
አዲስ አበባ፦ መንግሥት ለህዝቡ ያቀረበው ጥሪ “የእናት ጡት ነካሽ” የሆነውን የጁንታውን ቡድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግድ እንደሆነ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ንጉሴ አስታወቁ ።
አቶ ተሻለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት መንግሥት ያስቀመጠውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደጎን በመተውና በእምቢተኝነቱ በመግፋት እስከ አሁንም በህዝቡ ላይ ትልቅ በደል አድርሷል፤ ከትግራይ ህዝብ አልፎም አጎራባች ክልሎች ላይ እየፈጸመ ያለው ጥቃት እጅግ አሳፋሪ ነው። በመሆኑም አሁን መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን አንስቶ ለህዝቡ ጥሪ ማቅረቡ ትክክለኛና ወቅታዊ እንዲሁም ቡድኑን ከምድረ ገጽ የሚያጠፋ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ምንም እንኳን ህዝቤ በማለት በትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ ይወተፍ እንጂ ህዝቡን እራሱ እንደ ጠላት የሚያይ ነው ፤ያሉት አቶ ተሻለ እኛ እንደ ፓርቲም ድርጅቱና ህዝቡ የማይታረቁ ጠላቶች እንደሆኑ እናውቃለን ፤በተጨባጭም ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ይህንን እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ ቡድኑ አሁንም እራሱን ብቻ በመውደድና ስልጣንን ብቻ በመፈለጉ ህዝቡን እያሰቃየ ነው፤ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለሌለብን መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ሽሮ ወደተግባራዊ እርምጃ መግባቱ ሊበረታታ አቅምና ሁኔታው የሚፈቅድለት ዜጋ ሁሉ ከጎኑ ሊሰለፍለት የሚገባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በመወሰንና መከላከያውን ከክልሉ በማስወጣት ገበሬው እንዲያርስ። ነጋዴውም እንዲነግድ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ስራውን አውቆ እንዲሰራ ለማድረግ ቢሞክርም ጁንታው ሀይል ግን ከትግራይ አልፎ አጎራባች ክልሎች ላይ ያሉ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ህብረተሰቡም በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የተለያዩ ጥቃቶችን እያደረሰ መሆኑን አስታውቀው ይህ ሁኔታ ደግሞ በዚሁ ከቀጠለ ውጤቱ አስከፊ ስለሚሆን መንግሥት ህዝቡን ይዞ ወደ ተግባራዊ እርምጃ መግባቱ ያስመሰግነዋል ብለዋል።
ዜጎች የጁንታው ቡድን በሚያደርሳቸው ጥቃቶች እየሞቱ እና እየተፈናቀሉ ነው ያሉት አቶ ተሻለ መንግሥትን ውሳኔውን ዳግም በመመልከት ቡድኑን እንደ ባህርይውና እንደ አመጣጡ ለመመከትና ለማስወገድ መወሰኑን ጥሩ ነው ። መንግሥት እየሄደበት ያለው አግባብ ትክክል ነው ፤እኛም በዚህ አካሄድ አብረን ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
አገራችን በአሁኑ ወቅት ጭንቅ ውስጥ ናት፤ ከቤትም ከውጪም ጠላቶች አሰፍስፈው ተነስተውባታል ፤ ይህንን የሚመክተው ደግሞ የተባበረ የህዝብ ክንድ በመሆኑ ህዝቡ እንደ ከዚህ በፊቱ ልዩነቶቹን ወደጎን በመተው በቁርጠኝነት አንድ ሆኖ በመነሳት የአገሩን ደህንነት ይጠብቃል ፤ እንደውም ጥሪም የማያስፈልገው መሆኑን በታሪክም የምናውቀው ነው ፤አሁንም ያንኑ የቀደመ ታሪኩን እንደሚደግመው ምንም ጥርጥር እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 ቀን 2013 ዓ.ም