
አዲስ አበባ፦ የክልሉ ህዝብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለማጥፋት ከመላው የሀገሪቱ ህዝብ ጎን ተሰልፎ የሚጠበቅበትን ተጋድሎ እንደሚያደርግ የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ አስታወቁ ።
አቶ ሙስጠፌ ትናንት የመከላከያ ሠራዊትንና የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል የሚደግፍ ህዝባዊ የድ ጋፍ ሰልፍ ጅግጅጋ ከተማ በተካሄደበት ወቅት እንዳስታወቁት ፣ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለረጅም ጊዜ ሲሰራ የቆየውን ኢትዮጵያውያን የማፍረስ እቅድ ለማሳካትና ዳግም የማእከላዊ መንግሥት ስልጣን ላይ ለመውጣት የተለያዩ የጥፋት ተግባር እየፈፀመ ነው ፡፡
ጁንታው ሀገር የማፍረስ አቅም የለውም ያሉት አቶ ሙስጠፌ ፣ይህንን የጥፋት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብአተ መሬቱን በመፈፀም የሀገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሶማሌ ህዝብ ባለፉት 30 ዓመታት በጁንታው የተጎዳ ህዝብ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙስጠፌ፣ ክልሉ ህዝብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለማጥፋት ከመላው የሀገሪቱ ህዝብ ጎን ተሰልፎ የሚጠበቅበትን ተጋድሎ ያደርጋል ብለዋል።
በጅግጅጋ ከተማ እስታዲየም በተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የከተማው ነዋሪዎች ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና አሸባሪውን የህወሓት ጁንታ የሚያወግዙ የተለያዩ መልክቶችን አስተላልፈዋል።
የከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ መፈክሮችን አንግበው ለመከላከያ ሠራዊትና ለሶማሊ ልዩ ኃይል ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ባለፉት 30 ዓመታት በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ የፈፀመው አስከፊ በደሎች ከህሊናቸው መቼም እንደማይጠፋ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ወቅቱ የመላው ህዝቦችን አንድነት የሚያስፈ ልግበት በመሆኑ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ግጭትና መከፋፈል የሚፈጥሩ ኃይሎችን እኩይ ሴራ በማክሸፍ በፍቅርና በአንድነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በሰልፉ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እንዲሁም ሌሎች አመራሮች መገኘታቸውን የሶማሌ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 ቀን 2013 ዓ.ም