
አዲስ አበባ ፦ ትውልድን አጥፍቶ፣ ቀሪውን ሕዝብ በባርነትና በድህነት እንዲኖር አቅዶ የመጣን ክፉ ጠላት እንደ ሕዝብ ተረባርቦ ማስቆም ታሪካዊ ግዴታ መሆኑን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ፣ አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ያለሀጥያቱ “ሒሳብ አወራርዳለሁ” እያለ በሚዲያ ተናግሯል። በአደባባይ ዓለም እየሰማው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል መግባት ካለበት እንደሚገባ አስታውቋል።
ትርክቱም ሆነ ድርጊቱ በእውን የማይታሰብ የእብደት ገጸ ባህሪ ቢመስልም ከመቼውም ጊዜ በላይ በግብር ትርክቱን እውን ለማድረግ የጥፋት ሰይፉን በአማራና በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ መምዘዙን አስታውቋል።
ይህንንም “የአማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ” ያለው ትህነግ፣ ሽብርና ወረራ ለሚፈፅሙለት የሽብር አባላቱ ምን አይነት ተልዕኮ እንደሰጣቸው ከምርኮኞች በምርመራ የሰበሰብናቸው መረጃዎች ያረጋግጣሉ ብሏል ።
በርግጥም ትህነግ በእብሪት በወረራቸው አካባቢዎች እየፈፀማቸው ያሉ ወንጀሎች በአማራ ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድም የአፋር ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ የጥፋት ሰይፉን መዝዟል ያለው መግለጫው ፣ በዚህም የአፋር ሴቶችን ደፍሯል፣ ሕጻናትንና ወጣቶችን ገድሏሎ፣ የአርብቶ አደሩን የቁም እንስሳት በገፍ ዘርፏል። የጠኔ ማወራረጃው አድርጎታል። አቅዶ የመጣውን ቂም በቀል በግልፅ በተግባር እያሳየ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
በሌላ በኩል በየቀኑ ሲረግመው የሚውለውን የአማራ ልሂቅ ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው ትህነግ፣ ነገ አድገው አማራን ይጠቅማሉ ያላቸውን የአማራ ልጆች የማጥፋት ውጥን መያዙንም ፓርቲው አስታውቋል።
በዚህም ትውልዱን ለማምከን ባቀደው ክፉ እቅድ መሰረት በየከተማው ያገኛቸውን ታዳጊ ወጣቶች በራቸው ላይ ገድሎ ጥሏቸዋል ሲል ገልጾ፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ባለሀብቶች፣ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ትኩረት አድርጎ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከወሰነ መቆየቱንም አመልክቷል።
የአእምሮ ህሙማንን በስለላ ማሰማራት የለመደው ትህነግ፣ ሁሉም እንደ እሱ መስሎትና በህመም የሚሰቃዩትንም በየደረሰበት አካባቢ ገድሏቸዋል። ከሚገድላቸው በተጨማሪ ሕዝብን በገፍ በማፈናቀል ከቀዬው ተፈናቅሎ ተቅበዥባዥ ማድረግን፣ እረፍት መንሳትን የደስታው ምንጭ አድርጎታል ብሏል ።
ሕዝብ ሲፈናቀልለት ከተማውን በሙሉ ዘርፎ ለማሸሸም እድል እየፈጠረ ይገኛል። ትህነግ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚኖሩትን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ለሚኖሩት የሽብር አባላቱና ተባባሪዎቹ አማራን ወርረው እንዴት ንብረቱን ዘርፈው ወደ ትግራይ እንደሚወስዱት የዘረፋ ዕቅድ ማውጣቱንም አስታውቋል።
አንዳንድ የትግራይ ተወላጆችም ለአማራ ወዳጆቻቸው እስከ መስከረምና ጥቅምት ባለው ጊዜ ያለቀው ኃይላቸውን አልቆ ወረራውን እንደሚያሳኩና የአማራን ሀብትና ንብረት ዘርፈው፣ የተረፈውንና መውሰድ የማይችሉትን አውድመው የአማራን ሕዝብ አደኸይቶ የመበቀል አላማ እንዳላቸው ገልፀውላቸዋል። ይህን መረጃ ከምርኮኞችና ከመረጃ ክትትላችን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል ።
የትህነግ አሸባሪ ኃይል አባል አልቆ አማራም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚልሰው የሚቀምሰው ማሳጣት የሽብር ቡድኑ ግብ ነው ያለው መግለጫው፣ ወትሮም በአማራ ቁልቁለት፣ በተዳከመች ኢትዮጵያ ታላቋን ትግራይ የመፍጠር ፖለቲካዊ ግብ ይዞ የተነሳው የጥፋት ኃይል፣ ዛሬ በመላ ኢትዮጵያውያን የደም ጎርፍ ራሱን ነጻ ለማውጣት ጋኔሉን ከጠርሙሱ አስወጥቶታል። ዛሬ በአማራም ሆነ በአፋር ወረራና የሽብር ተልዕኮ ላይ የተሰማሩ የሽብር ቡድኑ አባላት ከጠርሙሱ የወጣው ጋኔል ተምሳሌት ናቸው ብሏል።
አሸባሪ ቡድኑ በወረራቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች የተደራጀ ኃይል አሰማርቶ የመንግሥት ተቋማትን፣ የግል ንግድ ቤቶችን፣ የግለሰብ ንብረቶችን በከባድ የጭነት መኪናዎች እየጫነ ይገኛል ያለው መግለጫው፣ አጠቃላይ ግቡ የኢትዮጵያን ሕዝብ 100 ዓመት ወደኋላ መጎተት እንደሆነ አመልክቷል። ይህን ደግሞ በአማራና በአፋር ክልሎች እንደሕዝብ ወረራ ፈጽሞ እንደጀመረው ጠቁሟል።
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ በእብሪት በወረራቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች የጀመራቸው የዘረፋና የጭፍጨፋ ወንጀሎች የወረራ አላማው ቢሳካለት በመላ ኢትዮጵያ ምን ሊያደርግ እንደሚችል እያስመሰከረ መሆኑንም ጠቁሟል። አነስተኛ የመንገድ ዳር ኪዮስኮች ሱቅ ውስጥ ገብቶ ቁሳቁሶችን ዘርፎ ከመጫን በተጨማሪ በወረራቸው አካባቢዎች ያገኛቸውን ተሽከርካሪዎች በሎቬድ ጭኖ አይን ያወጣ ዘረፋ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክቷል።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሌሎችን በሐሰት ሲከስስ የነበረው አሸባሪው ትህነግ በወረራቸው የክልላችን አካባቢዎች ግን በግልፅ ዘረፋን የወረራው አላማ አድርጎ እየሰራበት ነው ብሏል። ከአሸባሪው ተዋጊ አባላት ባልተናነሰ በኋላው ለዘረፋ በአደረጃጀትና በዕዝ የትግራይ ሴቶችንና አዛውንቶችን ማሰለፉንም ጠቅሷል።
ታሪክ ይቅር ሊለው በማይችልበት ሁኔታ ከ70 ዓመት በታች ያለ የትግራይ ተወላጅ የወረራውና የዘረፋው ተሳታፊ እንዲሆን አደረጃጀት ተፈጥሯል፤ ስምሪትም ተሰጥቷል። “… ሂዱ አማራንና አፋርን እንዲሁም ቀሪውን የኢትዮጵያ ህዝብ ውረሩ፣ ሀብት ንብረቱንም ዝረፉ ኢትዮጵያንም አፍርሱ…” የሚል መመሪያ ከአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ የወረደለት ኃይል፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት የአማራንና አፋርን ክልሎች እንደአንበጣ በመውረር ላይ ነው ሲል አብራርቷል። ይህ አደገኛ ተስፋፊ ኃይል እንደሕዝብ ካልተመከተ የጥፋት አድማሱን በማስፋት ኢትዮጵያን ወደታሪክ ሊቀይራት እንደሚችል ሕዝቡ ግንዛቤ መያዝ እንደሚኖርበት አሳስቧል።
አሸባሪው አባላቱን ሲመለምል የተጣባውን ክፉ የአማራ ጥላቻ ትርክት ከመስበክ በተጨማሪ የአማራንና የሌላውን ኢትዮጵያዊ ሀብት ዘርፈው ጥሪት ይዘው እንደሚመለሱ በማሳመን ጭምር ስለመሆኑ ምርኮኞች ላይ ባደረግነው ምርመራ የተደረሰበት መሆኑን መግለጫው አስታውቋል።
ይህ ኃይል የወረራ አላማው ሕዝብን እንደ ሕዝብ ማጥፋትን ዒላማ ያደረገ ነው። ከጭፍጨፋ የተረፈው ሕዝብ በድህነት ቀንበር እንዲኖር የጥላቻ ጥግ የሆነ እቅዱን አስቀምጦ የመጣ በመሆኑ እንደ ሕዝብ ተነስተን ካልመከትነው በቀጣይ በአማራውና ሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ ሊያደርሰው የሚችለውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ለመገመት እንደሚከብድ አስታውቋል።
ዓለም በቃኝ ያሉ አባቶች የሚኖሩባቸውን ገዳማት ጨምሮ ቤተ እምነቶችን ዘርፎ፣ ቀሪውን የሚያወድም ይህ አሸባሪ ኃይል ትውልድን ገድሎ፣ የአማራ ክልልና የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥረቱ ያፈራውን ሀብት ዘርፎ ለመበቀል የያዘውን የዘረፋና የጭፍጨፋ አላማ በአጭሩ መቅጨት እንደሚያስፈልግም ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013