ከሃዲው ትሕነግ እርሱን ሲመቸው ባለስልጣንም ባለሀብትም፣ ባለታንክም ባለባንክም፣ ምሁርም ኢንቨስተርም፣ አስመጭም ላኪም፣ ቀጣሪም ተቀጣሪም፣ አሠሪም ሠራተኛም፣ ሠራተኛ አገናኝም፣ ውል ሰጭና ተቋራጭም፣ ጨረታ አውጭም ተጫራችም… በሁሉም ቦታ ሁሉንም ነገር ሆኖ ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን እንዳሻው አድርጓታል፣ አድርጎባታል።
በቀጣይም ለእርሱና ለእርሱ ብቻ የምትመች በጎሳ፣ በቋንቋና በሃይማኖት ተከፋፍላ የተዳከመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ ማለትም ሁሌም እርሱ ብቻ የበላይ ሆኖ የሚኖርባት “አዲሲቷ ኢትዮጵያ”ን ዕውን ለማድረግ ታጥቆ እየሠራ ነበር።ይህን ዓላማውን ለማሳካት ትሕነግ ለግማሽ ክፍለ ዘመናት ያህል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጥላቻ መርዝ ሲረጭ ቆይቷል።ይህም አገሪቱ ተዘርዝሮ በማያልቅ ግፍና መከራ እንድትሰቃይና በታሪኳ አይታው በማታውቀው ሁኔታ እንድትዋረድና እንድትጎሳቆል አድርጓታል።
ይሁን እንጂ ልጆቿ ባደረጉት መራር ትግል በከፈሉት ውድ መስዋዕትነት ትሕነግ ሁሌም በኢትዮጵያ ላይ በብቸኝነትና በበላይነት ነግሦ የመኖር ዲያብሎሳዊ ህልሙ ከሽፎበታል።በመሆኑም ስግብግቡ ትሕነግ ለሃያ ሰባት ዓመታት ሁሉንም በሞኖፖል ጠቅልሎ ይዞ ሁሉንም ሆኖ ያሻውን እያደረገ በድሎትና በቅንጦት ተከብቦ በጌትነት የኖረባትን፣ አልፎ ተርፎም የምዕራባውያን ሀብታሞችን ሳይቀር ያማለለ፤ አንዳንዶችንም ከሀብታምነት ክብራቸው አውርዶ ተላላኪ ቅጥረኛ ያደረገ በትሪሊዮን ዶላር የዘረፈባትን ሃገር “በእኩልነት ተጠቀምብኝ” ስላለችው ብቻ ሊያፈርሳት ተነሳ።እናም ሃገርና ሕዝብ ሃገርን ሊያፈርሱ የሃገርን ዘብ ከወጉ፣ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል መግባት ካለብን ሲኦል መግባት አለብን” ከሚሉ ሃገር በቀል ሃገር አፍራሾች ጋር የሕልውና ትግል እያደረገ ይገኛል።
ከዚህ አኳያ ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት በሌላ ዓለም ላይ እንደታየውና እንደሚታየው ዓይነት ከውጭ ጠላት ጋር የሚደረግ ወይንም በስልጣን፣ በሀብት ሽሚያ የተነሳ እርስ በእርስ የሚደረግ ጦርነት አይደለም።ጦርነቱ እየተደረገ ያለው በግልጽ ሃገርን ለማጥፋት ፎክሮ ከተነሳ የራስ ጠላት ጋር ነው።
ሃገርንና ሕዝብን ከጥፋት ለመታደግ እየተደረገ የሚገኝ የሕልውና ጦርነት ነው።ስለሆነም ሃገርን ለማጥፋ እየተዋጋ ያለው አሸባሪው ትሕነግ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የህልውና ጦርነት በተጻራሪ የቆሙ ማናቸውም አስተሳሰቦችና ድርጊቶችም ጁንታው በጦር መሳሪያ እያካሄደ ከሚገኘው ሃገርን የማፍረስ ድርጊት ባልተናነሰ ሃገርና ሕዝብን የሚያጠፉ ናቸው።ከህልውና ዘመቻው በተቃራኒ የቆመ ማናቸውም አካልም ከትሕነግና ከጀሌዎቹ ሸኔዎች እኩል አሸባሪ ነው።ልዩነቱ አሸባሪው ትሕነግና ሸኔ ቀድሞውኑም ጠላትነታቸው ታውቆ በሕዝብና በመንግሥት በግልጽ “አሸባሪ” ተብለው የተፈረጁ መሆናቸው ነው።በአስተሳሰቡና በድርጊቱ የእነኝህን የአገር ጠላቶች ድርጊት የሚገልጽ አካል የአሸባሪዎች የግብር ወይንም ባህሪይ ልጅ ነውና “አሸባሪ” ተብሎ ባይፈረጅም አሸባሪ ነው።
ይህን ለምን እንዳልን ጥቂት ማሳያወችን እያነሳን ጉዳያችንን እናስረዳ።በሃገርና በሕዝብ ውስጥ እየኖሩ በልዩ ልዩ መንገድ ሃገርን በማፍረስ ሥራ ላይ ከተሰማሩ አካላት መካከል በዋነኝነት በዚህ ጽሑፍ ላሳይ የምፈልገው ሁለቱን ነው።በሕዝብ ሥነ ልቦና እና በሕዝብ ኑሮ ላይ ሽብር በመፍጠር የተጠመዱትን የአሸባሪው ትሕነግ የግብር ልጆችን ነው።የመጀመሪያወቹ የአሸባሪው ትሕነግ የግብር ልጆች ኃይልና ሀብት የሆነውን መረጃን ለጥፋት የሚጠቀሙ ሽብር ፈልሳፊና አስፋፊ የሃገርና የሕዝብ ጠላቶች ናቸው።እነዚህ አሸባሪዎች ኃይል የሆነውን መረጃ በአግባቡና በተገቢው መንገድ ለጥቅም በማዋል የሰው ልጆችን ሊጠቅም የሚችል አዎንታዊ ኃይል በመፍጠር መረጃን ቆራርጠው፣ አዛብተውና አሳስተው ሆን ብለው ለጥፋት ይጠቀሙበታል።
ምንጫቸው ያልታወቁና የተሳሳቱ መረጃወችን በስፋት በማሰራጨት የሕዝብን ሥነ ልቦና ይረብሻሉ፤ ፍርሓትና አለመረጋጋትን ይፈጥራሉ።እናም ሃገር ለማዳን የሚደረገውን የህልውና ትግል ኃይሉን ያዳክማሉ።የሃገር አፍራሹን አሸባሪ ጠላት ኃይል ያጠናክራሉ።ታዲያ እነዚህ አካላት ከአሸባሪው ትሕነግ በምን ይለያሉ፤ ደግሞስ ሃገር የማፍረስ ኃይሉን እንዲያጠናክር አስተዋፅኦ እያደረጉ ከሆነ ከእርሱ ከአሸባሪውስ አልባሱምን?
በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ደግሞ ሃገርና ሕዝብ የገቡበትን ፈተና ለእነርሱ እንደ ምቹ ሁኔታ፣ ችግርን እንደ መልካም ዕድል ተጠቅመው በወገን ጥፋት ለመልማት፣ በሕዝብ ችግር ለመበልጸግ የሚፈልጉ በየቀኑ አላግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው።በዚህም ሕዝብ በኑሮ ውድነት እንዲጎሳቆል፣ ለምሬትና ለተስፋ መቁረጥ እንዲዳረግና ከአገር አፍራሹ የሽብር ቡድን ጋር እያደረገ ያለውን የህልውና ትግል እንዲተውና ዳግም ለግፍና ለባርነት እንዲያድር እየሠሩ የሚገኙ ህሊና ቢስ ቁሳውያን ናቸው።ይህ ደግሞ ባለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመን የሚጠጉ ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነውንና እየገነገነ የመጣውን “የእኔ ብቻ ልጠቀም እና የልብለጥ” ባህል ተከትሎ ትብብርን መሰረት ያደረገውና ለፍትዊ ዕድገት ድልድይ ሆኖ የሚያገለግለውን የኢትዮጵያውያን የማህበራዊነት ባህልም በአደገኛ ግለኝነት እንዲተካ ያደረገ የትሕነግ አስተሳሰብ ውርስ በመሆኑ ፍጹም ሊታገሉት የሚገባ አደገኛ ጅምር ነው።
በማህበራዊ አኗኗር በምትታወቀው ሃገር ውስጥ፤ በመተባበርና ተደጋግፎ በመኖር በምትታወቀው ሃገር ውስጥ የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድም፣ ስለሌላው መጎዳትና መውደቅ ደንታ የሌለው፣ መተሳሰብና መተዛዘን የሚባል ነገር የማያውቅ አጅግ አደገኛና ቅጥ ያጣ ትሕነጋዊ የስግብግብነት ባህሪ በእንጭጩ ሊታረም ይገባል።
እንዲህ ዓይነቱ ትህነጋዊ ስግብግብነት ሃገር የማዳን የህልውና ትግሉንም እያስተጓጎለ በመሆኑ ዕርምጃ ሊወሰድበት ይገባል።የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊና የዚህ ጽሑፍ አቋምም ይኸው ነው።አገርን ከመፍረስ ለመታደግ በአሸባሪው ትሕነግ ላይ እየተደረገ ያለው የህልውና ዘመቻ አሸባሪ ተብለው ሳይፈረጁ በአገርና በሕዝብ ውስጥ እየኖሩ በልዩ ልዩ መንገድ አገርን በማፍረስ ሥራ ላይ የተሰማሩ የአሸባሪው ትሕነግ የግብር ልጆችንም እንዲያካትት ጥሪ ማቅረብ፣ መንግሥትና ሕዝብ ልክ እንደ አሸባሪው በእነርሱ ላይም ዕርምጃ እንዲወሰድ መጠየቅ ነው።ለራስ ብቻ መኖር፣ ግለኝነት፣ ጥቅመኝነትና ስግብግብነት፣ ትሕነጋዊነት ይውደም፤ አብሮነት፣ እኩልነትና መልካምነትና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑር!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013