ሰው ነፍስና ስጋ ያለው ፍጡር ነው።ነፍስና ስጋ እንዳለው ሁሉ ህሊናና አዕምሮ የተባሉ ወቃሾች በሰውነቱ ውስጥ አሉ።ሰው በህሊና እና አዕምሮ ተመርቶ መልካም እና መጥፎውን ደጉንና ክፉውን ይለያል።አዕምሮውንና ህሊናውን ተጠቅሞ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከድንቁርና ወደ እውቀት ማማ ይሸጋገራል።ይህ የጤነኛ ሰው መገለጫ ነው።በሽተኛው ደግሞ በተቃራኒው መንገድ ይጓዛል።በህሊናው እና በአዕምሮ ተመርቶ ከጨለማ ብርሃንን ከመምረጥ ይልቅ፤ በተቃራኒው ጨለማን ይመርጣል።ይህ ሰው ህሊና እና አዕምሮ አለው ብሎ ለመገመት ያዳግታል።
ይህ ከደግነት ይልቅ ክፋትን መርጦ የክፋት ጥግን የሚመርጥ ህሊና ሲሰባሰብ የአሸባሪ ጥርቅም ይሆናል።አሸባሪው ህውሓትም ህሊና ቢስነት የተጠናወተው የአረመኔዎች ጥርቅም ነው።አሸባሪው የህውሓት ቡድን የእርሱን ፍላጎት ለማስፈፀም የወገን ሞት ምኑም አይደለም።ምክንያቱም ህሊና እና አዕምሮ የሌላቸው ስጋ ብቻ ለብሰው የሚላወሱ በድኖች የተሰበሰቡበት ነው።ለእነርሱ ፍላጎት ሕፃናት መሞታቸው እናቶች የምሬት ዕንባን ማፍሰሳቸውን ከቁብ አይቆጥረውም።አሸባሪው ህወሓት የሚሠራቸውን ግፎች ከማየት ሞት እንደሚመረጥ ታዋቂው የኢትዮጵያ ደራሲ በዓሉ ግርማ ግን በአንድ ወቅት ይህንን ብሎ ነበር።
ጩኸቴን ካላዳመጥህ፤ ልመናዬን ካልሰማኸኝ
እንደቆሰለ ጅብ ሲበላሉ ፤ ወገኖቼን ከምታሳየኝ
እባክህ ከአገሬ በፊት አስቀድመኝ
ከህይወት መዝገብ ሰርዘኝ
በቃኝ!!!
ይህንን በዓሉ ግርማ ሲል እነግፍ አይፈሬ እነጌቾ ግን በተዛባ አዕምሮ ግጥሙን ገልብጠው የቀን እና የለሊት ፍላጎታቸው እንደቆሰለ ጅብ ወገን ከወገን ሲበላላ ማየት ብቻ ነው። በዓሉ ይህን ከማየት ብሎ ሲጮህ እና መሞትን ሲመኝ እነርሱ ግን ከተንደላቀቀ ኑሯቸው ከመውረድ እና ከመሞት ብለው ወገንን በደመኛ እና በጠላት ስም ሰይመው እርስ በእርስ ያናክሳሉ።
ጠመንጃ መሸከም አቅቷቸው የሚንገዳገዱ፤ ቀጥ ብለው ቢሄዱም እጃቸው የሚዝልባቸው እና መተኮስ ቀርቶ መሳሪያን አንከርፍፈው የሚይዙ ያልጠነከሩ የአስራ ሁለት እና የአስራ ሦስት ዓመት ሕፃናት ልጆችን ከእናቶች ጉያ ነጥቀው ለጦርነት እየማገዱ የዘመቻውን ስም በእናቶች ስም መሰየም በእርግጥ ትክክለኛ አዕምሮና ህሊና ካለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም።
ጥግ በወጣ ጭካኔ ልጆች ለቀናት ምግብ ሳይበሉ እየተሰቃዩ በጦር ሜዳ እያሰለፉ ድል ተቀናጅተናል ብሎ መለፈፍ ከዚያ የዘመቻውን ስያሜ ‹‹የትግራይ እናቶች ዘመቻ›› ብሎ መሰየም የሚያመዛዝን አዕምሮ ላለው ሰው እጅግ ዘግናኝ እና አስገራሚ ነው።
