‹‹መሪ ነኝ›› ባዩ ሰው መቀሌ ከተማ ‹‹ማይ ወይኒ›› ትምህርትቤት ተገኝተዋል። አካሄዳቸው እንደወጉ ለተማሪዎች ሽልማት ለመስጠት፣ አልያም ‹‹አይዟችሁ›› ብሎ ለማበርታት አይደለም። ከቦታው የመድረሳቸው ዓላማ በእሳቸው ጠብ አጫሪነት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እናቶችና ሕፃናት ለመጎብኘት ነው።
‹‹የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ›› ሆኖ አሸባሪው ደብረጽዮን በስፍራው ሲገኙ እንደተለመደው ‹‹አለሁላችሁ›› ከሚል ቀጣፊ አንደበት ጋር ሆኗል። ሰውዬው ዛሬም የፈጸሙት እኩይ ተግባር ያሳፈራቸው አይመስልም። እንደውም ርህሩህ በሚመስል አቀራረብ ብዙዎችን ለማሳመን ችለዋል።
ከማይ ወይኒ ትምህርትቤት ወለል ከወደቁት አብዛኞቹ አዛውንትና ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ጨቅላ ሕፃናት የታቀፉ አራስ እናቶች በርሀብ ጎናቸው ያዛጋሉ። ደብረጽዮን ወደ ጥቂቶቹ ተጠተግተው ሁኔታቸውን ጠየቁ። እናቶቹ በጦርነቱ ማይካድራና ሳምሪ ከተባሉ ቦታዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ተናገሩ። ሰውዬው ስለነዚህ ቦታዎች ሲሰሙ ፈጽሞ አልደነገጡም። በይማካድራ በርካታ ንጹሐን በግፍ መጨፍጨፋቸውን አሳምረው ያውቃሉ። ስለሆነው እኩይ ድርጊት ሁሉ እሳትና ክብሪቶቹ እሳቸውና መሰሎቻቸው ናቸው።
እውነታውን እንዳልነበር ንቀው ገሸሸ ያሉት ደብረጽዮን በትሁት ገጽታ ተፈናቃይ እናቶችን ማናገር ይዘዋል። እናቶቹ ጨቅላ ሕፃናቱን እያባባሉ የውሳጣቸውን ይተነፍሳሉ። ከእነዚህ መሀል አንዲት ወጣት ልጇን የወለደችው በዚሁ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለመሆኑ ገለጸች።
ወላዲቱ እንደ እናቶች ወግ መጋረጃ ተጥሎ ፣ገንፎ ተዘጋጅቶ፣ ማር ቅቤው ቀርቦ አልታረሰችም። በቂ ምግብ ያላየው ጎኗ ያረፈው ቅዝቃዜ በወረሰው የትምህርት ቤቱ ወለል ሆኗል።
ደብረጽዮን ይህ እውነት አልደነቃቸውም። የእናቶቹን መጎሳቆል፣መራብና መፈናቀል፣ ነገሬ አላሉትም። ዛሬም ትምክህት የሞላው፣ ጦርነት የሚሻው አንደበታቸው ያለማቋረጥ ክፋትን ይሰብካል።
ሰውዬው አሁንም ማይካድራን የሚያስቡት የንጹሐንን ሞት እያስታወሱ አይደለም። ለእሳቸው የበርካቶች ደም መፍሰስ የተለመደ ባህላዊ ጦርነት ነው። ለእሳቸው አንድ ወገንን ለይቶ መጨፍጨፍ ተገቢ የሚባል ተግባር ነው። ዛሬም ቢሆን አልሞት ባይ ማንነታቸው መሬት ስለማስመለስ ፣ ድንበር ስለመውረር ደጋግሞ ይጮሓል።
ደብረጽዮን በስፍራው የወደቁ እናቶችን ሲቃኙ የእሳቸውና የመሰሎቻቸው ልጆች ምቾት ለአፍታ ውል አላላቸውም። በእናቶቻቸው ክንዶች ያረፉ ምስኪን ጨቅላዎች፣ ደረቅ ጡት እየማጉ ስለመሆኑም ነገሬ ያሉት አይመስልም። በአውሮፓና አሜሪካ የሚንደላቀቁ ልጆቻቸው ስለእነዚህ ወገኖች መኖርና መፈጠር አንዳች እንደማያውቁ እርግጠኛ ናቸው።
ችግር ያጎሳቆላቸው፣ ርሀብ የጎበኛቸው፣ መታረዝ ያያቸው እናቶች በምቾት ከሚንደላቀቁ ሴቶቻቸው ጋር ፈጽሞ አይወዳደሩም። እነሱ በሀብት ላይ ሀብት፣ በወርቅ ላይ ወርቅ፣ የሚደርቡ ቅንጡዎች ናቸው። ዘመናዊ መኪኖቻቸውን ሲለዋውጡ ፋሽኑ ሳያልፍበት ዘመኑ ሳይቀየር ነው። በውጭ አገራት እየኖሩ አገርቤት በውድ ዋጋ የገነቧቸው ሕንፃዎች ከበርካታ ዜጎች ላብና ደም የተቀዱ ናቸው።
እነሱ እንደ ትግራይ እናቶች ልጆቻውን በትምህርት ቤት ወለልና በየጫካው አይወልዱም። ሁሌም የልጅን ሲሳይ የሚቀበሉት ‹‹አሜሪካዊ›› ከሚል ዜግነት ጋር ነው። እንዲህ ይሆን ዘንድ ከስልጣን ያሉ፣ ባሎቻቸው ያከማቹት የህዝብ ሀብትና ንብረት ያሻውን ይፈጽማል።
የሁለቱ እናቶች ወግ ፈጽሞ አንድ አይደለም። ይለያያል። በመሀላቸው ያለው የኑሮ መልክ፣ የህይወት ትልምና የመኖር ተስፋ የተዥጎረጎረ ነው። ‹‹እናት›› የሚለው ስያሜና የመዳረሻው ጥግ ሲመረመር ትርጓሜውን ያዛባል። ዕንባና ሳቅ፣ ኀዘንና ደስታ፣ ርሀብና ጥጋብ መቼውንም አንድ ሆነው አያውቁም። የኑሮ ገጽታና የህይወት መስመራቸውም በእኩል መስፈርት ሚዛን አይደፋም። ምናልባትም ከጾታ መመሳሳል ውጪ አንድ የሚያደርጋቸው አንዳች ምክንያት ሊኖር አይችልም።
አሁንም በ‹‹ማይ ወይኒ›› ትምህርት ቤት የዶክተር ደብረጽዮን ጉብኝት ቀጥሏል። ሰውዬው በስፍራው ያሉ ተፈናቃይ እናቶችን በትህትና እያነጋገሩ፣ ተስፋ የለሽ ተስፋን መለገስ ይዟል። የዶክተሩ የአንደበት ቃል ሰላምና ፍቅርን አይሰብክም። ዙሪያቸውን ለቆሙ በርካታ ተፈናቃዮች ‹‹ወራሪ›› ያሉትን የመንግሥት ኃይል ለመውጋት ከጦር ሜዳ እንዲውሉ አጥብቀው ያነሳሳሉ።
ቴሌቪዥን ቀረጻና ትርክት እንዲያመች ሆኖ ለአስተያየት የተመረጡ አንዳንዶች ደጋግመው የመንግሥት ጦር መደምሰሱን ይናገራሉ። ከዚሁ ተያይዞም ራሳቸውን ለጦር ሜዳ በመመልመል ልጆቻቸውን ጭምር ለመስዋዕትነት እንደሚያቀርቡ ቃል ይገባሉ።
ዶክተሩ ‹‹እንሞትላችኋለሁ›› ለሚሏቸው የትግራይ ህዝቦች ደጋግመው የጦርነትና የውጊያ ታሪክን ይሰብካሉ። የትግራይ እናት ልጇን ለማስገደል በዕጩነት እንድታቀርብ ከግዴታ ሲጥሏትም በእሳቸው መሪነት የተፈጸመን ግፍ ሸምጥጠው በመካድ ነው።
አንዳንድ እናቶች ‹‹መሪያችን›› የሚሏቸውን ሰው ስብከት ተከትለው ለወደመው፣ መሰረተ ልማት የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ ያደርጋሉ። ይህን አባባል ከልብ የሚሹ የስፍራው አሳሳቾችም ቃላቸውን አድምጠው ልጆቻቸውን ለሞት እንዲገብሩ ቃል ያስገባሉ።
እነሆ! አሁን የትግራይ እናቶች ለጦርነቱ የልጅ ግብር ይዘዋል። ይህ እንዲሆን ግዳጅ የጣሉባቸው የህወሓት አመራሮች የእነሱን ልጆች ባህር ማዶ ካሸሹ ቆይተዋል። በድሀዋ እናት ልጆች ደም የጦርነት ጨዋታ የጀመሩት ህወሓቶች ዕለት በዕለት የሚማግዷቸው ሕፃናት ስቃይና መከራ ለአፍታ አሳስቧቸው አያውቅም።
ከአርባ አምስት ዓመታት በፊት ህወሓት ትግል ልጀምር ብሎ ሲነሳ ምክንያትና ሰበቡ የትግራይ ህዝብ ነፃነት ነበር። ስልጣኑን ከደርግ ተረክቦ በቆየባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ግን ከህዝቡ ነፃነትን ይሉት ታሪክን ገፈፈ፣ስልጣኑን መከታ አድርጎም የግል ጥቅሙን አሳደደ። ከህዝብ በሚዘርፈው አንጡራ ሀብት የባለስልጣናቱን ኑሮ አዘመነ።
ዛሬ በአውሮፓና አሜሪካ የሚንፈላሰሱ የባለስልጣናት ሚስትና ልጆች ካሉበት ሆነው አገር ለማፍረስ ይተጋሉ። ይህን ሲፈጽሙ አገር ቤት ለሚገኙ ድሀ ወገኖቻቸው፣ በርህብ አለንጋ ለሚቀጡ ጨቅላዎች ደንታ ኖሯቸው አያውቅም። እነሱ በኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት እየተማሩ፣ በዘመናዊ ኑሮ ይንፈላሰሳሉ። የድሀዋን ልጅ ለእሳት እየማገዱ በዶላር ይጫወታሉ።
መቼም ቢሆን የሁለቱ እናቶች ማንነት ተመሳሳሎ አያውቅም። የአገር ቤቷ ‹‹አደይ›› ከባህርማዶዋ ቅንጡ ‹‹ማሚ›› በእጅጉ ትለያለች። ምሰኪኒቷ የትግራይ እናት በዕርዳታ ስንዴ ልጇቿን ያሳደገች፣የትዳር አጋሯን ለዘመቻ የሰዋች፣የአብራኳን ክፋዮች ለጦርነት የማገደች ናት።
የትግራዋይ እማማ ጫጩቶቿን ከአሞራ እንደምትጠብቅ እናት ዶሮ ተሳቃ ኗሪ ናት። ጭልፊቶች በሰማይ እንደሚያንዣብቡ፣ ልጅ መልማዮች በሰፈሩ በዞሩ ቁጥር አቅሏን ታጣለች። ልጇቿን ከጉያዋ ነጥቀው፣ ፍሬዎቿን ከእጇቿ ፈልቅቀው ለጦርነት ሲማግዱባት ለምን? ባይ አንደበት የላትም። ከድህነት ማጥ ዳክራ ያሳደገቻቸውን ልጆች በጨካኞች ስትዘረፍ ፣ ጨኸቷ ሰሚ ጆሮ አያገኝም።
አደይ ‹‹ልጆቼ ደረሱልኝ›› ባለች ጊዜ ጠላፊዎች ፈጥነው ይነጥቋታል። ባልጠና ጉልበት ባልጠነከረ አካል መሳሪያ አስታጥቀው በረሀ በላኳቸው ጊዜ ትኩስ ዕንባ ከማውረድ ውጪ መብት አይኖራትም። እንዲህ ይሆን ዘንድ ምስኪን የትግራይ እናት መሆኗ ብቻ ግድ ይላታል። የትግራይ እናቶች የዘመናት ታሪክ እንዲህ ሆኖ ቀጥሏል። ጦርነት፣ የልጅ ንጥቂያ ፣ የከፋ ኀዘንና ዕንባ ።
በአውሮፓና አሜሪካ ያለችው ማሚ ታሪክ ደግሞ ከአገርቤት እህቷ ህይወት በእጅጉ ይለያል። ይህቺኛዋ እናት የበቀለችው እንደ አገር ቤቷ ‹‹አደይ›› በትግራይ ምድር ነው። የሁለቱ ህይወትና ማንነት ግን በመልክ የወተትና ከሰል ያህል ተለያይቶ ዓመታትን ተሻግሯል።
የአውሮፓዋ እናት ኑሮና ህይወቷ እጅግ የዘመነ ነው። ልጆቿን በምቾት ለማሳደግ ከአገር የወጣችው በባለቤቷ ትዕዛዝና መመሪያ ነበር። ባለቤቷ በአገር ቤት ስልጣኑ አድራጊ ፈጣሪ ነበርና ያለችውን ለመፈጸም ዓይኑን አያሽም።
ይህች እናት ልጆቿን ውድ ከተባለ ትምህርት ቤት ታስተምራለች። ለእሷና ለቤተሰቦቿ በቂ የህክምና ኢንሹራንስ አላት። በፈለገች ጊዜ አገርቤት ለመምጣት፣ያመራትን ቦታ ከድሆች ነጥቃ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ለመገንባት መብቱ አላት። ይህን ለማድረግ ከዘመድ ወዳጅ ብድርና ዕዳ አትገባም። ባለስልጣን ባሏ ከበርካታ ባንኮች የሚያፍሰው ረብጣ ገንዘብ ከእሷ አልፎ ለዘመዶቿ ይተርፋል።
የአውሮፓዋ ማሚ ለሽርሽር በምትመርጣቸው ዱባይና ቱርክ የቅንጦት ዕቃዎች ለማምጣት፣ ከልካይ የላትም፤ ያለቀረጥ ያሻትን እንድታስገባ፣ በእጥፍ ዋጋ ያማራትን እንድትሸጥ፣ እንድትለውጥ መንገዷ ክፍት ነው። ራሷን ባተኮሳት ብርድ ብርድ ባላት ጊዜም የውጭ አገራት ሆስፒታሎች በር ሁሌም ተከፍተው ይቆዩዋታል።
አንዳንዴ እሷና መሰል እናቶች ለዕረፍት አገር ቤት ብቅ ሲሉ ከወዳጅ ዘመዶች መታደም ያምራቸዋል። እነሱ ‹‹ግብዣ ቢጤ›› ሲሉ በሚያሳንሱት ታላቅ ቀንም ከባለ ኮከብ ሆቴሎች ደግሰው በጭፈራ ያነጋሉ። ይህ ዓይነቱ ልማድ ሸራተንን በመሰሉ ታላላቅ ሆቴሎች የልጆቻቸውን ልደት ጭምር በማክበር የተለመደ ሆኖ ኖሯል።
የአሜሪካዋይ ማሚ በአንድ ቀን የምትመነዝረው ዶላር ለትግራዋይ አደይ የዓመታት ቀለብ መሆን ይችላል። የትግራዋይዋ አደይ እንደ አሜሪካዊቷ ማሚ ለልጆቿ ጣፋጭ ኬኮችን አታስብም። ለእሷ ጉልበቷን ገብራ ከሴፍቲ ኔት የሚቆነጠርላት ስንዴና የሚሰፈርላት ዘይት በቂዋ ነው። ያም ቢሆን በወጉ የማይገኝበት፣ ስፍሩ የማይሞላበት፣ ጊዜ የበረከተ ነው። ልጆቿንም ለጦርነት ካላዋጣች ዕርዳታውም ይቆማል።
ትግራዋይዋ አደይ መከራና ችግር ፣ጦርነትና ስደት ለእሷ ብቻ የተሰጡ እስኪመስል ተቀብላው እንድትኖር ግዳጅ ተጥሎባታል። ዛሬ በትግራይ ምድር ልጆችን ማስተማር፣ መዳርና መኳል፣ ለወግ ማዕረግ ማብቃት ነውር ሆኗል። እያንዳንዷ እናት የወለደችውን ልጅ ለጦርነት፣ እሳት እንድትማግድ ግድ ይላታል።
አደይ ልጆቿን በተዘረፈች ማግስት የመኖር ተስፋዋን ጭምር ታጣለች። አንድ ቀን ደግሞ የጠዋት ማታ ዕንባዋን አብሳ ‹‹ልጆቼስ›› ማለት ከጀመረች እሷም ውጊያውን እንድትቀላቀል ትጠየቃለች። ይሁንታዋ ከተሳካ ህወሓቶች ዳግም ስለዛ ቤተሰብ የሚጠይቃቸው አይኖርም። ትውልድ አጥፍተው፣ ጎጆ አዘግተው፣ የሌሎች ትግራዋይ ህልሞችን ሊያጨልሙ ይፈጥናሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም አሁን ለደረሱበት ደረጃ ኢትዮጵያ ያደረገችላቸውን ውለታ አሳምረው ያውቁታል። የእሳቸው መሰረት ከህውሓት ምንጭ መቀዳቱ ግን የክህደት እጃቸውን አስቀድመው እንዲያሳዩ መስክሮባቸዋል።
ቴድዎሮስ እስከዛሬ ህውሓት ይሉት ድርጅታቸው ስለፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት ሲያወግዙና ሲቃወሙ አልተሰሙም። ይባስ ብለው በዓለም አደባባይ ማንነቱን ማወደስና ዓላማውን ማቀንቀን ጀምረዋል።
እኚህ የዓለማችን ጉምቱ ባለስልጣን ከተረከቡት ታላቅ ኃላፊነት አንጻር በህውሓት የትግራዋይ ልጆች በጦርነት መማገዳቸውን ጠቅሰው ለዓለም ማህበረሰብ ‹‹አቤት›› ሲሉ አልተደመጡም። መማር የሚገባቸው ሕፃናት ዛሬ ለውጊያ የመሰለፋቸውን ሀቅ ማጽደቅ በሚመስል እውነታ በዝምታ አልፈውታል።
ዶክተሩ የትውልድ አገራቸው ሕፃናት ህልም ስለመምከኑ ደንታ የሰጣቸው አይመስልም። ልጆቹ በዚህ ዕድሜያቸው ከደብተሩ፣ መሳሪያውን፤ ማንገባቸው፣ ከወተቱ፤ ጥይቱን መጠጣታቸው ፈጽሞ አላሳዘናቸውም። ይግረማችሁ ብለው በውጭ አገር ትምህርትቤቶች፣ በኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት ያስተረማሯት ልጃቸው ስለመመረቋ ሊያሳዩን ፈጠኑ።
ቴዎድሮስ ይህን ሊያውጁ ሲነሱ በጦርነቱ በትግራይ ስለተዘጉ ትምህርትቤቶች አልተጨነቁም። እንደቆሎ ተበትነው ስለቀሩት ተማሪዎችም ደንታ አልነበራቸውም። ዓላማቸው ልጃቸውን አሳድገው፣ አስተምረው ለወግ ማዕረግ ማብቃታቸውን ማሳየት ብቻ ነው። እሳቸው ማንነታቸውን ሊያስመሰክሩ ሲሞክሩ ስለትግራይዋ እናትና መና ስለቀሩት ልጆቿ አልተደነቁም።
የዶክተሩ የፊት ጸዳል በደስታ የመፍለቅለቁ ምክንያት ስለሀገራቸው እልፍ ሕፃናት መማር አይደለም። የውስጣቸው እርካታ ምስጢሩ በላብ በጉልበታቸው ልጅን ለፍሬ ማብቃታቸው አልነበረም። የእሳቸውን ልብ ደርሶ ደስ ያለው ከዓለማችን እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ ልጃቸውን የማስመረቃቸው ኩራት ሆኗል።
የሀገርን ሀብትና ንብረት ዘርፎ ወደውጭ አገራት መሸሽ ልምዳቸው የሆነው ህወሓቶች አሁንም ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ለመሹለክ መሞከራቸው አልቀረም። የሰላም ማስከበሩ ሂደት ከተጀመረ በኋላ አንገታቸው የተያዘው ርዥራዦች በየአጋጣሚው ድንበር ለማቋረጥ ሲሞክሩ ተይዘዋል።
በአንድ ወቅት የሠራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ በሰጡት መግለጫ የጁንታው አባላት ከሀገር ለመውጣት ያደረጉት ጥረት በመከላከያ ሠራዊት ክንደ ብርቱነት ለመክሸፍ ችሏል። እነዚህ አካላት አስቀድመው ቤተሰባቸውን ያሸሹና ኑሯቸውን በውጭ አገራት ያደላደሉ ናቸው።
ጁንታዎች ስልጣናቸውን በህዝቡ ከተነጠቁ ወዲህ ወደ ባህርማዶ ለማምለጥ ሲጣጣሩ መቆየታቸው ተረጋግጧል። ለእነሱ መንገድ ሲጠርጉ የቆዩ ተባባሪዎች ልብሳቸውን ቀይረውና የተለየ መታወቂያ ሰጥተው ካሰቡበት ሊያደርሷቸው ሞክረው ነበር። እንዳሰቡት ሆኖ ዕቅዳቸው አልሰመረም። አብዛኞቹ ከመደምሰስና ጥቂቶቹ ወደ አይጥ ዋሻቸው ከመመለስ አልዳኑም።
በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሲሸሹ ከተያዙትና ርምጃ ከተወሰደባቸው ጁንታዎች ኪስ የተገኘው መረጃ በኦሮሞ ብሄር የተሰየመ የሐሰተኛ መታወቂያ ነበር። ይህን ስልት መጠቀማቸው በአማራ ክልል ድንበር ሲያልፉ ማንነታቸውን ለመደበቅ ሲባል ነው።
ዛሬም ቢሆን የአሸባሪው ህውሓት አንገት አልተደፋም። ሕፃናትን ከቀያቸው እየመለመለ ለውጊያ መማገዱን ቀጥሏል። አሁንም የትግራይ እናቶች ዕንባ አልደረቀም። እንደ ክፉ ቀን ጅብ ከእናቶቻቸው ጉያ የሚነጠቁ ሕፃናት ደም እየጮኸ ነው። ውጊያው ተባብሶ ቀጥሏል። ትምህርት ቤቶች፣ የድሀ እናት ጎጆዎች የኋሊት ተዘግተዋል።
የርሀብ ጎናቸውን የደገፉ እናቶች በየቀኑ በየጫካው ስለሚሞቱ ትናንሽ ልጆቻቸው ይሰማሉ። መኖር መሞታቸው ያልታወቀ ብዙሐን፣ የነገ ህልማቸው መክኖ ከሌሎች ወገናቸው ጋር ደም እንዲቃቡ ፣ ቁርሾ እንዲያተርፉ ተገደዋል። ሁለት መልክ ያላቸው የትግራይ እናቶች በደስታና መከራ፣ በምቾትና ለቅሶ መሀል ሆነው የዚህችን ዓለም ህይወት በእኩል ያወጋሉ። የሁለቱ እናቶች ወግ በዕንባና ሳቅ፣ በምቾትና መከራ ተከቧል።
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013