የይሁንልን ትርክት፤
ጠቢቡ ሰለሞን “እንዲህ ብሏል” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ መዝግቦልናል። “የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፤ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም። ‹እነሆ፣ ይህ አዲስ ነው› ሊባል ይቻላል? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተድርጓል።” (መጽሐፈ መክብብ፤ ምዕ. 1፤9-10)። ፍልስፍናውን በአሜንታ የተቀበልንለት ይህ ጠቢብ የደመደመውን እውነታ በእኔ የመረዳት ልክ እየፈለቀቅሁ በአንድምታ ልተርጉመው ብል የብዕሬን ጉልበት ከመፈታተን ውጭ የምጨምረው ኢምንት ነቁጥ አይኖርም። ስለዚህም “ከፀሐይ በታች አንዳችም አዲስ ነገር ከሌለ፤ ይኖራል የምንለውም የነበረ ከሆነ” የሚሻለው ይህንን መደላድል ተንተርሰን ወደ መነሻ ሃሳባችን መዝለቁ ነው።
የታሪክና የይድረስ ማስታወሻ፤
ልንሻገረው ቋፍ ላይ የቆምነው ይህ አሮጌ ዓመት (አንዳንድ ብስጩዎች ዘመንን አሮጌና አዲስ በማለት አትበይኑ እያሉ መቆጣታቸውን ሳንዘነጋ) የሚሰናበተው የዕንባ ጎርፍና የደም ኪሳራ አስከፍሎን ነው። በዕንባና በደም ታጥቦ ነበር ብንልም ያስኬዳል። የጦር ሜዳው “የደም ፍልሚያ” ያነሰን ይመስል የኑሮ ቡጢውም እየደቆሰ አስራ ሁለቱን ወራት እያለፍን ያለነው፤ “እንበል አሥራ ሁለት” በሚል በክርያላሶን (አቤቱ ማረን) የእንባ መቃተት ነው። የጦርነት ኤኮኖሚ ደንቡ ነው አንደማንባል ተስፋ እናደርጋለን።
የ2014 ዓ.ም “አዲስ ዘመንን” በፈጣሪ ቸርነት፣ በመንግሥት ትጋትና በሕዝባችን ሁለንታናዊ ኅብረት የምንቀበለው አሳሮቻችንን ሁሉ ቀብረንና የመከራችን ጀምበርም እንደ አሮጌው ዓመት መሽቶባት እንደሚሆን አንጠራጠርም። የጳጉሜን ዝናብ ከባህላዊ የተለምዶ መጠመቂያነት ከፍ አድርገን አምስቱን ቀናት በሰላም፣ በይቅርታ፣ በመደጋገፍና በመደናነቅ ብናሳልፍ ለፈጣሪ ምሥጋና ለመንግሥትም ሀሴት እንደሚሆን እናምናለን።
የሀገራዊ ዕንባችንና መከራችን እርሾም ሆነ ቅሪት ወደ “አዲሱ ዘመን” ባይሸጋገር እንመርጣለን። የአሸባሪው የትህነግ የጠመንጃ ላንቃ ተዘግቶ ሕዝባዊው ሠራዊት “ሆ!” እያለ የድል ብሥራት ይዞልን እንዲመጣም በፀሎትና በዱአ ፈጣሪን ደጅ እንደጠናን አለን። ሰማይ ሰማያት ከንፎ እንደ ንሥር ቁልቁል የሚመለከተን የዕለት ማዕዳችን ጉዳይ ግን በቀላሉ ተፈትቶ የኑሮ ወድነቱ ያሽቆለቁላል የሚል እምነት ለጊዜው ልባችን ውስጥ ጠለቆ አልገባም። ለምን ቢሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍ ወዳለ ሥልጣን ላይ የወጣ ሹም ቁልቁል ለመውረድ እንደሚከብደው ሁሉ ወደላይ ያሸቀበ የኑሮ ውድነትም እንደዚሁ የከፍታው ጣሪያ ሽቅብ ሲንር እንጂ ሲቀንስ በታሪካችን አይተን ስለማናውቅ ነው።
“እናንተ እምነት የጎደላችሁ እስከ መቼ በግማሽ ልብ ታነክሳላችሁ?!” እያለ የሚገስጸን ነብይም ሆነ መሪ በዚህ የጭንቀታችን ወራት አለሁላችሁ ቢለን ደስታውን አንችለውም። ነብያቱ ሱባዔ ይግቡ ወይንም ያንቀላፉ ለጊዜው አጽናኝ ድምጻቸውን ለማድመጥ አልቻልንም። ማዕዳችንን ጦም የሚያሳድረውን የኑሮ ውድነት አንበርክኮ የሚደቁስልን የመንግሥት ጡንቻ ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮችን ስላንጠለጠለ ለጩኸታችን ምላሽ ለማግኘት እንኳን ዛሬ ይቅርና በቅርብ ወራት ውስጥም ምላሽ እናገኛለን ብለን ለማመን እምነታችን ርዷል።
በአዲሱ ዓመት በትረ ሥልጣኑን የሚጨብጠው መንግሥት እንደ እስራኤሉ መሪ እንደ ታላቁ ነብይ እንደ ሙሴ የእንቆቅልሾቻችንን አሳሮች በሙሉ “በበትረ ክህነቱ ባህሩን በመክፈል” ያሻግረናል ብለን ተስፋ ጥለንበታል። ተስፋችንን በአደራ የምናሸክመው ከጥርጣሬ ይልቅ ተስፋን ማደስ ስለሚበጅ ብቻ ነው። “መፃኢውን ዘመነ ማርቆስ የምንቀበለው እንደ ቀድሞ የበሬ ቅርጫ እየተቃረጥን ሳይሆን ወደ ዶሮ ቅርጫነት እንዳንሸጋገር በእጅጉ እየሰጋን ነው” ብሎ ያጫወተኝ የአንድ ወዳጄ ንግግር ትዝ ባለኝ ቁጥር ስሜቴ በማዕበል እንደሚመታ ባህር ሲነዋወጥ ይታወቀኛል።
ነገ ጠዋት መንበረ ሥልጣኑን የሚረከበው መንግሥት የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አደራ ሲቀበል የመጀመሪያው ተግባሩ “የጉርሻችንን ጉዳይ” መልክ እንዲያሲዝልን ጉጉታችን ነው። ሹመኞቹም ወንበራቸው ላይ ከተደላደሉ በኋላ ከሕዝቡ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው “ሥጋ” እያዳሉ እንደ ቀደምቶቹ እንዳይቀጡን ከወዲሁ ይታሰብበት ብንል ለትችት አትፍጠኑ ልንባል አይገባም።
“የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ እንዲሉ” ትዝብታችንን ብቻም ሳይሆን ምክርም አክለንበት በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአሸናፊነት ሜዳሊያ ያጠለቁትን “ተወካዮቻችንን” ስሙን ብንል ክፋት የለውም። በዛሬው ጽሑፍ ከሀገራችን ቀደምት ታሪኮች መካከል አንዱን ሰበዝ ብቻ መዘን በሥልጣን ሽግግር ዋዜማ የተፈጸሙ ተሞክሮዎችን እየጠቃቀስን በቤተሰብ ወግ ብንጨዋወት የተሻለ ስለሚሆን ይህንኑ አካሄድ መርጠናል። ተሞክሮው ስለመጥቀም መጉዳቱ የሚዳኘው አንባቢው ይሆናል።
ከስም ክብር የተግባር ምሳሌነት ይቅደም፤
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) በዳግማዊ ምኒልክ ታላላቅ ሀገራዊ የስኬት ትሩፋቶች “ይኮሩም ይቀኑም ነበር” ይባላል። ይህ እውነታ የጸሐፊው ግምት ሳይሆን የታሪክ ምሁሩ የባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ማረጋገጫ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ። ለተጠራጣሪዎች ያግዝ ከሆነ በመጽሐፋቸው ውስጥ የጠቀሱትን አንድ ፍንጭ ላስታውስ። “ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀኃሥ) ገናናውን አፄ ምኒልክ ቢቻል ለመብለጥ ካልሆነም ለመስተካከል ከነበራቸው ጽኑ ምኞት የመነጨ [ተቋማትን በማቋቋምና ስያሜያቸውን በራሳቸው ስም በመሰየም ይተጉ] ነበር” (ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኞች በኢትዮጵያ፤ በሃያኛው መቶ ዓመት መባቻ – ገጽ 37)።
መቼም ይህን መሠሉ የገዘፈ የመሟገቻ ሃሳብ በቂ ማስረጃ ስለሚፈልግ ጸሐፊው ከልቡ የሚያፈቅራቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ከምሳሌነት ግብር ይልቅ ስማቸውን ያስቀደሙባቸውን አንዳንድ ማስረጃዎችን በመጠቃቀስ እንደምን የምኒልክን ዱካ እግር በእግር እየተከተሉ እቅዳቸውን ያስፈጽሙ እንደነበር ጥቂት አመላካች ማስረጃዎችን በመጠቃቀስ የሞራል ማሳሰቢያው ለነገ የመንግሥት ስልጣን ተሸካሚዎች ትምህርት እንዲሆን በጥቂቱም ቢሆን እናስታውስ።
ታላቁና ጠቢቡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዘመነ መንግሥታቸው ከከፈቷቸውና ከተከፈተላቸው በርካታ ዘመናዊ ተቋማት መካከል ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት (1900 ዓ.ም)፣ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል (ግንባታው ከ1890 – 1891 ዓ.ም ተከናውኖ በእነዚሁ ዓመታት የተወሰኑ ክፍሎች ለአገልግሎት በቅተው ነበር)፣ ምኒልክ አደባባይ (የሀገሪቱ ዜሮ ማይሌጅ የሚጀምርበት) ወዘተ. በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ለምኒልክ ብቻም ሳይሆን ለክብርት ባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱም “ጣይቱ ሆቴል” እና ጣይቱ ብጡል ት/ቤት በስማቸው ቆሞላቸው ነበር። ለራሶቹ፣ ለደጃዝማቾቹ፣ ለፊታውራሪዎቹና በየማዕረጋቸው አንቱታን ላተረፉት ባለስልጣኖቻቸውም በስማቸው የመታሰቢያ ስያሜ እንዲቆምላቸው ተደርጓል። ለልጃቸው ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱም እንዲሁ ዘውዲቱ ሆስፒታል በስማቸው እንደተሰየመላቸው ይታወሳል።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ግን በቁጥርም በግዝፈትም ከፍ ያለ ነበር። በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን ከዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት የሚወዳደረውን የተፈሪ መኮንን ት/ቤትን በ1918 ዓ.ም አሰርተው በስማቸው እንዲሰየም አድርገዋል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል (የዛሬው የካቲት 12 ሆስፒታል)፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስቴዲዬም፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር (የዛሬው ብሔራዊ ቴያትር)፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ወዘተ. ላንዘልቅበት ዝርዝሩን እዚሁ ላይ መግታቱ ይበጃል። የባለቤታቸው የእቴጌ መነን ት/ቤት፣ በልጃቸው ስም የተሰየመው የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል (የዛሬው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል) እና የልዑል መኮንን ት/ቤት (የዛሬው አዲስ ከተማ ት/ቤት) ለማሳያነት ሊበቁ ይችላሉ። ለዘመኑ ሹማምንቶች የተሰጡትን የሠፈርና የመንገድ ስሞችና ሌሎች ተቋማት መዘርዘር ስለሚያታክት መዝለሉ ይመረጣል።
እነዚህ ሁለት ቀዳሚና ተከታይ ነገሥታት ዘመናቸው በፈቀደላቸው ልክና በወደዱት መጠን የሥራቸውንም ሆነ የስማቸውን ክብር ማሳያ አሻራ አትመው አልፈዋል። ድርጊቱ ተገቢም ይሁን አይሁን ዛሬ ላይ ቆመን ያልኖርንበት ትናንት “ስህተት ነበር!” ብለን ለመፍረድ ሞራል ይሉት ስብእናችን ባይፈቅድልንም አንባቢው ግን የራሱን አስተያየት ቢሰጥ ለፍርድ ፈጠነ አያሰኝም። እነዚህ ነገሥታት ያገዘፉት ስማቸውን ብቻም ሳይሆን ተግባራቸውም ጮክ ብሎ ስለሚናገር ብዙ ከማለት እንቆጠባለን።
የዘመነ ደርግ መሪዎች ግን በአብዛኛው የቀዳሚዎቹ ዘመናት ነገሥታት በስማቸው የሰየሟቸውን ተቋማትና መታሰቢያዎች እየናዱ “ኮሚኒስታዊ ወይንም ብሔራዊ” ስያሜዎች ሰጧቸው እንጂ የግል ስሞቻቸውን አልጫኑባቸውም። እርግጥ ነው በሆሳዕና ከተማ የተገነባው ሆስፒታል በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ስያሜ ይጠራ እንደነበር ትዝ ይለናል። በቤንሻንጉል ክልልም እንዲሁ ቀደም ሲል የሠፈራ መንደር የነበረና በአሁኑ ጊዜ ወደ መለስተኛ ከተማነት ያደገ መንጌ የሚባል ቦታ መኖሩን በዓይን ምስክርነት አረጋግጠናል። ሀገሪቱ “በጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ” ፎቶግራፎች መጥለቅለቋ ሳይዘነጋ በተቋማት ስያሜ ረገድ ግን ደርግ ስግብግብ ነበር ለማለት አንደበትን ይይዛል።
የዘመነ ህወሓቱ ጉድና ገመና ግን “ትኩስና የሚያቃጥል ደረጃ ላይ ስለሆነ ቀዝቀዝ ብሎ ሲሰክን” ታሪኩ እየተፈተሸ ለሰነድ የሚበቃ ይሆናል። ያኔ የምንለውን በድፍረት ለማለት እንችላለን። የሀገሪቱ አረንጓዴ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖችና አደባባዮች በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ስም ይኳሉ እንደነበር ግን ሳይጠቀስ አይታለፍም።
በአጠቃላይ ለመግለጽ ህወሓት ዕድሜውን የፈጀውና ወደ ሞት እየተንደረደረ ያለው የሀገርን ክብርና ስም በማጠልሸትና በማዋረድ ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት ተጠምዶ የነበረው በሀብት ዘረፋና በሴራ ፖለቲካ ላይ ነበር። “የተቋማትን ስም ለመሪዎችና ለጀሌዎቹ ለማዋስ” እጅግም ጊዜ አልነበረውም ለማለት ይቻላል። እርግጥ ነው አንዳንድ ተቋማት በጀብደኛ ታጋዮቹ ስም መሰየማቸው አይዘነጋም። ዱሮስ ቢሆን ሌባ፣ ወሮበላና ሀገር አፍራሽ ቡድን ለሆዱ እንጂ ክብሩን፣ እውነተኛ ስሙንና ታሪኩን መች ለአደባባይ ደፍሮ ያጋልጣል።
ከመስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በኋላ መንበረ ሥልጣኑን የሚያደላድለው የብልፅግናው መንግሥት ከስሙ ይልቅ በተግባሩ፣ ከዝና ይልቅ በስራ እንደሚክሰን ተስፋ እናደርጋለን። የታሪክ ተቋማትን የስም አሻራ በማጥፋት ወይንም በማደብዘዝ “በነባር ታሪኮች” ላይ እንደማይፈርድም ተስፋ ጥለንበታል። በተለይም የአሸናፊነትን ሞገስ የደረበላቸው የፌዴሬሽንና የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ከአገልጋይነት ይልቅ “እከሌ” የመባላቸውን የስማቸውን ክብር ብቻ በየተመረጡበት “ሠፈራቸው” አግዝፈው እንዳይተክሉና በሥራ ሳይሆን “…ነኝ እኮ!” እያሉ የሕዝባቸውን ጠረን እንዳይጠየፉ ከወዲሁ መስመር ሊሰመርላቸው ይገባል።
በተለይ በተለይ ግን በአስፈጻሚ ወንበሮች ላይ የሚያስቀምጣቸው ሹማምንቱ ዝቅ ብለው እንዲያገለግሉን እንጂ በራሳቸው ቁመና ልክ ሐውልት ተቀርጾልኝ ካልተመለክሁ ብለው እንዳይኮፈሱ ከወዲሁ ሥራ ሊሰራ ይገባል ባይ ነን። በስብሰባ የብረት አጥር እራሳቸውን አጥረው ቢሯቸው ደጃፍ ላይ ዘብ እያቆሙ እንዳይገፈትሩን በሕዝብ ቃል እንማጠናለን። የደረቀውን የእንባችንን ቀረጢት ዳግም እየጨመቁ ለመከራ እንዳይዳርጉንም የመረጥንበትን ካርድ ዋቢ አቁመን ለአዲሱ መንግሥት አደራ እናሸክማለን።
ስለ ሀገሪቱ የትምህርት ጥራት እየደሰኮሩ ልጆቻቸውን ወደ ፈረንጅ ሀገር ለትምህርት በመላክ ላይ እንዳይጠመዱ፣ ስለ “ተራቀቀው የሀገሪቱ የሕክምና ዕድገት እየሰበኩ” አመመኝ ብለው ባህር ማዶ እንዳይሻገሩ፣ ስለ ኤኮኖሚው መቀጨጭ እየሰበኩ እነርሱ ግን በኮንትሮባንድና በዶላር ሳቦታጅ እንዳይተበተቡ ሀብታቸውን ሲያስመዘግቡ የቤተሰባቸውን አቋምም አብረው ማስታወሻ እንዲያሲዙ ደግምን በብዙኃኑ ስም እንማፀናለን።
አዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋና አዲስ መንግሥት ይዞ መምጣቱን የምናረጋግጠው ስሙን በማግዘፉና በፕሮፓጋንዳ ማማለያ ቃሉ ሳይሆን በተግባር ጭምር እንዲሆን በእጅጉ እንጓጓለን። በኤሎሄ መቃተት የሰለለው ደምጻችንም በሃሌሉያ ዝማሬ እንዲለወጥ እንናፍቃለን። መጻኢው መንግሥታችን ሆይ! ስጋታችን ስጋትህ ሆኖ በቅድሚያ እንድትከውንልን የምንፈልገውን ጥቂት የሕዝባዊ አደራ ቃል እነሆ በፈጣሪ ስም ሸምልለን ከምትገባው ቃለ መሃላ በፊት የአዲስ ዘመን ስጦታ አድርገን ልከንልሃል። ወደፊትም እየቆነጠርን የምንለውን እንላለን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013