
“ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ወሳኝ ሀገር እንደመሆኗ የሉዓላዊ አንድነቷ ጉዳይ እኛንም ያሳስበናል” – የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሃን
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር የምታደርገውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ገለፁ፡፡ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ወሳኝ አገር እንደመሆኗ የሉዓላዊ አንድነቷ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ እንደምትፈታው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ቱርክ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከቱርክ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምታደርገው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት አላት፡፡ ለዚህ ኢትዮጵያ በቀጣይ መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለሚያፈሱ የቱርክ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ትፈጥራለች፡፡
ኢትዮጵያና ቱርክ ከንግድና ኢንቨስትመንት ባለፈ በትናንትናው ዕለት አዳዲስ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች በጋራ ለመስራት የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር እንዲገቡ ትሰራለች ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚስትር ዐብይ፣ የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች በየቀኑ በረራ ማድረጋቸው እንዲሁም የቱርክ የፊልም ኢንዱስትሪ ለግንኙነቱ ማደግ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ረጅብ ጣይብ ኤርዶሃን ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት ኢትዮጵያ የመቻቻልና አብሮ የመኖር አገር መሆኗን መናገራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤የቱርክ መንግሥት ኢትዮጵያ ድጋፍ በፈለገች ወቅት ለሚያደርገው እገዛ ምስጋና ችረዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊና ባህላዊ የቆየ ግንኙነት በ6ኛው ክፍለ ዘመን የጀመረ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ፤ ይህ የጠበቀ የታሪክ ትስስር የሁለቱን አገራት ግንኙነቱን አጠናክሮታል ብለዋል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው፣ ሁለቱ አገራት በትብብር ያሳለፉባቸውን የ125 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጉዞ እያከበርን ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን፣ የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሠረት የተጣለው በቱርኩ በሱልጣን አብዱል ሀሚድ እና በንጉሥ ምኒልክ ጊዜ ነበር። በአሁኑ ወቅትም ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት እየጨመረ መጥቷል። በኢኮኖሚ እና በሌሎችም ግንኙቶቻችን ለውጥ ታይቶበታል። በበርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ግንኙነት ፈጥረዋል። ቱርክ ኢትዮጵያ ውስጥ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፈሰስ አድርጋለች። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቱርክ ኩባንያዎች መገኛ አገርም ናት፤ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም የቱርክ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተባበረ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በሳይንስ እና በሌሎች ዘርፎችም ቁልፍ ሚና ያላቸው ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመስራት በተለያዩ ጊዜያት ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
በሰብዓዊ እርዳታ፣ በልማት እና በቅርስ እድሳት ዘርፎችም ወሳኝ የሆኑ ሥራዎችን ለመስራት ስምምነት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣናው እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር በመገናኘታቸው ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ደስተኛ መሆናቸውን ተናረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መገኘቷን እንደሚገነዘቡ የጠቀሱትፕሬዚዳንቱ፤ በአገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ተወያይተናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ወሳኝ አገር እንደመሆኗ የሉዓላዊ አንድነቷ ጉዳይ እኛንም ያሳስበናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ሁኔታም ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ እንደምትፈታው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ችግር በውይይት እንዲፈታ የቱርክ ፍላጎት መሆኑንም ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ ችግር በውይይት ይፈታ ዘንድ ቱርክ ማንኛውንም ድጋፍ ለማበርከት ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እያደረገች ስላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቱርክ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1896 ዓ.ም ሲሆን፤ በጊዜው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ፤ ሱልጣን አብዱልሃሚድ ዳግማዊ ገዢዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው የኦቶማን ቱርክ ቆንስላ የተከፈተው እ.አ.አ በ1912 ዓ.ም፣ በሐረር ከተማ ነበር፡፡ ቱርክ ከሰሀራ በታች የመጀመሪያውን ኤምባሲዋን የከፈተችው በአዲስ አበባ ሲሆን ዘመኑም እ.አ.አ በ1926 ዓ.ም እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
እ.አ.አ በ1933 ዓ.ም የተከፈተው በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዘመነ ደርግ፣ እ.አ.አ በ1984 ዓ.ም፣ ቢዘጋም እ.አ.አ በ2006 ዓ.ም በድጋሜ ሊከፈት ችሏል፡፡ በሁለቱ አገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት የተደረጉ ጉብኝቶች፣ የቱርክ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ ቀጥታ በረራ መጀመር፣ የቱርክ የትብብር ኤጀንሲ (TIKA) በአዲስ አበባ ቢሮ መክፈት እንዲሁም የልማትና የእርዳታ መርሃ ግብሮች መጠናከር የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጎለብትና ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡
በመሪዎች ደረጃ ከተደረጉ ጉብኝቶች መካከል የቀድሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንትና በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በ2009 ዓ.ም እና በ2011 ዓ.ም በቱርክ እንዲሁም የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በጥር ወር 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በገብኝታቸው ወቅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት እንደተሰጣቸው ይታወሳል፡፡
ከምጣኔ ሀብት አንፃር እ.አ.አ በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የቱርክ ድርጅት አንድ ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ የተሰማሩ የቱርክ ድርጅቶች 200 የደረሰ ሲሆን ለ20ሺ ኢትዮጵያውያንም የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ድርጅቶቹ ያስመዘገቡት የኢንቨስትመንት መጠንም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በልጧል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥም እ.አ.አ በ2020 ከ272 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ የጋራ የምጣኔ ሀብት ኮሚሽን (Ethiopia-Turkey Joint Economic Commission) አቋቁመው የምክክር መድረኮችንም ያካሂዳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የቱርክ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን በሚሰጠው የትምህርት እድል አማካኝነት እስካለፈው ዓመት ድረስ 632 ኢትዮጵያውያን የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
የቀድሞ የአምስት ሺ ሜትር ሩጫ ባለክብረወሰኗና የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ኤልቫን አቢ ለገሰ እና የሦስት ሺ እንዲሁም የአምስት ሺ ሜትር የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮኗ አለሚቱ በቀለ ለቱርክ የሮጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ባደረጉት ውይይት ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥና የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
የሱፍ እንድሪስ እና አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም