
የመከላከያ ሰራዊቱን ምልምል ሰልጣኞች ለማነቃቃት የተካሄደው ኪነ ጥበባዊ የመድረክ ዝግጅት አላማውን ያሳካ እንደሆነ ተገለጸ።
“ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ መቼም የትም በምንም” ለሚለው ሀገራዊ ጥሪ መልስ ለመስጠት በአዋሽ የውትድርና ማሰልጠኛ ለሚገኙ ሰልጣኞች ትናንትና የማነቃቂያ የኪነጥበብ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ በእንግድነት የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት እንደገለጹት፤ ለሀገራዊው ጥሪ መልስ የሰጡ የውትድርና ሰልጣኞችን ለማዝናናትና ለማነቃቃት የተካሄደው የመድረክ ዝግጅት አላማውን ያሳካ ነው።
የሀገርን የህልውና ጥሪ ተቀብለው የህይወት ዋጋ ጭምር ለመክፈል በመወሰን ወደስልጠና ለገቡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተደረገው የኪነጥበብ ዝግጅት አስደሳች ነው ያሉት ወይዘሮ ብዙነሽ፤ የአባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ ለመድገም ቆርጠው የተሰለፉ ወጣቶች በተለያዩ የሀገርን ስሜት በሚቀሰቅሱ ህብረ ዝማሬዎችና የመድረክ ሥራዎች የማበረታታት ሥራ በአግባቡ መከናወኑን ገልጸዋል።
በስፍራው በመገኘት ሰልጣኞችን በማነቃቃት የተሳተፉት ተዋናይት አስቴር አለማየሁ እና ኮሜዲያን ማርቆስ ፍቅሩ በበኩላቸው፤ ዋናው አላማችን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑትን የሰራዊት አባላት በሙዚቃና በኮሜዲ ሥራዎች እንዲሁም በቴያትራዊ ዝግጅቶች ማዝናናትና ማነቃቃት ነው። በመድረክ ዝግጅቶቹም ለሰራዊቱ ሰልጣኞቹ አይዟችሁ ጠንክሩ ከጎናችሁ ነን የሚለውን መልዕክት በአግባቡ ማስተላለፍ ተችሏል ብለዋል።
እንደ ኪነጥበብ ባለሙያዎቹ፤ የሀገርን ስሜት በሚቀሰቅሱ የመድረክ ዝግጅቶች አማካኝነት ለወጣቶቹ የሞራል ስንቅ እና የአብሮነት ስሜትን ማስተላለፍ ተችሏል። የኪነጥበብ ባለሙያዎችም አሁን በየማሰልጠኛው በመዘዋወር የሚያካሂዱትን የመድረክ ዝግጅት በማጠናከር እስከ ጦር ግንባር በመዝለቅ ሰራዊቱን ማበረታታትን ያለመ እቅድ ይዘዋል። በመሆኑም በቀጣይም ግንባር ድረስ በመዝመት ሀገራዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍናና ስነመለኮት መምህር ዮናስ ዘውዴ እንደገለጹት፣ ደግሞ፤ የውትድርና ሙያ የተመረጠ እና የተከበረ ሙያ ነው። በዚህ የተከበረሙያ ውስጥ ተመርጠው የመጡ ሰልጣኝ የሰራዊት ምልምል አባላት የእኛ ዘመን ጀግኖች ናቸው። እነሱንም ለማነቃቃት የሚደረግ የመድረክ ዝግጅት ግብም ታላቅ ነው።
ወጣቶቹ በውትድርና ስልጣናቸው በሀገር ፍቅር፤ ጠላትን በማሸነፍ እና ትብብርን በሚያጎናጽፍ አንድ ታላቅ ገመድ እንዲተሳሰሩ እንደሚደረግ ይታመናል ያሉት የፍልስፍና ስነመለኮት መምህሩ ዮናስ፤ የኪነጥበብ ሥራዎችም አንድነትን በመፍጠር ረገድ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
አቶ ዮናስ ለሰራዊቱ ሰልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ሰንደቋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ከፈለጋችሁ፤ አንድነታችንን ቀና አድርገን እንድንናገር ከፈለጋችሁ በሩጫችሁ መሃል ብዙ ነገሮች በሚባሉባት ዓለም ላይ ሁሉንም መጠጣት ሳይሆን የማያስፈልገውንም በመለየት እንትፍ እያሉ መተው ይገባል ብለዋል።
የሰራዊቱ ሰልጣኞች በተዘጋጀው የማነቃቂያ የኪነጥበብ መድረክ ላይ ከሀገር ፍቅር ቴያትር፤ ከራስ ቴያትር፤ ከአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ እንዲሁም ከህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት የተውጣጡ ሙያተኞች ተሳትፈዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013