አገር መውደድ ማለት ጥልቅ ትርጉም አለው። አገር ማለት ህዝብ፤ ህዝብም ማለት አገር ነው። አገርና ህዝብ የማይነጣጠሉ አንዱ ካላአንዱ ትርጉም የማይሰጡ እጅግ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። አገር መውደድ ማለት ህዝብን መውደድ፣ ህዝብን ማገልገል፣ ለህዝብ መሞት፣ ለህዝብ መጎዳት ማለት ነው። አዎ አገር ወዳድ ዜጋ ማለት ራሱን ለብዙሃኑ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣ ብዙሃኑም ስለአንዱ የሚገዳቸው ማለት ነው። ይህ ነው የአገር ፍቅር፤ ይህ ነው የህዝብ ፍቅር ማለት።
የአገር ፍቅር የሚገለጽበት ሁኔታ ከጊዜው ጋር የሚለያይ እንደ ወቅቱ ሁኔታ የሚቀያየር ነው። የጥንት አባቶቻችን የአገራቸውን ፍቅር በጠለቀ ስሜት ከመግለጻቸውም በላይ አገራቸው በውጭ ወራሪ መዳፍ ውስጥ እንዳትገባ አድርገዋል። የአሁኑ ትውልድ የአገር ወዳድነት ስሜቱ መገለጫ መሆን ያለበት ደግሞ አገራችን ከገባችበት ራስን የማዳን ጦርነት ፈልቅቆ ማውጣት ብቻ ነው።
የአገራችን ህዝቦች ህወሓት 27 ዓመት ሙሉ ሲከፋፍላቸው ቢቆይም እነሱ ግን ተነጣጥለው አያውቁም። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ትሁን እንጂ ሁሉም ቢሄሩ ውስጥ እንዲወተፍ ሆኖ ነው የኖረው ፤በዚህም የሚባለውን ያህል ብዝሀነትን ማስተናገድም አቅቷት ቆይታለች። አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ህዝቦችን በማንነታቸው፣ በዕምነታቸው፣ በባህላቸውና በመሳሰሉት በመከፋፈል አንዱን በማቅረብ ሌላውን በማራቅ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ቢከተሉም ህብረተሰቡ አልተለያየም። አሸባሪው በቀደደላቸው የመለያየት መንገድ አልተጓዙም። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በተለይም አሁን አገርን ለማዳን በተጠራው የክተት አዋጅ ላይ ሁሉም ከያለበት ነቅሎ በአንድነትና ፍጽም ልብን በሚነካ አገራዊ ስሜት መትመሙ ነው።
አገራችን በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከውጭ ወራሪ ሃይሎች ለመከላከል ሲሉ ልዩነታቸውን ወደጎን በማለት ከጫፍ እስከ ጫፍ በመሰባሰብ በአንድነት ዘምተው ወራሪውን ኃይል አድዋ ላይ አሳፍረውታል። የአገራቸውንም ዳር ድንበር በደማቸው አስከብረዋል። ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት፣ ይህ ነው የአገር ፍቅር! ይህ ድል ለመላው አፍሪካዊያን ከዚያም ባሻገር ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ ለመዝለቁም እማኝ አያሻም ። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የአድዋ ድላችን ለእኛ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመንን ፈጥሮልናል።
ዛሬስ? ዛሬም ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ሊገዳደር የቃጣውን አልጠግብ ባዩን አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት አገርን በማስቀደም ስሜት ድል ለማድረግ ተዘጋጅተናል፤ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ ዳግም አንዳያንሰራራ አድርገን ልንቀብረው ይኸው በአንድነት ተነስተናል ። እስከ አሁንም በየአውዶቹ ላይ የሚሰሙት የድል ብስራቶች ቀላል የሚባሉ አይደሉም ፤አዎ! የአገሬ ወጣት በአገሩ በእምዬ ኢትዮጵያ ከመጡበት “አራስ ነብር” መሆኑን ቁልጭ አድርጎ እያሳያቸው ነው።
ሽብርተኛው ቡድን እንደ እባብ መንታ በሆነው ምላሱ የሚረጨውን የጥፋት ፕሮፖጋንዳ ወደጎን የተወው የዘመኔ ወጣት ጁንታውን አይቀጡ ቅጣት ሊቀጣው በሙሉ ልቡ ስለመነሳቱ ሰሞኑን ያየናቸው በማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ ያሉ ወጣቶች ስሜትና ተነሳሽነት በቂ ማሳያ ነው።
“የበላበትን ወጪት ሰባሪ” የሆነው ህወሓት እንግዲህ ቅጥረኞቹንና ጥቅመኞቹን ይዞ የተነሳው አገር የማፍረስ ሴራና አካሄድ የት እንደሚያደርሰው የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን የምናውቀውም ሆነ የገባን ይህንን ቡድን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዋጋውን ሰጥተን ግብዓተ መሬቱን የምንፈጽም መሆኑን ብቻ ነው።
ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ክቡር ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረው እብሪተኛ ልቡ በጥጋብ የተወጠረን አካል ለማስተንፈስ ተነስተዋል ፤ ቀጥለውም በፍትህና በእኩልነት ህዝቦቿን የምታስተናግድ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ይመሰርታሉ። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የእኔ ናት የሚሏት አገር ለመሆን ትበቃለች፤ አዲሲቷ ኢትዮጵ ሁሉም በነጻነትና እኩልነት የሚተዳደሩባት ዴሞክራሲያዊት ብዝሃነትን ማስተናገድ የምትችል አገር ትሆናለች ። ይህ ሳይታለ የተፈታና በቅርቡም የምናየው ሀቅ ነው። ከእኛ የሚጠበቀው ደጋግሜ እንዳልኩት ፍጹም በሆነ የአገር ወዳድነት ስሜት በአንድነት መቆም ብቻ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ለ27 ኣመታት ወጣቱ ሀገር ጠልና ግዴለሽ እንዲሆን ብዙ ቢደክምም ወጣቱ እንደቀድሞው አባቶቹ የሀገሩን ዳር ድንበር ላለማስደፈር በአንድነት በመዘመት ላይ ይገኛል፡፡ወጣቱ እንደ አባቶቹ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ የሀገሩን አንድነት ለማስጠበቅ ዘብ ቆሟል፡፡ይህንን ቀን በአንድነት ስሜት ጠላትን አሳፍረን በድል ከተሻገርነው ደግሞ የህዝቦች ትስስርና አብሮነት ይጎለብታል ፣ ማንነቶቻቸውይከበራሉ ፣ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ያገኛሉ። እኩልነት ይሰፍናል ፣ ዘላቂ ሰላምም ይረጋገጣል፤ አዲሲቷ ኢትዮጵያም የፈጣን ልማትና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተምሳሌት በመሆን ምስራቅ አፍሪካ ብሎም አለምን የምታስደምምበት ቀን እሩቅ አይሆንም ።
በየዘፈኑና በየድርሰቱ አልያም በማናቸውም ሃሳብን የመግለጫ ዘዴዎች ላይ ስለአገር ፍቅር የሚገለጹ ነገሮች ሁሉ ቢተገበሩ በአገራችን መተሳሰብና መረዳዳት ምን ያህል እንደሚጎለብት መረዳት የሚከብድ አይደለም። በእርግጥ በርካቶች ይህን በተግባር አስመስክረዋል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ካላቸው ከፍለው ለተራቡ አብልተዋል፣ ለታረዙ አልብሰዋል፣ ለተቸገሩ ረድተዋል። አሁን ደግሞ የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ብሎም ጁንታውን ቡድን ልክ ለማስገባት ደፋ ቀና ለሚለው መከላከያ ሰራዊት አቅማቸው በፈቀደው መጠን ሁሉ ከደም ልገሳ ጀምሮ እስከ ገንዘብ ማዋጣትና ስንቅ ማዘጋጀት ድረስ እየተሳተፍን እንገኛለን! አዎ ይህ የሚያኮራ ባህላችን ነው። ሁሉም እወዳታለሁ ለሚላት አገር፣ አሊያም እንወዳቸዋለን ለሚሏቸው ህዝቦች በተግባር የሚከፈል መስዋዕትነት ማለትም ይህ ነው።
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በቀድሞዎቹ ጊዜያት አያት ቅድመ አያቶቻችን በአድዋ ድል በከፈሉት መጠነ ሰፊ መስዋዕትነት የአገር ፍቅራቸውን በገቢር ያስመሰከሩ በርካታ ሰዎችን ማንሳት ይቻላል። አሁን እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች ከአያት ቅድመ አያቶቹ በወረስነው የአገር ፍቅር ስሜት ይህን የአገር ጠላት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ከኢትዮጵያ መሬት የምናጠፋበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን። ስለሆነም ቢቻል በግንባር ካልሆነም ደጀን ሆነን አሸባሪው ህወሓትን በጋራ እንቅበር፡፡
በእምነት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013