የየትኛውም ሀገር ሥልጣነ መንግሥት በመሠረታዊነት በሚከተሉት ሦስት አእማድ ላይ የቆመ ነው፤ ሕግ አውጪ (Legislative)፣ ሕግ አስፈጻሚ (Executive) እና የዳኝነት አካሎች (Judical):: ሦስቱም መዋቅራዊ አደረጃጀቶች በሥራቸው ያቀፏቸው ተቋማት እጅግ በርካቶች ስለሆኑ መተንተኑ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ የጥቅሻ ያህል ከተንደረደርኩባቸው ይበቁ ስለመሰለኝ መነሻቸውን በወፍ በረር ቅኝት ዳስሼ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳዬ አቀናለሁ፡፡
የሦስቱ አእማድ ጽንሰ ሃሳብ መነሻው የአውሮፓዊያን ጥንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ፍልስፍና አንደሆነ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።ቀደምት አውሮፓዊያን የሀገረ መንግሥታቸውን ሥልጣን ሸንሽነው በሢሦ ያከፋፍሉ የነበረው ለሦስት ዋነኛ የማሕበረሰቡ አካላት ሲሆን፤ ቀዳሚው ለካህናት (Clergy)፣ ሁለተኛው ሢሦ “ለምርጦቹ የነገሥታት ዘሮች” (Nobilities)፣ ሦስተኛው ሢሦ “ለተራ ዜጎች” (Commoners) ነበር።የእኛውም ሀገር ፊውዳላዊ የሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር ከዚህ መሠረታዊ መርህ ያፈነገጠ እንዳልነበር እጅግም ያልመሸበት ታሪካችን ያስታውሰናል።“ሢሦ ለቀዳሽ (ለቤተ ክህነት)፣ ሢሦ ለነጋሽ (ለሞዓ አንበሳ ሥርወ ዘር)፣ ሢሦ ለአንጋሽ (ለተራው ሕዝብ)” ይባል እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ይህንን እውነታ መሠረት ያደረገው “የዘመነ ሥልጣኔ ዘመነ ዴሞክራሲ” የመንግሥታት ሥልጣን በሕግ አውጪ፣ በሕግ አስፈጻሚና በዳኝነት አካላት ብቻ መገደብ እንደሌለበት በማሳመኑ በሢሦ የተከፋፈለው አወቃቀር ፍልስፍናው ተለጥጦ “አራተኛ ረድፈኛ” ተብለው ለተሰየሙት ለፕሬስና ለኤሌክትሮኒክስ ብዙኃን መገናኛ ተከፍሎ የተሰጠ በማስመሰል መንግሥታዊ ክብሩና ጥቅሙ ሳይሆን ስሙን ብቻ ተሸክመው እንዲኮፈሱ ተፈቅዶላቸዋል።በዚህም ምክንያት “The media is referred to as the fourth branch of government because it has the capability to change the policy agenda and policy opinion based on what it reports.” ተብለው በመንቆለጳጰስ “በሽንገላ የደፉት የዘውድ አክሊል እኛ እኮ….” እያሰኛቸው በሩብ የሥልጣን ተጋሪነት መኩራራት ከጀመሩ በዘመን ላይ ዘመን ጠብቷል፡፡
በርካቶቹ የአውሮፓ ሀገራትም ይህንን የአራተኛ መድፈኛነት ጽንሰ ሃሳብ ወደ ቋንቋቸው አስርገው በማስገባት በኢጣሊያንኛ (quarto potere)፣ በጀርመንኛ (vierte gewalt)፣ በስፓኝ ቋንቋ (cuarto poder)፣ በፈረንሳይኛ (quarirème pouvoir) እያሉ በአሜንታ መቀበላቸውን በጋራ አፀደቁ፡፡
ከዘመን ጋር እየዘመነ ያለው ይህ አራተኛ የሚዲያ ሠራዊት የብዕርና የዓየር ሞገድ አቅሙን በመጠቀም ለጦርነትና ለባህል ወረራ አገልግሎት እየዋለ ከጠብመንጃ እኩል ሰልፉን መቀላቀሉን ተያያዘው።የየሀገራቱ የመስፋፋትና የተጽእኖ ፈጣሪነት ቅዠትና ህልምም በመላው ዓለም የሚፈታበት አንዱ ዋና መሣሪያ ተደርጎ ተቆጠረ።ሀገራት የፕሬሱንና የዜና አውታሮችን አቅም አጉልተውና አግዝፈው ለማሳያት ሲሞክሩም የፈረንሳዩ ገናና ንጉሥ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ “ከሦስት ባታሊዮን ጦር ይልቅ ሦስት የብዕር ሰዎችን አፈራለሁ!” ያለውን አባባል እየጠቀሱ የዓለማችንን አየር የሥልጣናቸው መገለጫ መንበር በማድረግ ፋነኑበት።
ውሎ ሲያድርም የዓለማችን ታላላቅ ታሪኮች የሕዝቡ ትሩፋቶች መሆናቸው ቀርቶ የድንገቴ-በቀል ጀግኖች ታሪኮች” ናቸው በማለት የጀብደኛ አምባገነን ግለሰቦችን ክንድ ማፈርጠምን ተያያዙት።የአራተኛ የመንግሥት ሥልጣን ተሰጥቶሃል የተባለው እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው የዓለም ጋዜጠኛም በሚያራምደው ነፃ ሃሳብ እየታሰረ፣ በጻፈው ብዕር ምክንያት ለዘብጥያ እየተዳረገ፣ አንዳንዴም ሕይወቱን እስከ መገበር እየደረሰ ዋጋ መክፈል የዕለት “እንጀራው” እስከ መሆን ደረሰ፡፡
የዜና አውታሮች የአራተኛ ረድፈኛነት የመነሻ ሃሳብ “የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ መታገልና መንግሥት አምባገነናዊ ሆኖ በሕዝብ ላይ እንዳይፈነጭ ለማጋለጥ ነው” የሚል ቢሆንም ለዚህ መሠረታዊ መርህ ታምነው ከልባቸው የሚሠሩትን ማግኘት አሁን አሁን የሰማይ ያህል እየራቀ በመሄድ ላይ ስለመሆኑ ከዕለት ወደ ዕለት እያስተዋልን ነው።አብነት መጥቀስ ካስፈለገም ሩቅ ሳናማትር ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ህልውናችንን ለማስከበር በሚካሄደው ዘመቻ ላይ እነዚሁ “የገናና ስም ባለቤት” እየፈጸሙብን ያለውን ኢሥነ ምግባራዊ እኩይ ተግባር መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚሁ ጋዜጣ የነሐሴ 12 ቀን 2013 ዕትም ላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደሞከርኩት “ታላቅ” የተሰኘ ግዙፍ ስም የተሸከሙ አንዳንድ የዓለማች የዜና አውታሮች የሙያ ሥነ ምግባራቸውን ክደው ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር በማበር እየዘመቱብን ስለመሆናቸው አበክሬ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ።እነዚህ የሚዲያ ተቋማት እንኳንስ በአራተኛ ረድፈኝነት ገለልተኛ የመንግሥት ሥልጣን ተጋሪ ሊሰኙ ቀርቶ የኅሊናቸውን ድምፅ እንኳን በቅጡ መስማት እየተሳናቸው ለአሸባሪ ቡድኑ ጉልበት መሆናቸውን በይፋ እየገለጡ ስለመሆናቸው መመስከር አይገድም።“እሳት ካየው ምን ለየው” እንዲሉ አይዞህ እያሉ በውሸት ከሚተባበሩት ቡድን ጋር ደምረን ለእርሱ የሰጠነውን ስያሜ ብናጋራቸው ልንተች አይገባም፡፡
“በሬ ወለደ” ዜናና ትንታኔያቸው ከፍ ያለ ዋጋ እንዲያስገኝላቸው ሲፈልጉም “በሬውን ያዋለድነው እኛው ራሳችን ነን!” እስከ ማለት ለመድረስ ትንሽ አንኳን ሀፍረት ይሉት ነገር አይሸነቁጣቸውም።ይህ ድርጊታቸው የዝቅጠታቸው መገለጫ መሆኑ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም።“The 4th branch of government is a rhetorical device, not a serious statement of fact” እንዲሉ ከላይ የጠቀስነው ፍልስፍና ከተግባራቸው ጋር እጅጉን ሲቃረን እያስተዋልንም ነው፡፡
የጀግናውንና የሉዓላዊነታችንን ጥላ የመከላከያ ሠራዊታችንን መክዳትና የንፁሐን ዜጎችን መጨፍጨፍ በዓለም ማሕበረሰብ ፊት ከማጋለጥ ይልቅ ከአሸባሪው ቡድን ጋር “ዋንጫ ኖር!” እያሉ እውነታውን ሲደፈጥጡ መመልከት እንኳን እኛን ባለቤቶቹን ባዕዳንንም ቢሆን የሚያሳቅቅ ነው።ለካስ ልዋሽ ብለው ራስን ካሳመኑ የራስንም ነፍስ ማቄል ይቻላል።“አሸባሪው ቡድን ወደፊት እየገፋ ነው! በብዙ ንፁሐን ላይ የመከላከያ ሠራዊት ግፍ እየፈጸመ ነው!” ወዘተ እያሉ የሚያቀርቧቸው የሐሰት ዜናዎችና ዘገባዎች ነፋስ ላይ የተሰጣ እብቅ እንደሆነ አልገባቸው ከሆነ ይወቁት።“ውሸትና ገለባ እያደር ይቀላል” የሚለው ብሂል በቋንቋቸው ይኖር ከሆነም ራሳቸውን ይፈትሹ?
እነ CNN, BBC, Aljazeeraን የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት እና የዘመናት ዕድሜ ያስቆጠሩ የዜና ወኪሎችና የአሜሪካ ጋዜጦች ከሆድ አደር ስደተኛ ባንዳዎች የሚቀርቡላቸውን የፈጠራ ወሬ እንደ ትኩስ ኬክ ጋግረው የሚያከፋፍሉት አንድም ለማሻሻጫነት አንድም የጎረሱበትን እጅ አመድ አፋሽ ላለማድረግ ይሉኝታ ይዟቸው ይመስላል፡፡
ጆናታን ዲምብልቢ የተባለው የሀገራቸው ጋዜጠኛ በ1966 ዓ.ም በሀገራችን የተከሰተውን ርሃብ አስመልክቶ “The unknown famin” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ፊልም አማካይነት የዓለም ማሕበረሰብ ከዳር ዳር ተነቃንቆ እንዲረዳን ምክንያት ሆኗል።የኼው የሐቅ ዘገባ ለፊውዳላዊው የዘውድ ሥርዓት የማብቂያ ሰበብ በመሆንም በታሪካችን ውስጥ ሲታወስ ይኖራል።እኒህን መሰል የሚዲያ ጀግኖች የተፈጠሩበት ሚዲያ ዛሬ መልኩን ለውጦ ከሀገር አፍራሾች ጋር በተባባሪነት ቆሞ ሲወጋን ማስተዋል ምን ያህል አሳፋሪ ተግባር እንደሆነ ማንም ሊረዳ ይችላል፡፡
ከዐሥር ዓመታት በኋላም ድጋሚ በተከሰተው የ1977 ዓ.ም ርሃብና ከትህነግና ከሻዕቢያ ጋር በተደረገው የተራዘመ ጦርነት ወቅት ብርቱው ፎቶ ጆርናሊስት ሞሐመድ አሚን በድብቅ የቀረጻቸውን እጅግ ዘግናኝ ፎቶግራፎችና ፊልሞች ለዓለም ማሕበረሰብ በማድረሱ የተራድኦ ድርጅቶች ተረባርበው እንዲታደጉን ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የደርግ መንግሥት ሁነኛ ሹም የነበሩት ብርሃኑ ባይህ (ሌ/ኮሎኔል) በቅርቡ ለህትመት ባበቁት መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሱታል።“የፓርቲው (ኢሠፓ) ምሥረታ በዓል … እየተቃረበ ሲሄድ የምዕራብ ፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ ዘመቻ ጀመረ።የድርቁን ሁኔታ ለመደበቅ ቢሞከርም በ1966 ዓ.ም የተከሰተውን ድርቅ ዲምብልቢ የተባለ የእንግሊዝ ጋዜጠኛ በድብቅ ገብቶ በፊልም ቀርጾ ለዓለም ሕዝብ እንዳጋለጠው ሁሉ አሁንም መሐመድ አሊ (ሞሐመድ አሚን ማለታቸው ነው) የተባለ የህንድ ዝርያ ያለው ኬኒያዊ ጋዜጠኛ በዳዊት (ሻለቃ ዳዊት ወ/ ጊዮርጊስን መጥቀሳቸው ነው) ጥያቄ ነው ይባላል ሀገር ውስጥ ገብቶ ቀርጾ ለዓለም ሕዝብ አሳየው።በመሆኑም ፊልሙ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መነሻ ሆነ” (ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ፤ ገጽ 585)፡፡
ይህ ደፋር ጋዜጠኛ የትህነግ ሠራዊት አዲስ አበባ በገባ በሳምንቱ በ1983 ዓ.ም ግንቦት 26 ለ27 አጥቢያ ሌሊት በበቅሎ ቤት አካባቢ ይገኝ የነበረው የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ዴፖ ሲፈነዳ በቦታው ተገኝቶ የትራዤዲ ክስተቱን ሲዘግብ ግራ እጁን በፈንጂ ፍንጣሪ ቢያጣም ለዓላማው ጨክኖ ዜናውን ለዓለም ማኅበረሰብ አድርሷል። ታሪክ በደማቁ የሚያስተውሰው ይህ የሚዲያ አርአያ ሰብ በተቆረጠው እጁ ላይ አርቴፊሻል ሰው ሠራሽ አካል በማስገጠም እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ተግባሩን አከናውኖ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ህዳር 14 ቀን 1989 ዓ.ም የበረራ ቁጥሩ 961 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮሞሮስ ደሴት ላይ ወድቆ በመከስከሱ ሕይወታቸውን ካጡት 125 ተሳፋሪዎች መካከል አንዱ ሆኖ በሙያው እንደተከበረ ሊያልፍ ችሏል፡፡
እነዚህን መሰል ጀግኖች ያፈራው ዓለም አቀፉ ሚዲያ ዛሬ ደርሶ በአንዳንድ ሙያቸውን ባረከሱ ጋዜጠኞች አማካይነት ውሸት እንደ ሐቅ ሲነገር ማድመጥና ህሊናን ሸጦ ሲርመጠመጡ ማስተዋል በእጅጉ ያሳፍራል።ለእነዚህ የሚዲያ ተቋማት የምናስተላልፈው ሀገራዊ መልዕክት አጭርና ግልጽ ነው።“ሚዲያችን አራተኛው ረድፈኛና ከመንግሥታትም የተሻለ ሥልጣንና ተሰሚኒት አለው!” እያሉ ራሳቸው መኮፈሳቸውን ትተው ለሐቅ ኖረው ይለፉ።በእኛው ቋንቋ እየዘገቡ ሐሰት የሚነዙት የእነዚሁ ተቋማት ቤተኞች የሆኑ “ጋዜጠኛ ተብዬዎችም” የመቀበሪ ጉድጓዱ ዳርቻ ቆሞ እየተንፈራገጠ ላለው የአሸባሪ ቡድን መካደማቸውን ትተው ለእውነት ይገዙ ዘንድ እንመክራለን።ይሄው ነው።ሰላም ይሁን!
እነ CNN, BBC, Aljazeeraን የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት እና የዘመናት ዕድሜ ያስቆጠሩ የዜና ወኪሎችና የአሜሪካ ጋዜጦች ከሆድ አደር ስደተኛ ባንዳዎች የሚቀርቡላቸውን የፈጠራ ወሬ እንደ ትኩስ ኬክ ጋግረው የሚያከፋፍሉት አንድም ለማሻሻጫነት አንድም የጎረሱበትን እጅ አመድ አፋሽ ላለማድረግ ይሉኝታ ይዟቸው ይመስላል፡፡
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013