
አዲስ አበባ:- አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ የሚገኘውን የሽብር ተግባር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰፊ ስራ እያከናወነ መሆኑን የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው አስታወቁ ።
ዶክተር ሰይፈስላሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ የሚገኘውን የሽብር ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳው ለማድረግ እናት ፓርቲ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየሰራ ይገኛል።
የአሸባሪነትን ድርጊት ለመመከት እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል የእናት ፓርቲ ወቅታዊ መግለጫዎችን በማዘጋጀት ለዓለምቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ከማሳወቅ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አሸባሪነትን ከኢትዮጵያ ምድር የማጽዳትና ሀገርን ከውጭ ጣልቃ ገብነት የመታደጉ ዘመቻ የሚደነቅና እስከመጨረሻው መቀጠል ያለበት ድርጊት ነው ያሉት ዶክተር ሰይፈስላሴ ፣ ለዘመቻው ውጤታማነት አንድነታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የአሸባሪነትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ጉዳይ ተያያዥ፣ አንዱ አንዱን ተከትሎ የሚመጣ ክስትትና ሉዓላዊነትንም በእጅጉ የሚፈታተን ጉዳይ እንደሆነ ያስታወቁት ዶክተር ሰይፈስላሴ ፤ ሀገርን ከአሸባሪዎችና ከውጭ ጣልቃ ገብነት ለማዳን ሁሉም የበኩሉን ማበርከት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ፣ በዘርና በጎሳ ለመለያየት ብዙ ስራዎችን ሰርቷል። በተለይ አሁን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ሳይቀር በማበር ሀገርን የማፍረስ ውጥን ይዞ እየሰራ ይገኛል። ይህና መሰል ተግባሩ የቡድኑን ፍጹም አሸባሪነት የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው ብለዋል።
ቡድኑ በአሸባሪነት ከመፈረጁ በፊት በህዝብ ማዕበል ተጠርጎ ከአራት ኪሎ መቀሌ እንዲመሽግ ተደርጓል ያሉት ዶክተር ሰይፈስላሴ፤ ‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› እንዲሉ ይባስ ብሎ የሀገር መከላከያን ከጀርባው በመውጋት ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ ጥሎ ማለፉን አስታውቀዋል።
የሀገር ሉአላዊነትን ለመድፈር አማራጭ ያላቸውን መንገዶች ሁሉ እየተጠቀመ ይገኛል፣ ስለሆነም ይህ አይነቱ ድርጊት ከኢትዮጵያ ምድረ ገጽ እንዲጠፋና የሀገር ሉዓላዊነት እንዲከበር ከተፈለገ ሁሉም በአንድነት መቆምና በያለበት ጠንክሮ መስራት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።
መንግስት ለትግራይ ገበሬዎች ወቅቱ የእርሻ ጊዜ በመሆኑ ፋታ አግኝተው እንዲያርሱ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርግም፤ አሸባሪ ቡድኑ ግን ስምምነቱን ባለመቀበል የሚታወቅበትን የሽብር ድርጊት አድማሱን በማስፋት በአማራና በአፋር ክልሎች በማስፋት ጥፋቶችን እያደረሰ ይገኛል።
በዚህም ንብረት ዘርፏል፣ ንጹሃንን ገድሏል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ልክ እንደበፊቱ ሁሉ በጥበብና በብቃት ይህን አስቸጋሪ ጊዜ በሀገር ወዳድ ዜጎቿ ታልፈዋለች ያሉት ዶክተር ሰይፈስላሴ፣ የጎሳ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ምድር ጠፍቶ አንድነትን የበለጠ ማጠናከር ላይ መስራት የመንግስት ቀጣይ አቅጣጫ መሆን እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡
መሰረት በኃይሉ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013