
አዲስ አበባ፡- ስግብግብ ነገዴዎች እየፈጸሙት የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር አሸባሪው ትህነግ አገር ለማፍረስ ከከፈተው ጦርነት ያልተናነሰ ድርጊት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ ፡፡የኢኮኖሚ አሻጥሩ የተጠና የኢኮኖሚ ጦርነት መሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ እና መንግሥት በተቀናጀ ሁኔታ ሊከላከሉት እንደሚገባ አመለከቱ ፡፡
አስተያየት ከሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አፀደ ብዙነህ እንዳስታወቁት ፤ ህዝቡ ትኩረቱን የህልውና ዘመቻው ላይ ባደረገበት በአሁኑ ወቅት የአገር ክብርና ሰብዓዊነት የማይሰማቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ሸቀጦችን በማከማቸት ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠርና የተጋነነ ዋጋ በመጨመር ህብረተሰቡን እያማረሩ ይገኛሉ፡፡
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የኑሮ ውድነት ማሻቀብ እየታየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የታየው የኑሮ ውድነት ግን በከፍተኛ ሁኔታ የተጋነነ ነው ያሉት ወይዘሮ አፀደ፤ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የኑሮ ውድነት እልባት የሚያሻው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የአቅርቦት እጥረት ሳይኖር በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት በልቶ ማደር አዳጋች ሆኗል፣ እነዚህ ነጋዴዎች ገበያን በማራቆት ቢያንስ ውድ ህይወቱን ሰውቶ እየተፋለመ ያለውን የሰራዊት ቤተሰብ እያስራቡ ነው ።ይህ ደግሞ ጦርነት ከመክፈትና ከአገር ክህደት ያልተናነሰ ተግባር እንደሆነ አመልክተዋል ፡፡

ህብረተሰቡ አውቆም ይሁን ባለማወቅ የኢኮኖሚ አሻጥረኞች ተባባሪ መሆን የለበትም፣ መንግሥት ላይ ጣትን ከመቀሰር ባለፈ እነዚህን አካላት በግልፅ ሊታገላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ህዝቡ ስግብግብ ነጋዴዎች በሚጨምሩት ዋጋ በተለይ ቶሎ የሚበላሹ መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ተባብሮ ባለመግዛት ነጋዴዎቹ ከሴራቸው ትምህርት እንዲወስዱ ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ገብርኤል ጋላት በበኩላቸው፤ በአንዱ ህመም ሌላው ማትረፍ ሳይሆን፤ ከሌለው ጋር ተካፍሎ መብላት አኩሪ የኢትዮጵያ ባህል ነው ።በተለይ ደግሞ በእንደዚህ አይነቱ የፈተና ወቅት ባህሉ ሊዘነጋ አይገባውም ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ኢትዮጵያን በሀይል የማፍረስ አንዱ መንገድ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ገብርኤል ፣ ህዝቡ ይህን የሚፈቅድ ባለመሆኑ በዚህ በኩል ያለው የጠላት ሴራ እንደማይሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በበኩላቸው ፤ መንግሥት ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሀገርን መታደግ ይገባዋል ብለዋል፡፡ የኢኮኖሚ ጦርነት የከፈተው ስግብግብ ነጋዴ በምንም መልኩ ጠብመንጃ አንስቶ እየተዋጋ ካለው አሸባሪ የህወሓት ቡድን ጋር ተለይቶ የሚታይ ባለመሆኑ ህዝቡን አስተባብሮ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ኬሮ ጀማል፤ አሻጥረኛው ነጋዴ ከህብረተሰቡ እይታ ውጭ የሆነ ስውር ፍጡር አይደለም ። ህብረተሰቡ እያየ ወገን መስሎ ሸቀጦችን በስፋት በመደበቅና በማከማቸት ወገን የሚጎዳ አካል ነው ። ህብረተሰቡ ይህንን እኩይ ድርጊት በቁርጠኝነት ሊታገል ይገባዋል ብለዋል ፡፡ ለዚህም ጥሪ አቅርበዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም