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም አሳልፎ የመስጠት ፍላጎትና ድፍረታቸው በግልጽ የሚታይ ወጣቶች በሆርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያን ቁስል ሊጠግኑ ፣ ሽንቁራን ሊደፍኑ በማእከሉ ከሚገኙ መካከል ፈቃዱ አለማየሁ አንዱ ነው።ለፈቃዱ አሸባሪው ህውሓት ‹‹ዛሬ አፈርሳታለሁ›› የሚላትን አገር ቀድሞም ሲገነባ አልነበረም። ሀገር የማፍረስ ታሪክ የመደምሰስና ብሄራዊ ዓርማን የማንኳሰስ አባዜ ከቡድኑ ጋር አብሮት የተፈጠረ ፣ ስልጣን ሲያጣ የጨመረና የደደረ ክፉ ልክፍቱ ነው።
ፈቃዱ ተወልዶ ያደገው በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ምድረ ገነት ቀበሌ ነው።ከአዋሳ መምህራን ኮሌጅ ተመርቋል።አዲስ አበባ ከተማ በግል ትምህርት ቤት በመምህርነትና በዳይሬክተርነት አገልግሏል።በስራውም በቂ ገንዘብ ስለሚከፈለው ጥሩ ሕይወትን ይመራ ነበር፡፡
በአሸባሪ ህውሓት ቡድን ኢትዮጵያ መደፈሯ ያንገበገበው ፈቃዱ.፣ በቀለም ሕይወቱ መድረስ የሚፈልግበትን ህልሙን ሁሉ ትቶ በብዕር ፋንታ ጠብመንጃ ለመጨበጥ የወሰነው የተደላደለ ሕይወቱን ወደ ጎን በመግፋት ነው፡፡
‹‹አገሬ ተደፍራ ቆሜ ከምመለከት ሞቴን እመርጣለሁ፣ እንደ መምህርነት ወታደርም አገርን እና ትውልድን ማስቀጠል ነው›› የሚለው ፈቃዱ፣ የሚወደውን ሙያ በመተው ወደ ማሰልጠኛ ለመግባት የወሰነውም ለራሱ በላይ ሀገሩን ብሎ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል መሆኑን ይናገራል፡፡
‹‹ወጣቱ ወደ ስልጠና ማእከላት ከፍ ባለ ወኔ ሲተም የምናየው እንዲሁ አይደለም። ቤተሰብ ከውስጥ በመነጨ ኀዘንና ቁጭት ልጆቻቸውን ፈቅደውና ወደው ስለ ሀገራቸው ሳግ በሚተናነቀው ምርቃት እየሸኙ የምናየው ስለ ኢትዮጵያችን ነው። በኢትዮጵያ ስለመጣበት ነው ይላል፡፡
‹‹እኛ የታላቋን ሀገር አደራ የተቀበልን ወታደሮች የእናት ጡት ነካሹን ዋጋውን ሳንሰጠው እንቅልፍ የለንም።ግብዓተ መሬት ለማፋጠን ዝግጁ ነን፣ ከህዝባችን ጋር ሆነን የድል ታሪክ የምንፈጽምበት ቀን ሩቅ አይሆንም›› ብሏል።
ወንደወሰን መለሰ ትውልድ እና እድገቱ አዲስ አበባ አብነት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው።አሸባሪው ሕውሓት በስልጣን እያለ በኢትዮጵያ ህዝብ ለይ የፈፀመው በደል እጅግ አስከፊ ስለመሆኑ የሚያስታውሰው ወንድወሰን፣ በተለይ በ1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ወጣቶችን በቀን በአደባባይ በስናይፐር ጭንቅላታቸውን በመምታት ከገደላቸው መካከል አንዱ ጓደኛው መሆኑን ይጠቁማል፡፡
ስራና ቤተሰቦቼን ትቼ ሁርሶ ማሰልጠኛ የገባሁትም ‹‹የእናት አገሬን ጥሪ ተቀብዬ፣ ከእኔ በፊት እርሷን አስቀድሜ፣ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን የሚሉ ጠላቶቻችንን ለመደምሰስ ነው›› የሚለው ወንድወሰን፣ የሚጠብቋት ልጆቿ እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ ሳትሆን አፍራሿ እንደሚፈርስ ያስገነዝባል።የሽብር ቡድኖቹ ሀገርን የማሳነስ ወገንን የማናከስ ተግባር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በቅርቡ መቋጫውን እንደሚያገኝ አይጠራጠርም።
‹አሸባሪው ህውሓት በጎሰመው የእልቂት ነጋሪት ቀብሩን በራሱ ላይ እንዳወጀ የሚገልፀው ወንድወሰን፣ ‹‹በኢትዮጵያ ጀግኖች የሽብርተኛው ቡድን ፋይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚዘጋበት ዕለት ሩቅ አይደለም። ቀኑ የዘገየ ቢመስልም ቀብራቸው አይቀርም።ወግ አልባው ቀብራቸው የሚበሰርበት ጊዜ በጣም እጅግ በጣም አጭር እንደሆነ ከፍ ባለ እምነት ይናገራል።
“ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆችም ሽብርተኞቹን ወደ ሞት የመሸኘቱን ስራ በትጋት ይሰራሉ።ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ የሚል ከሃዲ ሁሉ አሟሟቱ ከማያምረው አሸባሪው ህወሓት ይማራል›› ብሏል።በሁርሶ እየተከታተለ የሚገኘው ስልጠና በስነልቦናው ሆነ በአካል ጠንካራ እንዳደረገው የሚገልጸው ወንደወሰን፣ ጀግናን መሸለም ፈሪን ማጀገን የሚችል ማሰልጠኛ ሲልም ነው ያሞካሸው፡፡
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገር ለመጣብን ጠላት የምንሰስተው ነብስ የለንም።ለዚህም የአባቶቻችን የአርበኝነት ገድል ምስክራችን ናቸው የምትለው ደግሞ፣ ከአማራ ክልል ሞጣ ከተማ የተወለደችው የሺወርቅ ዘላለምአዲስ ናት፡፡
የሚያኮራ ደጀን ያለው ሠራዊት መቼም የትም የድል ባለቤት መሆኑ እሙን መሆኑን የምትጠቁመው የሺወርቅ ፣መከላከያ ሠራዊትን እንደ ዓይኑ ብሌን የሚመለከተው የኢትየጵያ ህዝብ ዋስ ጠበቃ፣ ከለላና መከታ በመሆን እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ትልቅ የሞራል ስንቅ እየሆናቸው መሆኑን ትናገራለች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንቱ መጨረሻ ደቡብ ክልል ባህል ቡድን አባላት በሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ በስልጠና ላይ ለሚገኙ ምልምል ወታደሮች የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ የኪነጥበብ ዝግጅቶች ሲያቀርቡ የተገኙት፣ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና ደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሃይለማርያን ተስፋዬ፣ የወጣት ወታደሮችን ስሜት ተጋርተውታል፡፡
‹‹የአገር ፍቅር ስሜት ስልጣን ላይ ስንሆን የሚሞቅ ስንወርድ የሚቀዘቅዝ አይደለም፣ ስልጣን ላይ ሲወጣ አገርና ህቡን ዘርፎ ከስልጣን ሲወርድ አገሩ የሚወጋ ሁሉ የአገር ጠላትና ባንዳ ነው” የሚሉት አቶ ሃይለማርያም፣ የአሸባሪው ህውሓት ቡድን እና የኦነግ ሸኔ ሃይሎች የአገር ፍቅር የማያውቁ ስግብግብ ባዳዎች መሆናቸውን በአደባባይ እያስመሰከሩ መሆናቸውን በመግለፅ፣ በኢትዮጵያ ልጆች አይቀጡ ቅጣት ሊቀጡ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ‹‹የትም፣መቼ፣በምንም በሚል ሁላችንም የዘመቻው ተሳታፊዎች ሆነናል›› የሚሉት አቶ ሃይለማርያም፣ ደቡብ ክልል ህዝብና መንግስት አባላቱን ከመላክ ባሻገር በስንቅ፣ በገንዘብና በአይነት በሚያደርገው ድጋፍ ለጁንታውና ለኦነግ ሸኔ ግብአተ መሬት መፈፀም ያለውን ፅኑ ፍላጎት እየገለጸ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የኤፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማእከል ሎጅስቲክስ ድጋፍ ስምሪት ሃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል ጠቅለው ክብረት፣ አሸባሪው የህውሓት ቡድን ከመሰሎቹ ሸኔና ሌሎችም የኢትዮጵያን እድገት ከማይፈልጉ ጋር በማበር ንፁኃን ህዝብ ላይ የክህደት ክንዱን ዘርግቶ በርካታ ሕይወጥ ቀጥፏል፣ ከፍተኛ አካልና የንብረት ውድመት ፈፅሟል፣ ለስደት እና ለመፈናቀል ዳርጓል›› ይላሉ፡፡
በማይካድራና በአፋር ጋሊኮማ እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች የፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ለእብነት ያነሱት ብርጋዴል ጄኔራሉ፣ ‹‹ተግባሩ አባቶቻችን ነፃነታችንን አቆይተው ባቆዩልን አገር ተደርጎ የማያውቅ ክስተት በመሆኑ እልህና ቁጭት ሊፈጥር ይገባል›› ብለዋል።ኢትዮጵያ የበቀለባትን ይህን ክፉ አረም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመንቀል ህዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ጊዜው አሁን ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም