
አዲስ አበባ፡- ግብርናን በማዘመን የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማስቆም እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡አሜሪካ አሁን ለደረሰችበት ዓለም አቀፍ የበላይነት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠቷ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዳለው አመለከቱ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተመራማሪ ዶክተር ኤርሚያስ አባተ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ግብርናው ባለመዘመኑ ምክንያት የሀገር ሉአላዊነት በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙት ይገኛል፡፡ የሀገርን ሉአላዊነት ማረጋገጥ የሚቻለው በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን ግብርናውን በማዘመን ጭምር ነው፡፡
ለግብርናው ትኩረት ባለመስጠታችን፣ ግብርናውን በቴክኖሎጂና በእውቀት እንዲመራ ባለመደረጉ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እያየን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ግብርና ከጤና፣ ከማህበራዊ ከኢኮኖሚ በላይ የሀገር ሉአላዊነትን ማስጠበቂያ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የግብርናውን ውጤታማነት ከፍ የሚያደርጉና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን በዘላቂነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ድህነትን ማስወገድና የሀገር ሉዓላዊነትን መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ግብርናውን ለማዘመን ለአንድ ተቋም ብቻ መተው ተገቢ እንዳልሆነ ያመለከቱት ዶክተር ኤርሚያስ ፣ በእውቀት የታነጸ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ዘርፉ ካለው ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አንጻር የትምህርትና የጤና ሚኒስቴር ሊሳተፉበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አሜሪካ ምግብን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሳሪያ በማድረግ በማንኛውም ሀገር ጣልቃ እየገባች የፈለገችውን እንድትስራ አስችሏታል ያሉት ዶክተሩ፤ ኢትዮጵያ ወደ ልማት መዞሯን ተከትሎ ቅር እንደተሰኘች ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ ሀገሮችን መርዳት፤ በመቀጠል ጥገኛ ማድረግና የማምረት አቅማቸውን ካጡ በኋላ ደግሞ እርዳታ ማቆም የሚል ፖሊሲን በመከተል የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት ሀገር እንዲፈርስ በማድረግ በሉአላዊ ሀገር ጣልቃ ለመግባት ትጠቀምበታለች፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ላይም እየሞከረችው ያለው ይህንኑ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አሜሪካ አሁን ለደረሰችበት ዓለም አቀፍ የበላይነት ያበቃት ለግብርናው ትኩረት መስጠት በመቻሏ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አንድ ሀገር እራሱን በምግብ ሲችል ከቁጥጥር ውጭ ይወጣል ብለው ሰለሚያስቡ በግጭቶች እንዲዳከም ያደርጉታል ብለዋል፡፡ ምግብን ተጠቅመው በሉአላዊ ሀገር እንደፈለጉ ይገባሉ፤ የበርካታ ሀገሮችን መሪዎች ይቀይራሉ ብለዋል፡፡
የግብርና አስፈላጊነቱ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ የውጭ ፖሊሲ መሳሪያ ማስፈጸሚያ እንዲሆን ዩ ኤስ ኤይድን በማቋቋም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በጸጥታ ተቋሞቿ ክትትል እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተወረሱና አዳዲስ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ተገቢ እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር ኤርሚያስ ፤ ግብርናውን እያጠና የገበሬውን ህይወት ሊለውጥ የሚችል ጥናትና ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡ የገበያ ፍላጎት ሁል ጊዜም ተለዋዋጭ በመሆኑ ለዚህ ምላሽ መስጠት የሚችል በቴክኖሎጂና በእውቀት የሚመራ ግብርና መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አሁን መጠቀም የማንችላቸው የዘር አይነቶች እየተፈጠሩ በመሆኑ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር የሚሄዱና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የዘር አይነቶችን ማቅረብ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም