
አዲስ አበባ፡- የውጭ ኃይሎች ንጹሃን ሲገደሉ ማውገዝ አለመፈለጋቸው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ታዛዥ መንግሥት እንደነበረ አመላካች መሆኑን የደባርቅ ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ተሰማ ዘውዱ ገለጹ።
ፕሮፌሰር ተሰማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት የአፋርና የአማራ ክልል የንጹሃን ጭፍጨፋና መፈናቀልን በተመለከተ አለማውገዛቸው አሸባሪው ትህነግ ታዛዣቸው መሆኑን ያመለክታል።
አሸባሪው ቡድን ከመነሻው ጀምሮ በማኒፌስቶው ያስቀመጠው ከቻልኩ ኢትዮጵያን እገዛታለው፤ ካልቻልኩ ደግሞ አፈራርሼ እሄዳለሁ የሚል እቅድ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ኢትዮጵያን ለማዳከም አሸባሪውን ቡድን እየረዱት ይገኛሉ። በመሆኑም አሸባሪው ትህነግን ጥፋተኛ ነው ብለው መፈረጅ አልፈለጉም ብለዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ የውጭ ኃይሎች የህወሓትን አሸባሪ ቡድን የሚደግፉበት ሌላኛው ምክንያታቸው የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ነኝ በማለትና ለብሔር ብሄረሰቦች ተቆርቋሪበመምሰል ብሔር ብሔረሰቦችን ከፋፍሎ የራሱን ጥቅም ሲያስጠብቅና በዜጎች መካከል ጥላቻን ሲሰብክ የኖረ ድርጅት በመሆኑ ነው።
በኢትዮጵያ ስም ለተለያዩ ድርጅቶች የሚመጣውን ሀብት ሲቀበልና ለነጮች ሲያከፋፍል የኖረ ድርጅት በመሆኑ በተነሳው ህዝባዊ አመጽ ከሥልጣን ሲወገድ ጥቅማቸው በመቅረቱ የተነሳ የውክልና ጦርነቱን ከፍተውብናል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ በቅድሚያ አማራን ማጥፋት አለብን ብለውም የውክልና ጦርነት በግልጽ ከፍተዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦ ፖለቲካዊ ስፍራ ስትራቴጂ በመሆኑ አብዛኛው የዓለም ሀገራት ይህን አካባቢ የመቆጣጠር ፍላጎት አላቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ኢትዮጵያን መቆጣጠርና መበታተን ለነሱ ጠቀሜታ ስለሚኖረው አሸባሪውን ቡድን በመደገፍ አላስፈላጊ ጦርነቶችንና ውስጣዊ ችግሮችን በመፍጠር የማዳከም ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ስር ሲገቡ ኢትዮጵያ ወራሪውን የነጭ ኃይል በመመከት ድል ማድረጓ ያስቆጫቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር ተሰማ ፤ አንድ ድሃ ሀገር ለዛውም በባዶ እግሩ የሚሄድ ጥቁር ህዝብ ነጭን ማሸነፉ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ወደ ፊት ሊኖራት የሚችለው ሀብት እንደሚያስፈራቸው የሚያነሱት ፕሮፌሰር ተሰማ ፤ የአረብ ሀገራትና ሌሎች ስጋት ያላቸው ኃያላን ሀገራት ከግብጽና ከሱዳን ጋር በመሆን የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዓለም በሦስት ጎራ እየተከፈለ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ተሰማ፤ የብሪክስ ሀገራት ቻይና፣ ብራዚል፣ ህንድና ሌሎች አባል ሀገራት እያደጉ መምጣት አሜሪካ ዓለምን የመቆጣጠር አቅሟን እየቀነሰው መጥቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያም ሀብቷን ተጠቅማ መልማት ከቻለች የምስራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ወደ መሆን ትቀየራለች የሚል ስጋት ስላላቸው ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን አይፈልጉም። በአንጻሩ ደግሞ በቀጠናው የአውሮፓውያንና የአሜሪካ የበላይነት ስለሚቀንስ በተለያዩ ስልቶች የማዳከም ሥራን አማራጭ አድርገው እየሰሩ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013