
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን ከትንሳዔና ብልፅግና የሚያስቆም አንዳች ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ። አሸባሪው ህወሓት የጥፋት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀበር ተባብረን እንስራ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
የቀድሞ የሰራዊት አባላት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ እና አሸባሪው ህወሓትን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ትናንት በመስቀል አደባባይ ባካሄዱበት ወቅት ምክትል ከንቲባ አዳነች እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያን ከትንሳዔና ብልፅግና የሚያስቆም አንዳች ምድራዊ ኃይል የለም።
የቀድሞ የሰራዊቱ አባላት የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል ለኢትዮጵያ ዘብ ለመቆም ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ከንቲባዋ፣ ይህ አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀበር ተባብረን እንስራ ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የአንድ የፖለቲካ ስርዓት አገልጋይ አድርጎ ሲፈርጅ መቆየቱ ምን ያህል ከእውነት የራቀ መሆኑን አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለው እውነታ አመላካች እንደሆነ ጠቁመዋል ።
አሸባሪው እየበደለ ያለው የትግራይ ህዝብን ጭምር ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች ፣ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ለመነጠልም ብዙ መስራቱንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እበለፅጋለሁ ፣የህዳሴውን ግድብ ገንብቼ አጠናቅቃለሁ፣ህዝቦቼ እየለመኑ መኖር የለባቸውም ብላ እየሰራች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት መበዝበዝ የለመዱ፣ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩና ትንሳዔዋን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል ።
የመርሀ ግብሩ ዋና አስተባባሪና የጀግናው 18ኛው ተራራ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጀነራል መርዳሳ ሌሊሳ የቀድሞ ጦር ሀይሎችና የፖሊስ ሰራዊት አባላት ኢትዮጵያን ከዓለም ካርታ ለማጥፋት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን አሸባሪው ህወሓትን እየተፋለመ ካለው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆማቸውን አረጋግጠዋል። በስልጠናም ግንባር ድረስ በመዝመትም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅም ቃል ገብተዋል። ለእዚህም የስነ ልቦና ዝግጁነት ለማድረግ በሚረዳው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙትን አካላት ሁሉ ሜጀር ጀነራሉ አመስግነዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ “ደማችንን ለእናት አገራችን እንገብራለን፣ ምእራባውያን እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ፣ አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ ወደኋላ አንልም፣ የሚሉ እና መሰል መልእክቶች ተንጸባርቀዋል።
በመርሀ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ፣የቀድሞ ጀነራሎች እና ከፍተኛ የጦር አመራሮች ፣በርካታ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ አባላት እንዲሁም የሰራዊቱ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013