
አዲስ አበባ፡- በዳኝነት ስርዓቱ ተጠያቂነትን ማስፈንና ሙስናን መከላከል የተቋማቸው የቀጣዩ ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ አስታወቁ።
ፕሬዚዳንቷ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በ2013 በጀት ዓመት ዋነኛ ትኩረት የነበረው የዳኝነት ስርዓት ነጻነት ማስፈን ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ከነጻነቱ ባሻገር በተጠያቂነትም ላይ ትኩረት በማድረግ የሙስና፣ ስነምግባር እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ልዩ ክትትል ይደረጋል።
እንደ ወይዘሮ መዓዛ ገለጻ፤ ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ ሁኔታ በፍርድ ቤት ሥራዎች ላይ የሙስና ችግር ፈጽሞ ሊነሳ የማይገባው ጉዳይ ነው። ፍርድ ቤት ህዝብ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ የሚመጣበት ተቋም እንደመሆኑ ከሙስናና ከስነምግባር ችግሮች ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆን አለበት። ለዚህ እንዲረዳ ህብረተሰቡም በሰፊው መተባበር ይኖርበታል።
አንዳንድ ግለሰቦች በዳኞችና የፍርድ ቤት ሰራተኞች ላይ የሚያነሷቸው የሙስና ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት ወይዘሮ መዓዛ ፤ ይህ ዳኛ ይህን ጠይቆኛል፤ ያኛውም እንደዛው የሚሉ ወሬዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ይሁንና ከወሬ ባለፈ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ይዘው በመቅረብ የቁጥጥር ሥራውንም ማገዝ እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።
በዚህም የተነሳ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች የሚስተናገዱበት እንዲሁም ክትትልና ጥናት የሚደረግበት የኢንስፔክሽን ክፍል በሰው ኃይል እንዲደራጅ የማድረግ ሥራ ከሞላ ጎደል እንደተጠናቀቀም ወይዘሮ መዓዛ ጠቁመዋል፡፡
በፍርድ ቤት አሰራር ላይ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ተሳትፎ ለሚያደርጉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ያሉት ወይዘሮ መዓዛ፣ በተለይም ከሙስና እና የስነምግባር ችግሮች ጋር በተያያዘ ማስረጃዎችን ለሚያቀርቡ ዜጎች አስፈላጊው ጥበቃ ይደረጋል ብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ በመግለጫቸው ፤ በ2013 በጀት ዓመት በፍርድ ቤቶች ለ166 ሺህ 758 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ ለ171 ሺህ 276 መዝገቦች እልባት መሰጠቱን ጠቁመው፤ ከነዚህም ውስጥ 150 ሺህ 283ቱ መዛግብት በዚሁ ዓመት የተከፈቱና ውሳኔ ያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አንዳንድ የፍርድ ሂደቶች 50 እና ከዚያ በላይ ምስክሮችን መስማት ግድ የሚልባቸው ሰፊ ጉዳዮች ሲሆኑ በአነስተኛ ጊዜ የተጠናቀቁ በርካታ ጉዳዮችም እንደነበሩ ወይዘሮ መዓዛ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ 518 አቤቱታዎችን ከባለ ጉዳዮች ተቀብሎ አጣርቷል። ከዚህም ውስጥ 18 መዝገቦች ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተልከዋል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ መዓዛ ከሆነ፤ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ 24 ልዩ ችሎቶች ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። በዚህም ከምርጫ ጋር የተያያዙ 74 ጉዳዮች ለፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል። ውሳኔ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች 22ቱ የወንጀል ጉዳዮች ሲሆኑ 52ቱ ደግሞ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ናቸው።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም