
አዲስ አበባ ፦ አሸባሪው ህወሓትም ሆነ ማንኛውም እናቱን ለመሸጥ የሚደራደር ኃይል የሀገራችን ክፉ ትዝታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረውና በቅርቡ ለዘለዓለሙ እንደሚሰናበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ ።የውሸት ፀሐይ ሲጠልቅ የሤረኞች ወጥመድ እንደሚበጠስም አመለከቱ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትናንት በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ሁልጊዜም ከመንጋቱ በፊት ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል። በምሽትና በንጋት ሽግግር ውስጥ ያላለፈ ሀገርና ትውልድ የለም። ብርቱው ጨለማ የንጋቱ ጸዳል አብሳሪ ስለሆነ፣ መቼም ቢሆን “ይኼ ምሽት እንደ ጨለመ ቢቀርስ?” ወይንም ‘ንጋት ባይመጣስ?’ ብለን አንሠጋም ብለዋል ።
ንጋቱ አይቀሬ ነውና አስደንጋጩ ጨለማ በማለዳው የብርሃን ጸዳል ይዋጣል። የአዲሱ ቀን ጎሕ ሲቀደድ አስፈሪዎቹ አውሬዎች ወደየጎሬያቸው መግባታቸው፣ የሌሊቱም ቁር ለቀኑ ሙቀት ሥፍራ መልቀቁ አይቀሬ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀን የተሰወሩት ከዋክብትም ቢሆኑ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደምቀውና ጎልተው የሚታዩት ጨለማው ሲበረታና ሌሊቱ ከመንጋቱ በፊት እንደሆነም አመልክተዋል።
በሕይወት ጉዟችንም ከጠበቅነው የተስፋ ንጋት ቀድሞ ጨለማ የሚመስል ፈተና ከፊታችን እንደ ጅብራ ሊደነቀር እንደሚችል ጠቅሰው፣ ፈተናው አዲስ እየመሰለን የስሜት መረበሽ ያጋጥመናል። በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በአስተዳደርና በሌሎች ማኅበራዊ ሂደቶች ሁሉ፣ ተግዳሮትና ፈተና ውስጥ ገብተን ራሳችንን እናገኘዋለን ብለዋል።
ግለሰቦችና ቤተሰቦች፣ መንግሥታትና ሀገራት በጥፋት ሥጋት የህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብተው በአጣብቂኝ ውስጥ ያልፋሉ። ጥያቄው ‘ይህ ጊዜ ያልፋል ወይስ አያልፍም?’ ሳይሆን ‘እንዴት ይታለፋል?’ ነው? ይህ ችግርና ተግዳሮት በጨለማው ውስጥ ደምቀውና አሸናፊ ሆነው ብዙዎችን አስከትለው ለሚወጡ ከዋክብት የድምቀትና የጀግንነት እድልም ነው ብለዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደምት ታሪኳ ብዙ ክረምትና በጋዎችን፣ ጨለማና ብርሃንን ያፈራረቁ ውጣ ውረዶችንና እንቅፋቶችን አሳልፋለች። በገባችበት የክረምት አረንቋና የውድቅት ሌሊት የፈተና ሰዓት የቁርጥ ቀን ልጆችዋ “በክፉዎች ሤራ ተጠልፋ ትወድቅ ይሆን?” የሚል ሥጋት ቢገባቸውም፣ እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ በተስፋ ጽናት በሕይወታቸው ተወራርደው ችግሯን ተጋፍጠውላታል። ጠላቶቿን ለማሳፈር አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተዋል ሲሉ አስታውቀዋል።
በዚህም እንደ ጨለማ የበረቱት ጠላቶችዋ ሲወድቁ፣ እሷ አንገቷን ቀና አድርጋለች። ብዙ የዓለም ሀገራትም እኛ ዛሬ የምናልፍበት በሤራ የመጠለፍ አደጋና የመበታተን ሥጋት፣ በአንድ ወይንም በሌላ ዘመን ገጥሟቸው ያውቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደ ዩጎዝላቪያና ሶሪያ፣ ሶማሊያና ሊቢያ ያሉ ሀገራት በሥጋታቸው ተጠልፈው መውደቃቸውንም አመልክተዋል።
እንደ ጀርመንና ጃፓን፣ ኮርያና ቬየትናም ያሉት ሀገራት ደግሞ በተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ አልፈው፣ ፈተናቸውን ፊት ለፊት ተጋፍጠው፣ ለጋራ ድል በአንድነት ሠርተው፣ ለስኬት ከበቁ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ ሲሉ ተናግረዋል። እነዚህ ሀገራት ዛሬ በኢኮኖሚ አቅማቸውና በዘመናዊ የፖለቲካ አስተዳደራቸው፣ በቴክኖሎጂ ምጥቀታቸውና በማኅበራዊ እሴታቸው እጅግ ዘመናዊ ከሚባሉት ሀገራት መካከል የሚመደቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አስቀያሚና ፈታኙን ቀውስ አይተው መሻገራቸውንም ጠቁመዋል።
ሀገሮቹ የገጠሟቸውን እንቅፋቶች እንደ መስፈንጠሪያ ነጥብ እየተጠቀሙ አሁን ካሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ወድቃና ተንኮታኩታ እንደነበር በአብነት ጠቅሰዋል። ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን እየተባለች ለሁለት ተከፍላ ለመቆየት ተገድዳ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጊዜው ቢረዝምም በመጨረሻ ሕዝቦቿ ተባብረው የለያቸውን የድንጋይና የርዕዮተ ዓለም ግንብ ማፍረስ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በ1860 አካባቢ ደም አፋሳሽ በሆነው የእርስ በርስ ጦርነት ገብታ ሁለት ከመከፈል ለጥቂት የተረፈችው አሜሪካ ራሷ ከደረሰባት ጥፋትና የመበታተን አደጋ የዳነችው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የልጆቿን ሕይወት ዋጋ ከፍላ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በድህነት ላይ የእርስ በርስ ጦርነትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ክፉኛ ፈትኗት ሳትረታና ሳትፈታ በድል ያለፈችው የደቡብ ኮርያ ታሪክም ከሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በእጅጉ ተዛማጅ እንደሆነም አስታውቀዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልክታቸው፣ ዛሬ እኛ እያለፍንበት በምንገኝበት መንገድ ውስጥ ያለፉ፤ ችግርና እንቅፋት የሩቅ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው የሆኑ፣ ሌሎች ሀገራትም ቁጥራቸው ጥቂት እንዳልሆኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያልገጠሟት ፈተናዎች፣ ያላለፈችበት ተግዳሮቶች የሉም። ሁሉንም የቀለበሰችውና ድል አድርጋ የወጣችው በአንድነት፣ በብልሐትና በመደመር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጭ የመጣ አደጋም ሆነ ከውስጥ የተነሳባት ፈተና፣ የቱንም ያህል የበረታ ቢሆን ልጆቿ በኅብረት ሲቆሙ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ እንደማያውቅ አስታውቀዋል።
“እኔ ከሞትኩ” ባዮች፣ ለግል ጥቅም ሲሉ እናታቸውን በሚሸጡና ሀገራቸውን አሳልፈው በሚሰጡ፣ ጠላት እንደፈለገው በሚጋልባቸው ከንቱ ልጆችዋ ምክንያት ኢትዮጵያ ከአንዴም ብዙ ጊዜ ብርቱ ፈተና ውስጥ መግባቱዋን አስታውሰዋል።
ዛሬም ኢትዮጵያ በደኅናው ቀን እፍታዋን ያጎረሰችው፣ የማጀቷን ምርጥ በልቶ የጠገበው የጁንታው ኃይል፣ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ዓይኑን የማያሽ ውስጥ ዐዋቂ ባንዳ በመሆኑ ምክንያት ፈተናው ጠንክሮብን ይሆናል::
ሲሉም አብራርተው፣ በአንድነት ከቆምንና ተደምረን ከተጋን ግን ይህን ፈተና አሸንፈን፣ ችግሩን ወደ ዕድል፣ ዕድሉንም ወደ ታላቅ ድል ለውጠን፣ ሀገራችንን ወደ አየንላት የሰላምና የብልጽግና ከፍታ ማማ ላይ እንደምናደርሳት ለአፍታም ልንጠራጠር አይገባም ብለዋል ።
ለዘመናት በሀገራችን የሰራ አካል ውስጥ ተሰግስጎ የኖረው አሸባሪው ህወሓት ራሱን እያፋፋ፣ ኢትዮጵያን በአንጀት – በደም ሥርዋ ሰርጎ ሲጣባ – ሲመርዛት ኖሯል ሲሉም ጠቅሰው፣ አሁን ተጠራርጎ ሊወጣ አፋፍ ደርሶና ጣዕረ ሞት ይዞት በመንፈራገጥ ላይ ይገኛል ብለዋል። እድሜውን ለማራዘም የመጨረሻ መፍጨርጨርና የሞት ሽረት ትግል ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የአልሞት ባይ አትርሱኝ መወራጨቱ በዝቷል። ከግብአተ መሬቱ በፊት ልትወጣ ያለች ነፍሱ እስካለች ድረስ መንፈራገጡና የሰላም ደንቃራ መሆኑ አይቀርም። ክፉ መርዙን ተክሎ ጥገኝነቱን ከመሠረተበት የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተነቅሎና ተጠራርጎ እስኪወጣ ድረስ ደዌ ነውና ሕመሙን ችለን፣ የማሻሪያ መድኃኒት እየወሰድን እንቆያለን ብለዋል።
“ኮሶ ሊያሽር ይመራል” እንደሚባለው፣ የማያዳግም ፀረ ሽብር መድኃኒቱ የጎን ጉዳት የሆነውን ምሬትና ሕመም ታግሠን ከቆየን፣ ህወሓትም ሆነ ማንኛውም እናቱን ለመሸጥ የሚደራደር ኃይል የሀገራችን ክፉ ትዝታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ላይኖረው በቅርቡ ለዘለዓለሙ እንደሚሰናበትም አስታውቀዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥሮች ውስጥ አልፈናል። ዛሬ በዲፕሎማሲያችን ላይ የሚታየው ከፍተኛ መንገራገጭ ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት በሁሉም ዘርፎች ላይ የሚታይ የየዕለት ስቃያችን ነበረ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊው ዘርፍ፣ በአስተዳደር፣ በሕግ ሥርዓቱ፣ በጸጥታና ደኅንነት ሥርዓቱ፣ ከክልል እስከ ወረዳ በሁሉም ቦታ ይሄ ቀውስ እንደነበር አመልክተዋል።
በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ ፈውስ እስኪገኝ ስቃይ ነበር፤ ሕመም ነበር። ስለዚህ አሁንም በዲፕሎማሲያችን ውስጥ ቀውስ ገባ ብለን መበርገግ አይገባም። ጠላት ሁሌም በማስፈራራትና በፕሮፓጋንዳ ቀድሞ ሊያሸንፈን ሲጥር ተሸንፈን አንጠብቀው ሲሉም ሕዝቡ ችግሮችን በጽናት እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013