በእነዚህ ህሊና ቢስ ራስ ወዳድ አረመኔዎች ተግባር ብዙ የትግራይ እናቶች የመረረ ስቃይ ውስጥ መግባታቸው ሐቅ ነው።ነገር ግን የትግራይ ሚዲያ ያለምንም ዕፍረት በትግራይ እናቶች ዘመቻ የተሳካ ድል ማስመዝገቡን እየለፈፈ ነው።‹‹ከሐምሌ 5 እስከ ሐምሌ 20 የፅናት ተምሳሌት በሆነችው የትግራይ እናት የተሰየመው ጦርነት በአፋር ግንባር ከአውራ እስከ ጭፍራ፣ በትግራይ ደቡብ ግንባር ኮረም፣ አለማጣ፣ ጎቤ፣ ቆቦ እና አለውሃ፣ በምዕራብ ማይፀምሪ እና ጨው በር ላይ በተካሄደው ጦርነት ዘመቻው በድል ተጠናቅቋል።ልጆችሽን ለጦርነት የላክሽው የትግራይ እናት ሆይ በስምሽ የተሰየመው ዘመቻ ተሳክቷልና እልል በይ!›› ሲል ዘገባውን አስተላልፏል።
አይ! ‹‹የበላችው ያገሳታል በላይ በላይ ያጎርሳታል›› እንዲሉ የለመደውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሲለፍፍ የትግራይን ወገኑን ለማስነከስ እና ለማነካከስ የማይታክተው ቡድን በትግራይ የእናቶች ዘመቻ በድል ተጠናቀቀ ከ30 ሺህ በላይ ሠራዊት ተደመሰሰ፤ 19 ታንኮች 1 ቢኤም እና በርካታ መሳርያዎች ተማረኩ፤ ተወንጫፊ ሮኬቶች፣ በመቶዎች የሚቆጠር የሬዲዮ መገናኛዎች ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችን ያዝን እና አቃጠልን ሲል የማይጠገብ ቀልዱን እየረጨ ይገኛል፡፡
የአማራ እና የኦሮሞ ሚሊሻዎች ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩ ኃይሎች ወደ መጡበት ተበታትነዋል።በአንድ ጊዜ በሦስት ግንባሮች በፅናት እና በብልሐት አንጀት የሚያርስ ተግባር በመፈፀም የትግራይ እናቶችን ዕምባ ማበስ መቻላቸውን ተናግረዋል።ነገር ግን የትግራይ እናት ዕንባ የሚታበሰው በውሸት ድራማ እና ልጆቻቸው በጦርነት ውስጥ ተሳትፈው ሲሞቱ ወይም ለዘለዓለም በሚከተላቸው መጥፎ ትዝታ ውስጥ ሲያልፉ አለመሆኑን የህውሓት አሸባሪ ቡድን አባላት ህሊና ስለሌላቸው አይረዱትም።ልጆቻቸው ለጦርነት ተማግደው ዘመቻው በእነርሱ ስም መሰየሙ የትግራይ እናቶችን ዕንባ ማበስ አይደለም።እንደውም በቁስላቸው ላይ እንጨት እንደመስደድ ነው፡፡
በትግራይ እናት ስም ድል ቀንቶኛል ያለው አሸባሪ ቡድን ወደ ስልጣኑ እና ወደ ተንደላቀቀ ኑሮ ለመመለስ የማይሞክረው እና የማይገፋው ዳገት፤ የማይገለብጠው ድንጋይ፣ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም።እናትን የመሰለች የተከበረች ፍጥረት በስሟ ዘመቻውን ሰይሞ በመዋጋት ድል መቀናጀት፤ አልፎ ተርፎ የፈለገውን ማሳካት የሚችል መስሎታል።ነገር ግን መጨረሻው ተቃራኒው ነው።ምክንያቱም በእናት ላይ ግፍ የሠራ መጨረሻው ይታወቃል።ዳገቱ አይገፋለትም።ይልቁኑ በቆፈረው ጉድጓድ ገብቶ በፈነቀለው ድንጋይ ይቀበራል።
መንግሥት የሰዎችን ሞት ለመቀነስ የተኩስ አቁም አዋጁን ሲያስከትል አዋጁን ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት በማድረስ ራሱም ተኩስ እንደማቆም የራሱን የበላይነት ለማስጠበቅ የትግራይን እናት ዕንባ ከማበስ ይልቅ ይበልጥ ከዕንባ ያለፈ ደም ማስለቀስን መርጧል።ምክንያቱም ቡድኑም ሆነ የቡድኑ አባላት ባለ ድሃ አዕምሮ እና ህሌና ቢሶች ናቸው።
ያልተሸነፈ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ለቆ ስለወጣ መከላከያ እንደተሸነፈ የማስመሰል ፕሮፓጋንዳን ከመዝራት ባለፈ በተለያየ ግንባር ጦርነት መክፈትን ተያይዘውታል።መንግሥት ቀዝቀዝ ብሎ ህዝብን ለማረጋጋት ተኩስ ቢያቆምም የትግራይ እናቶች ጠላት የሆነው የህውሓት አሸባሪ ቡድን ግን በስማቸው ዘመቻን እየከፈተ ወገንን ከወገን ጋር እያናከሰ አገርን እያንኳሰሰ ዘመኑን እያራዘመ ነው።
አሁን ደግሞ በየአቅጣጫው የሚፈፅመውን ከትንኮሳ ያለፈ ዜጎችን የማፈናቀል፣ የማሳደድ እና ቤታቸውን የማቃጠል እንዲሁም ህይወት የማጥፋት ድርጊቱን ተከትሎ ተኩስ አቁም ያለው መንግሥት፤ ሠራዊቱ ህግ ማስከበሩን ይቀጥል ማለቱን ተከትሎ ከትግራይ እናቶች የነጠቃቸውን ልጆች ቡድኑ ማጣት ጀምሯል።መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በአሸባሪው ድርጊት በመቆጣት የቡድኑን ግብአተ መሬት ለመፈጸም በመትመም ላይ ይገኛል።
ይህ ኢትዮጵያን አላስፈላጊ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ለመጨመር ቆርጦ በመነሳት የችግሮች ሁሉ ምክንያት ሆኖ እስከ አሁን የቆየው የአሸባሪው የህወሓት ቡድን፤ አባላቶች የራሳቸውን ልጆች ውጭ ሀገር እያሰተማሩ ሕፃናትን ትርጉም ለሌለው ጦርነት ከእናታቸው ጉያ እየነጠቁ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም ጉዳዩ ዕልባት ማግኘቱ አይቀርም።በአሸባሪው ህወሓት በግዳጅ የትግራይ እናቶች ዘመቻ በሚል በተሰየመው ጦርነት በአፋር ፈንቲ ረሱ ግንባር ያሰለፋቸው ሕፃናትና ወጣቶች እየጠፉ እጅ እየሰጡ ነው።ብዙዎች ደግሞ ሞተዋል።አሸባሪው ህውሓት አሁን በቆፈረው ጉድጓድ እየተቀበረ ነው።በገባበት ከተማ እየተከበበ ለመውጣት ተቸግሮ እጅ እየሰጠ እምቢ ያለው ደግሞ በማለቅ ላይ ነው።አሁን ደግሞ የትግራይ እናቶች ድል ያደረጉ ልጆቻችንን አሳዩን ሲሉ ቡድኑ የሚያሳየው ምን እንደሚሆን እናያለን።ከዚህ በኋላ እንኳን የቀረ ነገር ያለ አይመስልም።
የፌኔት እናት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013