
አዲስ አበባ፡- በክብር ሞተን ህዝብና ሀገርን በማስከበር ከፍ ያለ ታሪክ እንሰራለን እንጂ ተዋርዶ የመሞት ስነልቦና የለንም ሲሉ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለፁ፡፡የሽብር ቡድኑ በአማራ ህዝብና በሀገር ህልውና ላይ የደቀነውን አደጋ ህዝቡ በተቀናጀና በተናበበ መንገድ እየመከተው እንደሚገኝ አመለከቱ።
አቶ ግዛቸው በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በምንም ተአምር ተዋርዶ የሚሞት ህዝብ የለም፣ አባቶቻችን ተዋርዶ የመሞት ስነልቦና ሳይሆን በጀግንነት ተፋልሞ፣ ሀገርን በከፍታ ላይ አስቀምጦና ታሪክ አስመዝግቦ በክብር መሞት ነው ያወረሱን ።
አሸባሪው ቡድን በአማራ ህዝብ ላይ የሚያወራርደው ሂሳብ እንዳለ በመግለፅ ህዝቡን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለመበታተን አላማ አድርጎ እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ህዝቡም የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚመጥነው ልክ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የአሸባሪውን እኩይ አላማ ለማክሸፍ ሁሉም ህዝብ አካባቢውን በንቃት ለመጠበቅ ተነሳሽነቱ ወስዶ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው፤ የኋላ ደጀን የሚሆነው ህዝብ በሚገባ ተደራጅቶ፣ በንቃት እየሰራ
መሆኑን አስታውቀዋል።
በሁሉም አውደ ውጊያዎች ትላልቅ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ግዛቸው፤ ፤ ውጊያው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት እየተደመሰሱ ነው።ቡድኑ የመጣው ኃይል ሲደመሰስ ሌላ እየተካ የትግራይን ህዝብ እያስጨረሰ ይገኛል ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑን ከምድረ ገጽ ማጥፋት ዋና አላማችን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ለማሳካት የሚያስችል ልምድና ብቃት ተገኝቷል፣ ህዝቡን በማነሳሳት በኩል ጥሩ ሥራ ተሰርቷል። በምዕራብ ግንባር በወፍላና አካባቢው፣ በወልቃይትና አካባቢው እንዲሁም በአዲርቃይ አካባቢ ባሉት ግንባሮች ቡድኑ ታጣቂዎችን ሾልኮ እያስገባ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ መሆኑን አመልክተዋል።
በህልውናችን ላይ የደቀነውን ወረራና የህልውና አደጋ ለመቀልበስ መላው ህብረተሰብ ዘብ ቆሟል። በሰሜን ወሎ፤ ወልዲያ፣ መርሳ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ጋይንት አካባቢ ከባድ ውጊያ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጥፋት ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል፣ ፋብሪካ አቃጥሏል፣ የነዋሪዎችን ቤት አፍርሷል፣ ንጹሃንንም ገድሏል፣ ሀብት ንብረትም ዘርፏል ብለዋል።
ህዝባችን ይህ አሸባሪ ኃይል መንግሥት በነበረበት ጊዜ ላይ ያደረሰበትን ግፍና በደል ጠንቅቆ ያውቃል። ይህን የተገነዘበው የፀጥታ ኃይል በተገቢው መንገድ ለመመከት የተደራጀ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ያለምንም ልዩነት በአንድነት እንደ ህዝብ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመመከት በመናበብ እየተሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 ቀን 2013 ዓ.ም